ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ኤድና ሞል ፊት ለፊት የሚገኘውን አደባባይ ከመኪኖች ጋር እየተጋፉ ያለፉት አህዮች ናቸው፡፡ በአፀደ ሥጋ የሌለው ዕውቁ ደራሲ መንግሥቱ ገዳሙ ‹‹ከማን አንሼ›› የምትባል ቤሳ ልብወለድ ነበረችው፡፡ የፊት ሽፋኗ አህያ ሙሉ ሱፍ ከነሰደርያውና ካፖርት ደርባ፣ ባርኔጣ ደፍታ፣ መነጽር አጥልቃ ትታይበታለች፡፡ ድርሰቱ በአህያዪቱ ዙሪያ ሲያጠነጥን አንዱ የአህያ ጸሎት ነበር፡፡ ‹‹በስመ ጎርማንዴዎስ ወሰርዶ ወፋንድያ፤›› በማለት ጸሎቷን አድርሳ ወደ ቀለቧ እንደምታመራ ተጠቅሷል፡፡ በፎቶው የሚታዩት ስሚንቶና አሸዋ የተጫኑት አህዮችና በአደባባይ እንዳንንፈላሰስ ማናለን ከልካይ ብለው ይሆን? ወይስ እንደ መንግሥቱ ገዳሙ ‹‹ከማን አንሼ?››
– ሔኖክ መደብር
* * *
የሚሄድ በርጋታ
የሚሄድ በርጋታ ድምፁ ሳይሰማ
የሚኖር ይመስላል ከሁሉ እየተስማማ
ራሱን ሰውሮ
ከሰዎች አዕምሮ
ቀርበነዋል ሲሉት የሚገኘው ርቆ
በጥርሱ እየሣቀ ሕይወቱን ደብቆ
ባልተጠበቀ ቀን ድንገት የሚመጣ
የቅጽበት ፈገግታው ከልብ የማይወጣ
አንስተው ጥለውት ገድለነዋል ብለው
ተነስቶ የሚገኝ ከመካከላቸው
ቢቀርቡት ቢርቁት የማይለወጠው
ሰላም ፍቅር እንጂ ጥላቻ የማይገዛው
ድምጹ ሳይሰማ የሚኖር በርጋታ
ዓይኖቹ ቀዝቃዛ ግንባሩ ማይፈታ
ምን? ይሆን ምስጢሩ የሚደበቅበት
ፍቅሩ ወይ ጥላቻው የማይታወቅበት
ምንድነው? ከሰው ልጅ እሱ የሚፈልገው
ቢጥሉት ቢያፈርጡት የማይለወጠው፡፡
ንጉሤ ካሣዬ ወልደ ሚካኤል፣ ‹‹ቅጠሎች ነን›› (2010)
* * *
ዛሬ ነገ ማለትና ጤና
በቫንኩቨር ሳን ጋዜጣ ላይ የተጠቀሰ አንድ ጥናት ‹‹ዛሬ ነገ እያሉ ሥራን ማዘግየት ሊያሳምም ይችላል›› ይላል፡፡ በቅርቡ በቶሮንቶ፣ ካናዳ በተደረገ የአሜሪካ ሥነ አእምሮ ማኅበር ጉባኤ ላይ 200 የሚያክሉ የካናዳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተደረገ የጥናት ውጤት ‹‹መሥራት ያለባቸውን ሥራ ዛሬ ነገ እያሉ የሚያዘገዩ ሰዎች በዚህ ድርጊታቸው ምክንያት በራሳቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭነት ስለሚያስከትሉ ከሌሎቹ የበለጠ ከጭንቀት ጋር ተዛምዶ ባላቸው በሽታዎች እንደሚጠቁ አረጋግጧል፡፡ … የፈተናው ቀን እየቀረበ ሲመጣ በዛሬ ነገ ባዮቹ ላይ የሚደርሰው ውጥረት እያየለ ይሄዳል፡፡ በግድ የለሽነት ያሳለፉት ጊዜ በራስ ምታት፣ በወገብ በሽታ፣ በጉንፋን፣ በእንቅልፍ እጦትና በተለያዩ አለርጂዎች ይተካል፡፡ ከሌሎቹ የበለጠ በመተንፈሻ አካላት ችግሮች፣ በተለያዩ ኢንፌክሽኖችና ራስ ምታቶች ተጠቅተዋል፡፡››
- ንቁ መጽሔት (ሚያዝያ 2002)
* * *
ይከፍላላ!
ሦስት ጓደኛሞች ምግብ ሊበሉ ሆቴል ይገቡና ሁለቱ እጃቸውን ሲታጠቡ፣ ጋብሮቩ ውድ የሆኑትን የምግብ ዓይነቶች ከዝርዝሩ ላይ በፍጥነት ይሰርዝ ጀመር፡፡
የሆቴሉ ባለቤት፣ በድርጊቱ ተገርመው አፍጠው ሲመለከቱትም ‹‹ሒሳቡን የምከፍለው እኔ ነኛ!›› አላቸው፡፡
* * *
‹‹አዬ ልጄ የመጀመሪያውን ዕዳህን ሳትከፍል…››
ቀድሞ የነበረበትን ዕዳ ያልከፈለው የአያ ሚንዮ ጐረቤት ሁለተኛ ብድር ሊጠይቅ ይሄዳል፡፡ ሽማግሌው ሚንዮም በትህትና ተቀብለውት ችግሩን ካዳመጡ በኋላ፣ እፊት ለፊቱ ያለውን ጠረጴዛ እያመለከቱ ከመሳቢያው ውስጥ የሚፈልገውን ያህል ገንዘብ እንዲወስድ ይፈቅዱለታል፡፡
ባለ ዕዳው መሳቢያውን ይጐረጉርና ‹‹አያ ሚንዮ! ለምን ይቀልዱብኛል? መሳቢያው ውስጥ ሰባራ ሳንቲም እንኳ የለም’ኮ!›› ይላቸዋል፡፡
ይኼኔ አዛውንቱ ሚንዮ፣ ‹‹አዬ ልጄ፣ የመጀመሪያውን ዕዳህን ሳትከፍል እንዴት ሰባራ ሳንቲም እኔ ዘንድ ሊኖር ይችላል ብለህ ነው?›› ሲሉ መለሱለት፡፡
- አረፈዓይኔ ሐጎስ፣ ‹‹ቀልዶች ከጋብሮቮ ምድር›› (1979)
* * *
‹‹ለሰው ሞት አነሰው››
እባብ በክረምት ውኃ ሞልቶበት ዳር ዳሩን ሲንቀዋለል አንድ ሰው መጣ፤ እባቡም ሰውዬ እባክህ አሻገረኝ ብሎ ለመነው፡፡ ያም ሰው እጅ የለህ እግር የለህ ምንህን ይዤ ነው የማሻግርህ አለው፡፡ እባቡም ፈቃድህስ ከሆነ ራስህ ላይ ጠምጥመኝ ቢለው ጠምጥሞ አሻገረው፡፡ ካሻገረውም በኋላ በል ውረድልኛ ቢለው እምቢ አልወርድም አለ፡፡ ወደ ዳኞች (አራዊትም) ሁሉ ሂዶ ቢከሰው ዳኞቹ (አራዊቶቹ) በገዛ እጅህ እባብ ራስሀ ላይ ጠምጥመህ እያሉ ፈረዱበት፡፡
በመጨረሻውም በቀበሮ ዳኝነት ከስሰው ቀበሮዋም እባብን ምድር ወርደህ በግራ ቆመህ ሥርዓት ለብሰህ ተነጋገር አለችው፤ እሱም ተተረተረና ዱብ አለ፡፡ ከዚህም በኋላ ቀበሮዋን ሰውዬው እህ አላት እሷም ሰው በትር ይዞ ቆሞ እባብ እምድር ተጋድሞ ብትለው ራስ ራሱን ብሎ ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ ችሎትም ሲመለስ ብድሯን ለመክፈል ማታ በግ አመጣልሻለሁና ቤትሽን አሳዪኝ አላት እሷም አስከትላው ሂዳ ቤቷን አይቶ ተመለሰ፡፡ ማታም ውሻውን አስከትሎ ሂዶ ከበር አፏ ቁሞ እንኰይ ቀበሩት ብቅ በዪ አላት በግ ይዞልኝ መጥቶ ይሆናል አለችና ብቅ ብትል ያዠ ኩቲ ብሎ ውሻውን ለቀቀባት፤ እሷም ሰው ሰው ሰው ለሰው ሞት አነሰው እያለች ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡
- ደስታ ተክለወልድ ‹‹ገበታዋርያ›› (1926)
* * *
ከሰው የላቁት እንስሳት
ሰዎች የማይረዱ ወይም የማይሰሙት እንስሳት ግን የሚረዱት የመሬት መንቀጥቀጥ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ሁልጊዜ መኖሩ መታወቅ አለበት፡፡ ከሰው በተሻለ መልኩ እንስሳቱ የመሬት መንቀጥቀጥን ሲከሰት እንስሳቱ ከተለመደው ባሕሪያቸው ይለያሉ፡፡ ወይም የተለያየ ባህሪ ይኖራቸዋል፡፡ ሰው የሚረዳው ግን ከፍ ያለውን የመሬት መንቀጥቀጥ ደረጃ ነው፡፡ የመንቀጥቀጥ ሁኔታ ይለያያል፡፡ በጣም ዝቅተኛ አለ ይህም እንስሰሳቱ ብቻ የሚረዱት ማለት ነው፡፡ በሬክተር ስኬል ሲለካም አንድ፣ ሁለት፣ ሦስት እያልን የምናስቀምጠው ነው፡፡ ከፍ እያለ ሲሄድ ደግሞ እስከ አራትና እስከ አምስት ብለን የምናስቀምጠው ሲሆን ይህም ሰው ሊረዳው የሚችል ነው፡፡ በዚህም ሁኔታ ቤቶች ሲንቀጠቀጡና ዕቃዎች ሲወድቁ ይታያሉ፡፡ ይሰማልም፡፡ ከዚህም አልፎ ደግሞ ሰባት፣ ከዛም በላይ በሚሆንበት ጊዜ ድልድዮችና ሕንፃዎች ሲወድቁና ሌላም ነገር ሲደርስ ይታያል፡፡
- ደረጀ አያሌው (ዶ/ር) በመጽሔተ ሪፖርተር (1998)
* * *