Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

‹‹የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት›› በመባል የሚታወቁት አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ ምንጊዜም ቢሆን ከኢትዮጵያውያን ህሊና ውስጥ የማይጠፉ የአገሪቱ ምርጥ ልጅ ናቸው፡፡ አቶ ሀብተ ሥላሴ በ1950ዎቹ ‹‹ቱሪዝም›› የሚባለውን ጽንሰ ሐሳብ በኢትዮጵያ ምድር ሲያፈልቁ፣ ቱሪዝም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት አንደኛው ገቢ አመንጪ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ አይታወቅም ነበር፡፡ እሳቸው ቱሪዝምን ለማስፋፋት በማሰብ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን አሳምነው በጀት በማስመደብ መሥሪያ ቤት ሲያቋቁሙና የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ፣ ከመንግሥት ሹማምንት ሳይቀር ተቃውሞ ገጥሞአቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ፈተናዎችን ከመቋቋም አልፈው ‹‹የአሥራ ሦስት ወራት ፀጋ›› (Thirteen Months of Sunshine) በሚባለው መለያ (ብራንድ) የብዙዎችን ቀልብ ገዝተዋል፡፡ ከመስከረም እስከ ጳጉሜን የሚዘልቀውን የአገሪቱን ካሌንደር መሠረት ያደረገ ዕፁብ ድንቅ ብራንድ ነበር የፈጠሩት፡፡

አቶ ሀብተ ሥላሴ የአገሪቱን ቱሪዝም በታሪካዊ የጉዞ መስመሮች የጥቁር ዓባይ ተፋሰስን፣ የጣና ሐይቅን፣ ጎንደርን፣ ላሊበላንና አክሱምን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ እኝህ ድንቅና ባለራዕይ የኢትዮጵያ ልጅ በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር ያከናወኑ ከመሆናቸውም በላይ፣ ለብዙዎች መነቃቃትን የፈጠሩና ምንጊዜም በታሪክ የሚታወሱ ናቸው፡፡ በዚያ ዘመን ኢትዮጵያን ለዓለም ለማስተዋወቅ ሲሉ ብቻ ከነበራቸው ሥልጣንና ኃላፊነት ዝቅ ብለው ወርደው፣ የተለያዩ መስህቦችን በፖስት ካርድ እያሳተሙ ለዓለም ለማዳረስ ያደረጉት ጥረት እጅግ በጣም የሚገርምና የሚያስመሰግን ነው፡፡ እኝህን እጅግ የተከበሩ ሰው ምን ያህል እናውቃቸዋለን? ምን ያህልስ አክብረን ዕውቅና ሰጥተናቸዋል? ካስመዘገቡት ውጤት ጋር የሚመጣጠን ነገር አድርገንላቸዋል? ለሚሉ ጥያቄዎች መንግሥት መልስ ቢሰጥበት ደስ ይለኛል፡፡ በበኩሌ ግን እጠራጠራለሁ፡፡ እኝህ የተባረኩ ሰው ዝም የተባሉ ይመስለኛል፡፡ በቀደም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የዕውቅና ሽልማት ከመቀበላቸው በስተቀር፡፡

ሰሞኑን የአገሪቱ ቱሪዝም አዲሱ ብራንድ ‹‹ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት›› እንዲሆን መወሰኑን ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ‹‹Ethiopia Land of Origins›› ከሚለው የእንግሊዝኛ አቻ ስያሜ ያገኘው አዲሱ ብራንድ በበኩሌ ተስማምቶኛል፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያገለገለው ብራንድ ይህንን በመሰለ ገላጭና አስደማሚ ስያሜ ሲተካ ደስ ይላል፡፡ የእዚህ ብራንድ አመንጪ ሰው ማንነት ቢታወቅ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የቀደምት ሰው መገኛ አገር ከመሆኗ አንፃር ይህንን ብራንድ ተጠቅማ አመርቂ ውጤት ይገኛል ወይ? በሚለው ላይ ግን ጥያቄ አለኝ፡፡ የእዚህ ጥያቂዬ መነሻ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የተወሱት ችግሮች ዕድሜ ጠገብ መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ዘመን በቱሪዝም ዘርፍ የሚነሱ ተመሳሳይ ችግሮች ናቸው፡፡ አንዱ ለዘርፉ ትኩረት አለመስጠት፣ ሌላው በተቋማት መካከል ቅንጅት አለመኖር ይጠቀሳሉ፡፡ በቱሪዝም ብቻ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ አገሮች እንዴት ቢሠሩ ነው ብሎ የሚቆረቆር መጥፋት አይመስልም?

ወደ ዝርዝር ጉዳይ ስንገባ የገበያና የማስተዋወቅ ሥራ ለማከናወን የውጭ ምንዛሪ አለመኖር፣ በየመዳረሻ ቦታዎች የመግቢያ ክፍያዎች መናር፣ በመስተንግዶና በአገልግሎት መስኮች ድንገተኛ የዘፈቀደ ጭማሪዎች፣ በሚፈለገው መጠን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመኖር፣ በፓርኮች አያያዝና በዱር እንስሳት ጥበቃ፣ ወዘተ መፈታት ያልቻሉ ችግሮች፣ የሚመለከታቸው ተቋማት እየተናበቡ ለመሥራት አለመቻላቸውና የመሳሰሉት ተጠቁመዋል፡፡ ሥራ በሚሠራበት ወቅት ችግሮች ለምን አጋጠሙ መባል የለበትም፡፡ ነገር ግን የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአግባቡ ለመፍታትና ውጤታማ ለመሆን ምን ያህል ጥረት ይደረጋል? የዘርፉ ባለሙያዎችና ተዋንያን ለአገር ዕድገት እስከሠሩ ድረስ ለምን አይቀናጁም? አንድ ጠንካራና ተምሳሌታዊ የአገሪቱን ቱሪዝም ከምንም አንስተው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲያስተዋውቁና ክብር ሲያገኙ የነበሩ ኩሩ ዜጋ በተፈጠሩበት አገር፣ በአሁኑ ጊዜ በዘርፉ ውስጥ ያሉ ሰዎች ተመሳሳይ ችግሮችን ይዘው ሲቀመጡ ትንሽ አይሰቀጥጣቸውም? በበኩሌ ያሳዝነኛል፡፡

በአንድ ወቅት የአገሪቱን ቱሪዝም ዘርፍ ለፓርላማ ሪፖርት ለማቅረብ ሦስት ሹማምንት ተገኝተዋል፡፡ በምሽት የሁለት ሰዓት ዜና ላይ አንባቢው የሰዎቹን ማንነትና ኃላፊነትን እየገለጸ ለፓርላማ ያቀረቡትን ሪፖርት ይተነትናል፡፡ በዚህ መሀል የአንዱ ሹም ድምፅ ይገባል፡፡ የእሳቸው ማብራሪያ የዜናው ማጀቢያ እንዲሆን ተመርጦ ነው ድምፃቸው የገባው፡፡ በጣም የገረመኝ በወቅቱ እንደ ትልቅ ጀብድ የሚተርኩት የአገሪቱን ቱሪዝም ለማስተዋወቅ 30 ሺሕ ፖስተሮች ታትመው ለዓለም መበተናቸውን ነው፡፡ አገሪቱ በምትወከልባቸው የተለያዩ አገሮች ኤምባሲዎች ፖስተሮቹ መበተናቸውን የፕሮሞሽን ሥራ የመጨረሻ አድርገው ሲተነትኑ፣ አንድም ጥያቄ ያነሳባቸው የምክር ቤት አባል አልነበረም፡፡ ያውም ሃያ ያህል የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች በነበሩበት ምክር ቤት፡፡ አሁንም ፖስተርና ካሌንደር እያተሙ ማሠራጨት የአገሪቱን ቱሪዝም ሀብት የማስተዋወቅ ውኃ ልክ የሚመስላቸው ብዙ አሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የብቃት ማጣትና ከዘመኑ ጋር እኩል አለማሰብ ማሳያ ነው፡፡ ይኼ ያሳዝናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በርካታ በቱሪዝም ዘርፉ ውስጥ የሚሳተፉ የግል ባለሀብቶች አሉ፡፡ በውጭ ዜጎች ሳይቀር የሚታገዙም አሉ፡፡ ብዙዎቹ እንደሚሉት የቱሪዝሙን ዘርፍ የሚመራው ተቋም እንኳን ሌሎችን በቅንጅት ለመምራት ራሱ ብዙ እንደሚቀረው ነው፡፡ ተቋማዊ አቅሙ ሲዳሰስም ከሚፈለገው ውጤት አንፃር ብዙ ይቀረዋል፡፡ በአንድ ወቅት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የመጡ ባለሙያ ናቸው ተብለው ንግግር ሲያደርጉ የሰማሁዋቸውን ሰው ሳስብ ያመኛል፡፡ ግለሰቡ ወይ ቱሪዝም የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ አልገባቸውም፣ ካልሆነም ከሌላ ቦታ ተገፍተው መጥተው በነሲብ የተቀመጡ ናቸው፡፡ አስጎብኚ ድርጅቶች ስላሉባቸው ነገሮች ላነሱት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ እነዚህ ሰዎች ገንዘባቸውን ኢንቨስት አድርገው ወደ ዘርፉ የገቡ ሳይሆን አገር ለመዝረፍ የሚፈልጉ ዓይነት አድርገዋቸው ነበር ሲፈላሰፉ የዋሉት፡፡ ‹‹ቪኤይት መኪና እናስገባ ስትሉ አታፍሩም?›› ሲሉ እንኳን የዘመኑን የቱሪዝም መስተንግዶ አይደለም፣ ከተማ ውስጥ ለመኖራቸው ያጠራጥሩ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ትንሹ ማሳያ ነው፡፡

ጎረቤት ኬንያ ከእኛ የተሻለ ነገር ሳይኖራት የእኛን የእጥፍ እጥፍ ከቱሪዝም ታገኛለች፡፡ ይህችን የመሰለች ድንቅ አገር ይዘን መሥራት ካቃተን ማፈር ያለብን በራሳችን ነው፡፡ መንግሥት እንደ ተቆጣጣሪነቱ ጠንከር ብሎ በሚያሠሩ የሕግ ማዕቀፎች በመታገዝ ብቁና ንቁ ባለሙያዎችን ማሠማራት አለበት፡፡ በቂ ክፍያና ጥቅማ ጥቅም አቅርቦ ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ ብልኃተኞችን ማሠለፍ አለበት፡፡ መሠረተ ልማቶችን ማጣደፍ አለበት፡፡ የግል ባለሀብቶች ራሳቸውን ከሕገወጥ ነገሮች አፅድተው ለሥራ ዝግጁ ይሁኑ፡፡ ያኔ የሚፈልጉት ገንዘብ በገፍ ይገኛል፡፡ ሥራ ይፈጠራል፡፡ አገር ታድጋለች፡፡ ትገለፅጋለች፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት›› የሚለውን ብራንድ ይዛ እንድታድግና እንድትበለፅግ ኃላፊነት ያለባቸው በሙሉ መንፈስ ይነሱ፡፡ ሰበብ ድርደራና የተለመዱ ችግሮችን ጣዕሙ እንዳለቀ ማስቲካ እየደጋገሙ ማኘክ ይሰለቻል፡፡ አሁንም ሰልችቶናል፡፡ አንዲት የሥራ ባልደረባዬ ያለችው እዚህ ላይ መጠቀስ አለበት፡፡ ‹‹ባለጌ ዕውቀት ስለሌለው ስድብ ይቀናዋል፡፡ ደካማ መሥራት ስለማይችል ሰበብ ይደረድራል፡፡›› ልክ አይደለች?

(መስፍን ጌራወርቅ፣ ከቄራ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...