Monday, September 25, 2023

አቅጣጫ ያልጠቆመው የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝባዊ ስብሰባ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እሑድ ጥቅምት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ የሚገኘው የመብራት ኃይል አዳራሽ ውስጥ ሰማያዊ ፓርቲ ሦስት ወራት ያህል ከፈጀ ውትወታና ምልልስ በኋላ፣ በመንግሥት ዕውቅና የተሰጠው ሕዝባዊ ስብሰባ ለመታደም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በዕለቱ ሕዝባዊ ስብሰባው ይጀመርበታል ከተባለበት ሰዓት ዘግይቶ ቢጀመርም፣ በዝግጅቱ መጀመርያ ላይ በርከት ያሉ ወንበሮች ባዶ ነበሩ፡፡ እየቆየ ግን በርካታ ወንበሮች ስብሰባውን ለመታደም በመጡ ታዳሚዎች ሞልተው ነበር፡፡

አዲስ አበባ ሕዝባዊ ስብሰባም ሆነ ሰላማዊ የተቃውሞ ሠልፍ ካስተናገደች ዘለግ ያለ ጊዜ ከመውሰዱ አንፃር በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከወቅታዊ የፖለቲካ ችግር፣ ከኑሮ ውድነት፣ ከትራንስፖርት ዕጦት፣ እንደሁም በአጠቃላይ ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይተነፍሳሉ የሚለው በብዙኃኑ ዘንድ የተጠበቀ ነበር፡፡    

በተለይ አሁን በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየተፈጠሩ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የሚያግዝ የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀምጣል በሚል፣ የስብሰባውን መካሄድ እንደ አዲስ አማራጭና አጋጣሚ የጠበቁ ነበሩ፡፡

ሆኖም በዕለቱ የፓርቲው ኃላፊዎች በተለያዩ ወቅት ከሚሰጧቸው መግለጫዎች የተለየ አማራጭ፣ ወይም ችግሩን ለመፍታት እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ ይህን እናደርጋለን ወይም እንዲህ ያለውን ሥልት እየተከተልን ለአገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ እንሰጣለን ሲሉ አልተደመጡም፡፡

አጠቃላይ የስብሰባው መንፈስ

ሕዝባዊ ስብሰባው የተጀመረው የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ አካሉ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ሲሆን፣ ወደ ዝርዝር የዝግጅቱ መርሐ ግብሮች ከመግባታቸው በፊት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተፈጠሩ ግጭቶች ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎችን ለማሰብ ለአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዲከናወን አድርገዋል፡፡  

በመቀጠልም ፓርቲው ይህን ስብሰባ ለማሳካት ለሦስት ወራት ያህል ተጋድሎ እንዳደረገ በመግለጽ፣ የስብሰባው ዋናኛ ዓላማ በአገሪቱ የተንሠራፋውን ሥርዓት አልበኝነት፣ ችግርና ቀውስ ለመፍታት በሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴው በኩል ምን ማድረግ ይገባል የሚለውን ለመለየት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት የዕለቱ ስብሰባ ዋነኛ ርዕስ ‹‹ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?›› የሚል የነበረ ሲሆን፣ በተጨማሪም ‹‹አገራችን በመንታ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ ኑ በጋራ የአገራችንን መፃኢ ተስፋ እንምከር፤›› የሚል ጥሪም ከወደ መድረኩ ይስተዋላል፡፡

በዕለቱም በስብሰባው ከተገኙ የተወሰኑት ሰዎች የፓርቲውን አባልነት ፎርም ሲሞሉና የፓርቲው ዓርማ ያለበትን ካናቴራ እየገዙ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ይታይ ነበር፡፡

በስብሰባው ላይ የተገኙት አብዛኛዎች ወጣቶች የነበሩ ሲሆን፣ የዝግጅቱንም ሥርዓትና አካሄድ ሲያስተናብሩ የነበሩት እንዲሁ የፓርቲው ወጣት አባላት ነበሩ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲው ወጣት አባላት የተለያዩ የወግና የግጥም ዝግጅቶችን ለተሳታፊዎች አቅርበዋል፡፡

ከአቶ አበበ በመቀጠል ወደ መደረኩ ወጥተው ንግግር ያደረጉት የኦሮሞ ፌዴራሊት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ዋና ጸሐፊ አቶ ሙላቱ ገመቹ ሲሆኑ፣ ለሰላማዊ ትግሉ አጋርነት ለማሳየት መገኘታቸውን በመግለጽ ስለሰላማዊ ትግል አስፈላጊነትና የፓርቲዎች በአንድነት የመሥራት ሐሳብ ላይ አጽንኦት ሰጥተው ንግግር አድርገዋል፡፡

‹‹አሁን አገራችንን የገጠማትን ችግር ለመፍታት እንዲሁ ዝም ብሎ ማዶ ለማዶ ገመድ ይዞ ጉተታ ማካሄድ ሳይሆን፣ ሥርዓት በያዘ መልኩ ተናቦ አብሮ ሆኖና አንዱ የአንዱን ሸክም ተሸክሞ ትግሉን ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ሆኖ ትግሉን ለማካሄድ መሞከር ለገዥው መደብ የሚመች ስለሚሆን፣ ከዚህ ላይ ጥንቃቄ መውሰዱ ጥሩ ይሆናል፤›› በማለት የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነትና በተባረረ ክንድ መንቀሳቀስ ጊዜው የሚጠይቀው የትግል ሥልት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ ይህን ሁሉ ዓመት እንዲገዛ ያስቻለው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች አንድ አካሄድ ፈጥረው፣ ተገናኝተውና ልዩነታቸውን አቻችለው የግንኙነት መድረክ መፍጠር ባለመቻላቸው ነው፤›› በማለት፣ ለበርካታ ዓመታት ከሕዝቡ የሚነሳውን ‹‹ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ›› የሚለውን ጥያቄ አስተያየት አጠንክረው ገልጸውታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች እየታየ ያለው አለመረጋጋት በዕለቱ በከፍተኛ ሁኔታ በተደጋጋሚ የተነሳ ጉዳይ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር አቶ ሙላቱ የኦሮሞ ሕዝብ ችግር አሁን ያለውን መንግሥት መጣል እንዳልሆነና ከዚህ መንግሥት በኋላ ምን ይመጣል? የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ምን መሆን አለበት? የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህች አገር የሁላችንም ናት፤›› ያሉ አቶ ሙላቱ፣ ‹‹ስለሆነም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ደረጃ አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት ከእነ ግድፈቱም ቢሆን ተቀብለን አንድነታችንን ጠብቀን ለወደፊት ብንሄድበት ይሻላል፡፡ ስለዚህ እጅ ለእጅ ተያይዘን ትግሉን ማካሄድ እንዴት ይቻላል የሚለውን የቤት ሥራ ብንሠራና በዚህ ዓመት አንድ ላይ የሚኮንበት መንገድ ቢፈለግ መልካም ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ከእሳቸው በተጨማሪም የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም በስብሰባው ተገኝተው ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

አቶ ገብሩም ቢሆን ሰላማዊው መንገድ ዋነኛው የትግል ሥልት መሆኑን በመጥቀስ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከዚህ አንፃር ቢተባበሩ መልካም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አቶ ገብሩ ለትብብር መምጣት ያለባቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ‹‹ሀቀኞቹ›› ብቻ መሆን እንደሚገባቸው አውስተዋል፡፡

ከሁለቱ ተናጋሪዎች በተጨማሪም ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱና አቶ ዳንኤል ሺበሺ በዕለቱ ተገኝተው አጠር ያለ ንግግር አድርገዋል፡፡  

የፓርቲው አመራሮች በተደጋጋሚ ወደ መድረኩ በመውጣት የሕዝባዊ ስብሰባው መከናወን መቻሉ በራሱ እንደ አንድ ውጤት እንደሚቆጥሩት ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲህ ያለ አጋጣሚ በመፍጠር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሕዝቡ ጋር እንዳይገናኙ በመንግሥት በኩል በከፍተኛ ሁኔታ ሲሠራ ቢቆይም፣ አሁን የፓርቲው ውትወታ ምላሽ አግኝቶ ሐሳብን ለሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ ዕድል መገኘቱ አበረታች እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በሕዝባዊ ስብሰባው ነጥሮ የወጣ ገዥ ሐሳብ ወይም ቀጣይ የአገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳት አረጋግቶ ለመቀጠል ምን መሠራት ይኖርበታል የሚለውን ሐሳብ ከማንሳት አንፃር፣ አዲስ ነገር አለመታየቱን ብዙዎች ተችተዋል፡፡   

ፓርቲው ሕዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ማቀዱን አስመልክቶ ጥቅምት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት እንደተገለጸው የስብሰባው ዋነኛ ርዕስ፣ ‹‹የአገራችን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታና የፓርቲያችን ርዕዮተ ዓለም›› የሚል ነበር፡፡

ሆኖም በሕዝባዊ ስብሰባው ዕለት ስለአገሪቱ ወቅታዊ ችግሮችና ተግዳሮቶች የተለያዩ ሪፖርት መሰል ማብራሪያዎችን ከመስጠት ባለፈ፣ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት ከፓርቲው ርዕዮተ ዓለምና ስትራቴጂ አንፃር የተነደፉ ሥልቶች ምን እንደሆኑ በውል አልተገለጸም፡፡

የፓርቲውን አጠቃላይ ዓላማና ስትራቴጂ በመዘርዘር ደጋፊ ለማፍራትና የተጠናከረ የሰላማዊ ትግል ለማድረግ የሚያስችል ዕድልን መጠቀም ይችል እንደነበር ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ፓርቲው በተደጋጋሚ በተለያዩ መግለጫዎች እንደሚያስታወቀውና እንደሚስተዋለው፣ በተለያዩ ቢሮክራሲያዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ገዥው ፓርቲ የፓርቲውን እንቀስቃሴ በጽሕፈት ቤት ብቻ ተወስኖ እንዲቀር እያደረገው እንደነበር ይገልጻል፡፡  

በዚህም መሠረት ፓርቲው በሰፊው ወደ ኅብረተሰቡ ወርዶ የፖለቲካ ርዕየተ ዓለምና ስትራቴጂውን ማድረስ እንዳልቻለ ያምናል፡፡ ከዚህ አንፃር በሕዝባዊ ስብሰባው ለተገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች የትግል ሥልቱንና ርዕዮተ ዓለሙን በማብራራት ኅብረተሰቡን ከጎኑ ማሠለፍ የሚያስችሉ ፍሬ ነገሮችን በማቅረብ፣ በሥፍራው የተገኙ ነገር ግን የፓርቲው አባላት ያልሆኑ ሰዎችን ለመሳብ ይችል እንደነበር አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል፡፡  

ነገር ግን የተጋበዙት እንግዶችም ሆኑ የፓርቲው አመራሮች አትኩሮት ሰጥተው ሲያነሱት የነበረው ጉዳይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ሲዘገቡ የነበሩትን ጉዳዮች እየመዘዙ፣ አገሪቱ ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን ማመላከት ነበር፡፡

በስብሰባው ወቅት እነዚህ ችግሮች ተከስተዋል፣ ነገር ግን መጠናቸው እንዳይጨምርና ለመቆጣጠር ፓርቲው ይህን ለማድረግ አቅዷል የሚሉ አቅጣጫዎች ቢያስቀምጥ የተሻለ ይሆን እንደነበር አስተያየት ሰጪዎቹ አክለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዕለቱ እንደ ክፍተት የሚነሳው ጉዳይ ተሰብሳቢው የሚሰማውንና አማራጭ የሚለውን ሐሳብ ማቅረብ አለመቻሉ ነው፡፡ ለዚህም የስብሰባው መሪዎች ዝርዝር የዝግጅት መርሐ ግብር አለማዘጋጀታቸውና የሰዓት አለመከበር ምክንያት ሆነዋል፡፡

ስብሰባው እንዲናወን የተያዘለት ጊዜ ከቀኑ 7  እስከ 11 ሰዓት የነበረ ሲሆን፣ ስብሰባው ዘግይቶ በመጀመሩና አዳራሹ ከ11 ሰዓት በኋላ ለቢንጎ ጨዋታ የሚፈለግ በመሆኑ ታዳሚያኑ ሐሳባቸውን ሳይሰነዝሩ ከመድረኩ የተሰጠውን ሐሳብ ብቻ አዳምጠው ለመመለስ በመገደዳቸው ቅር ያላቸው ነበሩ፡፡

ሆኖም የስብሰባው መሪዎች ያለውን የሰዓት እጥረት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተወሰኑ ዝግጅቶች ማጠፍ ይችሉ ነበር የሚሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ ቢያንስ በፓርቲው ወጣት አባላት ሲቀርቡ የነበሩ የወግና የግጥም ዝግጅቶችን በማጠፍ፣ ሕዝቡ ሐሳቡን እንዲያንሸራሽር ቢደረግ የሕዝቡን የልብ ትርታ በማዳመጥ በዚህ መሠረት ቀጣይ አቅጣጫዎችን መተለምና መልሶ ሕዝቡ ውስጥ ገብቶ ለመሥራት መሠረት ይሆን እንደነበር ተገልጿል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ተንቀሳቅሰው ሐሳባቸውንና በተለይም ርዕየተ ዓላማቸውን ለማሳካት የኅብረተሰቡን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት የፖለቲካ አጀንዳ በመቅረፅ የሚወክሉትን ኅብረተሰብ ፍላጎት ለማሟላትና ለማሳካት ጥረት ማድረግ የዕለት ተዕለት ሥራቸው ሊሆን እንደሚገባ የተለያዩ የፖለቲካ ሳይንስ ጸሐፍት ያወሳሉ፡፡

ከዚህ አንፃር በአገሪቱ ውስጥ ያለው ቁልፍልፍና ጥልፍልፍ የፖለቲካ ምኅዳር መኖር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሰማያዊ ፓርቲ እሑድ ዕለት በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ወቅት የኅብረተሰቡን ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ባህላዊ ችግሮችን ነቅሶ አውጥቶ አማራጭ አቅርቧል ለማለት እንደማያስደፍር ሐሳባቸውን ለሪፖርተር ያካፈሉ የስብሰባው ተሳታፊዎች ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡     

  

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -