እነሆ መንገድ! እነሆ ጉዞ! ከወሎ ሠፈር ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። መንገድ አልቆ መንገድ ልንጀምር፣ ዕድሜ ጨርሰን ዕድሜ ልንቀጥል እንራመዳለን። ወያላው፣ ‹‹የሞላ ሁለት ሰው›› እያለ ይጮሃል። ‹‹ምንድነው የሚያወራው?›› አንዱ ተሳፋሪ ይጠይቃል። ታክሲው ባዶ ነበር። ‹‹የመዋሸትን መብት ለመንግሥት ብቻ የሰጠው ማን ነው? ትገቡ እንደሆነ!›› ግቡ ይላል ወያላው የሰውየውን መደናገር ግልጽ አደርጋለሁ እያለ ነገር ያወሳስባል። ‹‹አብዷል እንዴ ይኼ?›› ከመሀላችን አንዱ ይጠይቃል። ‹‹መቼ እሱ ሆነና? የትንኙን ርቢ፣ የዝንቡን ቁጥር መጨመር፣ የአዋጁ አዋጅ ላይ መደራረብ ሳይቀር ከመንግሥት ጋር ካላዛመዱ የማይሆንላቸውን እያየ እኮ ነው የሚቀባጥረው፤›› ይመልሳል ሌላው። እንዲህ ውጥንቅጡ በወጣ የእንካ ሰላንትያ ቅብብሎሽ ወጪ ወራጁ ይናከሳል። የሆነውን ሁሉ በመልካምና በክፉ ትውስታ ጉያ አሽቀጥረን ጥለን፣ በዘመን መለዋወጥ የምናምን ፍጥረታት በዘመን መለወጫ ዋዜማ ስንታይ ልዩ ስሜት እንፈጥራለን።
አዳሜ የእርስ በርስ ጉዳዩን ረስቶና በነገር ጉሽሚያ ወዲያና ወዲህ ተከፍሎ ያሳለፈውን ወራት ዘንግቶ፣ በአንድ እንቅብ ተሠፍሮ ያደመ ይመሳላል። እንደፈለገው፣ እንደወረደ ከሚያወራው ወያላ በቀር ዛሬ የሁሉም ሰው ቀልብ ያረፈው ራስን ለመለወጥ ተስፋ የሰነቀበት የሚለወጥ ዘመን ላይ ነው። በአሮጌ በሬ እያረሱ የፊትን ሩጫ በትዕግሥት መሮጥ ስለማይቻል፣ ባለመሆን ጥላሸት የከሰለን ዕድል በብርሃን ጉሎ ለማጠብ ተስፋ ስለሚያሻ ሁሉም ጥቂት ማንነቱን ረስቶ፣ ጥቂት ኑሮውን ችላ ብሎ ከአቅሙ አምሮቱን አስቀድሞ ስለሚሸኘው ጊዜ ይንደፋደፋል። ዓለም አሮጌ ጆንያዋን እንደ ወትሮው ሁሉ አራግፋ በአዲስ ጅማሮ በአዲስ ዓመት ልታስሮጠን ፍቅረኛውን እንደሚያማልል ኮበሌ የዓመት ግብሯን ታገባለች። ከእወቀት ሐዘን፣ ከጥበብም ብዛት ተስፋ ቢስነትን ያተረፈ ሁሉ መስሎ በማስመለስ የመኖር ጥበብ፣ ይህችን አታላይ ዓለም የናቃት ይመስላል። የመሆንና ያለመሆን መንገድ እንዲህ ቅዠት ባየለበት ስሜት ይጀመራል። እነሆ መንገድ!
ጉዟችን ጀምሯል። ‹‹ኧረ እናንተ ሰዎች ዛሬ ተገልብጠን ጉድ እንዳንሆን፤›› ትላለች። ‹‹ከአቅም በላይ የተጫኑትንና የተጫነባቸው ይጭነቃቸው እንጂ ብንገለበጥ ባህር አይበላን። በምላስ የተላሰ የመሰለ አስፋልት ላይ ነው ፈልሰስ የምንለው። በበኩሌ አብዛኞቻችን ከምንተኛበት ፍራሽ ይኼ አስፋልት የተሻለ ሳይመቸን አይቀርም፤›› ይላል መጨረሻ ረድፍ የተሰየመ ጎልማሳ። ‹‹በበኩሌ አሟሟቴ ነው የሚያስጨንቀኝ። እንዳልሆን ሆኜ ማለፌ ሳያንስ በመኪና አደጋ መሞት አልፈልግም። ከመኪና አደጋና ከዘንድሮ የግብር ይውጣ ጨቋኝ አዋጅ ሜዲትራንያን በስንት ጣዕሙ . . .›› ስትል መሀል ረድፍ አንዲት ባለሻሽ፣ ‹‹ሞት መቼም ልማዱን ዓይተው። ግን ከተለመደ ሞት ያልተለመደው በልጦ በረሃና ባህር ለበላው እንደምናዝነው በመኪና አደጋ በየቀኑ የሚያልቀውን ነፍስ ያቃለልነው መስሎ ይታየኝ ነበር። አሁን ግን ለካ ሌላም አለ እናንተ። የቀን ገቢ ግብር የሚሉት መቅሰፍት። ይልቁን ተጠንቀቅ ቀን እንዳይጥልህ እያልን ቀን እንዳይጥለን ስንዋደቅ ቀን እኛ ላይ ይውደቅ? እኔ እኮ ዘንድሮ አንዱን ከአንዱም መለየት ከበደኝ፤›› ስትል አንደኛዋ ወይዘሮ ትናገራለች፡፡
‹‹እሱ ሳይሆን ቁም ነገሩ ቋሚ ቆሞ ሲሄድ ሁሉን የምር አድርጎ በልቶ ለማይጨርሰው ሀብት እህት ወንድሙን አስለቅሶ፣ ሕዝብና መንግሥት አናክሶ ሳያስበው ማለፉ ነው። በረባ ባልረባው ክልትው እያልን (ያውም በዚህ ጊዜ) ሞት በጥጋብ ተሸሽጎ በሚናጠቀን ክፉ ቀን ልብ መግዛት ያቃተን ሚስጥሩ አይገባኝም፤›› አለች አንዷ። ‹‹ደላላችን በዝቶ ነዋ። ምን እናድርግ? ከመሠረታዊ እስከ የቅንጦት ምኞታችን ያለገንዘብ ምንም ናችሁ የሚሉን ደላሎችንን መቋቋም ከበደን። ይኼው ነው! ታዲያ በዚህ መሀል ሰው መሆን ትርጉሙ ቢጠፋብን ይገርማል? ፍትሕ ስንል ያለስም፣ ያለዝና፣ ያለሥልጣን የለም ካሉን፣ ሚስት ካለጥሪት ዝንብህን እሽ አትልም ከሆነ ጨዋታው ‹እሺ ለአንድ ራሴ ጠግቤ ልደር› ስንል እንኳን አፒታይት ቆላፊው ጫት ሳይቀር ዋጋው አሻቅቦ የ‹ኢንቨስተር ዲዘርት› ሲሆን ካየን ግራ እንደተጋባን ሞት ቢቀድመን ይገርማል? አሟሟታችን ቢከፋ ይደንቃል?›› ብላ አንዷ ደርባ አነበነበች። ‹‹ወይኔ በቀጣዩ ምርጫ ተወዳዳሪ መሆን ብችል በዕጩነት ቀርቤ ምን እንደምል ታውቃለህ? ‹ጫት በነፃ አድላለሁ››› የሚለኝ ከጎኔ የተቀመጠ ተሳፋሪ ነው። አንዳንዱ ሰው ምን እንደሚያወራም አላስተውል አለ እኮ እናንተ! ይኼ ያልታረመ ሐሳብ ‹ፖስት› እና ‹ሼር› የማድረግ አባዜ እኮ ነው!
ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላችን ጫቱን ቀነጣትሶ እየጎረሰ ሒሳብ አዘጋጁ ካለን ቆይቷል። ‹‹ረሳው እንዴ? ኧረ ባደረገው . . .›› ይላል አንድ ጎልማሳ። ተሳፋሪው ዓይን ዓይኑን እያየ ይጠባበቃል። ወያላው ሌላ ዓለም ውስጥ እየገባ ነው። ሁላችንም እጅ ላይ ብር መቀመጡን ያየች አንድ ወጣት፣ ‹‹አይገርምም ብለን ብለን የታክሲ ለመክፈልም ወረፋ ያዝን እኮ። ለዳቦ፣ ለነዳጅ፣ ለትራንስፖርት መሠለፋችን አንሶ ጭራሽ ለወያላም እንሠለፍ?” አለች። ‹‹ቻይው! ሌላ ምን ይባላል። ወያላችን ቶሎ ከመረቀነ ፈጣሪያችን እንደረሳን ሁሉ ሒሳብ መቀበሉን እሱም ይረሳው ይሆናል፤›› ይላል አንድ ችኩል ልጅ እግር። ‹‹ዓየህ ሙስና ከየት እንደሚጀምር? በፈጣጣ በሰው እጀ ጠባብ ዕጣ ስንጣጣል እያየህ ነው?›› ትለኛለች ቆንጂት።
መልኳ ብቻ ሳይሆን አዕምሮዋም ጭምር እንዴት ንፁህና ቆንጆ እንደሆነ ማስመስከር ሳትፈልግ አልቀረችም። ከኋላችን የተቀመጡት ወጣቶች የሚያጫወቱት ደግሞ እንዲህ ነው። ‹‹አንድ ዳቦ ለማትገዛ ገንዘብ እንደዚህ ከሆንን የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ሕይወት የሚለውጥ በጀት ስንጭበረበር ምን እንደሚያነጫንጨን እንጃ። አንገርምም?›› ብሎ አንደኛው ራሱን ይነቀንቃል። ወዲያው ወዳጁ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹እንዲህ አይደል ታዲያ የብዙኃን ስህተት ሳይፈተሽና ሳይመረመር ወግና ሥርዓት እምነት ሆኖ ትውልድ እየመጣ ትውልድ የሚሸኘው። በተናጠል ከምንወድቀው በመተባበር የምንከስረው ከየት ጀምሮ የት እንደሚደርስ ታያለህ?›› ይለዋል። ጨዋታቸው ጭልጥ ብሎ የሞራል ዋጋን መገምገም ሆኖ ሲከርብን ‹የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ› ለማለት አንድ ተሳፋሪ የሚከተለውን ቀልድ ጀባ አለን። ብሶትና ብስጭቱን በቀልድ ካላባረድነው ከእዚችም ዕድሜያችን ላይ መቀነሱ ይቀራል? እሱን ነው መፍራት አትሉም!
ታክሲዋ ጉዞዋን ቀጥላለች። በብዛት ከተደረደሩ ጥቅሶች መሀል አንዱን አስተውሎ ያነበበ ወጣት መናገር ጀመር። ‹ፍጥነት ዕድሜን ያሳጥራል እንጂ ጊዜን አይቆጥብም› ይላል። ገርሞት ፈገግ እንዳለ፣ ‹‹እኔ እኮ የማይገባኝ አሁን ይኼ ጥቅስ ለእኛ ነው መለጠፍ ያለበት? ወይስ ለሾፌሩ?›› ብሎ ጠየቀ። ‹‹ኧረ ተወኝ ወንድሜ!›› ይላል አጠገቡ የተቀመጠው ተሳፋሪ በሰለቸ ድምፀት። ወያላው በግልምጫ እያየው በምርቃናው የምናብ ሜዳ ላይ ወጣቱን የተናነቀው መስሏል። ‹‹ወይ ይኼ ምርቃና? ስንቱን ጀግና አደረገው?›› ይላል ይኼን የሚያስተውል። የሚስቀው ይስቃል። ወዲያው የዋናው ርዕሰ ጉዳይ ጨዋታ ተመልሶ ተነሳ። ወጣቱ፣ ‹‹በጣም እኮ ነው የሚገርመው። ‹ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ጠንካራ የልማት ሠራዊት እንፍጠር› ተብሎ የሚለጠፈው ለእኛ። ‹ለሙስና እጅ አንሰጥም› ተብሎ የሚለጠፈው ለእኛ። መቼ ይሆን ሁሉም የራሱን ጉድፍ ማጥራት የሚጀምረው?›› ይላል።
አሁንም አጠገቡ የተቀመጠው፣ ‹‹ህም ድረቅ ቢልህ! ልፋ ቢልህ! ሰሚ ያለ መስሎሃል። ለራሳቸው ጥልቅ ተሃድሶ ላይ ናቸው አንተ እዚህ . . .›› እያለው ይተያያሉ። ‹‹ወሬ! ወሬ! ኧረ ወሬ ጠላሁ!›› ሲል ወያላው እንደ መወናጨፍ ይቃጣዋል። ‹‹የመጣ የሄደው ዝም ብሎ ሲቀደድ . . . አንተ ምን አለብህ የምቀዳው እኔ . . .›› ብሎ ሾፌሩን ይተነኩሰዋል። ሾፌሩ ግራ እንደ መጋባት እያለ፣ ‹‹ታዲያ መሥራት ካልቻልን፣ መብላት ካልቻልን፣ ቢያንስ ማውራት መቻል የለብንም?›› ይለዋል በስፖኪዮ እያየው። ‹‹እውነት ነው! ስናወራ ነው የሚያምርብን፤›› ቀጥሏል ወጣቱ። በዚህ መሀል ነበር፣ ‹‹መንግሥት ይኼን እየሰማ እንቅልፍ ይወስደዋል?›› ብሎ የጠየቀውን ፍለጋ ጥቂት ደቂቃ ዝምታ ሰፍኖ የቆየው። ‹‹ከወሰደውማ ቆየ እኮ። ያውም የዘንድሮው የእንቅልፍ ኪኒን እጅ አለበት ሁሉ እየተባለ ነው፤›› ሲል ከኋላ፣ ሰው በድንጋጤና በፈገግታ እርስ በርሱ ተፋጠጠ። ብርቅ ነው እንዴ መፋጠጥ አትሉም?
ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። ‹‹እንዲያው ይኼ ዘመን ምን ይሻለዋል?›› ስትል አንዷ፣ ‹‹መናከስ መቻል ብቻ ነው መፍትሔው። ዘመን ምን አደረገን? እኛ ነን እጃችንን አጣጥፈን ተቀምጠን መና ከሰማይ ካልወረደ ብለን ልንሞት የደረስነው፤›› አላት ከጎኗ የተሰየመው ጎልማሳ። ‹‹መናከስ ስትል አልገባኝም?›› ጠየቀች። ‹‹ስንት ዓይነት ውሻ አለ?›› ጠየቃት መልሶ። ‹‹ብዙ!›› አለችው። ‹‹አይደለም። ሁለት ዓይነት ብቻ አሉ። አንደኛው ልክ እንደ አብዛኞቻችን ያለ ነው። የመጣ የሄደው ሂድ ከዚህ ሲለው የሚሄድ። ተቀመጥ ሲባል የሚቀመጥ። ተነሳ ሲባል የሚነሳ ነው። ይኼ ማንም የሚንቀው ማንም የማይፈራው ማንም የማያወራለት ዓይነት ነው። ሁለተኛው ግን ተናካሽ ነው። ሰው በሩቁ ዓይቶት ወይ ሰምቶት ይደነግጣል። ሌባማ ድርሽ አይልም። እነ እከሌ ቤት ያለው ውሻ እየተባለ ይወራለታል። ለምን? ይናከሳላ። አሁን ገባሽ? አልናከስ ብለን በስንቱ ነገር ሲቀለድብን ኖርን። ድሮስ የሞተን ውሻ ማን ይደበድባል? ማንም። በጫት ደንዝዘን በመጠጥ ጠንብዘን 24 ሰዓት ከሳምንት እስከ ሳምንት ጭፈራ ድለቃ እንቅልፍ በቃ ሌላ ሥራ የለንም። እና የምላችሁ ተናካሽ ሁኑ። መብታችሁን እወቁ። ግዴታችሁን ተወጡ። ግን አሁንም ተናከሱ፤›› ሲል ወያላው እየተርበተበተ ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው። የሆነስ ሆነና ምነው ተናካሹ በዛ? መልካም ጉዞ!