Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ መሪዎች ላይ የተመሠረተው ክስ

በዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ መሪዎች ላይ የተመሠረተው ክስ

ቀን:

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እ.ኤ.አ. በ2016 ባደረጉት የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ የቅስቀሳውን ዘመቻ ይመሩ በነበሩ አባላትና በሩሲያ መካከል ግንኙነት ነበር በሚል ጥርጣሬ መጫር የጀመረው በዚያው ጊዜ ቢሆንም፣ ጉዳዩ በይፋ እንዲጣራና ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄድ ምርመራዎች የተጀመሩት ዘንድሮ ነው፡፡

በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳና በሩሲያ መካከል አለ ተብሎ ስለተጠረጠረው ግንኙነት ትራምፕም ሆኑ የምርጫ ዘመቻ አቀንቃኞቻቸው ‹‹ጉዳዩ ከእውነት የራቀ ነው›› ቢሉም፣ ዓርብ ጥቅምት 17 ቀን 2010 የትራምፕን የምረጡኝ ዘመቻ ሲመሩ የነበሩ ኃላፊዎች ክስ ሊመሠረትባቸው እንደሚችል፣ ሲኤንኤንን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲያስተጋቡት ነበር፡፡

ሰኞ ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ደግሞ ትራምፕ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲወዳደሩ የቅስቀሳ ዘመቻውን ሲመሩ የነበሩ ሦስት ሰዎች ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብለው ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

በዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ መሪዎች ላይ የተመሠረተው ክስ

 

ክሱ ከመመሥረቱ በፊት ትራምፕም ሆኑ ዋይት ሐውስ በትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻና በሩሲያ መካከል ግንኙነት እንዳልነበር፣ ይልቁንም ሒላሪ ክሊንተን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ከዩራኒየም ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከሞስኮ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው በመግለጽ፣ ትራምፕ ከሩሲያ ንክኪ ንፁህ ስለመሆናቸው ሲናገሩ ከርመዋል፡፡

ሆኖም ሩሲያ ትራምፕ በምርጫው እንዲያሸንፉ ጣልቃ ገብታለች ብሎ የአሜሪካ የደኅንነት ቢሮ በመደምደሙ፣ በአሜሪካ የምርመራ ቢሮ ምርመራው ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

በሮበርት ሙለር የሚመራውን ምርመራ ትራምፕም ሆኑ ሩሲያ ያጣጣሉት ቢሆንም፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የትራምፕ የቀድሞ የውጭ ፖሊሲ አማካሪ የነበሩት ጆርጅ ፓፓዶፑለስ፣ የምርጫ ዘመቻ ኃላፊው ፖል ማናፎርት፣ እንዲሁም የምርጫ ቅስቀሳ ምክትል ኃላፊ የትራምፕ በዓለ ሲመት አመቻች ሪቻርድ ጌትስ ተከሰዋል፡፡

ለፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ ጠቅሶ ቺካጎ ትሪቡን እንዳሰፈረው፣ ፓፓዶፑለስ የተከሰሱት የሩሲያ ባለሥልጣናት በትራምፕ የፕሬዚዳንታዊ ዘመቻ ወቅት ጫና እንዲፈጥሩ ሁኔታዎችን አመቻችተዋል ተብለው ነው፡፡

ማናፎርትና ጌትስ ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ማጭበርበርን፣ ሸፍጥንና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ጨምሮ በ12 የተለያዩ ወንጀሎች ሲሳተፉ ቆይተዋል ተብለው ለየብቻ ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

ሰኞ ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በነበራቸው የፍርድ ቤት ቀጠሮም ማናፎርትም ሆኑ ጌትስ የተከሰሱበትን ድርጊት አልፈጸምንም ብለው ተከራክረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ማናፎርት በአሥር ሚሊዮን ዶላር ዋስትና፣ እንዲሁም ጌትስ በአምስት ሚሊዮን ዶላር ዋስትና እንዲፈቱ ወስኗል፡፡ አያይዞም ሁለቱም ፓስፖርታቸውን እንዲያስረክቡና የቁም እስረኛ እንዲሆኑ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ማናፎርትና ጌትስ ላይ የተመሠረተው ክስ ለዓመታት ያህል የሚያሳስራቸው ቢሆንም፣ የፓፓዶፑለስ ጉዳይ ግን የተለየና ለዋይት ሐውስ መተራመስ በር የሚከፍት ነው፡፡ ምክንያቱም የፓፓዶፑለስ ክስና የተሰጠው መልስ የትራምፕ ምርጫ ዘመቻ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት እንደነበረው ፍንጭ ያሳየ ነው፡፡

በዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ መሪዎች ላይ የተመሠረተው ክስ

 

ፓፓዶፑለስ ፌዴራሉ የምርመራ ቢሮ በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ሲያቀርብላቸው ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንና ከሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው ከተባሉ ሰዎች ጋር መገናኘታቸውን ክደው የነበረ ቢሆንም፣ መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በነበረው ዝግ ችሎት ግን ግንኙነት እንደነበራቸው አምነዋል፡፡

ፓፓዶፑለስ እንዳሉት፣ ስማቸውን ካላወቁዋቸው ፕሮፌሰር ጋር በለንደን ተገናኝተው የነበረ ሲሆን፣ ‹‹ፕሮፌሰሩም በከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ የሩሲያ ባለሥልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ የኢሜይል መልዕክቶችን ጨምሮ፣ ከሒላሪ ክሊንተን ጋር የተያያዙ መረጃዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ነግረውኛል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሩሲያውያን ሒላሪን ማጠልሸት የሚችሉ መረጃዎች አሏቸው፤›› የሚሉት ፓፓዶፑለስ፣ በለንደን ፕሮፌሰሩን ባገኙበት በሚያዝያ 2009 ዓ.ም. ትራምፕ በሪፐብሊካኑ ቅድመ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እመርታ ያገኙበት እንደበርም አስታውሰዋል፡፡

የ30 ዓመቱ ሐሳብ አፍላቂና አማካሪ (ቲንክ ታንክ) ፖፖዶፑለስ፣ የፑቲን ዘመድ ከተባለችና በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይሠራል ከተባለ ሌላ ባለሥልጣን ጋር መገናኘታቸውን፣ የፑቲን ዘመድ የተባለችው ግን በሐሰት እንደበረ የተመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል፡፡

በደለስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እጁን ሰጥቶ ከታሰረ ከሐምሌ 2009 ዓ.ም. ወዲህ በሩሲያና በትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻ መካከል ግንኙነት ነበርን? በሚለው ላይ በተከታታይ ሲመረመርና መረጃ ሲሰጥ የነበረው ፓፓዶፑለስ መጀመሪያ አካባቢ መርማሪዎችን መዋሸታቸው ተዘግቧል፡፡

የማናፎርትና የጌትስ ጉዳይ ግን ከትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ጋር የተገናኘ አይደለም የሚሉ ዘገባዎችም እየተስተዋሉ ነው፡፡ ትራምፕ በትዊተራቸውም ‹‹በማናፎርትና በጌትስ ላይ የተመሠረተው ክስ ከምርጫ ዘመቻው ጋር የሚገናኝበት ጉዳይ የለም፤›› ብለዋል፡፡

ሁለቱ ተከሳሾች በቆጵሮስ፣ በሲሸልስና በካሪቢያን አካውንት በመክፈት 75 ሚሊዮን ዶላር መደበቃቸው፣ ማናፎርት የተለያዩ ወጪዎችን ለመሸፈን 18 ሚሊዮን ዶላር በሕገወጥ መንገድ ማዘዋወራቸው በክሱ ከተመለከቱ ጥፋቶች ይገኙበታል፡፡

በዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ መሪዎች ላይ የተመሠረተው ክስ

 

ጌትስ ለሞርጌጅ፣ ለልጆች ክፍያና ለቤት ማስዋቢያ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ማዘዋወራቸውም የተከሰሱበት አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ የማናፎርት ጠበቃ ኬቨን ዶውኒንግ እንደሚሉት፣ ክሱ ተዓማኒነት የሌለው ነው፡፡ የትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻ ከሩሲያ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንደበረውም ምንም ማስረጃ የለም፡፡

ዶውኒንግ እንደሚሉት፣ ማናፎርት ዩክሬን ከአሜሪካና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር እንድትቀራረብ ሲሠሩ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ. በ2014 ማለትም የትራምፕን የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ከመቀላቀላቸው ከሁለት ዓመታት በፊት የቆመ ነበር፡፡

በሁድሰን ኢንስቲትዩት የቀድሞ ተመራማሪ ፓፓዶፑለስ፣ የትራምፕን የምረጡኝ ዘመቻ የተቀላቀሉት በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ሲሆን፣ በወቅቱ በጎ ፈቃደኛና የነበራቸው ሚናም ውስን እንደነበር የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ሣራ ሳንደርስ ተናግረዋል፡፡ ጠበቃው ግን ምንም አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸውን ሎስአንጀለስ ታይምስ ዘግቧል፡፡

የሙለር ምርመራ ቡድን በሪፐብሊካኑ ላይ ብቻ ሳይሆን በሒላሪ ክሊንተን የምርጫ ዘመቻ መሪ ላይም ያነጣጠረ ነበር፡፡ በዴሞክራቶች ዘንድ ጠንካራ የምርጫ ዘመቻ መሪ የነበሩት ቶኒ ፖዴስታ በሙለር መርማሪዎች ከተመረመሩት አንዱ ናቸው፡፡

ፖዴስታ ፖዴስታ ግሩፕ ከተባለው ድርጅቱ ሥልጣን እንደሚለቁ አስታውቀዋል፡፡ የፖዴስታ ግሩፕ ማናፎርት በምርጫ ዘመቻው ሲያግባቡዋቸው ከነበሩ ሁለት ድርጅቶች አንዱ ሲሆን፣ የፖዴስታ ወንድም ጆን ፖዴስታ ደግሞ የሒላሪ ክሊንተን የምርጫ ዘመቻ ኃላፊ ነበሩ፡፡

በትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ዙሪያ የሩሲያ ጣልቃ ገብነት አለ በሚል የተጀመረው ክስ አነሳሱ በሪፐብሊካኑ ላይ ቢሆንም፣ ዴሞክራቶችም በተጠርጣሪነት እየተመረመሩ ነው፡፡

በዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ መሪዎች ላይ የተመሠረተው ክስ

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...