Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበየዓመቱ 200 ሺዎችን የሚያጠቃው ቲቢ

በየዓመቱ 200 ሺዎችን የሚያጠቃው ቲቢ

ቀን:

የቲቢ በሽታ የያዘው ሰው ታክሞ ለመዳን የስድስት ወር ሕክምና የሚያስፈልገው ቢሆንም፣ አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚሉት ባክቴሪያው የዋህና በቀላሉ ሊከላከሉት የሚቻል ነው፡፡ በቤት ውስጥም ሆነ በትራንስፖርት ላይ መስኮት በመክፈትና አየር እንዲንሸራሸር በማድረግ ባክቴሪያውን አቅም ማሳጣትም ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገሮች በብዛት የሚገኘው ማይኮባክቴሪያም ቲዩበርክሎሲስ የተባለው የቲቢ አማጭ ባክቴሪያም የታፈገ አየር እንጂ ፀሐይ አይወድም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ዝናብ በምታገኝባቸው ወቅቶች እንኳን ፀሐይ አይለያትም፡፡

ሰዎች ረዥም ጊዜ በሚቆዩባቸው ቢሮዎችና ቤቶች እንዲሁም ትራንስፖርት ላይ አየር እንዲተላለፍ በማድረግ የቲቢ በሽታ አምጪ ተዋህስያን እንዲሞቱ ወይም ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ማድረግ ቢችሉም፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በኢትዮጵያ በዓመት 200 ሺሕ ያህል ሰዎች በቲቢ በሽታ እንደሚያዙ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኢትዮጵያ ከ1960ዎቹ ጀምሮ የቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር አገልግሎት መስጠት የጀመረች ቢሆንም፣ ዛሬም በአገሪቱ ከሚገኙ ቀዳሚ የጤና እክሎች አንዱ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 የወጣው ግሎባል ቲቢ ሪፖርትም፣ ቲቢ በዓለም ከሚገኙ አሥር ቀዳሚ ገዳይ በሽታዎች አንዱ እንደሆነ አስፍሯል፡፡ ኢትዮጵያም በችግሩ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቁ 30 አገሮች አንዷ ናት፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቲቢና ሥጋ ደዌ ፕሮግራም ኬዝቲም አስተባባሪ አቶ ሌሊሳ ፈቃዱ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ በዓመት ከ192 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ አዳዲስ የቲቢ በሽተኞች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ከእነዚህ ውስጥ በልየታ የሚገኙት ሁለት ሦስተኛው ሲሆኑ፣ አንድ ሦስተኛ ያህሉ የሕክምና አገልግሎት ያላገኙ ወይም ለማግኘት ወደ ጤና ተቋም ያልመጡ ናቸው፡፡ ስለሆነም ለበሽታው ስርጭት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑት ክፍሎች ደግሞ ኤችአይቪ፣ ካንሰር፣ ስኳርና በሌሎች በሽታን የመከላከል አቅምን በሚቀንሱ ሕመሞች የተጠቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ በተለይ ወደ ከተሞች አካባቢ ሲመጣ፣ የቲቢና የኤችአይቪ ቁርኝት መሳ ለመሳ ነው፡፡

የተፋፈገ ኑሮና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሁም የኤችአይቪ ሕሙማን በብዛት በሚገኙባት አዲስ አበባም በዓመት የሚመዘገበው የቲቢ ሕሙማን ቁጥር በዘጠኝ ሺሕና በ10 ሺሕ መካከል የሚወድቅ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የግሎባል ፈንድ ቲቢ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዘሪሁን ያረጋል እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ላይ በ2008 ዓ.ም. ብቻ 9600 የሚሆኑ የቲቢ ታማሚዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 89 በመቶው ለመጀመሪያ ጊዜ ቲቢ የታከሙ ሲሆኑ፣ 11 በመቶው ድጋሚ ሕክምና የወሰዱ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ በ2008 ዓ.ም. የተሠራው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ 83 በመቶ የሚሆኑት የቲቢ ታማሚዎች በመሥራት ዕድሜ ማለትም ከ15-54 የዕድሜ ክልል ውስጥ ነበሩ፡፡ በከተማዋ ውስጥ ቲቢ ከተያዙት 25 በመቶው ደግሞ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ናቸው፡፡

ኤችአይቪ ፖዘቲቭ የሆኑ ሰዎች ቲቢ ሲታመሙ ለማከም የሚያስችል ሥርዓት ቢኖርም፣ ሕክምናው ግን ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ካልሆኑት የከበደ አንዳንዴም ውስብስብ ችግሮችን የሚያስከትል ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም በቲቢ ከተያዙት 8 በመቶ ያህሉ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ናቸው፡፡ ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ በአማካይ ሲታይ እንጂ በተለይ በከተሞች ቁጥሩ ከፍተኛ ነው፡፡

ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆነው የቲቢ መድኃኒት የሚወስዱ እንደነገሩንም፣ ለጉበትና ለኩላሊት ሕመም ተጋልጠው ያውቃሉ፡፡ ይህንን የጐንዮሽ ጉዳት የማያስከትል መድኃኒት ቢኖርም፣ ማግኘቱም ቀላል አይደለም፡፡

ኤችአይቪንና ቲቢን አስመልክቶ በየሆስፒታሉ ጭምር አገልግሎት ቢሰጥም፣ ብዙ መድኃኒቶችን በአንድ ጊዜ የሚወስዱ ሰዎች ለጐንዮሽ ጉዳት ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ የጐንዮሽ ጉዳቱ እየታየ ለህሙማኑ መድኃኒት የሚቀርብበት ሁኔታ ቢኖርም፣ ታማሚዎች ግን የጐንዮሽ ጉዳቱን የሚቀንሰውን መድኃኒት ለማግኘት ተቸግረው እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ይህንን አስመልክቶ አቶ ሌሊሳ እንዳሉት፣ መድኃኒቶቹ በጥምር ሲወሰዱ ለሚያስከትሉት የጐንዮሽ ጉዳት ተቀያሪ መድኃኒት በስፋት ላይገኝ ይችላል፡፡ በመሆኑም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አቅርቦቱ መሻሻል እንዳለበት አምኖበት፣ ችግሩ ለሚገጥማቸው ሕሙማን የተመረጡ ምትክ መድኃኒቶች በብሔራዊ ፕሮግራሙ እንዲቀርብ ለማስቻል ልየታ እያደረገ ነው፡፡

በአገሪቱ የቲቢ መድኃኒት ጀምሮ ማቋረጥ ለሞት አልያም በሽታውን ለተላመደ ቲቢ የሚያጋልጥ መሆኑን አስመልክቶ በጤና ተቋማትም ሆነ በተለያዩ ሚዲያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ቢሰጥም ሳይሳካላቸው ቀርቶ መድኃኒቱን ለተላመደ ቲቪ የሚጋለጡም አሉ፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በ2005 ዓ.ም. የተሠራው አገር አቀፍ ጥናት 3 ሺሕ ያህል ዜጎች መድኃኒት በተለማመደ ቲቢ መታመማቸውን ያመለከተ ሲሆን፣ በ2009/10 ዓ.ም. ደግሞ ሌላ ዳሰሳ ይደረጋል፡፡

መድኃኒት የተለማመደውን ቲቢ ለማከም ይህንን መለየት የሚችሉ የላቦራቶሪ ማሽኖች በ146 ጤና ተቋማት ይገኛሉ፡፡ ሕመሙ የተገኘባቸውም በ46 ጤና ጣቢያዎች ሕክምናውን እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላም በየመጡበት አካባቢ በተዘጋጁ የጤና ማዕከላት ሕክምናውን እንዲጨርሱ የሚደረግበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡

በኢትዮጵያ በ1990ዎቹ የቲቢ ሕሙማን ቁጥር ከ300 ሺሕ በላይ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አሁን ላይ በዓመት ወደ 191 ሺሕ ቀንሷል፡፡ እንደ አቶ ሌሊሳ፣ ይህ ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን ሪፖርት እየተደረገ ያለው ቁጥር የሚያሳየውም ከፍተኛ የቲቢ በሽታ ስርጭት መኖሩን ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሦስተኛ ያህሉ ሕዝብ ለቲቢ ባክቴሪያ የተጋለጠ ነው፡፡ ሆኖም በሽታን የመከላከል አቅማቸው ጥሩና ከኤችአይቪ ነፃ የሆኑ ሰዎች ውስጥ ከ90-95 በመቶ ያህሉ በሽታውን የመከላከል አቅም አላቸው፡፡ ከ5-10 በመቶው ደግሞ በቲቢ የመያዝ ዕድል ሲኖራቸው፣ ብዙዎቹም ኤችአይቪ ፖዘቲቭ፣ ካንሰር ወይም ስኳር በሽታ ያለባቸው ናቸው፡፡ አዳዲስ ጥናቶች እንደሚያሳዩትም የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ለቲቢ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ጨምሯል፡፡

‹‹ከሕዝባችን አንፃር አብዛኛው ሰው ባክቴሪያው በውስጡ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም የቲቢ ሥርጭቱ ከፍተኛ ነው፣ ብክለቱም አለ፡፡ ይህ ማለት ግን በሽታ ሆኗል ማለት አይደለም›› የሚሉት አቶ ሌሊሳ፣ በአገሪቱ ከቀዳሚ ገዳይ በሽታዎች የተፈረጀውን ቲቢ ሕክምና ከ3 ሺሕ በላይ የጤና ተቋማት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

የቲቢ ሕክምና አገልግሎት በሁሉም ክልሎች በመዳረሱ በርካታ ታማሚዎችን ከሞት መታደግ ተችሏል፡፡ አጠቃላይ የቲቢ በሽታ ስርጭት ምጣኔ እ.ኤ.አ. በ1990 ከነበረበት ጋር ሲነፃፀርም አሁን ላይ በ50 ከመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ በየዓመቱ የሚያጋጥም የቲቢ በሽታ ስርጭት ምጣኔም እ.ኤ.አ. በ1990 ከነበረው ጋር ሲነፃር በ48 በመቶ ቀንሷል፡፡ በቲቢ በሽታ ምክንያት የሚደርስ ሞት መጠንን እ.ኤ.አ. በ1990 ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በ63 ከመቶ መቀነስ ችሏል፡፡ ይሁንና አገልግሎቱን በተመለከተ ዛሬም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንዳሉ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይገልጻል፡፡

በአገሪቱ የቲቢ በሽታ ይገኝባቸዋል ተብለው ከሚታሰቡት ሰዎች 35 ከመቶ የማያንሱ ወደ ሕክምና አልመጡም፡፡ ከእነዚህም ሁለት ሦስተኛ ያህሉ በሽታውን እያሰራጩት ይገኛሉ፡፡

የቲቢ በሽታ ታካሚዎች መድኃኒቱን በሐኪም ትዕዛዝ መሠረት አለመጠቀምና ማቋረጥ፣ በባለሙያዎች የሚሰጥ የመድኃኒት አጠቃቀም ትዕዛዝና ክትትል ጉድለት እንዲሁም የኤችአይቪ ወረርሽኝ መከሰት ሌላው ችግር ነው፡፡

በመሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት ያለፉትን ዓመታት አፈጻጸሞች ገምግሞ እ.ኤ.አ. ከ2015 በኋላ በሥራ ላይ የዋለውንና ‹‹ኢንድ ቲቢ ስትራቴጂ›› (End TB Strategy) የተባለውን ሥልት አዘጋጅቶ አቅርቧል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ የሚቆይ ስትራቴጂክ ዕቅድ ተነድፏል፡፡

የአገሪቱ የጤናው ዘርፍ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል የሆነው ቲቢ በሽታን የመከላከልና የመቆጣጠር ዕቅድም የአጠቃላይ ቲቢ ስርጭት ምጣኔን እ.ኤ.አ. በ2013 መጨረሻ ከነበረው 224 ከ100 ሺሕ እ.ኤ.አ. በ2020 በ35 ከመቶ መቀነስ፣ በየዓመቱ የሚያጋጥም የቲቢ በሽታ ስርጭት ምጣኔን እ.ኤ.አ. በ2013 መጨረሻ ከነበረው 247 ከ100 ሺሕ እ.ኤ.አ. በ2020 በ30 ከመቶ መቀነስ ሲሆኑ፣ የፕሮግራሙ ስትራተጂክ እርምጃዎችም እንዲሁ በቲቢ የሚደርሰውን የሞት ምጣኔ እ.ኤ.አ. በ2013 ዓ.ም. መጨረሻ ከነበረው 35 ከ100 ሺሕ እ.ኤ.አ. በ2020 በ45 ከመቶ መቀነስ የሚሉ ግቦችን አስቀምጧል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...