Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሥነ ጽሑፍ ባለውለታው

የሥነ ጽሑፍ ባለውለታው

ቀን:

የተለያዩ ሃይማኖታዊና ዓለማዊ ወይም ትምህርታዊ መጣጥፎችን ጽፎ ለሕዝቡ ለማድረስ ቆዳ ፍቆ፣ ብራና ዳምጦ ማዘጋጀት ከዚያም መከተቢያ ቀለም መቀመም ግድ ይላል፡፡ ይህም የጽሑፍን ሥራ እጅግ አድካሚና ሥራውም ለተመረጡ ትጉኃን የተሰጠ ያስመስለው ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን (1881- 1906) የነበሩ ማተሚያ ቤቶች ሳይቀሩ የሚንቀሳቀሱት በእጅ ጽሑፍ እንደነበር፣ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡

ነገሮች መልካቸውን የቀየሩት ዘመናዊ ኢትዮጵያን የማየት ጉጉት የነበራቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ በ1914 ዓ.ም. ዘመናዊ ማተሚያ ቤት እንዲቋቋም ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ልዑል ራስ ተፈሪ ማተሚያ ቤት በመባል ይታወቅ ነበር፡፡

የጋዜጣው የመጀመሪያ እትም ሐሙስ ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም. ሲወጣ ‹‹ብርሃን የጨለማ ተቃራኒ ነው፡፡ ሰላምም ደግሞ የጠብ ተቃራኒ ነው፡፡ ብርሃን በሌለበት ጨለማ ይሰለጥናል፡፡ ሰላም በሌለበትም ጠብና ሁከት ጦርነት ይሰለጥናል፡፡ ፀሐይ ብርሃን ለሰውና ለእንስሳት ለተክል ሕይወት ሊሆን የሚያስፈልግ ነገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ ልዑል ተፈሪ መኰንን ባገራቸው ብርሃንና ሰላም እንዲሆን የሚፈልጉ ስለሆነ ይህንን ጋዜጣ ብርሃንና ሰላም ብለው ሰየሙት፤›› የሚል ጽሑፍ ይዞ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ብርሃንና ሰላም የሚል የማተሚያ ቤቱን ስያሜ የያዘ ጋዜጣ ይታተምበትም የነበረው፡፡ አጋጣሚው ለአገሪቱ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ዕድገት መሠረት የጣለ ጥቂት የማይባሉ ጸሐፍት ከሕዝቡ ጋር እንዲተዋወቁ የሆነበት ነው፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ማተሚያ ቤቱ ከተቋቋመ ከ1914 ዓ.ም. እስከ 1917 ዓ.ም. ድረስም 18 መጻሕፍትን ማሳተም ችሏል፡፡ ከእነዚህም መካከል የዮሐንስ አፈወርቅ ንባብ ከነትርጓሜው፣ መጻሕፍተ ሰሎሞን፣ የአማርኛ ሰዋስው (በከንቲባ ገብሩ) መጽሐፈ ሲራክ፣ ውዳሴ ማርያም ንባብ ከነትርጓሜው፣ የበገና ግጥም፣ መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር (በነጋድረስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ) የሕይወት ታሪክ – የመሳፍንትና መኳንንት (በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ)፣ የልዑል አልጋወራሽ የኤደን መንገዳቸው ጉዞ (ነጋድረስ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ) ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

የዘመናዊ ኅትመት ጅማሮ በነበረበት በዚያ ዘመን አገልግሎት ላይ ይውሉ የነበሩ የተለያዩ ማሽኖች አሠራር ውስብስብነት በእጅ ከመጻፍ የተሻለ ቢሆንም፣ አሠራራቸው ውስብስብነት አለው፡፡ ከዛሬው የቴክኖሎጂ ምጥቀት ጋር ሲነፃፀሩም የሁለት ዓለም ግኝቶች ያህል የተለያዩ ናቸው፡፡ አሠራራቸው የተጻፈን ነገር ኮፒ የማድረግ ያህል ሳይሆን ሌላ የሒሳብ ስሌት የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡

እነዚህ ማሽኖች በሌሎች ዘመናዊ ማሽኖች ቢተኩም ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጪ አልሆኑም፡፡ ወደ ድርጅቱ ዋና ሕንፃ ከመግባትዎ ከበሩ ትይዩ የተቀመጠችውን የመጀመርያዋን የድርጅቱን ማሽን ይመለከታሉ፡፡ እሷን አልፈው ወደ ላይ ሲወጡ በጊዜ ማሽን ወደ ኋላ የተመለሱ ዓይነት ስሜት ከሚፈጥሩት የድሮ ማሽኖች ከተደረደሩባቸው ክፍሎች ይደርሳሉ፡፡ እነዚህ ዕድሜ የተጫናቸው ማሽኖች የአገሪቱ ሥነ ጽሑፍ ባለውለታዎች ከዚያም ሲያልፍ ድርጅቱን ያቀኑ ናቸው፡፡

በእነዚህ ማሽን አንድን ፊደል ቀርፆና በወረቀት ላይ አትሞ ለማውጣት የተለየ ጥበብ፣ የተለየ ድካምና ትኩረት ይጠይቃል፡፡ እያንዳንዱን ፊደል የሚቀረፀው በእርሳስ  ነው፡፡ ፊደል ለመቅረፅ የሚረዳው እርሳስ በ525 ዲግሪ ፋራናይት ፈልቶ እንደ ወጥ በማሽኑ በአንደኛው ጎን በሚገኘው ድስት መሳይ ነገር ይቀመጣል፡፡ ከዚያም የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ እያንዳንዱን ፊደል በቁርጥራጭ ብረቶች ላይ እያተመ ይተፋል፡፡ እነዚህ ቁርጥራጭ ብረቶች ከቀለጠው ሊድ ላይ እየተቀነሱ የሚቀረፁ ናቸው፡፡

ቀጥሎ የተቀረፁትን ፊደሎች ሰካክቶ ቃላት የመመሥረትና ዓረፍተ ነገር የመገጣጠም፣ አንቀጾችን የመገንባት ሥራ ይሠራል፡፡ ‹‹ሁሉ ነገር በሒሳብ ነው የሚሠራው አለዚያ መኪና ውስጥ ገብቶ ይበታተናል፤›› ይላሉ አቶ ሙሉጌታ ድንበሩ፡፡ አቶ ሙሉጌታ በማተሚያ ቤቱ ሊኖታይፕ ኦፕሬተር ናቸው፡፡ በዚህ ክፍል ለዓመታት አገልግለዋል፡፡ በክፍሉ ውስጥ ከሚገኙት የተለያዩ ማሽኖች ወደ አንደኛው በእጃቸው በመጠቆም፣ ‹‹ብረት በብረት የሆነ የጣሊያኖች ሥሪት ነው፤›› አሉ የማሽኑን ጥንካሬ በማድነቅ ዓይነት፡፡

ዕድሜ ጠገብ የሆኑት እነዚህ ማሽኖች አሁንም ድረስ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ብዙ ጊዜም ሠንጠረዦችን፣ መታወቂያዎችና ማኅተሞችን ለመቅረፅ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ዕድሜ ጠገብ እንደመሆናቸው ሊያስቸግሩ፣ አሊያም እየሠሩ በመካከል ቀጥ ሊሉ ይችላሉ፡፡ እነ አቶ ሙሉጌታ ግን በዚህ አይማረሩም ‹‹እንደ ባህሪያቸው ነው የምንይዛቸው፤›› በማለት ተረጋግተው ሥራቸውን ይሠራሉ እንጂ እንደማያማርሩ ይናገራሉ፡፡

ሪፖርተር ባነጋገራቸው ወቅት የኤጀሬ ወረዳ የቀበሌ መታወቂያ በማዘጋጀት ላይ ነበሩ፡፡ በክፍሉ በአንደኛው ጥግ በተደረደሩት መደርደሪያዎች ላይም የብረት ቁርጥራጮችና በመልክ በመልኩ የተዘጋጁ የተለያዩ በሊድ የተቀረፁ ማኅተሞች ይታያሉ፡፡ እንዲህ ተደርጎ የተዘጋጁት ሥራዎች ወደ ማኅተም ክፍል ይሄዳሉ፡፡  

‹‹አንድ ፊደል ብንሳሳት እንደገና መሥራት ይኖርብናል፡፡ ለዚህም አንድ መታወቂያ ለመሥራት ሦስት ሰዓት ያህል ይፈጅብናል፡፡ እኛ በሊድ ካዘጋጀን በኋላ ነው ወደ ኅትመት ክፍል የሚገባው፤›› የሚሉት በማተሚያ ቤቱ ለ35 ዓመታት ያህል ያገለገሉት አቶ ሰለሞን እርገጤ ናቸው፡፡ በየዕለቱ የሚወጡ ጋዜጦችን ጨምሮ ሁሉም ኅትመቶች የሚሠሩት በእነዚህ ማሽኖች ነበርና፣ ‹‹ሥራው በጣም አድካሚ ነበር፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብለን ሠርተን ሲነጋ ነው የምንወጣው፤›› በማለት ነገሮች እንዳሁኑ ቀላል ከመሆናቸው በፊት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡

ለአገሪቱ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት ባለውለታ የሆኑ እነዚህ ዕድሜ ጠገብ ማሽኖች ይሠሩት የነበረውን አብዛኛውን ሥራ  የሚሠራው የዘመኑ ትሩፋት በሆኑ ቴክኖሎጂዎች ከሆነ ቆይቷል፡፡ አጋጣሚውም ለእንደነ አቶ ሰሎሞን ላሉ የክፍሉ ሠራተኞች የሥራ ጫና እንዲቀንስላቸው ሆኗል፡፡ ‹‹በኮምፒዩተር መሥራት ከተጀመረ በኋላ ትልቅ የሥራ ጫና ቀንሶልናል፤›› አሉ ጋዝ የነካ እጃቸውን እየጠራረጉ፡፡

የድርጅቱ ታሪክ አካል የሆኑት እነዚህ ቀደምት ማሽኖች፣ እንደ አቶ ሰሎሞንና አቶ ሙሉጌታ ያሉ ሠራተኞች የኅትመትን ሀ፣ ሁ፣ . . . የወቅቱን ሠራተኞች ትጋት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በንፅፅር ሲታይም በአሁኑ ወቅት ጥቅም ላይ የሚውሉ ማሽኖችን ደግሞ ቅንጡና እንከን የለሽ ያስመስላቸዋል፡፡ የድርጅቱ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምም ከጊዜ ወደ ጊዜ በምን ያህል መጠን እያደገ መምጣቱን ያሳያል፡፡

በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ቡድን መሪው አቶ ሚሊዮን ተሾመ እንደሚሉት፣ በኅትመት ዘርፍ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጥሩ ውጤት ማግኘት ተችሏል፡፡ የሞባይል ካርዶችን የማተም፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም አንፃር ዘመናዊ የዌብ ኦፍሴት መሣሪያ በመጠቀም ሙሉ ቀለም የሆነ ጋዜጣና የመጻሕፍት ኅትመት አገልግሎት መስጠት ዘመናዊ የባለ አራት ዩኒት የኦፍሴት ኅትመት መሣሪያን በመጠቀም ጥራቱ የተሻሻለ የባለሙሉ ቀለም ኅትመት ማከናወን፣ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን እንደ ብሔራዊ ፈተና፣ የቦንድ ኅትመት፣ የሌሎች ምስጥራዊና መደበኛ ኀትመት ያሉ አገልግሎቶች መስጠት የሚቻልበት አቅምም መፍጠር ተችሏል፡፡

ከዚህም ሲያልፍ ሐሰተኛ የማስረጃ ሰነዶችን ጥቅም ላይ የማዋል ችግርን የሚቀርፍ አሠራር መዘርጋት ተችሏል፡፡ የዲግሪ፣ የመሬት ካርታ፣ የወሳኝ ኩነቶች፣ የኢንሹራንስና ሌሎች መሰል ማስረጃዎችን በሐሰተኛ መንገድ ተሠርተው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚያስችል የኅትመት ውጤት በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ ሶፍትዌርና ሚስጥራዊ የኅትመት ግብዓቶችን በመጠቀም ደኅንነቱ የተረጋገጠ የማስረጃ ኅትመት ሰነድ ለማተም የሚያስችለውን ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

በተጨማሪም እንደ የገንዘብ ኖት፣ ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውል የፕላስቲክ፣ ስማርት ካርድ፣ የሚፋቅ ካርድ፣ ኢ-ፓስፖርት፣ ቪዛና የመሳሰሉትን ጥቅም ላይ ለማዋልም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ደንበኞች በአጭር የስልክ መልዕክት ልውውጥ ሥራቸው የደረሰበትን ደረጃ የሚያውቁበትን አሠራርና ሌሎችንም ዓይነት ዘመናዊ አሠራሮችን በመከተል የድርጅቱን አሠራር ማዘመን ተችሏል፡፡

 ይህ በእንዲህ እንዳለ ቴክኖሎጂዎችን በተግባር ከማዋል ጋር ተያይዘው የሚታዩ አንዳንድ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ‹‹ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በበቂ የማግኘት ችግር አለ፡፡ በኅትመት ቴክኖሎጂ የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር ቴክኖሎጂን በተመለከተ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር ተቀናጅቶ ያለመሥራት ችግር አለ፤›› የሚሉት አቶ ሚሊዮን የተዘረዘሩት ተግዳሮቶች ድርጅቱ በተገቢው መጠን አገልግሎቱ እንዳይዘመን ወደ ኋላ እየጎተቱት እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡  

ይህ የቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ያሉትን ቴክኖሎጂዎችም በተገቢ መጠን ጥቅም ላይ ከማዋል ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮች በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጀት ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ይልቁንም በተለያዩ የመንግሥት የልማት ድርጀቶች በስፋት የሚንፀባረቅ ነው፡፡

‹‹የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን የቴክኖሎጂ አቅም በመገንባት ምርታማነታቸውንና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን እናሳድጋለን፤›› በሚል መሪ ቃል ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የተዘጋጀው መድረክም ይህንኑ ዕውነታ የሚያጠናክር ነበር፡፡

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተሯ ወይዘሮ አስማ ረዲ የልማት ድርጅቶች የቴክኖሎጂ ክፍተትና ፍላጎት የሚያሳይ አጭር የዳሰሳ ጥናት አቅርበው ነበር፡፡ በጥናቱ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ ሸበሌ ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት፣ ግዮን ሆቴሎች፣ የፍል ውኃ አገልግሎት ድርጅት፣ ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅና ሌሎችም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተካተዋል፡፡

በዳሰሳ ጥናቱ ተቋማት የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተመለከተ ከፍተኛ ክፍተቶች እንዳሉባቸው ገልጸዋል፡፡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ከመረዳት አኳያም ችግሮች መኖራቸውን አስምረዋል፡፡ ድርጀቶቹ ባለባቸው ክፍተት ልክ ትኩረት ሰጥተውና በዕቅድ አካተው መፍትሔ ለመስጠት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አለመኖር፣ ወቅቱን የጠበቀና በቂ በጀት መመደብ ላይ ችግር መኖር፣ ቴክኖሎጂን ሊያላምድ፣ ሊፈጠርና ሊተገብር የሚችል የሰው ኃይል መዋቅር አለመኖር፣ ተቀናጅቶ የመሥራት፣ የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች አስተዳደር ክፍተቶች መኖር፣ አተገባበራቸውም የተንጓተተ መሆንና የመሳሰሉት በልማት ድርጅቶቹ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶች ናቸው፡፡

ወ/ሮ አስማ እንደሚሉት፣ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስተባባሪነትም ሆነ በድርጅቶች የእርስ በርስ ቅንጅት በጋራ ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎችን ለይቶ ማውጣትና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ መሥራት፣ ከተለያዩ የትምህርና ሥልጠና ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ተተኪ የሰው ኃይል ማፍራት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጁ የቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታዎች ትግበራን በዕቅድ አካቶ፣ በቂ የሰው ኃይልና በጀት መድቦ መሥራት ግድ ይላል፡፡        

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...