በተፈራ ይርጉ
በዚህ አገር ውስጥ የምንኖር ሕዝቦች ታሪክ የውድቀትም ይሁን የድል፣ የዕድገትም ይሁን የክሽፈት በየዘመኑ በነበሩ አባቶች ጥልቅ አገራዊ ስሜት አብሮነት የተገነባ መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ በገዥዎች መካከል በነበረ የግዛት ማስፋፋትም ይባል፣ እርስትና ግብርን የማብዛት ህልም ጦርነቶች እየተካሄዱ የሰውም የንብረትም ጥፋት (በየትኛውም ዓለም የነበረ የኃያልነት ፍልሚያ የወለደው ቢሆንም) ተፈጽሟል፡፡ በዚህ ሒደትም ሕዝቡ እንደ ሕዝብ ተሳስሮና ተባብሮ ከመኖር ያገደው አልነበረም፡፡
ማንም ቢሆን (መሪም፣ ፓርቲም፣ መንግሥትም) ኃላፊ፣ ጠፊና የሚቀያየር ነው፡፡ አገር ግን ቢቻል እንደገና እየተሻሻለ ባይሆንለት ደግሞ ነባር ይዞታውን ይዞ ተማምኖና ተሳስቦ እንዲቀጥል ማድረግ ተገቢና አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየትም ነው፡፡
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ያለፉትን ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዞች በአመለካከትም ሆነ በአወቃቀር እንዲፈራርሱ አድርጓል፡፡ ቢያንስ የዴሞክራሲ ጭላንጭል (ከነችግሩ) እንዲታይም ማድረግ ችሏል፡፡ በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ የአገሪቱን መሠረተ ልማቶች፣ የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች ለማምጣት የሄደበት ርቀትም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡
በዓለም አቀፍ መረጃዎች ወይም በመንግሥት አኃዞች እንደሚታየው ባለፉት 25 ዓመታት የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ 100 ሚሊዮን ተቃርቧል፡፡ ከዚህ ውስጥ 30 በመቶ በትምህርት ላይ እንዲገኝ መደረጉ፣ በ1983 ዓ.ም. 45 ዓመት የነበረው በሕይወት የመኖር አማካይ ዕድሜ አሁን 64 ዓመት መድረሱ፣ የነፍስ ወከፍ ገቢውም አምስት እጥፍ አድጎ ወደ 600 ዶላር በዓመት መጠጋቱ ተጨባጭ የለውጥ ማሳያዎች ናቸው፡፡
እነዚህ መልካም ተስፋዎች ቢኖሩም አሁንም 22 በመቶ የሚደርሰው ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ሲሆን፣ 17 በመቶ ያህሉ ደግሞ ሥራ አጥ ነው፡፡ ይህ ሥራ የሌለው ደሃ የሚባለው ኃይል ወጣትና በትምህርትም ሆነ በግንዛቤ ‹‹የተሻለ የሚባለው›› በመሆኑም አገር ጥሎ ከመሰደድ ጀምሮ የለውጥ ቀዳዳ የሚለውን ፈለግ ሁሉ ጥሶ ከመሄድ ወደኋላ ሊል አይችልም፡፡ በተግባርም እየታየ ያለው ይኼው እውነታ ነው፡፡
ኢሕአዴግ የመሠረተው መንግሥት ከኢኮኖሚያዊ ተስፋዎቹ በተቃራኒ የሚተችባቸው ጉዳዮችም (ገና ከመነሻው ጀምሮ) ትንሽ አይደሉም፡፡ የኤርትራን የነፃነት ጥያቄ የመለሰበት በተለይ የአገሪቱ ወደብ አልባ መሆን፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ለሩብ ክፍለ ዘመን ያልተቋጩ የጋራ ድንበሮች ጉዳይ፣ በአገር ውስጥ ከብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት መላላቱና አንድነት መሸርሸሩ ይጠቀሳሉ፡፡
ከሁሉ በላይ ሥርዓቱ በግንባር ቀደምነት መርቶ ሥራ ላይ ከዋለው ሕገ መንግሥት ጋር የሚጋጩ ሕግጋትና የአፈጻጸም አቅጣጫዎች መውረዳቸው፣ ዴሞክራሲውን እየጎዱት እንደሆነ ተደጋግሞ መነገር ይዟል፡፡ በተለይ ከመደራጀት፣ ሐሳብን ከመግለጽ፣ የተቃውሞ ሠልፍ ከማድረግ፣ ነፃ ማኅበራትን ከመፍጠር፣ ወዘተ. አንፃር ያለው ፈተና የቁጣና የቅሬታ ምንጭ ነው፡፡ እዚህ ላይ በሕገ መንግሥቱ ከተጻፈው በተቃራኒ የፖለቲካ ምኅዳር እየቀፈደደው የመጣው የኢሕአዴግ ፍልስፍና ከሌሎች አገሮች ተሸራርፎ የተዳቀለ ነው የሚሉም ብዙዎች አሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በ1949 የቻይናው አብዮታዊ መሪ ማኦ ዜዲንግ ‹‹አዲሱ ዴሞክራሲ›› ያለውን መርህ ‹‹ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የበላይነት›› በሚል ስያሜ የተቃዋሚ ኃይሎች ድምፅ እንዳይሰማ መቆጣጠሪያ ሥልት አድርጎት ነበር፡፡ የሩሲያው ሌኒንም ‹‹ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት›› ሲል ያወጣውን የፍፁም ሥልጣን መሠረት (Democratic Dictatorship) ያለ ጥያቄና ያለ መንገራገር ‹‹በተወስኗል›› ፈሊጥ አድርባይነት እንዲነግሥ አድርጓል፡፡ የእነዚህ አገሮች መሪዎች ተሞክሮ አምሳያ በዚህች አገር የፖለቲካ አየር ውስጥ እያረበበ መምጣት፣ አማራጭ ሐሳቦች (በራሱ በገዥው ፓርቲም ውስጥ ሆነ በውጭ) ቦታ እንዳይኖራቸው አድርጓል የሚለው ሙግት ክብደት እያገኘ መጥቷል፡፡
‹‹ከ26 ዓመታት በኋላ በመነቃቃትና ለውጥ ውስጥ የነበረችን አገር ወደ ኋላ የሚመልስ ሁከት፣ የሕዝብ ቁጣና ተቃውሞ ያመጣው የፌዴራል ሥርዓቱ አይደለም፤›› የሚሉ ነባር የፖለቲካ ተንታኝ አጋጥመውኛል፡፡ እኝህ ሰው በዓለም ላይ 29 አገሮችና 2.4 ቢሊዮን ሕዝቦች በፌዴራል ሥርዓት መተዳደራቸውን ብቻ አይደለም የሚገልጹት፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ የምትከተለው ‹‹ብሔር ተኮር›› የሚባለውን ፌዴራሊዝም ግን እንደ ህንድና ናይጄሪያ ያሉት አገሮች እንደተገበሩት ይጠቅሳሉ፡፡
በእነዚህ ሁለት አገሮች ግን የዴሞክራሲያዊነት ጉዳይ ህልውናቸውን ክፉኛ ሲፈትን ታይቷል፡፡ ለአብነት እንኳን ናይጄሪያ ብታድግም፣ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖራትም የብሔርና የሃይማኖት ፍጥጫን የጋበዘ ኪራይ ሰብሳቢነት (Rent Seeking) እና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ውስጥ ተዘፍቃለች፡፡ በተቃራኒው ከ1,600 በላይ የብሔር ብሔረሰብ ቋንቋዎች የተመዘገቡባት ህንድ ቀስበ በቀስ ከእርስ በርስ ግጭትና መፋጠጥ እየወጣች፣ የበለፀገ ኢኮኖሚና ለሦስተኛው ዓለም ሞዴል የተባለ ዴሞክራሲን በመገንባት ላይ ባለች አገር ብዝኃነት ያለ ዴሞክራሲ ‹‹ከብት ባልዋለበት ኩበት ፍለጋ›› ነውና፡፡
እንደ ተንታኙ እሳቤ በብሔርና በቋንቋም ሆነ በጂኦግራፊና በሥነ ልቦና ትስስር ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝም የዴሞክራሲያዊነት ወፍራም ማገር ካላበጀ ከውድቀት አይድንም፡፡ ከፌዴራሊዝም የዓለም ታሪክ ስንመዝ ጀርመን ናዚ ባስከተለባት ውርደት ምክንያት እ.ኤ.አ. ከግንቦት 9 ቀን 1945 በኋላ መንግሥት አልነበራትም፡፡ በኃያላን አገሮች ወታደራዊ ዕዝ ሥር እስከ 1949 ቆይታለች፡፡ ሕገ መንግሥቱ እ.ኤ.አ. በ1949 ከፀደቀ በኋላ የመጀመርያው የአገሪቱ ቻንስለር በመሆን የተመረጡት ኮንራድ አደናወር (የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት ሊቀመንበር) ግን መሠረታዊ መነሻ ያደረጉት ዴሞክራሲያዊነትን ነበር፡፡ በመሀል ላይ በሥርዓቶች መለዋወጥ፣ በርዮተ ዓለም የቀዘቀዘው ጦርነት ፍልሚያ ጀርመንን እስከ መለያየት ቢደርስም አንድ ጊዜ መሠረቱን በማይናወጥ አለት ላይ አስፍሯልና የዳበረ ኃያል አገር ለመሆን በቅቷል፡፡
የእንግሊዝ፣ የአሜሪካና የፈረንሣይ ዓይነቶቹን የፓርላማ ዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ሠለጠነው ፈለግ እየተመሙ ያሉ አገሮች የለውጥ ታሪክ መሠረቱ ልማት ብቻ አይደለም፡፡ ዋነኛው የአገራዊ ጉዞው ምሰሶ ዴሞክራሲ (ነፃነት፣ መደማመጥ፣ ፍትሐዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ የማሻያማ ግልጽነትና ተጠያቂነት. . .) እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡
ልማት፣ ድህነት ቅነሳና አገራዊ ዕድገት ብቻውን ምሉዕነት ያለው የሕዝብ እርካታን እንደሚያመጣ ከ60 ዓመታት በፊት የባቡር፣ የግዙፍ መሠረተ ልማትና መሠረታዊ ፍላጎት ያሟሉት ከሁለትና ሦስት አሠርት ዓመታት በፊት መካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ የደረሱት ሊቢያ፣ ግብፅ፣ ቱኒዚያና አልጄሪያ. . . የለውጥ ማዕበል ባልተቀሰቀሰባቸው ነበር፡፡ እነ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ሶሪያና የመንም ዕልቂት የሚጋብዝ ውጥንቅጥ ውስጥ ባልገቡም ነበር የሚለውን መከራከሪያ አለመፈተሽ ሞኝነት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ገና ብሔራዊ መግባባትን ፈጥሮ በዴሞክራሲያዊ አንድነት ያልቆመባቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ ቀዳሚው አሻሚው የታሪካችን እውነታ ነው፡፡ አንዱ ድል፣ ስኬትና አገራዊ ማንነት የሚለውን ጉዳይ ሌላው ሽንፈት፣ ጥቃት ወይም ጥፋት ይለዋል፡፡ አንዱ ‹‹የአገሪቱ አባት›› የሚለውን ቀደምት መሪ፣ ሌላው ‹‹ጠላት›› እያለ ለትውልድ የሚተላለፍ ሐውልት ይሠራበታል፡፡
ያለመግባባቱ ከሕገ መንግሥቱ አናቅጽትም ጋር ይገናኛል፡፡ አንዱ አንቀጽ 39 ‹‹ይበትነናል›› ሲል ሌላው ‹‹ዋስትናችን ነው›› ይላል፡፡ በቡድንና በግል መሻት፣ በመንግሥት ሦስቱ ክንፎች የሥልጣን መለያየት፣ በፌዴራል ሥርዓቱ አከላለል፣ በማንነት ጥያቄ አመላለስ. . . ቀላል የማይባል አለመተማመንና መጠራጠር እንደተጋረጡ ናቸው፡፡
ከሁሉ በላይ ገዥው ፓርቲ ፖሊሲ አውጥቶ እየተገበራቸው ባሉ የልማት ሥራዎች፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ግንባታ ተግባራት ላይ እንኳን የተሟላ አጋርነት የማያሳዩ የፖለቲካ ኃይሎች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ታላቁ የህዳሴ ግድብን ያህል ግዙፍና ወሳኝ ፕሮጀክት ‹‹የሚያልቅ ሥራ አይደለም፣ በአነስተኛ ፕሮጀክቶች ሊተካ ይገባ ነበር፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያፋጥጥ ሥራ ነው፣ አገሪቷን ለከፍተኛ ብድር ያጋልጣል፣ ኢሕአዴግ ለፖለቲካ ትርፍና የሕዝቡን አመለካከት ለማስየቀር ነው. . .›› እያሉ ሲተቹት ነበር፡፡ ይኼ በልማት ሥራዎች ላይ ሳይቀር ያለው ልዩነት አሁንም መስፋቱን ያሳያል፡፡
ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ በአንድ እውነት መስማማት ተገቢ ነው፡፡ ሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎችና ዜጎች በሁሉም ጉዳዮች ላይ ላይስማሙ ይችላሉ፡፡ የመግባባት ምልዑነት የትም አገር ቢሆን የለምና፡፡ ይሁንና ዴሞክራሲያዊ ባህልን በመገንባት አገሪቷን ወደፊት ለመግፋት እንደሚመኝ መንግሥትና ሕዝብ፣ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መግባባትና መተማመን መፍጠር የግድና አስፈላጊ ነው፡፡
ለአብነት ያህል ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊና ወሳኝ በሚባሉት ተቋማት ገለልተኝነት፣ ፍትሐዊነትና ብቃት ላይ ብቻ ሳይሆን የባለቤትነት ስሜት ላይ የተራራቀ ማኅበረሰብ አንድ የጋራ እሴት ለመገንባት አይቻልም፡፡ በዚህ ረገድ በምርጫ ቦርድ፣ በእንባ ጠባቂ፣ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና በመንግሥት ሚዲያዎች ላይ እየወረደ የነበረው ትችትና ‹‹አናምናቸውም›› ቅዋሜ በአንድ ዕርምጃ ሊሻሻልና ሊታረም ግድ ይኸው ነበር፡፡
በተመሳሳይ የመከላከያ ኃይሉ፣ የፖሊስ፣ የደኅንነት ኃይሉና የሥርዓቱ መለያየት (ገለልተኝነት) ጉዳይም አዲስ ዓይነት ዕርምጃ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ሂሳዊ አስተያየት እንደሰነዘሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት (ጆቤ) እምነት፣ የመከላከያና የፀጥታ ኃይሉ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ የኢሕአዴግ ርዕዮት ካልተለቀቀ እስከ መቼውም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ማምጣት አይቻልም፡፡ እንዳለፈው ሥርዓት ወደ ዜሮ ድምር ፖለቲካ መውረድንም ያስከትላል፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የዴሞክራሲ ሽግግር (Transformation) ያስፈልጋል የሚባልበት ሌላው ምክንያት፣ ሲቪል ሰርቪሱና የኢሕአዴግ ድርጅታዊ መዋቅር የተሰናሰሉበትን ገመድ የመበጠሱ ተግባር ነው፡፡ በየትኛውም ዓለም የገዥው ፓርቲ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ሳይበጣጠሱ በሲቪል ሰርቪሱ መተግበር አለባቸው፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ግን ትስስሩ ከፖሊሲ ማስፈጸም በላይ ነው፡፡
የገዥው ፓርቲ ተሿሚዎች ሲቪል ሰርቪሱን ይመራሉ፡፡ የኢሕአዴግና የአባል ድርጅቶቹ አባላት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ‹‹ሠራዊት›› ናቸው››፡፡ የፓርቲ አባላት ምልመላ፣ ስብሰባና መዋጮ በቢሮክራሲው ውስጥ ያለገደብ ይከናወናል፡፡ የመንግሥት የጽሕፈት ቤት መሣሪያ፣ ተሽከርካሪ፣ አዳራሽ፣ አለፍ ሲልም በጀት ለፓርቲ ሥራ ማዋል የተለመደ ነው፡፡ አሁን አሁን ደግሞ የሚደበቅና የሚያስወቅስ ሳይሆን የሚያስመሰግን በመሆኑ በተለይ በክልሎች በእጅጉ ተስፋፍቷል፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ወይም አመራር ሆኖ የተገኘ የሚደርስበት ውግዘት ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ኢሕአዴግም ሆነ ሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች የፓርቲና የመንግሥት መደበላለቅን ለማስቀረት ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የተገዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊና ሕጋዊ መንገድን እስከተከሉ ድረስ፣ በመላው አገሪቱ በነፃነት ያለሥጋት እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ጉዳይ ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም፡፡ እንደስከዛሬው ‹‹የትም አይደርስ›› የተባለውን ለቅቆ፣ ሕዝብ የሚደግፈውን ለጉሞ ለማቆም መሞከር ትርፉ የሕዝብ ቁጣን መጋበዝ ነው፡፡
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ አገራዊ ስሜቶችን የሚገነቡ ሥራዎች በጣም ያስፈልጋሉ፡፡ አንደኛው ልማቱን በፍጥነትና በፍትሐዊነት ማስቀጠል ነው፡፡ ሁለተኛው ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ማስወገድ ነው፡፡ ሦስተኛውና ዋናው ግን ግልጽነትና ተጠያቂነትን የመሳሰሉ የዴሞክራሲ እሴቶችን የመተግበር ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ አሁን እየታየ እንዳለው ገዥው ፓርቲ በልማቱ መስክ ያሳየው ዓይነት ውጤት በሌሎች መስኮች አለማሳየቱ ውድቀት እያሳየ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚጋፉ ብሔር ተኮር ግጭቶች አስፈሪ ገጽታ መያዛቸው ሊተኮርበት ይገባል፡፡
በተለይ የፌዴራል መንግሥት የጋራ እሴቶች በማጠናከር በኩል ያለው ክፍተትም ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡ እንደ አገር ያለን የጋራ የሥራ ቋንቋ፣ የጋራ ሰንደቅ ዓላማችንና የወል ተቋማት እንዴት እየተከበሩና እየተጠበቁ ነው? ሥነ ጥበቡና መንፈሳዊ ቅርሶች እንዴት የጋራ ሀብት እየሆኑ ነው? ከሃይማኖት ነፃነት በተጨማሪ የአማኞች አብሮነትና መተሳሰብ እንዴት እየተገነባ ነው? በብሔርና ብሔረሰቦች መካከል የነበረውን ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር (መዋለድ፣ መጋባት፣ ማኅበር፣ ዕቁብና አክሲዮን መመሥረት. . .) እንዴት እያበረታታ ነው? . . . የሚል ሙግትና ውይይት ያስፈልጋል፡፡
እነዚህ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የሚፈጸሙ ማኅበራዊና ልማዳዊ ክስተቶች ከዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጋር ምን አስተሳሰራቸው? የሚል ይኖራል ብየ አልገምትም፡፡ ዛሬ ከ50 በላይ ራሳቸውን የቻሉ ግዛቶች ያቀፈችው አሜሪካ አገራዊ ልዕልና (Hegmomy) ከዜጎችም አልፋ በዓለም ሕዝብ አዕምሮ በማንገሷ ነው፡፡ ያውም አሜሪካ የራሱ ባህልና ግልጽ ማንነት ያለው ሕዝብ የሚኖርባት እንዳልሆነ እየታወቀ፡፡
በእኛ ሁኔታ ደግሞ ገና ከኋላ ቀርነትና ድህነት ሙሉ በሙሉ ባልተላቀቀ ማኅበረሰብ ውስጥ ከአንድነትና አብሮነት ይልቅ ልዩነትን በማንቀሳቀስ፣ ከጋራ እሴቶች በበለጠ የተናጠል መገለጫዎችን እያሟሟቁ የጋራ ቤት መሥራት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ‹‹በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት›› የሚለውን መፈክር ገልብጦ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ኅብረትን ማስቀደም ካልተቻለ፣ አሁን እየታየ ያለውን ሥጋት ማስቀረት በቀላሉ የሚቻል አይደለም፡፡
ለማጠቃለል ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ትራንስፎርሜሸን ለማምጣት እንነሳ ሲባል በአንድ ወገን (በመንግሥት) ጥረት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መገናኛ ብዙኃንና የተለያዩ ሲቪክ ማኅበራትን ጨምሮ ዜጎችንም የሚመለከት ነው፡፡ የዴሞክራሲ ባህል ሥርፀትና ትግበራ ከእነዚህ ተዋናዮች ውጪ ዕውን ሊሆን እንደማይችል ተገንዝቦ መትጋት ያስፈልጋል፡፡
የአገራችን ዴሞክራሲ ሽግግራዊ ለውጥ ማምጣት ወይም በአሳታፊነቱና የሕዝብ ተጠቃሚነቱ ማደግ ለሁሉም ተግባራት ወሳኝ መሆኑን መፈተሽም ግድ ይላል፡፡ ለተጀመረው ልማት ወይም ለሰላምና ለአገራዊ ደኅንነት ትልቁን ሚና የሚጫወት ነው፡፡ ካልሆነ ግን አንዱ የቤት ልጅ፣ ሌላው የእንጀራ ልጅ፣ አንዱ ዋነኛ የአገሩ ባለቤት ሌላው አኩራፊና ‹‹ጠላት››፣ አንዱ ተሽቆጥቁጦ አዳሪ ሌላኛው ሰማይ ልቧጥ ያለ፣ አንዱ ደሃና ዋስትና ቢስ ሌላኛው በጥቂት ዓመታት የናጠጠ ቱጃር. . . እየተሆነ የወል አገር መገንባት የሚታሰብም የሚሆን አይደለም፡፡ በዚህ ላይ ብሔርተኝነት ሲገን ደግሞ መጨረሻው ይከብዳል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡