በአዳማ ከተማ ገልማ አባገዳ እየተካሄደ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሰባተኛ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ በአንድ ቀን ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ ቢያዝለትም፣ አራት ቀናት ጨምሮ እስከ ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚቆይ ታወቀ፡፡
ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ የተጀመረው እሑድ ጥቅምት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲሆን፣ ይጠናቀቃል ተብሎ በተያዘለት ጊዜ ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ እስከ ሐሙስ ድረስ የሚቀጥል መሆኑን፣ የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቁ ጫላ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ የኦሕዴድ ሊቀመንበርና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ጨምሮ የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች የሚፈልጉትን አንድነት ለማረጋገጥ ሁሉም በጋራ ሊሠራ እንደሚገባ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየለ የመጣውን የሕዝብ ጥያቄ ለመመለስም ኦሕዴድና የክልሉ መንግሥት፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ አሠራር ዘርግቶ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ከመልካም አስተዳደርና ከሥራ ፈጠራ ችግሮች ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች እንደነበሩ፣ ኦሕዴድ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተለየ ሥልት ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኦሮሚያ ክልል ያልተነካና ሰፊ ሀብት ያለው መሆኑን ጠቁመው፣ በወጣቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ኦሕዴድ ከመቼውም በላይ ቁርጠኛ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
‹‹ኮንፈረንሱ የክልሉንና የአገሪቱን ልማት ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የሰላም ሥጋቶችን ለመታገል በአንድነት የምንሠራበት ነው፤›› ብለዋል፡፡
በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ውይይት ከሚደረግባቸው አጀንዳዎች መካከል ጥልቅ ተሃድሶ ከተገባ ወዲህ የተገኙ ስኬቶችንና ጉድለቶችን ገምግሞ ውሳኔዎችን ማፅደቅ፣ የድርጅቱን ውስጣዊ መዋቅር ማጠናከር፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የሕዝቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማጠናከር የሚረዱ ሥልቶችን መቀየስ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ብልሹ አሠራርና ኪራይ ሰብሳቢነትን ማስወገድ፣ ሕገወጥነትን ለማጥፋት የተጀመረው ትግል እንዲቀጥል ማድረግ፣ የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ ወዘተ. የሚሉት እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
ኮንፈረንሱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ እየተስተዋለ ላለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተገቢው ሁኔታ ምላሽ ይሰጣል ተብሎም ይጠበቃል፡፡
በኮንፈረንሱ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ የኅብረተሰቡ ተወካዮች፣ ምሁራንና ደጋፊዎችን ጨምሮ ከ2,000 በላይ ሰዎች እየተሳተፉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡