Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየፍላጎት ናዳን የሚመክት ፍትሐዊ የመኖሪያ ቤቶች አቅርቦት መስፈን አለበት

የፍላጎት ናዳን የሚመክት ፍትሐዊ የመኖሪያ ቤቶች አቅርቦት መስፈን አለበት

ቀን:

የመኖሪያ ቤት ችግር የብዙ ዓለም አገሮች በተለይ የከተማ ነዋሪዎች ፈተና ነው፡፡ ዛሬ ሠለጠኑ በምንላቸው አገሮች እንኳን እስከ 36 በመቶ ከተሞች የቤት እጥረት ያለባቸው፣ በአማካይ እስከ 50 በመቶ ገቢያቸውን ለቤት ኪራይና መሰል የመኖሪያ ወጪ የሚገፈግፉ ዜጎች በርክተው ይታያሉ፡፡

የአገራችንም እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በተለይ አዲስ አበባን ለመሳሰሉ ለዘመናት በኋላቀር ሁኔታ ያለፕላን ሲለጠጡ የቆዩ ከተሞች የፈተናው ገፈት ቀማሽ ናቸው፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት በመዲናዋ መስተዳድር በተካሄደ ጥናት ከ160 ሺሕ በላይ (48 በመቶ) የሚሆኑ የከተማዋ ቤቶች ለኑሮ ተስማሚ አልነበሩም፡፡ የመፀዳጃ፣ የማብሰያ፣ ንፁህ የመኝታና የመኖሪያ ክፍሎች የሌላቸው ወይም የተጓደሉ፣ በአንዳንዱ አካባቢም ለድንገተኛ አደጋና ለአምቡላንስ አገልግሎት የሚውል የውስጥ ለውስጥ መንገድ እንኳን ያልነበራቸውም ነበሩ፡፡

እነ ባሻ ወልዴ ችሎት፣ ዶሮ ማነቂያ፣ ልደታ፣ ሰን ጋተራ፣ ሠራተኛ ሠፈር፣ አሜሪካ ግቢ፣ . . . ዓይነቶቹን የአዲስ አበባ ገጽታዎች የሚያስታውስ የአዲስ አበባ የቤት እጥረትና የአኗኗር ብልሹነትን በቀላሉ መገንዘቡ አይቀርም፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮን የሚቆጠረው የከተማዋ ነዋሪ የመኖሪያ ቤት ችግር ያለበት፣ በኪራይና በደባልነት የሚኖር ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአንድ ቤት ውስጥ ከ20 እስከ 40 ሰዎች በጊዜያዊነት ‹‹ወገብ ለማሳረፍ›› (አንዳንዶች ኬሻ በጠረባ ይሉታል) የሚታደርባቸው ‹‹ቤቶች› ብዙ ናቸው፡፡

ይኼንን አስከፊ ገጽታ የተገነዘበው መንግሥት በከተሞች የጀመረው የቤቶች ግንባታ መርሐ ግብር በተለይ ባለፉት 13 ዓመታት ገደማ አበረታች የሚባል ሥራ ተከናውኖበታል፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 140 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው እስከ 700 ሺሕ የሚደርስ ቤተሰብ ሊያስኖሩ በሚችሉበት ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በ10/90፣ በ20/80 እና በ40/60 ፕሮጀክቶች አማካይነት 130 ሺሕ ቤቶች እየተገነቡ መሆናቸውን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ይኼ ጥረት በተለይ በከተማዋ ዳርቻ ቦታዎች በስፋት እየተከናወነ ቢሆንም፣ አሁንም ከዘርፉ አንገብጋቢ ፍላጎት አንፃር የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው አልቀረም፡፡ አንደኛው በተለይ በ2005 ዓ.ም. ከተመዘገበው አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚደርስ ሕዝብ አንፃር ግንባታው ቀርፋፋ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የግንባታ ወጥነት መታጣትና የጥራት ጉድለት አንዱ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ እንደ ሦስተኛ ሊነሳ የሚችለው የኮንትራት አስተዳደርና የሀብት ብክነት እየሰፋ የመምጣቱ ተግዳሮት ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች የዘርፉ እንቅፋቶችን በዝርዝር ማሳየት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡

የፍላጎቱን ጎርፍ የሚቋጥር ኩሬ የለም

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በተለይ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የከተማ ነዋሪ የቤት ባለቤት ለማድረግ በሚኒስቴርና በቢሮ ደረጃ የቤት ገንቢ መሥሪያ ቤቶች አቋቁሞ ጥረት ቢጀምርም፣ ሒደቱ ግን ከፍላጎቱ ጋር አልተጣጣመም፡፡ በመሠረቱ የቤቶቹ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ ጀምሮ፣ በመቶኛ የግንባታ ሒደት፣ ተገንብተው ሲጠናቀቁ፣ ሲጎበኙ፣ ሲመረቁ፣ ዕጣ ሲወጣ፣ የቁልፍ ርክክብ ሲደረግ፣ . . . የሕዝብ ግንኙነት ሥራው (ፕሮፓጋንዳ ማለት ይሻላል) ስለሚደጋገምና ስለሚጮኽ እንጂ፣ ሥራው ገና ብርቱ ርብርብ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች በተለየ ጉድ የሚባልለት ከፍተኛ የሚባል ግንባታም አይደለም፡፡

ለምሳሌ ‹‹ኮንስትራክሽን ሪቪው ኦንላይን›› የተባለ ድረ ገጽ በአፍሪካ ያለውን የቤት ፍላጎትና አቅርቦት በተመለከተ እ.ኤ.አ. በ2016 ያወጣው መረጃ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ከ95 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ግብፅ በመንግሥት ፕሮጀክቶች ብቻ በዓመት ከ100 ሺሕ በላይ ቤቶች እየገነባች (በነገራችን ላይ አዳዲስ ከተማ እስከ መፍጠር መሄዳቸውን ‹‹ፊውቸር ሲቲ››ን ማንሳት ይቻላል) ቢሆንም፣ ፍላጎቱ በዓመት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ በናይጄሪያም በተመሳሳይ በዓመቱ 200 ሺሕ ቤቶች በመንግሥትና በግል ተገንብተው የዓመት ፍላጎት በሰባት መቶ ሺሕ ሲያድግ ይታያል፡፡ በኬኒያ እንኳን በየዓመቱ የቤት ፍላጎት በሁለት መቶ ሺሕ እያደገ አቅርቦቱ ከ50 ሺሕ የበለጠ አይደለም፡፡

የደቡብ አፍሪካ መንግሥትም በድጎማ ጭምር እ.ኤ.አ. ከ1994 ጀምሮ ሦስት ሚሊዮን ቤቶችን በተለይ በከተሞች ቢገነባም፣ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ አልቻለም፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ በከተሞች በመቶ ሺዎች የመንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የግል የሪል ስቴት ሥሪት ልማቶችም በአሥር ሺዎች የቤት ግንባታ ቢያከናወኑም አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች የግል የመኖሪያ ቤት ግንባታ ተዳክሟል፡፡ ስለሆነም የአቅርቦትና የፍላጎት ክፍተቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ በዓመት መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ማለት ነው፡፡  

በቅርቡ በአንድ መንግሥታዊ የኅትመት ሚዲያ የወጣ ትንታኔ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በሁለት ዙሮች ተመዝግበው ገንዘብ መቆጠብ ለጀመሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ቤት ለማዳረስ፣ በአሁኑ ከአካሄድ ከ52 ዓመታት በላይ እንደሚወስድ አሳይቷል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ (ባለፉት ሁለት ዓመታት) እንደታየው ደግሞ በበጀት፣ በቦታና በአቅም ማነስ ሥራው የሚቆራረጥ ከሆነ ከ65 ዓመታት በላይ ይወስዳል፡፡ ይኼን ሥሌት አሁን ካለው የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የመሬት ፍጥጫ ጋር ካስተሳሰርነው ደግሞ አሳሳቢ ነው፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደተናገሩትም 60 በመቶው የሚደርሰው የከተማዋ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን የቤት ፈላጊው ቁጥርም እየጨመረ የሚሄድ ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት የአቅጣጫ ለውጥ አድርጎ አካሄዱን ካልፈተሸ ችግሩ በአጭር ጊዜ ሊቃለል አይችልም ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

በእርግጥ ምንም ዓይነት የመንግሥት ቤት የመሥራት ፍላጎት ባልነበረበት አገር ውስጥ ጅምሩ መደነቅ አለበት፡፡ እስከ 18፣ 15፣ 12፣ 9 እና 7 ከፍታ ያላቸው የ40/60 ዘመናዊ ቤቶች ከመገንባት አንስቶ የተለያዩ የ10/90 አነስተኛ መኖሪያ ቤቶች በስፋት እየተሠሩ ነው፡፡ በዚህ የግንባታ ሒደት ውስጥም በርካታ ኮንትራክተሮች፣ የግብዓት አቅራቢዎችና አንቀሳቃሾች ተፈጥረዋል፡፡ ይነስም ይብዛም የሕዝቡ አኗኗርና የኑሮ ደረጃም የመሻሻል ምልክት አለው፡፡ ግን መስፋትና መጠናከር አለበት፡፡

አሁንም በአፅንኦት መታየት ያለበት ግን በየዓመቱ እየጨመረ የሚመጣውን የፍላጎት ጎርፍ የሚሸከመው የመንግሥት አቅም የለም የሚለው ነው፡፡ እነ ደቡብ አፍሪካ በሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ቤቶችን እንኳን ገንብተው ፍላጎቱን ማርካት አልቻሉም፡፡ እኛ ደግሞ 100 ሚሊዮን ሕዝብ (ይሁን ቢባል በከተሞች 20 ሚሊዮን) በ13 ዓመታት የሦስት መቶ ሺሕ ቤቶችን ግንባታ እንኳን አጠናቀን ውኃ፣ መብራት፣ መንገድ፣ ማኅበራዊ አገልግሎት አሟልተን ወደ ሕዝቡ ማድረስ አልቻልንም፡፡

የተለያዩ የዘርፉ ምሁራን እንደሚያነሱትም በቤቶች ግንባታው ላይ መንግሥት ወሳኝ ድርሻ ቢጫወትም፣ አልፋና ኦሜጋው ግን መንግሥት ብቻ ሊሆን አይችልም፣ አይገባም፡፡ የመንግሥት የተዳከመ ቢሮክራሲ፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት አሠራር የሌለበት፣ የመልካም አስተዳደር ጫና ያረበበበት መዋቅር ብቻውን የሚሊዮኖችን ፍላጎት ሊመልስ አይችልም፡፡ ይልቁንም በተመጣጣኝ የሊዝ ዋጋና የድጎማ ቀመር የቤት መሥሪያ ቦታዎችን ለግል ተቋራጮች በመስጠት፣ የውጭ ልምድ ያላቸው ቤት ገንቢዎች በማሳተፍ፣ እንዲሁም ቤት በራስ የመሥራት ፍላጎትና አቅም ያላቸው ዜጎችን እንዲገነቡ በማድረግ ፈተናውን መቋቋም ያስፈልጋል፡፡ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ዜጎች በረዥም ጊዜ ‹‹ሞርጌጅ›› ቤቶች እንዲገነቡላቸው አቅም የፈቀደውን ሁሉ የማድረግ ጉዳይም ለነገ ሊባል አይችልም፡፡

የግንባታ ጥራትና ወጪ ቆጣቢነትም ይታይ

የጋራ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ወጪ ቆጣቢ የምጣኔ ሀብት መርህን እንደሚከተል ይታወቃል፡፡ በተለይ መንግሥት የመሬትና የግብዓት ታክስን ከመደጎሙ ባሻገር፣ ዋጋቸው ተመጣጣኝ የሆኑ ማቴሪያሎችን ለግንባታ መጠቀሙና የታችኛው የሕንፃ ወለሎችን በጨረታ መሸጡ የቤቶቹን ዋጋ በመጠኑም ቢሆን እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል አሁንም በቤቶቹ ዋጋ ላይ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች እንዳሉ መጤን ይኖርበታል፡፡

አንደኛው የወጪ ምሬት ከግንባታ መጓተት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ቤት ይደርሰናል ብለው ከአፍ በመንጠቅ ጭምር ገንዘብ የሚቆጥቡ ሰዎች ቁጥር ትንሽ አይደለም፡፡ ይኼ ጅምር ምንም እንኳን የቁጠባ ባህልን ሊያሳድግ ቢችልም፣ ‹‹እነዚህን ያህል ዓመታት በገንዘቡ ብንሠራበት የት እንደርስ ነበር?›› የሚል ቁጭትም ይፈጥራል፡፡

ለምሳሌ የ40/60 ቤቶችን ዕጣ ከሚጠብቁ 160 ሺሕ ያህል ተመዝጋቢዎች መካከል እስከ 500 ሺሕ ብር የሚደርስ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ገቢ ያደረጉ 16 ሺሕ ዜጎች አሉ (በአማካይ ስምንት ቢሊዮን ብር ይሆናል)፡፡ 50 በመቶ የቆጠቡትም ከ20 ሺሕ እንደማያንሱ ተገምቷል፡፡ ለአብነት ይኼን እናንሳ እንጂ በሁሉም የቤት ሥራዎች ከአነስተኛ ቆጣቢው ጀምሮ ከፍ ያለ የሕዝብ ገንዘብ ወደ ባንክ መግባቱ በመንግሥት ግንባታ ፍጥነትና ጥራት ላይ ጫና መፍጠሩ ዕሙን ነው፡፡ ይኼ ግፊት በራሱም የፖለቲካ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርም መታመን አለበት፡፡ ስለዚህ የግንባታ ፍጥነትና መጠናከር ጉዳይ በትኩረት ሊታይ የሚገባው ነው፡፡

በሌላ በኩል የግንባታ ወጪን የሚያባክኑ አሠራሮች ሊዳፈኑ አልቻሉም፡፡ ለአብነት ያህል ሕዝብ ቅሬታ የሚያነሳባቸው የጋራ ማብሰያ ቤቶች (ኮሙዩናል ሕንፃዎች) ጉዳይ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሥራዎችና ለዓመታት በመጋዘኖችና በቆሻሻ ተይዘው ክፍት የሆኑ ቦታዎች ጉዳይ እልባት ማግኘት ይኖርበታል፡፡ በአንዳንድ የጋራ መኖሪያ ቤት ሳይቶችም መገንባት ካለባቸው ሕንፃዎች ያነሰ የግንባታ ቁጥር መኖሩ፣ ያላለቁ ሕንፃዎች ተገትረው መታየታቸውና ባለቤት አልባ ክፍሎች በእንጥልጥል መቅረታቸው የብዙዎችን ቁጭት ያጭራሉ፡፡

ከሰሞኑ በሪፖርተር ጋዜጣ ርዕስ አንቀጽ በግልጽ እንደተመለከተውም በ20/80 መርሀ ግብር በቱሉ ዲምቱ፣ በቦሌ አራብሳ፣ በኮዬ ፊጬ፣ በየካ አባዶ፣ በቂሊንጦና በመሳሰሉት የጋራ መኖሪያ ግንባታ ሳይቶች ወጥ አሠራር አልታየም፡፡ ምንም እንኳን የሁሉም የግንባታ ሳይቶች ዲዛይንና ጥራት ተመሳሳይ እንዲሆን ባይጠበቅም፣ በአንድ ወቅት በተቀራራቢ ግብዓትና በጀት የተሠሩ ቤቶች ላይ የጎላ ልዩነት መፈጠሩ ግን እንደ ክፍተት ተወስዶ መታየት ያለበት ነው፡፡ ከግንባታ ተቋራጮች፣ ከአማካሪዎችና ከመንግሥታዊ አካላት የቁጥጥር አቅምና አንዳንድ ጊዜም አሻጥር ጋር የሚገናኘው ይኼ የጥራት መጓደል ተፈጥሯዊ ቢመስልም፣ በአገርና በሕዝብ ሀብት ላይ የሚያሳድረው ጫናና ጉዳት የከፋ ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ ‹‹በተመጣጣኝ ዋጋ›› ስም በብዙዎቹ የጋራ ኮንዶሚኒየም ቤቶች እየተገጠሙ ያሉት በርና መስኮቶች፣ የመታጠቢያና መፀዳጃ ዕቃዎች ጥራትም አሳሳቢ ነው፡፡ በቅርቡ በተደረገ አንድ መለስተኛ ጥናት እስካሁን ተገንብተው ከተላለፉ 140 ሺሕ ቤቶች ውስጥ ቢያንስ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ባለቤቶች ዕቃዎቹን ቀይረዋል፡፡ የማብሰያና መታጠቢያ ክፍሎችን ንጣፍ (ሴራሚክ) ቀይረዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ‹‹ለቅንጦት›› ብለው የቅርፅና የዓይነት ለውጥ ለማምጣት ከሞከሩት ውጪ ነው፡፡

እነዚህ ነዋሪዎች በሒሳብ ቀመር ቢሠሉ እስከ መቶ ሺሕ ቢሆኑና እያንዳንዳቸውም በአማካይ ከ30 ሺሕ ብር በላይ ወጪ ቢያደርጉ፣ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የአገር ሀብት ባክኗል፣ ዜጎችም ለኪሳራ ተዳርገዋል ሲሉ ባለሙያዎች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ይህ በመሆኑም አንዳንድ የመስኩ ሙያተኞች መንግሥት የዜጎችን ፍላጎት መገደብ ስለሌለበት የማጠናቀቂያ ግንባታ ሥራዎች በባለ ዕድለኞች እንዲሠሩ ማድረግ አለበት እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ ወይም በቤቶቹ ስፋት ልክ ደረጃቸውን የጠበቁ የማጠናቀቂያ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡

በኮንትራክተሮችና በመናኛ ‹‹ዕቃ አቅራቢዎች›› አሻጥር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የደሃ አገር ገንዘብ ያላግባብ በመርጨት የሚገኘው ፖለቲካዊ ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ እንደሆነ መመርመርም ተገቢ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አመርቂ መፍትሔ ማበጀት ይገባል፡፡

የቤቶች አስተዳደርና ማስተላለፍ ሥርዓቱም ይታይ

ከላይ የተጠቃቀሱ የአፍሪካ አገሮች በድጎማ፣ በብድርም ሆነ በግልጽ ጨረታ ገንብተው ለሕዝብ የሚያስተላልፏቸውን ቤቶች በማያሻማ አሠራርና የሕግ ማዕቀፍ መልሰዋል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካና በናይጄሪያ ዜጎች በኑሮ ደረጃ፣ በብሔር፣ በፖለቲካ፣ በሥልጣን ወይም በሌላ መለኪየ ሳይለያዩ በቆጠቡት ገንዘብና በቅደም ተከተላቸው መሠረት የመኖሪያ ቤቶችን እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታም ቤቶችን ገንብቶ በማስተላለፍ ረገድ የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለመፍጠር የተደረገ ጥረት መኖሩ አልቀረም፡፡ ይሁንና ከምዝገባው ጀምሮ አሠራሩ ገና አዲስ ስለነበር ከነባሩ የከተማዋ ነዋሪ ይልቅ ከሌላ አካባቢ የመጣውና በሥርዓቱ መርሐ ግብር ተስፋ አድርጎ የነበረው ይበልጥ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ የቤት ዕደላ ሲደረግም በተለይ በቀዳሚዎቹ ዙሮች የአሠራር ክፍተት እንደነበር ውስጥ አዋቂ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ ጥገኛ የዘርፉ አመራሮች በዘር፣ በጥቅምና በመሳሰሉት ለተሻረኳቸው ሰዎች በክፍያም ቢሆን ቤት እንዲያገኙ ማድረጋቸው በቅርቡ ተሃድሶም ተገልጿል፡፡

ከአራተኛው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አወጣጥ አንስቶ ግን በኮምፒዩተራይዝድና በጥብቅ ዲሲፒሊን ለማስተላለፍ የተደረገ ጥረት አለ፡፡ አሁንም መፈተሽ ያለባቸው አሠራሮች ቢኖሩም ሒደቱ በጥብቅ አመራር እንደሚፈጸም በቅርቡ የከተማዋ ከንቲባ ሲናገሩም ተደምጧል፡፡ ‹እንዲያውም እስካሁን ተመዝግቦ እየቆጠበ ያለውን የቤት ባለቤት ሳናደርግ ወደ አዲስ ምዝገባ አንገባም፣ ተመዝግቦ ያለውም ቢሆን የቀበሌም ሆነ የግል ቤትና ይዞታ እንደሌለው ሳናረጋጋጥ የሕዝብ ጥቅምን አሳልፈን አንሰጥም› ማለታቸው በተግባር መታየት ያለበት ነው፡፡

ከጋራ መኖሪያ ቤቶች አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የጋራ ሀብት አስተዳደር፣ አጠባበቅና የጋራ ተጠቃሚነትን የተመለከተው ሥራ ነው፡፡ በእርግጥ አስተዳደሩ ቤቶቹን ለግለሰቦች ካስተላለፈ በኋላ የማስተዳደሩ ሥራ የነዋሪዎች ማኅበራት መሆኑ ቢታወቅም በጋራ ማብሰያ ኪራይ፣ በተሽከርካሪ ፓርኪንግ፣ በመጋዘን ኪራይ… የሚገኝ ገንዘብን እንዴት እንደሚያስተዳድሩ ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ነዋሪዎች በየወሩ የማከፍሉት መዋጮ ለፅዳት፣ ለፀጥታና ለጋራ ልማት ስለመዋሉ በጥብቅ ቁጥጥር ካልተረጋገጠ ሕዝብ መጎዳቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የአካባቢ አስተዳደር አካላትና ሕዝቡ ራሱ ብርቱ ትግል ማድረግ ይጠብቀዋል፡፡

ለአብነት ያህል በአንድ የሕዝብ ውይይት ላይ በቅርቡ እንደተሰማው በትልልቅ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግቢ ውስጥ የጎዳና ንግድ፣ አነስተኛ የመንገድ ላይ ቡናና መሰል ሥራዎችን የሚሠሩ (የተሰማሩ) ሰዎች፣ በውንብድና ኪራይ የሚሰበስቡ የማኅበርና የወረዳ አመራሮች እንዳሉ ተጋልጧል፡፡ በግንባታ ግብዓት መያዣ ያገለግሉ የነበሩ መጋዘኖችን ለግል ጥቅም ያከራዩና ከግንባታ በኋላ በኋላ ያልተሰበሰቡ የመንግሥት ሀብቶችን ለዝርፊያ የሚያጋልጡ አሠራሮችም ተለይተዋል፡፡ (በቅርቡ በ15 ሲኖትራኮች የ40/60 ግንባታ ብረቶች ተሰውሮ በፍለጋ መገኘቱ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡)

በአጠቃላይ መንግሥት የከተሞችን በተለይም የአዲስ አበባን የቤቶች ችግር ለመቅረፍ እያደገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተሠራ ተዓምርና እንደተገኘ መና ብቻ ከመቁጠር ወጥቶ አሠራሩን እየፈተሹ፣ እየገሰገሰ የመጣውን የፍላጎት ናዳ የሚመክት የቤት ግንባታ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት ‹‹እኔ ብቻ ልገንባ›› ከማለት ወጥቶ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የተሳተፈውን ዓይነትና ብዛት ማሳደግ አለበት፡፡ ሕዝቡም በማስተላለፍ፣ በማስተዳደርም ሆነ በግንባታው ረገድ ተጠቃሚና ተሳታፊነቱን በፍትሐዊነት እያረጋገጠ መሄድ አለበት፣ ይገባልም፡፡ ይኼ ሲሆን ነው ጅምሩ የሚሰምረው፣ ከተሜው እፎይ የሚለው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...