Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብቸኛው የግል ላቦራቶሪ የታሸጉ የመጠጥ ውኃዎችን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለመፈተሽ መዘጋጀቱን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የሥጋና የሰብል ምርቶችን የኬሚካል ቅሪት የሚፈትሽ ቴክኖሎጂ አስተዋውቋል

በአገሪቱ ከሚገኙት ሁለት የጥራት ፍተሻ አገልግሎት ከሚሰጡ የግልና የመንግሥት ተቋማት አንዱና ብቸኛው የግል ላቦራቶር በአገሪቱ የታሸጉ የውኃ ምርቶች ከግማሽ በላይ ናሙናዎች ወደ ውጭ ተልከው ይመረመሩ የነበረበትን አሠራር በማስቀረት ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ለማካሄድ የሚቻልበትን የላቦራቶሪ ቴክኖሎጂ ለማስገባት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

በፈረንሣይና በኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የተቋቋመው ብሌስ አግሪፉድ ላቦራቶሪ ሰርቪሲስ ኩባንያ፣ በምግብና ምግብ ነክ ምርቶች፣ እንዲሁም በግብርና መስክ ለተለያዩ ምርቶች የጥራት ፍተሻ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ህሊና በለጠ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ተቋሙ በርካታ የጥራት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን በማስገባትና በማደራጀት የፍተሻ አቅሙን እያዳበረ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ በተሰጠው የሦስተኛ ወገን የምርቶች የጥራት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት እየሰጠ የሚገኘው ብሌስ ላቦራቶሪ፣ በተለይ በምግብና ምግብ ነክ በሆኑ ምርቶች ላይ እንደ አፍላቶክሲን፣ ኦክራቶክሲን የተሰኙትን ጨምሮ ኦርጋኖክሎሪንና ኦርጋኖፖስፈረስ ይዘቶችን በመተፈሽ ለተጠቃሚዎች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን የማረጋገጥ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ኃላፊዋ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን አብራርተዋል፡፡

የፀረ ተባይ ኬሚካሎችንና በሥጋ ውስጥ የሚገኘውን የእንስሳት መድኃኒቶችን ቅሪት መጠን በመፈተሽ ተፈላጊውን የጥራት ደረጃ ማሟላት አለማሟላታቸውን የሚፈትሸው ላቦራቶሪው፣ የሕፃናት ወተት ውስጥ የሚገኘውን የአፍላቶክሲን መጠን፣ ወደ ውጭ በሚላኩ እንደ ቡና፣ በርበሬ፣ ለውዝና ማርን ጨምሮ በተለያዩ ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ላይ የጥራት ፍተሻ ያካሂዳል፡፡ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ የወተት፣ የዘይትና ሌሎችም የምግብ ሸቀጦች ላይ የጥራት ፍተሻ የሚያካሄደው ብሌስ ላቦራቶሪ፣ በአፈርና በውኃ ላይ ከሚያደርጋቸው የጥራት ፍተሻዎችን በማካተት በየወሩ እስከ 1,700 የምርት ናሙናዎችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል፡፡

አብዛኞቹ የጥራት ፍተሻዎች በብቸኝነት የሚያከናውናቸው እንደመሆናቸው፣ አዳዲሶችንም ለማካተት በርካታ ቴክኖሎጂዎችን በመግዛት አገልግሎቱን እያስፋፋ እንደሚገኝ ያስታወቀው ብሌስ ላቦራቶሪ፣ ውኃን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለመተፈሽ ከሚያስችሉ የጥራት መፈተሻዎች በተጓዳኝ በርካታ ግዥዎችን በመፈጸም አዳዲስ የላቦራቶሪ መሣሪያዎችን በማስገባት ላይ እንደሚገኝ የኩባንያው ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ የምርቶች የአገልግሎት ዘመንን የሚያመላክት ወይም ምርቶች ከተመረቱ በኋላ ሳይበላሹ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ ማረጋገጫ የሚሰጥ ቴክኖሎጂ ለማስገባት ዝግጅት ማጠናቀቁንም ኩባንያው ለሪፖርተር አብራርቷል፡፡

በዚህም ሳቢያ በአሁኑ ወቅት የሚገለገልበት ስያሜውን በማሻሻል የላቦራቶሪ አገልግሎት መስጠት ብቻም ሳይሆን፣ የኢንስፔክሽ ሥራዎችንም ያካተተ ሚና ያለው ተቋም ለመሆን መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል፡፡ ምንም እንኳ ዘመናዊ የጥራት ደረጃዎችን የሚያረጋግጡ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በተለይ ምግብና የምግብ ግብዓቶችን የጥራት ደረጃ ለማረጋገጥ እየሠራ ቢሆንም፣ በኅብረተሰቡም ሆነ በኩባንያዎች ዘንድ ለጥራት የሚሰጠው ዝቅተኛ ግምት በሚፈለገው ደረጃ የጥራት ሥራዎች እንዳይስፋፉ ማድረጉን የብሌስ ላቦራቶሪ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም ለሕዝቡ ልዩ ልዩ ሸቀጦችን ከሚያቀርቡ ሱፐር ማርኬቶችና ሌሎችም የገበያ ማዕከላት ውስጥ የሚቀርቡለትን ምርቶች የጥራት ደረጃቸውን በብሌስ ላቦራቶሪ በኩል በማስፈተሽ ለገበያ የሚያቀርበው ሸዋ ሱፐር ማርኬት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ሌሎችም የሸዋ ሱፐር ማርኬትን ፈለግ በመከተል የጥራት ጽንሰ ሐሳብን በደንበኞቻቸው ዘንድ እንዲያሰርፁ ጠይቀዋል፡፡

ይህም ሆኖ የጥራት ፍተሻ በማካሄድ የምርቶችን ደረጃ ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመንግሥት ድጋፍ ዝቅተኛ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጇ፣ ለላቦራቶሪ ሥራ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎችንና አዳዲስ የፍተሻ መሣሪዎችን ከውጭ ለማስገባት በጉምሩክ ሥርዓት በኩል የሚገጥማቸው ፈተና ከባድ መሆኑን አውስተዋል፡፡ የታክስ ማበረታቻ የማይሰጠው ይህ ዘርፍ፣ ለጥራት ከሚጫወተው ሚና አኳያ በተለይም ወደ ውጭ የሚላኩ ልዩ ልዩ የግብርናና የምግብ ሸቀጦችን ጥራት በመፈተሽና በማረጋገጥ ረገድ ከሚጫወተው ሚና አኳያ የሚያገኘው ድጋፍ እንደሌለ ኃላፊዋ ገልጸው፣ ይብሱኑ በገበያው በእኩል ዓይን እንደማይታይ፣ የፍትሐዊነት ችግር እንደሚያጋጥመው ገልጸዋል፡፡

የህሊና ገንቢ ምግቦች አምራች ድርጅት እህት ኩባንያ የሆነው ብሌስ አግሪ ፉድ ላቦራቶሪ፣ ለእህት ኩባንያው በሚሰጠው ያልተቋረጠ የጥራት ፍተሻና ማረጋገጥ ሥራ በዓመቱ ከ12 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት የቻለ ተቋም እንደመሆኑ፣ ተገቢውን ድጋፍ ሊያገኝ አለመቻሉ አሁን ከሚገኝበት ደረጃም በላይ የማደግ አቅሙ ላይ ጫና እንዳሳደረበት ይናገራሉ፡፡

ይህም ሆኖ በ100 ሚሊዮን ብር ጠቅላላ ካፒታል የተቋቋመው ብሌስ ላቦራቶሪ በአሁኑ ወቅት እያካሄደ ከሚገኘው ማስፋፊያና የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ግዥ አኳያ በአጭር ጊዜ ውስጥ አቅሙን በእጥፍ የማሳደግ ውጥን እንዳለው አስታውቋል፡፡

ከኢትዮጵያ የጥራት ደረጃቸው ሳይፈተሽ እየተላኩ ከሚገኙ ምርቶች መካከል በርበሬና ለውዝ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን ወይም የፈንገስ (ሻጋታ) ክምችት እየተገኘባቸው በተደጋጋሚ ውድቅ እየተደረጉ ሲሆን፣ በቡና ውስጥም ኦክራቶክሲን የተሰኘ ለጤና አስጊ የኬሚካል ይዘት እየተገኘበት ለውጭ ገበያ የሚቀርበት አጋጣሚ እየታየ እንደሚገኝ የብሌስ ላቦራቶሪ ውጤት እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ ለውጭ ከሚቀርቡ ምርቶች ባሻገር ለአገር ውስጥ የሚውሉ ምርቶችም ተመሳሳይ የጥራት ፍተሻ ቢካሄድባቸው በርካታ ለጤና ጠንቅ ሊሆኑ ከሚችሉ ምርቶች ሕዝቡን መታደግ እንደሚቻል፣ አምራቹም ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምርቶችን ከማምረት የሚድንበትን የጥራት አመራረት ሥልት እንዲከተል ማድረግ እንደሚቻል የብሌስ ኃላፊዎች ይመክራሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች