Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበኦሮሚያ ልዩ የፖሊስ አደረጃጀት አለመኖሩን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ

በኦሮሚያ ልዩ የፖሊስ አደረጃጀት አለመኖሩን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ

ቀን:

  • የአማራና የሶማሌ ክልሎች መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ‹ልዩ ኃይል› የሚባል የፖሊስ አደረጃጀት እንደሌለው፣ ይህ ስም ለአድማ ብተና ኃይል እንደሚሰጥ የክልሉ ፖሊስ ገለጸ፡፡ የአማራና የሶማሌ ክልሎች መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከሰቱ የተለያዩ መነሻዎች ባሉዋቸው ግጭቶች ክልሎች ያደራጇቸው ‹‹ልዩ ኃይል ፖሊስ›› በመባል የሚታወቁ ኃይሎች በወገንተኝነት በግጭቶቹ ተሳትፈዋል የሚሉ መረጃዎች በተደጋጋሚ ጊዜ መውጣታቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ መረጃዎች በአብዛኛው በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲገለጹ የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የመንግሥት ተቋማትና የሥራ ኃላፊዎችም አንዳንድ ክልሎች ‹‹ልዩ የፖሊስ ኃይል›› በመባል የሚታወቅ ኃይል እንዳላቸው እየጠቀሱ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በ2008 ዓ.ም. በአማራና በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ተቀስቅሰው በነበረ ግጭት አዘል የተቃውሞ ሠልፎችን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅቱ አቅርቦት በነበረው ሪፖርት፣ ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ በወገንተኝነት መሳተፉን ገልጿል፡፡

- Advertisement -

የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች ሕገ መንግሥቶች ላይ መደበኛ የፖሊስ ኃይል በሁለቱም ክልሎች እንደሚመሠረት፣ የመደበኛ ፖሊስ ተጠሪነትም  ለርዕሰ መስተዳድሮቹ እንደሚሆን ተቀምጧል፡፡

ይሁን እንጂ የክልሎች የልዩ ኃይል ፖሊስ አደረጃጀት ጉዳይ በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል ተከስቶ ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ በድጋሚ ልዩ ትኩረት አግኝቷል፡፡

ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤተ ተገኝተው ለነበሩት ለጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከቀረቡት ጥያቄዎች አንዱ፣ በክልሎች ተደራጅተዋል ስለሚባሉ ልዩ የፖሊስ ኃይሎችን የተመለከተ ነበር፡፡

የክልሎችን ሥልጣን በሚደነግገው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ክልሎች የሕዝባቸውን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ የራሳቸው ፖሊስ እንደሚያደራጁ ቢደነገግም፣ ከዚህ በዘለለ መደበኛ ሠራዊት የሚመስል ልዩ ኃይል የሚባል የታጠቀ የተደራጀ ኃይል አደራጅተው እንደሚገኙ ጥያቄውን ያነሱት የፓርላማው አባል አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ይህ ኃይል በክልሎች ወሰን ምክንያት በሚነሱ ግጭቶች በመሳተፍና መደበኛ ውጊያ በማድረግ በርካታ የሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ፈጥሯል፡፡ ይህ በየክልሉ ያለው የልዩ ኃይል አደረጃጀት ሕገ መንግሥታዊነቱ ታይቶ እንዲፈርሰ ዕርምጃ ለምን አልተወሰደም?›› ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ክልሎች ያደራጃቸው የፖሊስ ኃይሎች መጠሪያ ስያሜ ችግር አለመሆኑን፣ ነገር ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ስለፖሊስ አደረጃጀትና ኃላፊነት የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ የተፈጠረ ችግር መኖሩን አምነዋል፡፡

በቅርቡ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት የሁለቱም ክልሎች ልዩ የፖሊስ ኃይሎች አመርቂ ሥራ ቢያከናውኑም፣ አንዳንዶቹ ግን በሕዝቦች ላይ ቃታ በመሳብ ሕይወት ማጥፋታቸውን በግልጽ ይፋ አድርገዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልከቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ተወካይ ምክትል ኮማንደር አዲስ ጉተማ፣ በክልሉ መንግሥት የተደራጀ ልዩ ኃይል የሚባል ሠራዊት አለመኖሩን ይገልጻሉ፡፡

በክልሉ መንግሥት የተደራጀው ሰላምና ፀጥታ የሚያስከብረው የክልሉ መደበኛ ፖሊስ ኃይል የሚባል መሆኑን የጠቆሙት የሕዝብ ግንኙነት ተወካዩ፣ በዚህ መደበኛ የፖሊስ ኃይል ሥር የተደራጀ የአድማ ብተና የፖሊስ ኃይል መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ይህንን የአድማ ብተና ኃይል በተለምዶ ልዩ የፖሊስ ኃይል ብሎ የመጥራት ዝንባሌ እንጂ፣ በክልሉ መንግሥት ዕውቅና ተሰጥቶት የተደራጀ ልዩ የፖሊስ ኃይል የለም ብለዋል፡፡

ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የሶማሌ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ እድሪስ አህመድ ጥያቄውን ካዳመጡ በኋላ፣ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት አማካሪም ጉዳዩን በተመለከተ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. በአማራ በሰሜን ጎንደር ዞን ተከስቶ በነበረው ግጭት ጉዳትና የሰብዓዊ ጥሰት ምርመራ በማድረግ ሪፖርት ያቀረበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ጥሰት ፈጽመዋል ካላቸው መካከል የክልሉ ልዩ የፖሊስ ኃይል ተገልጿል፡፡

ጉዳን አስመልክቶ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሆኑት ሙሉጌታ ሰዒድ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፣ ‹‹የደኅንነት ጉዳይን የተመለከተ በመሆኑ የክልሉን የፖሊስ አረጃጀት መናገር አልችልም፤›› ብለዋል፡፡

የሚመለከተው የመንግሥት አካል በቅድሚያ በደብዳቤ ጠይቆ ከተፈቀደለት በአካል ቀርቦ ስለአደረጃጀቱ መረጃ ሊሰጠው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ‹‹በሕገ መንግሥቱ ላይ አንቀጽ 55 (7) ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱን የፖሊስ አረጃጀት ሥርዓት ያበጃል ይላል፡፡ ‹‹ይህ ስታንዳርድ በጥናት ላይ ተመሥርቶ እስካሁን የሕግ ማዕቀፍ አልተበጀለትም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከፖለቲካ ራሱን ያገለለ የፖሊስ አደረጃጀት ካልተፈጠረ ለአንዱ ወግኖ መዋጋቱ አይቀርም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን አደረጃጀት የተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ መረቀቁንና ከክልሎች ጋር ውይይት ተካሂዶ ለፓርላማ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 (7) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባራትን በሚዘረዝረው አንቀጽ ሥር፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት የአገርና የሕዝብ መከላከያ፣ የደኅንነትና የፖሊስ ኃይል አደረጃጀትን ይወስናል፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...