Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ በ5.5 ቢሊዮን ብር አዲስ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ተጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚገነባው ኮዬ ፈጬ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮጀክት ፊት ለፊት በሚገኘው መሬት ላይ፣ በ5.5 ቢሊዮን ብር ወጪ አዲስ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ተጀመረ፡፡

‹‹ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ›› በሚባል ስያሜ የካቲት 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ ግንባታው በተጀመረው በዚህ ሳይት በርካታ የኮንስትራክሽን ማሽኖች የአፈር ቆረጣ፣ የአፈር ማንሳት፣ የመሬት ማስተካከልና የጉድጓድ ቁፋሮ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ብዙም ባልተለመደ ፍጥነትና በበርካታ የኮንስትራክሽን ማሽኖች ታግዞ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት 320 ገልባጭ ተሽከርካሪዎች፣ 78 ኤክስካቫተሮች፣ 30 ሎደሮች፣ ቡልዶዘሮችና የጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽኖች አካባቢውን ተቆጣጥረውታል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተወዳዳሪነትና የሥራ ፈጠራ አስተባባሪ አቶ ሰማ ገዳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሥራው በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ግንባታው ከተጀመረ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ እስከ ረቡዕ መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ 470 ሺሕ ኪዩቢክ ሜትር አፈር ተነስቷል፡፡

‹‹አፈሩ እየተደፋ የሚገኘው የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በፈቀደው ቦታ ላይ ነው፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ በማያመጣ መንገድ ከዚህ ቀደም ድንጋይ የወጣባቸው ካባዎች በፈጠሩት ገድጓዳማ ቦታዎች ውስጥ እየተደፋ ይገኛል፤›› ሲሉ አቶ ሰማ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአፈር ቆረጣው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ግንባታ ለመግባት ጠጠርና አሸዋ የመሳሰሉ ግብዓቶችን ለማምረት የሚያስችሉ ካባዎችን ለማቋቋም የቦታ መረጣ እየተካሄደ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ጥር 12 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ስምምነቱ ተፈርሞ ወደ ግንባታ የተገባው የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ337 ሔክታር መሬት ላይ ያርፋል፡፡ ይህ ግንባታ በሁለት ምዕራፎች የሚካሄድ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ዙር ግንባታ በ153 ሔክታር መሬት ላይ ይካሄዳል፡፡

በአጠቃላይ 5.5 ቢሊዮን ብር ወጭ የሚደረግበት ግንባታ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ታቅዷል፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ ክልል ውስጥ የፋርማሲውቲካል መሣሪያዎች፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ እንዲሁም የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ይፈበረኩበታል ተብሏል፡፡

አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቂሊንጦ አካባቢ በርካታ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ በአካባቢው ካሉት መካከል የቱሉ ዲምቱና የኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ የሐይኒከን ቢራ (ቂሊንጦ ፋብሪካ)፣ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤትና የአይሲቲ ፓርክ ይገኙበታል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች