Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊህልም የተሳካበት ጥንካሬ

ህልም የተሳካበት ጥንካሬ

ቀን:

በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡ የሕይወት ጥሪያቸውን ተከትለው ታሪክ ሠርቶ ለማለፍ የቆረጡ ይመስላሉ፡፡ ከፊታቸውም ጥንካሬና ተስፋ ይነበባል፡፡ ኤክስሀብ አዲስ የተባለው የማኅበረሰብ ሥራ ፈጠራ ማበልፀጊያ ማዕከል (Social Entrepreneurship Business Incubation Center) ቅዳሜ ጥቅምት 18 ቀን 2010 ዓ.ም በሞርኒንግ ስታር ሕንፃ ላይ አዘጋጅቶ በነበረው ፕሮግራም ላይ አብዛኛዎቹ የተገኙት ‹‹የሐበሻ ቀጠሮ›› በሚባለው ብሂል አርፍደው ሳይሆን በሰዓቱ ነው፡፡

አዳራሹ ሞልቶ ስለነበር ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በረንዳ ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ተጠጋግተው የተደረደሩት ወንበሮች ሁሉንም መያዝ ባለመቻላቸው የተወሰኑት በየጥጉ ቆመዋል፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ መሬት ላይ ተደርድረዋል፡፡ በተስፋ የተሞላ ነጋቸውን፣ በሞራል የጠነከረ ፍላጎታቸውን በእርሷ ስኬት ለማየት ይጠባበቁዋት ይዘዋል፡፡

ከአሥር ዓመታት በፊት ሕልመኛ የነበረችውና በአሁኑ ወቅት ሕልሟን እየኖረችው የምትገኘው ዲዛይነር ማኅሌት አፈወርቅ (ማፊ) ልምዷን ማከፈል የጀመረችው ‹‹እንደምታዩኝ ትንሽ ልጅ አይደለሁም፡፡ በዕድሜ ከእናንተ ከፍ እላለሁ፤›› በማለት ነበር፡፡ ‹‹ሰባተኛ ክፍል ስማር ጀምሮ ብዙ ህልሞች ነበሩኝ፤›› ትላለች፡፡ ራፐር፣ ሞዴል፣ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች፣ ዲዛይነር መሆን ከብዙ ህልሞቿ የምታስታውሳቸው ናቸው፡፡

በወቅቱ ብዙ ነገር የመሆን ምኞቷ ከማንኛውም ታዳጊ የሚያመሳስላት ሊሆን ይችላል፡፡ ለየት የሚያደርጋት ምኞቶቿን አንድ ቀን እውን አደርጋቸዋለሁ ብላ በይደር አለማለፏ ነው፡፡ መሆን እፈልጋለሁ ያለችውን ሁሉ ትሞክር ነበር፡፡ በምኞትና በሁነቶች መካከል ሆና ለሚያዩዋት ‹‹እብድ እመስላቸው ነበር፤›› ትላለች፡፡

የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለች በብዙዎቹ የዕድሜ እኩዮቿ መታወቅ ጀመረች፡፡ ‹‹15 ዓመቴ ላይ አንድ ሙዚቃ ሠራሁ፤›› የምትለው ማፊ፣ በሠራችው ሙዚቃ የተለየ ጥቅም ባታገኝም የበለጠ ዕውቅና እንድታገኝ አጋጣሚውን ፈጠረላት፡፡ ከድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ ጋር እንድትገናኝ መንገድ እንደከፈተላትና ‹‹ጆሲ ኢን ዘ ሐውስ›› የተሰኘውን በብዙዎች ዘንድ እንድትታወቅ ዕድል የፈጠረላትን ሙዚቃ አብረው ሠሩ፡፡ የሙዚቃ ክሊፑ ላይ የተጠቀሟቸውን አልባሳት የሠራችውም እሷ ነበረች፡፡ ሙዚቃውም አልባሱም እንደተወደደላት ትናገራለች፡፡

ይህ ሲሆን ገና የ16 ዓመት ታዳጊ ነበረች፡፡ ‹‹በ18 ዓመቴ ብዙ ሙያ ያለኝ ሰው ሆንኩ፤›› የምትለው ማፊ፣ በሙዚቃና በልብስ ዲዛይን መካከል አንዱን ሙያ ለመምረጥ ብዙ ተቸግራ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ረዥም ጊዜ ወስዳ ካሰበችበትና ሌሎች በዙሪያዋ የሚገኙን ካማከረች በኋላ ሙዚቃውን ወደ ጎን ብላ በዲዛይን ለመቀጠል ወሰነች፡፡ ውሳኔዋን ብዙዎች አላመኑባትም ነበር፡፡ እርሷ ግን ከውሳኔዋ ውልፍት አላለችም፡፡

ትልቁ ችግር የነበረው በማኅበረሰቡ ዘንድ በራፕ ሙዚቃ የምትታወቀውን ማፊ ዲዛይነር ነች ብሎ በሌላ ሙያ ማስተዋወቁ ላይ ነበር፡፡ ይህም በጣም አስቸጋሪና እልህ አስጨራሽ ነበር፡፡ ስሟን ሳይቀር ‹‹ማፊ ኢን ዘ ሐውስ›› በሚል ለቀየሩ አድናቂዎቿ ማፊን በዲዛይነርነት ማስተዋወቅ ከባድ ሆኖ ቆየ፡፡ በጥረት ግን ነገሮች መልክ ያዙላት፡፡

ገና በልጅነቷ ዕውቅናን ማግኘት የጀመረችው ማፊ የፋሽን ሾው ፕሮግራሞች እጅግም ባልተለመደበት ወቅት የመጀመርያዋን የፋሽን ሾው መድረክ ለማዘጋጀት ስትሞክር ባይሳካስ የሚል ሥጋት አላደረባትም ነበር፡፡ በ21 ዓመቷ የመጀመሪያውን የፋሽን ፕሮግራም አዘጋጀች፡፡ ‹‹ፕሮግራሙ የተዋጣለት ነበር፤›› በማለት ሌላኛውን የስኬት መንገዷን የከፈተላትን አጋጣሚ ታስታውሳለች፡፡

በዚህ ፕሮግራም ምክንያት ኬንያ ተዘጋጅቶ በነበረ አንድ የፋሽን ሾው ፕሮግራም ላይ ሥራዎቿን የምታሳይበት ዕድል አገኘች፡፡ ‹‹ከብዙ ሰዎች ጋር መተዋወቅ ቻልኩ፡፡ ከዚያ ሳልመለስ ታንዛኒያ ተጋበዝኩ ቀጥሎ አንጎላ፤›› ትላለች፡፡ በዚህ የጀመረ የዲዛይን ሙያዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ መጣ፡፡ የብዙዎች ህልምና በፋሽን ኢንዱስትሪ እንደ ትልቅ ስኬት ተደርጎ በሚቆጠረው በኒውዮርክ ፋሽን ዊክ ላይ ሥራዎቿን የማሳየት ዕድሉን አገኘች፡፡

ለደረሰችበት የስኬት ደረጃ ‹‹አሥር ዓመታት ፈጅቶብኛል፤›› ትላለች፡፡ በወጣትነት ዕድሜዋ ከዕድሜ እኩዮቿ በተለየ ስኬታማ ሆና እዚህ ብትደርስም እስክትደርስ ያለው ውጣ ውረድና ከደረሰች በኋላ እያጋጠሟት ያሉ ፈተናዎች ቀላል የሚባሉ አለመሆናቸውን ትናገራለች፡፡

‹‹ምንም ይሁን ምን የመጀመሪያውን ዕርምጃ መውሰድ ግድ ነው፡፡ በራሳችሁ መንገድ የራሳችሁን ኦሪጂናል ሥራ ሥሩ፡፡ የተያዘ ነገር አትመኙ›› ስትል ነበር ከምንም ተነስታ አርአያ ለመሆን የበቃችበትን የስኬት ጉዞ ከፊት ለፊቷ ሆነው በተመስጦ ለሚያደምጧት ወጣቶች ከስህተቷ እንዲማሩ በጥንካሬዋ እንዲበራቱ ልምዷን ያካፈለችው፡፡

እንደ ማፊ ያሉ ስኬታማ ሥራ ፈጣሪዎች በፈጠራ ሥራ ለተሰማሩ ወጣቶች ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበት የተለያዩ መድረኮች ቢፈጠሩ በአሁኑ ወቅት ለአገሪቱ ትልቅ ችግር የሆነውን የወጣቶች ሥራ አጥነት በምን ያህል መጠን መቀነስ እንደሚቻል መገመት አይከብድም፡፡ የፈጠራ ሥራ በተለይም ሶሻል ኢንተርፕራይዞች ተሞክሮን በማካፈል ሊቀረፉ ከሚችሉ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ባሻገር የተለያዩ ማነቆዎች የተጋረጡበት ነው፡፡

ተግባር ላይ ቢውሉ በርካታ ችግሮች መቅረፍ የሚችሉ ፈጠራዎች መነሻ ገንዘብ በማጣት፣ ሐሳብ ብቻ ሆነው ሲቀሩ ይታያል፡፡ ከዚህ ሲያልፍም የሚሠሩ ሥራዎች በትክክል የማኅበረሰቡን ችግር መፍታት የማይችሉ ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ በሌላ በኩል የሶሻል ኢንተርፕራይዝ ጽንሰ ሐሳብ በአገሪቱ እምብዛም ያልተለመደና እንግዳ በመሆኑ አረዳዱ ላይ ችግር ይታያል፡፡

ሶሻል ኢንተርፕራይዞች የማኅበረሰቡን ችግር መፍታት ላይ ያተኮሩ ሥራዎች የሚሠሩበት፣ ትርፍን ዓላማ ያላደረገ ቢዝነስ ሲሆን፣ በሥራው የሚገኘውን መጠነኛ ትርፍ ለግል ጥቅም ከማዋል ይልቅ አገልግሎቱን ማስፋት መገለጫው ነው፡፡

አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ የኤክስ ሀብ አዲስና የሴንተር ፎር አፍሪካን ሊደርሽፕ ስተዲስ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ኤክስ ሀብ አዲስ የሥራ ፈጣሪዎችን ሐሳብ ቅርፅ እንዲይዝ የማድረግ፣ ፈጣሪዎች ቢዝነስ ሞዴል እንዲያዘጋጁና ሥራዎቻቸውም ለገበያ እንዲበቁ የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡ ሥራውን ከጀመረ አራት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በየወሩ የሥራ ፈጣሪው አስተሳሰብ ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ፕሮግራሞች ያዘጋጃል፡፡

‹‹ወጣቶች በራሳቸውና በሚያመጡት ሐሳብ እንዲያምኑ፣ የሚሠሩት ሥራም ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር እንዲገናኙ፣ የትብብር መንፈስ እንዲፈጥሩ፣ በሐሳባቸው እንዲፎካከሩ የሚያደርግ ፕሮግራም ነው፤›› ይላሉ፡፡ ይህኛው ፕሮግራም የሚለየውም እነዚህ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የሚሠሯቸው ሥራዎች ማኅበረሰቡ ላሉበት አንገብጋቢ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጡ እንዲሆኑ በእናቶችና በሕፃናት ጤና ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው፡፡

ማፊ ተሞክሮዋን ባካፈለችበት በዚሁ መድረክ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት ጤና ዳይሬክተር  ኤፍሬም ተክሌ (ዶ/ር) ተገኝተው በጤናው ዘርፍ ላይ አሉ የሚሏቸውን አንገብጋቢ ችግሮች ለወጣቶቹ አብራርተዋል፡፡

‹‹በጤናው ዘርፍ በሚታዩ ችግሮች ላይ ለወጣቶቹ የቤት ሥራ እንሰጣቸዋለን፡፡ ይህንን ችግር እኔ መቅረፍ እችላለሁ የሚል ወጣት ንድፈ ሐሳብ ጽፎ ያስገባልናል፡፡ የተመረጠው ወደ ቢዝነስ ሞዴል ወደ ፕሮግራምነት ተቀይሮ እንዲሠራበት እናደርጋለን፤›› በማለት የሚመረጠው ንድፈ ሐሳብ ወደ ሥራ እንዲተገበር ድጋፍና መነሻ ካፒታል የሚገኝበትን ዕድል በኤክስ ሀብ እንደሚመቻች አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...