ጎንደር ከተማ ውስጥ ፒያሳ አካባቢ ሲዘዋወሩ ከበርካታ አስጎብኚዎች ጋር መገጣጠም አይቀሬ ነው፡፡ አስጎብኚዎቹ ከተማዋ ውስጥና በዙሪያዋ ባሉ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎችም ይገኛሉ፡፡ በግንባር ቀደምነት በፋሲል ግንብና በመዋኛ ገንዳው ዙሪያ ቱሪስቶችን በጉጉት የሚጠባበቁ አስጎብኚዎች ይስተዋላሉ፡፡ በደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንና በቀድሞው የቤተ እስራኤላውያን መኖሪያ (ፈላሻ መንደር የሚባለው) አቅራቢያ የተመለከትናቸውን አስጎብኚዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡
የከተማዋን ከፊል ገጽታ ለመጎብኘት አልያም ሻይ ቡና ለማለትም ፒያሳን የሚያዘወትሩ ሰዎች ከሌሎች የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ባልተናነሰ ከአስጎብኚዎች ጋ ይገናኛሉ፡፡ ብዙዎቹ አስጎብኚዎች ፀጉረ ልውጥ ሲያስተውሉ፣ በአክብሮት ጠጋ ብለው ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡ ጎብኚው ከከተማዋ የቱሪስት ሀብቶች የትኞቹን እንደጎበኘና መዳረሻዎቹ ምን ዓይነት ስሜት እንዳሳደሩበት ይጠይቃሉ፡፡ ጎብኚው በጎንደር የቀረውን የቆይታ ጊዜ አጣርተውም ሌሎች መታየት ያለባቸው አካባቢዎችን ይጠቁማሉ፡፡ ቱሪስቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማስጎብኘትም ይደራደራሉ፡፡
ከከተማዋ ወጣ ብሎ የሚገኘው የስሜን ብሔራዊ ፓርክ አስጎብኚዎቹ ለቱሪስቶች ከሚያስተዋውቋቸው መዳረሻዎች አንዱ ነው፡፡ የመጎብኘት ፍላጎት ያላቸውን አሰባስበው ወደ ፓርኩ ይወስዳሉ፡፡ ጎንደር በኢትዮጵያ ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች በቀዳሚነት ከሚጠሩ ከተሞች አንዷ እንደመሆኗ፣ ብዙ የከተማዋ ተወላጆች አስጎብኚ የመሆን ዝንባሌ አላቸው፡፡ ፋሲል ግምብ ውስጥ ያገኘናቸው አስጎብኚዎች አሰግድና ፒያሳ አካባቢ ያገኘነው ደሳለኝ የነገሩንም ይኼንኑ ነው፡፡
በርካታ ታዳጊዎች ስለ ቱሪዝምና የአስጎብኚነት ሥራ የሚያውቁት ልጅ ሳሉ ነው፡፡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ትምህርት ክፍል አልያም በሌሎች የሆቴልና የቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋሞች ገብተው ትምህርት ይወስዳሉ፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ ያለ ሥልጠና በሙያው ለዓመታት ከመቆየት ባካበቱት ልምድ እየተመሩ ይሠራሉ፡፡ ለዓመታት በአስጎብኚነት ሙያ ዘልቀው ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩም ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
አስጎብኚዎቹን በተመለከተ ጥናት የሚሠሩ ተመራማሪዎችም በዛው ልክ እየጨመሩ ነው፡፡ ሙያውን ከሚቀላቀሉ ውስጥ ስንቶቹ የአስጎብኚነትን ሥነ ምግባራዊ መርሆች ይከተላሉ? አስጎብኚዎቹ የሚገጥሟቸው ፈተናዎችስ ምንድን ናቸው? የሚሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡
አሰግድና ደሳለኝ እንደሚናገሩት፣ ከከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እውቅና በማግኘት የሚሠሩ ባለሙያዎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በአስጎብኚ ድርጅቶች ተቀጥረው ወይም በግላቸው የሚያስጎበኙም በዘርፉ ይካተታሉ፡፡ ሙያዊ ብቃታቸውን ለማሳደግ መደበኛ ትምህርት የሚወስዱና በግላቸው የቋንቋና ሌሎችም ሥልጠናዎች የሚወስዱም አሉ፡፡ ሆኖም ሁሉም አስጎብኚዎች ሙያዊ ሥርዓቱን ተከትለው ይሠራሉ ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡
የጎንደር ከተማን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በተመለከተ በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች የአስጎብኚዎች ጉዳይ አንዱ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቅርስ ጥበቃ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ አበበ ፋንታሁን በጉዳዩ ጥናት ከሠሩ አንዱ ናቸው፡፡ ‹‹ቻሌንጅስ ኤንድ ፕሮስፔክትስ ኦፍ ቱሪስት ጋይድስ ኢን ኤንድ አራውንድ ጎንደር ሲንስ 1974›› የተሰኘ ጥናት ሠርተዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ፣ እንደ ኬንያ፣ ታንዛኒያ ግብፅ ካሉ አገሮች ያነሰ የቱሪስት ቁጥር ታስተናግዳለች፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ ካሉ ተዋናዮች አስጎብኚዎች ይገኙበታልና በቱሪዝሙ በሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዲሁም መልካም ነገሮችም ተያይዘው ይነሳሉ፡፡
‹‹አስጎብኚዎች የአገራቸው የእጅ አዙር አምባሳደር ስለሆኑ ስለሚያስጎበኙት አካባቢ ጥልቅ ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባል፤›› ይላሉ አጥኚው፡፡ ከታሪካዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ዕውቀታቸው በተጨማሪ ተግባቢ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ታጋሽና ችግሮች ሲገጥሙ በፍጥነት መፍትሔ የሚሰጡ መሆን እንደሚገባቸውም ያክላሉ፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (1923-1967) በነፃ የሚያገለግሉ አስጎብኚዎች እንደነበሩ አጥኚው ያስታውሳሉ፡፡ በፋሲል ግቢ ጌትነት ይግዛውና በላይ ግደይ የሚባሉ አስጎብኚዎች ‹‹ታዋቂ ነበሩ›› ይላሉ፡፡ በደርግ ዘመን (1967-1983) የማስጎብኘት ሥራው በብሔራዊ አስጎብኚ ድርጅት (ኤንቲኦ) በብቸኝነት ይመራ ነበር፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ የማስጎብኘት ሥራ በተቋምና በግልም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
አጥኚው በጎንደር ከተማ ከሚጎበኙ የቱሪስት መዳረሻዎች የፋሲል ቤተ መንግሥትን እንደ ማሳያ ይወስዳሉ፡፡ በ2005 ዓ.ም. የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር 162,522 ሲሆን፣ በ2006 ዓ.ም. 147,518፣ በ2007 ዓ.ም. 120,830 ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መዝገብ የሰፈሩ ታዋቂ ቅርሶች እያሏት የሚፈለገው ያህል ጎብኚ ለምን አይመጣም? ተብሎ ሲጠየቅ የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱ ኖረዋል፡፡
የቅርሶች በአግባቡ አለመተዋወቅ፣ የቅርሶች ተገቢው ጥበቃና ጥገና ማጣት፣ የቅርሶች መሰረቅና ሌሎችም ተግዳሮቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹ከጎብኚዎች ቁጥር ማነስ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ከሚያግዙ መካከል አስጎብኚዎች ይገኙበታል፤›› ሲሉ አቶ አበበ ይገልጻሉ፡፡ የጎንደር አስጎብኚዎች በማኅበር ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች መካከል የፋሲል ቤተ መንግሥት (57 አስጎብኚዎች)፣ ደባርቅ (70 አስጎብኚዎች)፣ ኮሶዬ (68 አስጎብኚዎች) እና ጎርጎራ (2 አስጎብኚዎች) ይገኛሉ፡፡
በእሳቸው ገለጻ፣ አብዛኞቹ ማኅበራት በአባላቱ ፍላጎት የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ከነዚህ የቱሪዝም ዕውቀትን ተመርኩዘው የሚሠሩት ደግሞ እምብዛም አይደሉም፡፡ በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩ አስጎብኚ ድርጅቶች በሕገ ወጥ አስጎብኚዎች ሥራቸው የሚስተጓጎልበት ጊዜም አለ፡፡ በታሪካዊ ዕውቀታቸው የተመሰገኑ አስጎብኚዎች እንዳሉ ሁሉ ስለ አካባቢው ታሪክና ባህላዊ እሴቶች መረጃ የሌላቸውም ይገኛሉ ይላሉ፡፡
አስጎብኚዎቹ በተለያየ ምክንያት እርስ በእርስና ከፖሊሶች ጋርም የሚጋጩበት ጊዜ አለ፡፡ ከሙያዊ ሥነ ምግባር ማጣት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳሉም ያስረዳሉ፡፡ አስጎብኚዎች ሙያዊ ባልሆነ ሁኔታ፣ ‹‹በተሻለ ሁኔታ የሚከፍሉ›› የሚሏቸውን ቱሪስቶች ማስጎብኘት ይመርጣሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከሙያው ክብር ይልቅ ገንዘብ ተኮርነት አመዝኖ ይታያል፡፡
ክፍተቱ ያለው በአስጎብኚዎች ዘንድ ብቻ አይደለም፡፡ አስጎብኚዎቹ የሚገጥሟቸው ፈተናዎችም የቱሪዝም ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ወጥ የሆነና ሙያቸውን የሚያስተዳድር መርህ ተዘጋጅቶ አለመተግበሩ የተዘበራረቀ አካሄድ እንዲኖር አድርጓል፡፡ በቱሪስት መዳረሻዎች ያለው የክፍያ ሥርዓት ወጥ አለመሆኑ ሌላው አንቅፋት ነው፡፡
አስጎብኚዎች ልዩ ልዩ የመስህብ ዓይነቶችን የማስጎብኘት ዘርፍ ማለትም በባህላዊ፣ በተፈጥሯዊ፣ በሃይማኖታዊና በሌሎችም ዘርፎች ጉብኝት የሚካኑበት (ስፔሻላይዝ የሚያደርጉበት) ሥርዓት የተመቻቸ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ዘርፍ ዘለግ ያለ ትምህርትና ስፔሻላይዜሽን ቢጠይቅም፣ ብዙዎቹ አስጎብኚዎች ይህን ዕድል አያገኙም፡፡ ሁሉንም ዘርፎች በአንድነት በማጣመር የተለያየ ይዘትና ገጽታ ያላቸው የቱሪስት መስህቦችን ለማስተጎብኘትም ይገደዳሉ፡፡
በአቶ አበበ ገለጻ፣ እንቅፋት የበዛበት ዘርፉ ተስፋ ሰጪ ገጽታዎችም አሉት፡፡ በዋናነት የሚጠቅሱት በተለያዩ የቱሪዝም ማሠልጠኛ ተቋሞች የተማሩ ወጣቶች ሙያውን መቀላል መጀመራቸው ነው፡፡ ወጣቶቹ ለሙያው ካላቸው ፍቅር ባሻገር ሁሌም ራሳቸውን በዘርፉ ለማሳደግ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡
‹‹የመንግሥት ተቋሞችና መንግሥታዊ ያልሆኑ የተራድኦ ድርጅቶች በየጊዜው ለአስጎብኚዎች ሥልጠና ይሰጣሉ፤›› በማለት በዘርፉ የወደፊት ተስፋ በሠልጣኞች መጣሉን ያስረዳሉ፡፡ ቱር ጋይዶች ወደ ቱር ኦፕሬተሮች ማደጋቸው ሌላው መልካም ጎን ነው፡፡ መንግሥት ለአስጎብኚዎች ፈቃድ የሚሰጥበትን ሒደት ከመቃኘቱ ጎን ለጎን፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እየተሻሻለ መምጣቱም ሥራቸውን የተቃና ለማድረግ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
በጎንደር ከተማ ያገኘናቸው አስጎብኚዎች በዘርፉ ለውጥ ማየት ከሚሹ መካከል ናቸው፡፡ በመንግሥት በኩል ቅርሶችን የመጠበቅ፣ ጉዳት ሲደርስባቸው የመጠገን፣ የማስተዋወቅና ሌሎችም ኃላፊነቶች እንዳሉ ሁሉ፣ አስጎብኚዎችም የራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች የቱሪስት መዳረሻዎችን ሲጎበኙ ከአስጎብኚዎች ሙሉ መረጃ ማግኘት አለባቸው፡፡ ለዚህም አስጎብኚዎች ተገቢው ዕውቀት ሊኖራቸው ግድ ይላል፡፡ በቱሪስቶችና በአስጎብኚዎች መካከል ተገቢው ሙያዊ ግንኙነት ተፈጥሮ ሥራው መከናወን እንዳለበትም ይስማማሉ፡፡