በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በእስር ላይ ከሚገኙት ስድስት የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊዎች በተጨማሪ፣ አንድ ዳይሬክተር 2.8 ሚሊዮን ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው ታሰሩ፡፡
ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ተናገር ይስማው በድርጅቱ የየብስና ወደቦች ኦፕሬሽን ዳይሬክተር መሆናቸውን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ጊዜ ቀጠሮ ችሎት አሳውቋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ቀረኝ የሚለውን ምርመራ ጎን ለጎን ሠርቶ በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ሲያቀርብ፣ ተጠርጣሪውም የሚከሰሱ ከሆነ እንዲከሰሱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
በሌሎቹ የድርጅቱ ኃላፊዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶ እንዲቀርብና በተሰጡት 15 ቀናት ውስጥ መርማሪ ቡድኑ ቀረኝ የሚለውን ተጨማሪ ምርመራ እንዲያጠናቅቅ፣ ፍርድ ቤቱ ለጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ግን ክስ ሳይመሠርት ቀርቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ለምን ክስ ሳይመሠርት እንደቀረ ከፍርድ ቤት ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ የተሰጠው ጊዜ በቂ ባለመሆኑ ሊደርስለት እንዳልቻለ ገልጿል፡፡
የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ዓቃቤ ሕግን አምርረው ተቃውመዋል፡፡ ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት የተሰጠው ትዕዛዝ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ በተደነገገውና የመጨረሻው በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቅድ የሚችልበት የሕግ አግባብ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ደንበኞቻቸው ዋስትና ተፈቅዶላቸው ከእስር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ምንም የሚከስበት ምክንያት በማጣቱ ሊከስ እንዳልቻለ በተደጋጋሚ መናገራቸውን በማስታወስ፣ ዓቃቤ ሕግ ቀረኝ የሚለውን ሥራ ሲያጠናቅቅ ቀርበው ምላሽ መስጠት እንደሚችሉ በመግለጽ፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ በሰጠው ምላሽ ቀደም ብሎ የነበረው ችሎት የሰጠው ትዕዛዝ፣ መርማሪ ቡድኑና ዓቃቤ ሕግ ጎን ለጎን ሠርተው ምርመራቸውን አጠናቀውና ክስ መሥርተው እንዲቀርቡ ለመጠባበቅ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ በወቅቱ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶ እንዲቀርብ 15 ቀናት ሰጥቻለሁ አለማለቱን፣ ቢልም እንኳን 15 ቀናት መቆጠር ያለባቸው የሥራ ቀናት ስለሆነ፣ ቅዳሜና እሑድ ሲነሱ ቀናቱ 11 ቀናት ብቻ በመሆናቸው፣ ተጨማሪ ቀናት እንዳለውም አስታውሷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን አጠናቆ ካስረከበው ገና አንድ ሳምንቱ መሆኑን በማስረዳትም፣ ሰባት ቀናት ቢፈቀድለት ክስ መሥርቶ መቅረብ እንደሚችል ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ የዓቃቤ ሕግን ክርክር በመቀበል ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ክስ መሥርቶ እንዲቀርብ የመጨረሻ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡