የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ከንጉሥ ተፈሪነት ወደ ንጉሠ ነገሥት አፄነት በጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም. ከተሸጋገሩ በኋላ ለ44 ዓመታት ግድም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን መርተዋል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዘውድ የደፉበት፣ ሉል የያዙበት፣ ሰይፍ የጨበጡበት ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› (የይሁዳ ነገድ የሆነው አሸናፊው አንበሳ፣ የንጉሦች ንጉሥ ሆኖ በእግዚአብሔር የተሾመው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ) ከተባሉ ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. 87 ዓመት ይሞላቸዋል፡፡ ፎቶው በ44 ዓመታት ውስጥ ከተገናኝዋቸው የዓለም መሪዎች አንዱ ከነበሩት መኪናዋን እያሽከረከሩ ካሉት የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ብሮዝ ቲቶ ጋር ሆነው ያሳያል፡፡
- ሔኖክ መደብር
የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ቀሪ 1000ኛ ቀን ተከበረ
የኦሊምፒክ በኩር (ሌጀንድ) አበበ ቢቂላ ከ53 ዓመታት በፊት ሁለተኛው የኦሊምፒክ ወርቅ በማራቶን ድሉ ያገኘባት የጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ፣ ዳግመኛ የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ለማዘጋጀት ደፋ ቀና እያለች ነው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ (ጥቅምት 18 ቀን 2010 ዓ.ም.) የኦሊምፒክ ቀሪ ቀናት መቁጠሪያ ሰሌዳን በአደባባይ በመትከል አስመርቃለች፡፡ ሰሌዳውን የመረቁት የቶኪዮ አገረ ገዥ (መሀል በግራ)፣ የኦሊምፒክ ሚኒስትር ሹኒቺ ሱዙኪና ሌሎች እንግዶች እንደነበሩ ዘጃፓን ታይምስ ዘግቧል፡፡
****
“አሞራ … የዳዊት አሞራ”
በዣን ተኵላ
[በ1400ዎቹ አማርኛ].
“አሞራ የዳዊት አሞራ
ተኸተለኝ በኋላ፤
ሥጋ አበላኽ ሐበላ (ከበላ)
የደም አጠጣኽ ነተራ (መራራ)
ተኸተለኝ በኋላ፤.
ወግዕቼ በቃራ (በካራ)
ሰኽቼ በጸመራ። (በጣምራ).
እኛስ ብንበልዓኽ መሐላ
ለጾር ይስጠን ለወርወራ፤ (ውርወራ)
የከንፍ ብናደርግ ጽላ
ለቀስት ይስጠን ለቀፈራ። (ለወጠራ).
ምን ከበአሰን ንበልአኹ መሐላ (እንበላለን)
ገላችን ከመሰል የፈጠጋር እምብላ (አምባር)
አፈችን ከመሰል በዓልቴት የገባች እንሶስላ
ፀዓታችን የመሰል በደም የዘራ ጭራ (ጣታችን).
ስማችን የዣን ተኵላ
አንበልዓም መሐላ። (አንበላም).
የዣን ተኩላ [ከአፄ ዳዊት ሠራዊቶች የአንዱ ስም] (1400ዎቹ)
.
- አንድምታ የጥበብ መጽሔት [ምንጭ] – Ms Bruce 88። Oxford Bodleian Library። ቅጠል 37ሀ።
*********
‹‹ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን››
ከጥንት ጀምሮ በቃል ሲነገር የሚኖረውን የአባቶቻችንን ተረት ብንመለከተው ብዙ የሚጠቅም ምክር እናገኝበታለን፡፡
‹‹ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን›› እንደሚለው ክፉ ሥራ መሥራት ጉዳቱ ለሠሪው ነው፡፡ ንብ ሌላውን አጠቃሁ ስትል በመርዟ ትነድፋለች፡፡ እሷም ይህን ክፋት ከሠራች በኋላ አንድ ደቂቃ ሳትቆይ ትሞታለች፡፡ የእሳት ራትም እንዲሁ መብራቱን ለማጥፋት ስትሞክር ተቃጥላ ራሷ ትጠፋለች፡፡ ትንኝ ሰው ዓይን ለማወክ ትገባና ሕይወቷን አጥታ ተጎትታ ትወጣለች፡፡ እንክርዳድን የዘራ እንክርዳድን ያመርታል፤ ክፉ የሠራም ሰው በክፋቱ ይጠፋል፡፡ በሰው የሚድነው በምነቱና በቅንነቱ ብቻ ነው፡፡
አያሌው ተሰማ ዘብሔረ ጎጃም (የካቲት 20 ቀን 1935 ዓ.ም.)
************
‹‹መጥረቢያውን ይዞ ግንባር ግንባሬን ይፈልጠኛል››
አንድ የወሎ ባላገር ወደ ሐኪም ቤት ሂዶ ‹‹ሕመምህ ምንድን ነው? ሲባል ‹‹አንድ አንከለፍ ነገር መላ ጂስሜን ጦርፎ ይዞ መጧሪያዬ ላይ ያስጨንቀኛል›› አለ፡፡ ዶክተሩ ተጨንቆ ‹‹ይህን የሚተረጉም ልጅ የለዎትም ወይ?›› ሲል ‹‹አንተ ራስህ አማርኛ አታውቅም ወይ?›› ተባለ፡፡ አንባቢዎችስ ምን ማለት ይመስላችኋል? ጅስም ሰውነት፣ መጦረፍ ቀሥፎ መያዝ፣ መጧሪያ ፊንጢጣ (ሰገራ መውጫ) ማለት ነው፡፡ ባላገሩ መናገር የፈለገው ‹‹ፊንጥጣዬ ላይ ብጉንጅ የሚመስል እባጭ ተፈጥሮ ሰውነቴን ቀሥፎ ይዞ ያሰቃየኛል›› የሚል ነው፡፡
ይህም ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንድ እናቶችም የራስ ሕመም መከራና ሥቃይ ሲፈጥርባቸው ‹‹መጥረቢያውን ይዞ ግንባር ግንባሬን ይፈልጠኛል፤ መዶሻውን ይዞ ራስ ራሴን ይመታኛል›› የሚሏቸው ቃላት ለትርጉም ያስቸግራሉ፡፡ አዎ የአማርኛ ቋንቋ በየክፍለ ሀገሩ እንደዚህ የተለያዩ የንግግር ፈሊጦች አሉት፡፡ ለምሳሌ በመሐል አገር የአዲስ አበባ ሕዝብ አባባል (ዘይቤ በእንግሊዝኛው Dialects) ለመኪና ተጓዥ የሚነገረው ቃል ‹‹ተሳፈር›› የሚል ነው፡፡ በጎንደር ግን ተሳፈር ለማለት ‹‹በመኪና ላይ ተሰቀል›› ይላል፡፡
- መክብብ አጥናው ‹‹የአእምሮ ማዝናኛ›› (2005)
***