Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሶማሊያን የሚያውቅ በሰላም ጉዳይ አይደራደርም!

ሶማሊያን የሚያውቅ በሰላም ጉዳይ አይደራደርም!

ቀን:

በያሲን ባህሩ

ለሽብርና ለአክራሪነት መነሻ እየሆነ የመጣ ፅንፈኛ አስተምህሮ በተለያዩ የዓለም አገሮች ታይቶ ከመቻቻልና መከባባር ባፈነገጠ መንገድ ለዕልቂትና ውድመት መንስዔ ሆኗል፡፡ በተለይ በየቀጣናው በሚፈጠሩ ፅንፈኛ ቡድኖች (አልቃይዳ፣ አይኤስ፣ ቦኮ ሐራም፣ አልሻባብ፣  . . . ) ዓይነቶችና የጥፋት ኃይሎች ብዙ ሕዝቦች ለዕልቂትና ለውድመት ተጋልጠው ቆይተዋል፡፡ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሶማሊያንም የገጠማት ይኼው ነበር፡፡

በእርግጥ የአፍሪካ ቀንድ ወይም ምሥራቅ አፍሪካ ተደጋጋሚ ቀውስና ግጭት የሚታይበት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በቀደመው ጊዜ የአገሮች የእርስ በርስ ግጭት፣ ድርቅና ረሃብ፣ የድንበር ፍጥጫ (ኢትዮ ኤርትራ፣ ኢትዮ ሶማሊያ፣ ሱዳን ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ ጂቡቲ) ይጠቀሳሉ፡፡

   ባለፉት አርባ ዓመታት በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ጎልተው የታዩ አምስት የሚሆኑ ጦርነቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ በየአገሮቹ የታዩ ጦርነቶች የጎረቤት አገሮችን የጎተቱ ነበሩ፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኝ አንድ አገር የራሱን ውስጣዊ ጉዳይ ማስተካከል ሲሳነው፣ ወዲያው የአካባቢውን አገሮች የሚያደፈርስ ፍንዳታ ይሆናል፡፡ ከአምስቱ ጦርነቶች አንደኛው የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ነበር፡፡ ይህ ጦርነት የየመንግሥታቱን ሀብት በማውደም በመጨረሻ ወደ ውድቀት እንዲያመሩ ያደረጋቸው ነበር፡፡ ሶማሊያ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በመዘፈቅ የተበታተነች አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ አልሸባብን ለመሰለ አሸባሪ ኃይል መፈልፈያ ምቹ ማህፀን ለመሆን የተዳረገችው በዚህ መንገድ ነው፡፡

አልሸባብ የተባለው ፅንፈኛ ቡድን ግን ህልሙ ከዚህች አገርም አልፎ፣ ዓለም አቀፍ ሽብርተኛ መሆን ነበር፡፡ በተለይ ከሁለት ዓመት በፊት በአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን የተገደለው የአሸባሪው መሪ አህመድ አብዲ ጎዳኔ ደጋግሞ እንደሚለው ከአፍጋኒስታን፣ ከፓኪስታን፣ ከአሜሪካ፣ ከጀርመን፣ . . . በሚመለምላቸውና በተለይ ከኬንያ ደቡብ ምዕራብ ግዛት አሰባስቦ ባስታጠቃቸው ተዋጊዎቹ ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን፣ ለምሥራቅ አፍሪቃ አገሮች የደኅንነት ሥጋት እንደሚሆን ይናገር ነበር፡፡

 ከካምፓላው የቦምብ ጥቃት በኋላ ጎዳኔ በሰጠው መግለጫ፣ ‹‹በካምፓላ የደረሰው ጥቃት የመጀመርያ ነው፡፡ ገና ምን ዓይታችሁ?›› ብሎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ጦርነቱን በአሜሪካ ምድር ላይ አደርገዋለሁ ሲልም ዝቷል፡፡ ሸሪዓ በመላው ዓለም አገሮች ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስም ጦርነቱ እንደማያባራ ሲናገር፣ የልብ ልብ እየተሰማው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ “The wars will not end until Shariya is implemented in all continents in the world’’.

 ይህ የሽብርተኞች ከንቱ ምኞት ደግሞ ተቀባይነት የሌለውና ዓለምን በአንድ የሚያሠልፍ አካሄድ ነበር፡፡ የአንዱን እምነት አንድ ሰበዝ መዝዞ በሌሎች እምነቶች  ላይ የመጫን ድፍን ዓለም የማይፈልገውና የማይቀበለው አቋም ነው፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ በትልቁ ሲፈሩ የነበሩት አልቃይዳና አይኤስ ሳይቀሩ እነ ሶሪያና ኢራቅን ቢያፈራርሱም ከገጸ ምድር እየጠፉ ሉት፡፡

 ባለፉት 20 እና ከዚያ በላይ ዓመታት ግን በሶማሊያ ውስጥ በተፈጥሮም ሆነ በበሽታ፣ ከሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ጋር በሚደረገው የእርስ በርስ ጦርነትም ሆነ ከአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪዎች ጋር በሚደረገው ሽኩቻ ካለቀው የሶማሊያ ሕዝብ ቁጥር፣ በአብዲ ጎዳኔ ታጣቂዎችና መሰል አሸባሪዎች የሞቱት ንፁኃን ዜጐችና ታጣቂዎች ቁጥር ይበልጣል፡፡ ከሞቱትና ከተሰደዱት የዚህች አገር ዜጎች በላይ የወደመው ልማትና አሁንም ድረስ አስተማማኝ ያልሆነው ሰላም አንድ ትውልድ ወደ ኋላ የሚመልስ ድቀት ነው፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ጎረቤት አገሮችም ሶማሊያን ያየ በሰላም ዕጦትና በሽብር አይጫወቱም የሚል አስተምህሮት አላቸው፡፡ 

 አልሸባብ የበቀለበት በእንግሊዝና በጣሊያን ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩት የሶማሊያ ግዛቶች እ.ኤ.አ. በ1960 ነፃነታቸውን ሲቀዳጁ፣ በእንግሊዝና በጣሊያን አገዛዝ ሥር የነበሩትን የሰሜንና የደቡብ ሶማሊያ ሁለት ግዛቶችን አንድ ላይ በማዋሀድ የተመሠረተ ነው፡፡ ከሶማሊያ መመሥረት በኋላ አገሪቱን ለረዥም ጊዜ የመራው የመሐመድ ዚያድ ባሬ መንግሥት ነው፡፡

ያ መንግሥት ለሶማሊያ ሕዝብ መሻሻልና ብልፅግና ከመሥራት ይልቅ፣ ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት አባዜ ተጠናውቶት በኬንያ፣ በጂቡቲና በኢትዮጵያ መንግሥታት ሥር ያሉ ትውልደ ሶማሌዎችን በራሱ አገዛዝ ሥር ለመጠቅለል ተንቀሳቅሷል። እናም እ.ኤ.አ. በ1964 በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት፣ ኋላ ላይም እ.ኤ.አ. በ1977 በደርግ መንግሥት ላይ ጦርነት አውጇል፡፡ በወቅቱ በነበረው የአገራችን ሠራዊትና በአይበገሬው የአገራችን ሕዝብ ድባቅ ተመቶ ተመለሰ እንጂ፡፡

 ወረራዎቹን ተከትሎም የዚያድ ባሬ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ውድመት ደርሶበታል፡፡ በዚህም ሳቢያ በዚያች አገር በተፈጠሩ አንጃዎች ምክንያት አገሪቱ መንግሥት አልባ ልትሆን ችላለች። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የሽብርተኝነት አደጋ አገራችን ላይ የተደቀነው ከዚያድ ባሬ መንግሥት መፈረካከስ ማግሥት በኋላ ነው፡፡

መንግሥት አልባ የነበረችው የያኔዋ ሶማሊያ ቢያንስ ለ22 ዓመታት ገደማ ሰላምና መረጋጋት አጥታ የአሸባሪዎች መናኸሪያ ሆና ቆይታለች፡፡ ምንም እንኳን ከጥቂት ዓመታት በፊት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶት፣ በአሁኑ ወቅት አንፃራዊ መረጋጋት ቢታይባትም፡፡ በዚህች አገር የመሸጉና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰባሰቡ አክራሪዎችና አሸባሪ ቡድኖች የሶማሊያ ሕዝብን ብቻ ሳይሆን፣ ቀጣናውን በማተረማመስ ጭምር በርካታ የሽብር አደጋዎችን ማድረሳቸው አይዘነጋም፡፡

 አሸባሪ ኃይሎቹ በኬንያ፣ በሩዋንዳ፣ በኡጋንዳና በኢትዮጵያ ያደረሷቸው ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶች ምንኛ አሰቃቂ እንደነበሩም አይዘነጋም። በዚህም ሳቢያ ሶማሊያውያን በገዛ አገራቸው ለደኅንነታቸው ዋስትና አጥተው፣ በየጎራው ያኮረፉ የጦር አበጋዞች ጠብመንጃና የኃይል ዕርምጃን ብቸኛው አማራጭ አድርገውባቸው፣ እንዲሁም በጎሰኝነት የመከፋፈል ጣጣ ተጭኖባቸው ለሞት፣ ለእንግልትና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ አሁን አገሪቱ የተረጋጋች፣ ቢያንስ በሰላማዊ ምርጫ ለመሪዋ ኃላፊነት ሰጥታ፣ ከጎሳ ጭቅጭቅ ቀስ በቀስ እየወጣች፣ አልሸባብን አዳክማ ወደ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አተኮረች ሲባል፣ ከሳምንት በፊት በመዲናዋ ሞቃዲሾ ከ300 በላይ ንፅኃን ዜጎችን ለአሰቃቂ ዕልቂት ከዚህ በላይ የሚሆኑትንም ለአካል መጉደል የዳረገ የሽብር ጥቃት ተፈጽሞባታል፡፡ ሰሞኑንም በርካታ ሰዎች ያለቁበት የሽብር ጥቃት ተፈጽሞባታል፡፡

 ለእነዚህ ጥቃቶች አልሸባብ የተባለው የለየለት ሽብርተኛ ቡድን በይፋ ኃላፊነቱን ባይወስድም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ፖለቲከኞች፣ ሚዲያዎችና መንግሥታት ጣታቸውን በእርሱ ላይ ከመቀሰር አልተቆጠቡም፡፡ በዚያው ልክ አሁንም የሶማሊያ መንግሥትና የፀጥታ ኃይሉ ዓለም አቀፍ ድጋፍን የሚሻና እንደ ሕፃን እግር ያልጠነከረ እንደሆነ በመነገር ላይ ነው፡፡ የሶማሊያ ሕዝብ ግን አሁንም ከአብራኩ በወጡ ጨካኞች ድንገት እንደወጣ የሚቀር መሆኑን ዳግም ከመመልከቱ ባሻገር፣ ዋስትና አልባ ሕይወት እየመራ እንደሆነ እየተናገረ ይገኛል፡፡

አልሸባብ በሶማሊያ ቆይታው ከአልቃይዳና አይኤስን ከመሰሉ ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር የተስማማ ቢሆንም፣ ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም። ወትሮም የሕዝብ ድጋፍ የሌለው ማንኛውም ኃይል መሰነጣጠቁ አይቀርምና ቡድኑም በሶማሊያ ሕዝብ በመተፋቱ ሳቢያ ዕጣ ፈንታው በሁለት ትንንሽ ቡድኖች መከፋፈል ነበር። አንደኛው በወቅቱ ሶማሊያን የሸሪዓ ሕግና የእስልምና መንግሥት እንደሚመራት በይፋ ያወጀው ብሎም ራሱን ‹‹የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ኅብረት›› እያለ የሚጠራው ፅንፈኛ ቡድን ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ ‹‹ሃረካት አልሸባብ አልሙጃህዲን›› (በአጭሩ ‘አልሸባብ’) የተሰኘው የሽብር ቡድን ነው። 

 ይህ ቡድን እንደ ሌሎቹ አሸባሪዎች ሁሉ በተቆጣጠራቸው ቦታዎች ውስጥ ያሉ ሶማሊያውያንን ቁም ስቅላቸውን ከማሳየት ባለፈ፣ በአገራችን ላይም የጀሃድ ጦርነት አውጇል። ግና አሸባሪዎች በአገራችን ላይ የያዙትን ዓላማ ሳይለቁ ራሳቸውን በስም መቀያየር ብቻ እየሰየሙ መፈራረቃቸው፣ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ያደረጉትን ከንቱ ጥረት ያሳያል፡፡ ሆኖም በኃይል ሕዝብን ከማሸበር ተግባራቸው ሊታቀቡ አልቻሉም፡፡

አልሸባብ ሶማሊያንና የአካባቢውን አገሮች ለማሸበር በግልጽ የአልቃይዳ ክንፍ መሆኑን ማወጁ አይዘነጋም፡፡ ቀደም ሲል በዚያች አገር የተገኘው አንፃራዊ የተረጋጋ ሁኔታ መልሶ መደፍረሱ ኃይሉ ክፉኛ ተዳክሟል ከተባለበት ጊዜ በፊት የሚነገር ነበር። በዚህም ሳቢያ የሽግግር መንግሥቱ ከሰባት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ዕገዛ እንዲያደርግለት ባደረገው ጥሪ መሠረት፣ የመከላከያ ሠራዊታችን ዳግም በ2003 ዓ.ም. ወደ ሶማሊያ ዘልቆ አልሸባብን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶታል፡፡ በአልሸባብ ደፍርሶ የነበረውን የአገሪቱን ሰላም መልሶ ወንድም ለሆነው የሶማሊያ ሕዝብ አንፃራዊ በሆነ ሁኔታ ለማስገኘትና ቀጣናዊ የሥጋት ደመናን ለማስወገድ ለሁለት ዓመታት ያህል ቆይታ አድርጓል፡፡

  በተጨባጭም የመከላከያ ሠራዊት በዳግም የሶማሊያ ቆይታው አሸባሪ ቡድኑን ለማዳከም ችሎ ነበር፡፡ የሽግግር መንግሥቱንም አጠናክሯል፡፡ በምርጫ አሸንፎ አገሪቱን የሚያስተዳድር መንግሥት እንዲመሠረትም የነበረው ሚና የላቀ ነበር፡፡ ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከዚህ አኩሪ ተግባር በኋላ ለሶማሊያ መረጋጋት ትኩረት እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ በመሆኑም የአፍሪካ አገሮች በሶማሊያ ጦራቸውን ለማሰማራት የገቡትን ቃል ተግባራዊ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል፡፡ በውጤቱም የኡጋዳና የቡሩንዲ ሰላም አስከባሪዎችን ለማገዝ የጅቡቲ፣ የኬንያና የሴራሊዮን ሰላም አስከባሪዎች የአሚሶምን ተልዕኮ መቀላቀላቸው ይታወሳል።

በተባባረ ክንድ የተዳከመው አልሻባብ ከሶማሊያ ዋና ዋና ከተሞች ተጠራርጎ ከመውጣቱ ባሻገር ዋነኛ የጥቃት መሠረቱ የነበሩ ቦታዎችንም እንደለቀቀ ይታመናል፡፡ ይሁንና አሁንም ህብዕ የሆኑ ህዋሳት ስላልተበጣጠሱና አሻባሪነት አንዱ አስቸጋሪ በሆነው ባህሪው ምክንያት፣ ሶማሊያውያንን ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡ በአንድ ተሽከርካሪ የአጥፍቶ ማጥፋት ጥቃት ሙሉ ሕንፃ ማፍረስ፣ ንፁኋን ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የራሱ ወገኖችን መፍጀት አሳፋሪ የአረመኔነቱ መገለጫ ሆኖ ይታያል፡፡

 የአሸባሪው ቡድን እጅግ ዘግናኝ ድርጊት ዓባይን በጭልፋ ሳይሆን በማንኪያ በመጭለፍ ዓይነት ለግንዛቤ ያህል እንዲህ ገለጽኩት እንጂ፣ ገዳይነቱ እንኳንስ በዚህ አጭር ጽሑፍ ቀርቶ በበርካታ መጻሕፍቶችም ተተርኮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከሞላ ጎደል ከሞቃዲሾ ብቻ ሳይሆን፣ ከሶማሊያም ተገፍቶ ወጥቷል፣ ተዳክሟል በተባለበት በዚህ ወቅት ንፅኃንን ዒላማ በማድረግ ያደረሰው ዘግናኝና የብዙ አገሮች ሕዝቦችን ያስቆጣ ጥፋትና ሳጥናኤላዊ ምግባሮቹ ዛሬም ድረስ በደጋፊዎቹ ልቦች ውስጥ እንዳሉ ያመላክታል፡፡

በመሠረቱ እንኳስ በምሥራቅ አፍሪካ ይቅርና በሶማሊያም ቢሆን አልሸባብ የበላይ ሊሆን የሚችልበት አንዳችም መሠረታዊ ለውጥ አለማሳየቱን ዛሬም ድረስ ሞቶ እየተነሳ በሚደርሰው ጥፋት መለካት ይቻላል። እንደሚታወቀው አሸባሪው ቡድን የሶማሊያን ሕዝብ እጅግ በሚዘገንን የጭካኔ ተግባር እየጨፈጨፈው ነው፡፡ ከዚም አልፎ ለቀጣናውና ለአካባቢው ልማትና ሰላም እንቅፋት በመሆን የለየለት ውንብድና ላይ ተሰማርቶ ዓለም አቀፍ ውግዘት ሲደርስበት ከርሟል፡፡ ይኼ ደግሞ ሰላምና ዕድገት ለሚናፍቁና ለሚያስፈልጋቸው ሕዝቦች ዘንድ ፍፁም ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችል አይደለም፡፡

ለነገሩ አልሸባብ በየጊዜው ‹‹ለእስልምና ቆሜያለሁ፤›› እያለ ቢለፍፍም በገዛ ሕዝቡ ላይ የሚፈጽመው ግድያና የከፋ እንግልት አሸባሪ እንጂ፣ የሃይማኖት ቡድን መሆኑን የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡ ለምን ቢባል እስልምና የሰላም ሃይማኖት እንጂ፣ ‘ሰዎችን ግደል፣ አንገላታ’ ብሎ ስለማያስተምር ነው፡፡ በቅዱስ ቁርዓን ላይ በግልጽ እንደተጠቀሰው እስላም ለዓለምና ለሰዎች ደኅንነት የሚፀልይ ሰላማዊ ሃይማኖት ነው፡፡ እናም ይህ እውነታም ዛሬ ራሱን በሃይማኖት ስም ጀቡኖ በማሸበር ተግባር ላይ ከተሰማራው ቡድን ጋር በፍጹም የሚገናኝ አይደለም፣ ‹አራምባና ቆቦ› እንዲል የአገራችን ሰው፡፡ ለዚህም ነው ድርጊቱ እነ አይኤስና አልቃይዳ እንኳን በተዳከሙበት ወቅት ዘግናኝ በመሆኑ ጥቃቱን እኔ ፈጸምኩት ለማለት ድፍረት ሲያጣ የታየው፡፡ ለሁሉም ቀጣናችንንም ሆነ አገራችንን ከሰላም ዕጦት እንጠብቅ፣ ሽብርተኝነትንም እንከላከል ብዬ ሐሳቤን ልቋጭ፡፡ ሰላም!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...