Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የቆምን እየመሰለን የወደቅን በዝተናል!

ሰላም! ሰላም! አንዱ ባለፈው እንዲህ እንዳሁኑ ሁለት ጊዜ ሰላም ስለው፣ ‹‹በኮማንድ ፖስት ለፀና ሰላም ደግሞ አንዱ አይበቃህም?›› አለኝ። እንዲያው እኮ። አሁን ለዚህ ምን ዓይነት መልስ ይመለስለታል? ያውስ ኢቢሲ ያነጋገራቸው አንዳንድ የከተማችን ነዋሪዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይራዘምልን ሲሉ እየሰማ እንዲህ ይለኛል? ‹‹ሌላው ቢቀር የሕዝብ ድምፅ አያከብርም?›› ስለው ለባሻዬ ልጅ ሆዱ እስኪነፍር ስቆ፣ ከተፈጠርኩ እንዲህ ቀልጄ እንደማላውቅ ነገረኝ። አሁን ማን ይሙት በመታቀብ አዋጅ በአንቀልባ ታዝለን ለፀና ሰላም አፀፋ አልመልስም የሚለው ነው አዋጁ እንዲራዘም የሚጠይቀው የኅብረተሰብ ክፍል? ወይስ እኔ ነኝ ቀላጅ? የምር ግራ ገብቶኛል። ለበለጠ ማብራሪያ አዋጁ በተነሳ ማግሥት የሆድ የሆዴን አጫውታችኋለሁ። ለጊዜው ግን ተከድኖ ይብሰል። ደግሞ በኋላ አፌ ቢስትስ? የዘንድሮ ሰው እንደሆነ አፉና ዓይኑ ሲፈጥረው ነው መሰል ዝም ብሎ ይስታል። ‘አይሽ አይሽና ይፈሳል እንባዬ…’ ብሎ ዘፈን ድሮ ቀረ እየተባለ ነው።

ምክንያቱም የዘንድሮ ዓይን ስህተቱ ከመብዛቱ የተነሳ የድርቀት እንጂ የእርጥበት ችግር የለበትም። እንኳን በደጉ ቀን መርዶ ሰምቶም የሚንከባለለል እንባ እየጠፋ ነው። ማስረጃ ካላችሁ ብዙ አለኝ። ከመቅበዝበዛችንና ቀልብ ከማጣታችን ብዛት የቲማቲም ዋጋ አርባ ብር መጠጋት አላንጫጫንም። ለምን? እንደ ወትሮው ቢሆን ‘እሪ በይ አገሬ… ተከልከይ ባዋጅ…’ ብለን የምናስነሳው አቧራ ስፔን ይደርስ ነበር። ምናልባት አንድ ቀን እኛም እንደ ስፔን ሕዝብ በቲማቲም የመደባደብ ቀን ለማክበር ያበቃንና ይኼ ሁሉ ይረሳ ይሆናል። እስኪረሳ ድረስ መረሳት ያልነበረባቸው ብዙ ጉዳዮች ነበሩ። ሌላው ቀርቶ እንዲያው እዚህ ድረስ ኪሳችን ሲዘረፍ ምንም ሳይመስለን ቀረ። ለምን አትሉም? ከመቅበዝበዝና ቀልብ ከማጣታችን ጋር ተዳምሮ ብዙ ስህተቶች ሳናስበው ስለለመድን ነው። ስህተትም ሲለመድ አያችሁ እንዴት እንደ ሀቅ እንደሚሰገድለት!

‘ውኃ ወርዶ ወርዶ አቀበት ይዋኛል፣ አትበሳጭ ልቤ የባሰ ይገኛል’ አለ የወንዙን ልጅ ትቶ የሰው አገር ሲያድን የመነመነው። ምን በምግብ ዋስትና ራስን ቢችሉ መመንመን አይተወንማ። እና ውዷ ማንጠግቦሽ ራሷን አልችል ብላው ደረቴ ላይ ጣል አድርጋው ሳለ ቅዠት ነው መሰል ብንን አልኩ። በቀን ሳንባንን ሌት ሌት ይቀናናል። እንዲያው እኮ! ስባንን ቀሰቀስኳት። እየተገላበጠች፣ ‹‹ስንት ሰዓት ነው?›› ብላ ጠየቀችኝ። አይገርምም? እስኪ አሁን ጨለማ ቆጠረ አልቆጠረ ምን ይፈይዳል? ‘ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው?’ ይሉናል ደርሰው። እንጃ የእናንተን። ብቻ እኔ ሳልደርስባቸው የሚደርሱብኝ እያደር ጨምረዋል። ምናልባት እኔ ሳባርራቸው ወደ እናንተ ከመጡ መልሱ ‘አልነጋም ገና ነው!’ ነው። አደራ ከእኔ አልቀዳችሁትም እሺ። ደግሞ ያስኮርጃል ተብዬ ኋላ ጣጣ እንዳታመጡብኝ። የባሻዬ ልጅ ‹‹ማንም አይነካህም አይዞህ። መጀመሪያ በኩረጃ እያለፉ ያስመረቁዋቸውን ይከልሱ፤›› ሲለኝ ነበር። ማን ተመራቂ ማን አስመራቂ እንደሆነ እሱ ሲያወራ ግራ ገባኝ።

ግን እንዲያው አደራችሁን ሌት ከሆነ ሰዓት ማሥላት ምን ይጠቅማል? እ? ሰቅዞ ይዞኝ እኮ የምደጋግምባችሁ። የቀኑን ብርሃን ሳይቀር ይህ የዘመን ጨለማ ከል እያለበሰው የመንገድ መብራት 24 ሰዓት ይብራልን ሳንል አንቀርም ትላላችሁ ትንሽ ቆይተን? ‹‹አይ አንበርብር! ‘ዩ አር ቱ ፋር ፍሮም ዘ ሪያሊቲ’›› ይለኛል ምሁሩ ወዳጄ። ‹‹አብራራ!›› ስለው፣ ‹‹አንተም ቤት ለቤት በቅጡ ያልተዳረሰና የሚቆራረጥ ኃይል እንዴት ሆኖ መንገድ ለመንገድ 24 ሰዓት ሊበራ እንደምታስብ አብራራ!›› ብሎ ይስቅብኛል። ኧረ እኔስ አልስቅም። ቀኑ በጨለማ ኃይል የተያዘበት ምስኪን ይኼን ሁሉ ዕልቂት፣ ይህን ሁሉ ፍጅት፣ ይኼን ሁሉ የፖለቲካ የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚደረግ የአውሬዎች ሴራ እያየ እንዴት ይስቃል? ማን ነበር ‘የሳቅ መቆራረጥ ያስቸገረን በዓለም መንግሥታት የአስተዳደር ብልሹነት ነው’ ብሎ ሲደመድም የሰማሁት?

ታዲያላችሁ ሰሞኑን አንድ ቪላ ቤት አሻሽጬ ነበር። ገዢዎቹ ቤቱን ገብተውበት ሰንብተው ምሳ ጠሩኝ። ቲማቲም ቁርጥ እንደ በግ አሮስቶ የሚናፈቅበት ዘመን ላይ ስለደረስን፣ ቤታችሁ ሰው መጋበዝ ካሰባችሁ 40 ብር በቂ ነው። ሌላውን በዘይትና በጨው መሸወድ ነው። እናላችሁ ሰዓቴን አክብሬ ስደርስ የደንበኞቼ የመጨረሻ ልጅ ቴሌቪዥኑ ላይ ተሰክቶ ኳስ ያያል። ‹‹ማንና ማን ናቸው?›› ስለው ‹‹አርሴናልና ማንቸስተር፤›› አለኝ። ‹‹ማን እየመራ ነው?›› ስለው ‹‹እኔ!›› አለኝ። ግራ ገባኝ። ትኩር ብዬ ሳያቸው ለካ ማንቼዎቹም አርሴዎቹም አሻንጉሊት ናቸው። ነገሩ ‘ጌም’ እንደሆነ ገባኝ። ‹‹ኧረ አንተ ልጅ በቃህ ዜና እንስማበት?›› ስትለው እናቱ፣ ‹‹አንዴ ጠብቁኝ ይኼን ጨዋታ ካላሸነፍኩ እባረራለሁ›› አላት። ‹‹ማን ነው የሚያባርርህ?›› ስለው፣ ‹‹የአርሴናል ቦርድ ነዋ፣ አሠልጣኛቸው እኔ ሆኛለሁ፤›› ሲለኝ አልቻልኩም ሳቄ አመለጠኝ። ነገሩም ዘመኑም ገረመኝ። ወይ ቴክኖሎጂ እያልኩ ሳስብ ምናለበት ሕይወትም እንደዚህ የ’ሲሙሌሽን ጌም’ የዝውውር መስኮት ቢኖራት ብዬ ተመኘሁ። አስባችሁታል? በዕውን አልገፋ ያላችሁን በሲሙሌሽን ስታዘዋውሩት?

እኔ ለምሳሌ የማዘዋውረውን ላስቆጥራችሁ። አንደኛ ከእኛ በላይ አዋቂ ላሳር እያሉ የአየር ሰዓቱን የሚያጣብቡ ጥራዝ ነጠቆችን ወደ ቦታቸው አዘዋውራለሁ። ያውም በነፃ ዝውውር። ሁለተኛ አድማጭ መሆን ሲገባቸው እኛን አዳምጡን የሚሉትን ‘ኦቨር ቤንች’ አደርጋቸውና በሦስተኛ ደረጃ ሰማይ ዳመነ፣ ሁዳዴ ገባ፣ እንቁጣጣሽ ጠባ እያሉ በመሠረታዊ የምግብ ፍላጎቶች ላይ ያለከልካይ፣ ያለመካሪ ዘካሪ እንዳሻቸው ዋጋ የሚያንሩትን ጫማ አሰቅላቸው ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል ህልም ነው። ታዲያ ሕፃን አዋቂው ወዶ መሰላችሁ ዓለም ስንት ሥራ በሚሠራበት የቴክኖሎጂ ውጤት ‘ጌም’ ሲቀጠቅጥ ውሎ የሚያድረው? ኑሮ ‘ክራሽ’ ሲያደርግባችሁ መቆጣጣር ካልቻላችሁ ‘ካንዲ ክራሽ’ አስጭናችሁ ተጫወቱ እሺ!

ጨዋታን ጨዋታ እያስታጠቀውም አይደል? ታዲያ የሚያስታጥቀው ሽጉጥ ስላልሆነ አይዟችሁ አትደንግጡ። ለነገሩ ብትደነግጡም አልፈርድባችሁም። ‘እንዴት?’ አትሉኝም? የከተማ ታጣቂው በዝቷላ! እንደ ነገርኳችሁ ቅጥቅጥ አይሱዙ ለማሻሻጥ ወዲያ ወዲህ ስል የባሻዬን ልጅ እግር ጥሎት አገኘሁት። ‹‹ሥራ እንዴት ነው?›› እየተባባልን ሳለን ከበስተጀርባችን አንባጓሮ ተፈጥሮ ገላጋዩና ታዛቢው ይግተለተላል። የመገላገላቸውን ቁርጥ ያወቁት ፀበኞች ማዶ ለማዶ ቆመው ‘እገልሃለሁ፣ እገልሃለሁ’ ይባባላሉ። እኛም እንደ ቀልድ እየሰማናቸው ለአፍ ልማድ ለፀብ ሞገስ እንዲያ የሚባባሉ ስለመሰለን ነገሩን አላካበድነውም (አቦ አታካብዱ በሚባልበት ዘመን ሁሉ እየከበደን ተቸገርን እንጂ)፡፡

ኋላማ አንዱ እንደ ጀምስ ቦንድ በብርሃን ፍጥነት ሽጉጡን አወጣና ‘ዶንት ሙቭ’ ቢል ሰማይ ምድሩ ድብልቅልቅ፣ አዳሜ ሁሉን ትቶ ሩጫ በሩጫ። ‹‹ወይ ዘመን! አንድ ዘራፍ የሚል ይጥፋ?›› ስል የሰማኝ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ከራሱ ዘራፍ ከሚለው ቃል ውጪ ዘራፍ ባይ ደመ መራራ በእነ አባዬ ጊዜ ቀርቷል፤›› ብሎ መለሰልኝ። ጉድ ነው አትሉም! (ጥያቄ፡- ለስንቱ ብለን እንችለዋለን? መልስ፡- ብናውቀው ምን አስደበቀን?) ኋላ ነገሩን ፖሊሶች መጥተው እንደ ምንም ሲያረጋጉት የባሻዬ ልጅ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹እኔምለው አንበርብር ባለፈው የመከላከያ ኤግዚቢሽን ላይ ሽጉጥ ዕደላ ነበረ እንዴ? ታጣቂው በዛብኝ፤›› እኔም ነገርን በነገር አውቅበት የለ? ‹‹ጓዴ! ዘመኑ ነው እንጂ የመረጃ፣ እኛ ስላልሆንን መልስ የሌለው ጥያቄ መጠየቅ አቁም፤›› አልኩታ። ወንዳታ አትሉኝም?! ለማንኛውም እግረ መንገዴን አንድ ሁለት ነገር ጣል ላድርግላችሁና ቅጥቅጡን ልሽጠው። አንደኛ ከአልፎ ሒያጅ መንገደኛ ጋር አፍ ዕላፊ ማብዛት ቀንሱ። ሁለተኛ አንደኛ ብዬ የተናገርኩትን ደጋግማችሁን አንብቡ። ‘እስኪ ፈገግ’ ይል ነበር ፎቶ አንሺ ቢኖር!

በሉ እንሰነባበት። በቀደምለት ባሻዬን ወደ ቤተስኪያን ልሸኛቸው ከቤት ወጣሁ። ሰዓታቱ ሳይጀመር ለመድረስ እየተጣደፉ ይራመዳሉ። አካላቸው ቢዝልም አዕምሯቸው ንቁ ነውና አንዳንዴ አነቅፏቸው ወይ ወለም ብሏቸው እንዳይወድቁ ስለምሠጋ ‹‹ቀስ ይበሉ እንጂ ባሻዬ፣ ይደርሳሉ…›› አልኳቸው። ኋላ ፈገግ ብለው፣ ‹‹ሂድና ለእነዚያ ችኩሎች ንገራቸው። እኔ ብቸኩልም በሁለት እግሬ ነው። ምነው ባለአራት እግሮቹ አይታዩህ?›› ብለው ማዶ ሲጠቁሙኝ አንድ ቪትዝ መኪና እንደ ካርቶን ተጨመዳዳ፣ አንድ አይሱዙ ደግሞ የፊት መስታወቱ ረግፎ አየሁ። ‹‹አሁን እኮ ሰላም ነበር፣ ከመቼው?›› ብዬ ክው አልኩ። ‹‹ለመዋደድ ስንዝር ለፀብም መዳፌ ነው ያለውን ባለቅኔ አታውቀውም እንዴ? ሰው ከንቱ፣ ሁሉ ነገር ቀሪ መሆኑ በምን ቋንቋ ቢነገረው እንዴት ባለ ልምድ ቢያየው እንደሚገባው እንጃ። ረግፎ ለመቅረት ይኼ ሁሉ አበሳ፣ ይኼ ሁሉ ሩጫ፣ ይኼ ሁሉ ስደት፡፡ አይገርምህም ግን አንበርብር? መጽሐፉ እኮ ማንም የቆመ ቢመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ የሚለው ያለ ምክንያት እንዳይመስልህ። ከሟች በላይ የቋሚ አበሳ ነው ከባዱ። ግን እኛ ነገር ካለለፈ አልገባን ብሏል፤›› ብለው የዕርምጃችንን ዙር አቀዘቀዙት።

‹‹ምነው ባሻዬ አመመዎ እንዴ?›› ስላቸው፣ ‹‹እንዴት አያመኝ አንበርብር? በየቀኑ ጥፋት መቁጠር እንዴት አያመኝ? በየቀኑ አስከሬን መሸኘት እንዴት አያመኝ? በየቀኑ ውሸትና ሀቅን መውገር እንዴት አያመኝ?›› ብለው ሲያፈጡብኝ ማረጋጊያ ዘዴና የምገባበት ጉድጓድ ጠፋኝ። ውሎ አድሮ የባሻዬ ሕመም ተጋባብኝ መሰለኝ የደመነፍስ ሩጫ፣ የስሜት ውዥንብር የሚነዳው ሆታና እልልታ፣ እየደገሰ የሚያስገብረን አካልና አዕምሮን መቁጠር እኔንም ታከተኝ። ጥቂት ማንቀላፋት ደግሞ መንቃት፣ እንደገና ማንቀላፋት ደግሞ መባነን፡፡ መልሶ ማንቀላፋት፡፡ የቆምን እየመሰለን የወደቅን በዝተናል መሰለኝ፡፡ መልካም ሰንበት!

    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት