Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በሽተኛው ብዙ መድኃኒቱ ትንሽ!

ሰላም! ሰላም! አንዱ ነው አሉ፡፡ አንዱ ስላችሁ ደግሞ ይኼ ኮምፒውተር ላይ ያለው ማለቴ አይደለም፡፡ እሱንማ መሆን ብንችል በምን ዕድላችን? የኑሮ ሩጫችንን አቋርጠን ኑሮን ራሱ አንዱ እያደረግን አንዘፍንም ነበር? እሱም አውቆ ሰማይን አርቆ ሆነና ነገሩ ሰው ሕይወቱን አንዱ ማለት ቢያቅተው በአምሳሉ ሮቦት ፈጠረ፡፡ ይኼም እንደ አንዱ ከተቆጠረ ቁጠሩት፡፡ ግን አንዱ ይቆጠራል እንዴ? ለጨዋታው ድምቀት ነው የምጠይቃችሁ፡፡ በጣም ከማዳመቄ በፊት ግን ስለዛ አንዱ ስላልኳችሁ መከረኛ ልንገራችሁ፡፡ ዓይኔን ጋረደኝ ብሎ ሆስፒታል ይሄድላችኋል፡፡ ቅድመ ምርመራ ለቪዛ ብቻ በሆነበት ዘመን አዳሜ ጉድሽን ማን ዶክተር በነገረሽ፡፡ የምሬን ነው፡፡ እና ሲመረመር በደምህ ውስጥ ብዙ ስኳር ተገኝቷል አለው ዶክተሩ፡፡ ሰውዬው ቀወጠው፡፡ ዶክተሩ ስለስኳር በሽታ ያለው ግንዛቤ መስሎት እንዲያ ያደረገው ዘና አለ፡፡ ከዚያ አንዱ ምን ቢለው ጥሩ ነው? ‹‹ዶክተር ስንት ኪሎ ነው?›› አይለው መሰላችሁ?

እኔ ግን ከኪሎው ጥያቄ የተመቸኝ ታሪኩን ሲነግሩኝ አንዱ ብለው መጥራታቸው ነው፡፡ እና ቅድም ስላችሁ እንደነበረው ሕይወትን እንደ ኮምፒውተር ምትኃት ወደ ኋላ ክሊክ ማድረግ ቢቻል የስኳር እጥረት፣ የውኃ ድርቀት፣ የቤት እጥረትና የአየር ንብረት ምን ቅጡ ባለበት ተመለሰ ማለት እኮ ነው፡፡ ዋ ነገር ሁሉ በነበር ቀረ እኮ ጎበዝ፡፡ ይኼን ብዬ ያማረልኝ መስሎኝ ለባሻዬ ልጅ አጫወትኩት፡፡ በአንዴ አመድ መስሎ ዙሪያ ገባውን ካየ በኋላ፣ “እንዴት እንዲህ ትላለህ? ጤና፣ ስኳር፣ ውኃ፣ መሬት፣ አየር ባለበት ሲመለስ ባለበት የማይመለስ እኮ በዙ አለ፤” አለኝ፡፡ ‹‹ምን?›› ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? በሁለት አኃዝ የሚምዘገዘገው ኢኮኖሚያችን ጀምሮ፣ ሰርቆ የከበረን አነሳስቶ በመንገድ አድርጎ ባቡራችንን ተሳልሞ ብዙ ብዙ ጠራልኝ፡፡ በቃ አሁን የተናገርኩትን አንዱ በለው ብዬ ፈትለክ አልኳ። ይሞታል እንዴ!

ነገርን ነገር ያነሳዋል፡፡ ስኳር እንጂ ማር አላጣንም፡፡ ያውስ ለጨዋታ? ይብላኝ ለነ ለዛ ሙጥጥ፡፡ ነገረኛ ሆንኩ እንዴ? ለነገረኛም ነገረኛ ያዝለታል፡፡ አላዝልን ብሎ የተቸገርነው በበሽታችን ልክ መድኃኒት ብቻ ነው፡፡ “በሽተኛው በዛ መድኃኒት አነሰ” ያለው ዘፋኙ ወዶ መሰላችሁ? ‘ማንም የወደደውን ያገባና የዘፈነ የለም’ እንዳትሉኝና እንዳልስቅ፡፡ ማንጠግቦሽ ሰሞኑን በገባች በወጣች ቁጥር፣ “ዱባይና ታይላንድ ለሽርሽር ሄጄ ያየሁ. . .” እያለች ትሞዝቅላችኋለች፡፡ እኔ ደግሞ ‘መልዕክት ይኖረው ይሆን? ሽርሽር አማረኝ እያለችኝ ይሆን?’ እያልኩ መጨነቅ፡፡ አሥር ጊዜ የባንክ ደብተሬ ወጪና ገቢ ላይ ማፍጠጥ፡፡ ስቀንስ ስደምር፣ የሆቴል የምግብ የትራንስፖርት ሳባዛ ሳካፍል መዋል፡፡ ግን ለምንድነው ዘንድሮ ለሽርሽር መጓዝ ሲታሰብ ገና ድካም የሚተርፈን? የኢኮኖሚው ዕድገት ማሳያ ይሆን እንዴ? ቢጨንቀኝ እኮ ነው የምጠይቃችሁ።

ኋላ ታዲያ አስቤ አስቤ ሲደክመኝ የባሻዬን ልጅ፣ “ምን አባቴ ባደርግ ይሻለኛል?” ብዬ ማማከር። ምን ይለኛል፣ “ቆይ ትንሽ ታገስ ማንጠግቦሽ ብቻ አይደለችም ዱባይና ታይላንድ እያለች የምትዘፍነው። ሁሉም ነው፤” አለኝ፡፡ “እንዴት ሁሉም?” ስለው፣ ‹‹በቃ ነዳጅ ልናወጣ መሰለኝ፤›› ሲለኝ፣ “ታዲያ ምነው እንዲህ ያለውን የምሥራች ቀደም አድርገህ ሳትነግረኝ?” ስለው፣ “ምን ይታወቃል? ‘የህዳሴው ግድብ ሳይጠናቀቅ በቦናፓርቲዝም ልታጨመላልቁን ነው ወይ?’ የሚል መልስ ከመጣስ ብዬ ነዋ፤” አይለኝ መሰላችሁ። ጉድ እኮ ነው እናንተ! “ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” አለች አሉ (ማን ነች ግን እሷ?)፡፡ “እኔ እኮ ነዳጅ ያወጣን መስሎኝ ነው አዳሜ ለዱባይና ለታይላንድ ሽርሽር ሐዋሳ ላንጋኖን ገልብጦ የሚጫወት የመሰለኝ፡፡ ጭራሽ?” ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው?፣ “ተው እንጂ በማለም መብታችንማ አትምጣ፤” ብሎ ተቆጣኝ፡፡ ኧረ እንዴት ነው ነገሩ ይኼ ዓለም እያደር የህልም ዓለም ሆነ እኮ ጎበዝ!

ይልቅ ባለፈው ሰሞን ምን ሆነ መሰላችሁ? እስኪ ደግሞ ስለሥራና አሳሩ ላጫውታችሁ፡፡ ጥጋብና ልክ የለሽነት የዘንድሮ ልማት የሚያከናንበን ጉድ ሆኗል መቼም፡፡ እና ከደንበኞቼ ጋር ተደዋውዬ፣ ሚሊዮንን እንደ ሽልንግ ወደ አቃለለው ቤት ሸመጠጥኩ፡፡ ስደርስ ገዥና ሻጭ ‘ባልኮኒው’ ላይ ‘ጎልድ ሌብል’ ቺርስ እየተባባሉ ደረስኩ፡፡ ያሻሻጥኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ሰዓቴን ሳየው ገና ማንጠግቦሽ ቡና አላቀራረበችም፡፡ እንዳልቀደም ላቤ በጀርባዬ እየተንቆረቆረ ያገናኘኋቸው ደንበኞቼ በሞቀ ፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡ ቢሸጥ ኮንቴይነር ሙሉ ሳልባጅ ገዝቶ የሠፈሬን ነዋሪ በሚያንበሸብሽ ብርጭቆ ተራዬን ቀድተውልኝ ‘ቺርስ’ አሉኝ፡፡ ‘ግዴለም ይቅርብኝ’ ብል የ‘ቦነሴ’ ነገር አሳሰበኝ፡፡ ስለዚህ ባዶውን እየጮኸ አሲድ በሚተፋ አንጀቴ ላይ አሲድ ቸለስኩበት፡፡ መስማማታቸውን ባልጠራጠርም ለማረጋገጥ ስለፈለግኩ፣ “እንዴት ነው ታዲያ?” እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡

አንዴ ወልዳ እንድትመጣ ወደ አሜሪካ ስላሳፈሩዋት ሚስታቸው (ወደ አሜሪካ ሲሉ አሁን እዚህ ጉለሌ እዚህ መካኒሳ እንጂ አትላንቲክን አቋርጠው የሚደርሱበት አኅጉርና አገር የሚጠሩ ይመስላል እናንተ?) አንዴ ዓመት ሳያሽከረክሯት ስላልተመቸቻቸው አውቶሞቢልና ሊቀይሩት ስላሰቡት የቅርብ ጊዜ ሞዴል መኪና በሰፊው ይጫወታሉ፡፡ ከተጠመቀ ቆየት ካለ ውስኪያቸው እየማጉ ከቁብ አልቆጠሩኝም፡፡ ‘ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በአምስት ዓመት አንዴ ከቆጠረህ አይበቃህም?’ ይመስላል፡፡ ነገሩን ላሳጥረውና (እንኳን አንዛዝተውን እንዲሁም አልቻልነው) አንደኛው ‘ቼክ’ አውጥቶ ፈረመና ‘ኮሚሽኔን’ ከባንክ እንድወስድ ሰጠኝ፡፡ ‘በቼክ’ መቀበሌን አደራ ለማንም አልተናገርኩም፣ እናንተም ለማንም አታውሩ፡፡ ደግሞ በኋላ “አንበርብር በ‘ቼክ’ ነው የሚጫወተው፤” ብሎ አንዱ ማጅራቴን ቢያስመታኝ ማን አለኝ? ትቀልዳላችሁ እንዴ! ነው ወይስ ውዷ ማንጠግቦሽ ‘አንበርብር ቢሞትም ‘ቼኩ’ አይሞትም’ በሚለው ትፅናናለች ብላችሁ ታስባላችሁ? ኧረ እንዴት ተቀለደ!

ከፅንፍ ፅንፍ ስወስዳችሁ ደግሞ በቀደም ከአንድ ክልስ ወዳጄ ጋር ወደ ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ጉዳይ ገጥሞን መጓዝ ጀመርን፡፡ ዕድሜ ለልማታዊው መንግሥታችን እንጂ ዘንድሮ መንገድ ባይኖር እግርን አለማየት ነበር፡፡ ይኼን የምላችሁ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ቁሙ ሲለን እኔ የማየው እግር እግሩን ነበር፡፡ ጫማው የወታደር ጫማ ነው፡፡ የለበሰው መለዮ የትራፊክ ፖሊስ ነው፡፡ ተጠራጠርኩ፡፡ የወታደር ጫማ ደግሞ ይለያል እንዴ? የሚል ካለ የኢሕአዴግ ልጅ ቢሆን ነው በሚል ዝለሉት፡፡ ታግሎ ትግልን ያስረሳን አውራ ፓርቲያችን እስካለ ድረስ ገና መለዮም የማያውቅ ትውልድ ሊነሳ ይችላል፡፡ እና ምን እያልኳችሁ ነበር? አዎ አቀርቅሬ ጫማ ጫማውን ሳይ፣ “ይኼ ፈረንጅ የየት አገር ሰው ነው?” አለኝ ክልሱን ጓደኛዬን። “ኧረ እዚሁ ነኝ፡፡ ተወልጄ ያደኩት እዚሁ ነው፤” አለው ወዳጄ በጠራ አማርኛ፡፡ ‹‹ታዲያ መጀመርያም እንደ እሱ አትልም?›› ሲል እርስ በርስ ተያየን፡፡ ታዲያ ምን ይባላል?

‹‹እኔ የምላችሁ ውጭ አገር የሚልክ ሰው ታውቃላችሁ? ወይ እናንተ ትልካላችሁ?” አለን እንደ ዋዛ፡፡ የመንጃ ፈቃዱን መዳፉ ላይ እንደ ካርታ እየገለባበጠ ይጫወትበታል፡፡ እኔና ኢትዮ ፈረንጁ ወዳጄ ደንግጠን ተያየን፡፡ ሁኔታችንን ዓይቶ፣ “ሲያዩዋችሁ የአዲስ አበባ ልጆች ነው የምትመስሉት፡፡ ምን ታካብዳላችሁ? እኔ የትራፊክ ፖሊስ አይደለሁም፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ነኝ፡፡ ግን እዚህ መድበውኝ ነው፡፡ በሰሞኑን ብጥብጥ ሦስቴ ተፈንክቻለሁ፡፡ ይኼው፡፡ እዩት፡፡ እና እዚህ አገር መኖር መሮኛል፡፡ ለማንኛውም ስልኬን እንኩ፤” ብሎ ስልኩን ሰጠን፡፡ የመንጃ ፈቃዳችንን መለሰ፡፡ ሚሊሻው ሁለት መቶ ብር ፈለጠንና ሂዱ ብሎ መንገዱን ለቀቀ፡፡ አሁንም በስፖኪዩ ምን ታያለህ ብትሉኝ? ያን የወታደር ጫማ፡፡

እንሰነባበት። እንደ ፈጠጥኩ ጉዳያችንን ጨርሰን ተመለስን፡፡ እኔና ወዳጄ መነጋገር ያቆምነው ያ የወታደር ጫማ የለበሰ የትራፊክ ፖሊስ መሰል ሰውዬ ባህር ማዶ የሚያሻግር ሰው ፈልጉልኝ ካለ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ እንዴት አንቆለፍ? እኔን ያሳሰበኝ ሰፊው መንገድ ነው፡፡ “ይህ የአንድ ሰው የሁለት ሰው ድምፅ አይደለም እኮ?” ብዬ ለባሻዬ ስነግራቸው፣ “እሱስ ልክ ነህ፡፡ ግን ምን ማድረግ ትችላለህ? ይኼንን ለፈጣሪ መተው ነው፡፡ ይህች አገር እንደሆነች ድሮም በእሱ ጥበብ እንጂ በማን ቀንድና ቀለም ተመርታ ታውቃለች?” ብለው አሸሞሩ፡፡ ባሻዬ የገባኝ ገብቷቸዋል፡፡ ያሳሰበኝ አሳስቧቸዋል፡፡ ምንም ቢሆን ትልቅ ሰው ናቸዋ፡፡

ወዲያው ከእሳቸው ጋር ስለያይ ደግሞ ምሁሩ ልጃቸው ደወለና አንድ አንድ እንበል አለኝ፡፡ ዛሬ አላሰኘኝም፡፡ ለሁሉም ቀን አለው፡፡ አይደለም እንዴ? አዎ ቢያንስ ይኼን እንኳን በልቦናችን ብንደጋግመው እኮ ከስንት ዕጦትና ኪሳራ እንተርፍ ነበር፡፡ እና ቀጥ ብዬ ወደ ቤቴ ሄድኩ፡፡ ተጫጭኖኛል፡፡ የሚሊዮኖች የብሶትና የመንገሽገሽ ስሜት በዛ የወታደር ጫማ ለባሽ ሰውዬ ጥያቄ ውስጥ ተመላልሶ ይጫወታል፡፡ ማንጠግቦሽ ራት ለማቅረብ ጉድ ጉድ ትላለች፡፡ ማርም አልስ ብዬ ያለ ልማዴ አልጋዬ ላይ ወጣሁ፡፡ “አልጋ ሲወጡ ነገር ያገኙ፣ ካልጋ ሲነሱ ነገር ይረሱ” ብሎ ተረት የገባኝ እርሜን ያለሞቅታ አልጋ ላይ ስወጣ ነው፡፡ ለካ ወዶ አይደለም የቢራ ማስታወቂያ የበዛው፡፡ እና እኔ የምለው እንዲያው ነገረ ሥራችን ወዴት እያመራ ነው? ኧረ እንጠያየቅ ግዴለም፡፡ በሽተኛው ብዙ መድኃኒቱ ትንሽ ሆነ እኮ? መልካም ሰንበት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት