Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበስህተት ላይ ስህተት

በስህተት ላይ ስህተት

ቀን:

  • ለፊፋ ውሳኔ ተጠያቂው ማነው?

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ የሚደረገው ፕሬዚዳንታዊና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ሲካሄድ፣ በተደጋጋሚ እንደሚስተዋለው ከተለያዩ አካላት በሚነሱ ተቃውሞችና ውዝግቦች ታጅቦ ለመሆኑ ከሰሞኑ የምርጫ ቅስቀሳ በመነሳት መናገር ይቻላል፡፡

ይህ እየሆነ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ)፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን ሊከውነው ቀነ ቀጠሮ ይዞለት የሰነበተው የምርጫ ሥነ ሥርዓት፣ ‹‹የዓለም አቀፉን ሕገ ደንብ የምርጫ አካሄድ የተከተለ አይደለም››፣ በሚል ቀነ ገደቡ እንዲራዘም ማዘዙ ታውቋል፡፡

ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፌዴሬሽኑ የደረሰው የፊፋ ደብዳቤ እንደሚለው ከሆነ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫው ቅድመ ሁኔታ ከመጠናቀቁ ከ30 ቀን በፊት በአስመራጭነት የሚሰየመውን ቦርድ ማንነት ለፊፋ ማሳወቅ እንደነበረበት፣ አሁን ባለው ሒደት ግን አባል ፌዴሬሽኑ ባስቀመጠው ጊዜ ገደብ ምርጫውን ማድረግ እንደማይችል ይገልጻል፡፡ ፌዴሬሽኑም ውሳኔውን በፀጋ ተቀብሎ ምርጫው መራዘሙን አሳውቋል፡፡

የፊፋ ዋና ጸሐፊ ፋትማ ሳሞራ፣ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ለማካሄድ ያሰበው ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ፣ ሒደቱ የተሳሳተና የፊፋን የመልካም አስተዳደር መርሆዎች እንዲሁም ያለማዳላት አካሄዱን ያላከበረ የምርጫ ሒደት ነው፡፡ ምክንያቱም የምርጫው ሒደት የሕግ ማረጋገጫ አካሄድ የተከተለ አይደለም፡፡

በተጨማሪም ምርጫውን ለሚከታተለው የፊፋ ምርጫ ኮሚቴ በቂ ጊዜ ያልሰጠ ሲሆን፣ ይህም በበቂ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ ለመስጠት ካለማስቻሉም በላይ የዕጩዎቹን ተገቢነት ለመወሰን እንደማያስችለውም ያስረዳሉ፡፡

ከዚህም ባሻገር በምርጫው ሒደት ላይ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ የሚገድብ ተገቢው ጊዜ ያልተሰጠው ሲሆን፣ እነዚህ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች  በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር ዕድላቸውን በተሳሳተ አካሄድ እንዲከለከሉ አድርጓል ሲል የምርጫውን ሒደት ይኮንናል፡፡

ደብዳቤው አስተያየቱን ሲያጠቃልልም ፌዴሬሽኑ ለጥቅምት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ለምርጫ የተያዘውን የጊዜ ሰሌዳ ለሌላ ጊዜ ማራዘም እንደሚገባው በጥብቅ ማሳሰቡ ተመልክቷል፡፡ በማያያዝም ለፌዴሬሽኑ ተገቢውን የዴሞክራሲያዊ ስልቶችን በተለይም የምርጫ ሕግና የአስመራጭ ኮሚቴ ከፊፋ ድጋፍ የታከለበት እገዛ እንደሚሰጥ ጭምር አስታውቋል፡፡

ይሁንና ፊፋም ሆነ ካፍ (የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን) ለሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞችና መሰል ጉዳዮች ጆሮ የሚሰጠው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ በአራት ዓመት የአገልግሎት ቆይታው፣ እነዚህን ለመሰሉና ለሌሎም አስገዳጅ ዓለም አቀፍ ደንብና መመርያዎች እንግዳ መሆን የተቋሙን አመራሮች ‹‹ንዝህላልነት›› እንደሚያመላክት ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡

የአመራሩ ንዝህላልነት በዚህ እንደማያበቃ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ከአንድ ዓመት በፊት ካፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለአህጉራዊው የሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮና ለሚያደርገው ምድብ ድልድል ይረዳው ዘንድ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከላካቸው ተደጋጋሚ የኢሜይል መልክዕቶች መልስ ማግኘት ባለመቻሉ ብሔራዊ ቡድኑ ከምድቡ ድልድል ውጭ እንዲሆን መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡

ከነዚህ አስተያየት ሰጪዎች መካከል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ላለፉት አምስት ዓመታት ማገልገላቸውን የሚገልጹት የሕግ ባለሙያው አቶ ኃይሉ ሞላ ይጠቀሳሉ፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በሚከተለው ጊዜውን ባልተከተለ ዘልማዳዊ አሠራር ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት መልቀቃቸውን የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ ‹‹በደንብና መመርያ እመራለሁ የምትል ከሆነ ወደ ፌዴሬሽኑ መምጣት አይጠበቅብህም፡፡ በደንብና መመርያ እሠራለሁ ካልክ ተግባብተህ መሥራት አትችልም፡፡ እኔም የገጠመኝ ይኼው ነው፤›› በማለት ከኃላፊነታቸው የለቀቁበትን ምክንያት ያስረዳሉ፡፡

በፌዴሬሽኑ ከተወሰኑት አመራሮች ጋር መግባባት እንዳይችሉ ምክንያት ያሉት የሕግ ባለሙያው፣ ፊፋ እንደገለጸው ተቋሙ ከሚተዳደርባቸው ደንብና መመርያዎች ጀምሮ በየደረጃው የተቀመጡ ሒደቶችን ተረድቶ የመተግበር ችግር በስፋት እንደሚስተዋልበት ያስረዳሉ፡፡

እነዚህን የመሰሉ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸውን አካሄዶች ቀርቶ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ከተለያዩ የሕግ አግባቦች ተነስቶ ውሳኔ ባስተላለፈባቸው የሕግ ጉዳዮች ላይ በጣልቃ ገብነት ‹‹ማደፍረስ›› ካልሆነ፣ አመራሩ በተሰጣቸው ኃላፊነት ልክ ለእግር ኳስ የሚያበረክተው አንዳች ነገር እንደሌለ ጭምር ነው የሚናገሩት፡፡

የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ውሳኔና አስፈላጊነት ትርጉም ከሌለው ‹‹ለምን አይፈርስም›› በማለት ብዙ ጊዜ ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ ፌዴሬሽኑ ዕድሜ ከመቁጠር ባለፈው እግር ኳሱ በተለይ በአሁኑ ወቅት ከደረሰበት ደረጃ አኳያ የሚመጥን አደረጃጀት ቀርቶ በተወሰነ መልኩ ሊያስኬድ የሚችል ለዘመናዊነት ቅርብ የሆነ የሰነድ አያያዝ ሥርዓት እንኳ የለውም፡፡

በዘመናዊው ዓለም የአንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ውሳኔ፣ መሻርም ካለበት ሊሻር የሚችለው በዓለም አቀፍ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት (ካስ) መሆኑን የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ ይህ ዓይነቱን የአሠራር ሥርዓት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተግበር ቀርቶ ማሰብ ከቶውንም እንደማይቻል ያስረዳሉ፡፡

በአዲስ አበባ ሒልተን ሊደረግ የታቀደው የምርጫ ሒደት መራዘም እንደተጠበቀ፣ ‹‹የአገሪቱ እግር ኳስ በፊፋ የአገሮች ደረጃ ምን ያህል እንዳሽቀለቆለ የአደባባይ
ምስጢር በሆነበት በዚህ ወቅት እንኳን፣ አሁን ያለው አመራር ለሁለተኛ የአገልግሎት ጊዜ ለመመረጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ውክልና አግኝተዋል፤›› የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ በእሳቸው እምነት እየሆነ ያለው ግራ የሚያጋባ ነው፡፡

እንደ አቶ ኃይሉ፣ በአገሪቱ ከሚገኙ የስፖርት ተቋማት መካከል ከትችትና ቅሬታም በላይ ለመስማት የሚዘገንኑ የ‹‹ስድብ ናዳ›› ከሚወርድባቸው እግር ኳስ ፌዴሬሽን አንዱ ነው፡፡ ‹‹አንዳንድ ጊዜ ስለዚሁ ጉዳይ ሳስብ በቦታው በኃላፊነት የተቀመጡ ሰዎች ሆደ ሰፊነት ይገርመኛል፡፡ ምክንያቱም በፌዴሬሽኑ እስካለሁበት ጊዜ ድረስ በመልካም ፈቃደኝነት ነፃ ግልጋሎት ከመስጠት ባለፈው የማገኘው አንዳች ነገር አልነበረም፡፡ በእርግጥ ይኼ በእኔ በኩል ያለውን እንጂ በሌሎች በኩል ያለውን የሚያውቁት እነሱና እነሱ ብቻ ናቸው፤›› በማለት ጭምር የግርግሩን መንስዔና ምክንያት ምንነት በውል ለመረዳት እንደሚያዳግት ይገልጻሉ፡፡

ምርጫ ወይስ ውክልና?

በጥቅምት መጨረሻ ሊደረግ ጊዜ ቀጠሮ ተቆርጦለት የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ ሒደት፣ በፊፋ ውሳኔ መሠረት ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ ኃይሉ ሞላን ጨምሮ በርካታ የዘርፉ ባለሙያተኞች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ዕጩ ሆነው በቀረቡት ሰዎችና የዕጩ አቀራረቡን ሒደት አስመልክቶ ቅሬታ አላቸው፡፡

የሕግ ሙያተኛውን ጨምሮ እንደ ብዙዎቹ እምነት፣ ምርጫው፣ ምርጫ ከተባለ ትክክለኛ የምርጫ መስፈርት የሚያሟላው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫው ከዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ውክልና ካገኙ አሥራ አንድ ዕጩ ተወዳዳሪዎች አሥሩ ይመረጣሉ፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ይህን ዓይነቱን የምርጫ አካሄድ ምርጫ ልንለው የሚገባው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ቅሬታቸውን በግልጽ ያስቀመጡት አቶ ኃይሉ፣ ‹‹የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ምርጫ በእኔ ምርጫ ሳይሆን ውክልና ነው፡፡ ምክንያቱም በዓለም አቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ገደብ ባልተቀመጠለት የዕጩ አቀራረብ ሒደት፣ ክልሎች አንድ ለፕሬዚዳንት፣ አንድ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ እንዲያቀርቡ መደረጉ ከሕግ አግባብም ወንጀል ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ምርጫ ሕገወጥ እንዲሆን ያደርገዋል፤›› ይላሉ፡፡

እንደ ሕግ ባለሙያው፣ በ2006 ዓ.ም. በወጣው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ በአንቀፅ 31 እንደተደነገገው ከሆነ፣ ‹‹ክልሎች ለፕሬዚዳንትም ሆነ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ የሚያቀርቡት ዕጩ ዕድሜው ከ21 ዓመት በላይ መሆን ይኖርበታል፤›› ከዚህ ውጪ ግን አንድ ወይም ሁለት የሚል ድንጋጌ የለውም፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየተነገረ ያለው አንድ ክልል ዕጩ ተወዳዳሪ ማቅረብ የሚችለው፣ አንድ ለፕሬዚዳንትና አንድ ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሚል እንደሆነ የሚገልጹት የሕግ ባለሙያው፣ ሒደቱ ትክክል አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በወንጀል ጭምር ያስጠይቃል ባይ ናቸው፡፡

ክልሎች የሚወክሉዋቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎችን አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ፣ መመርያውን ሲያስተላልፍ መነሻቸው ምንድነው? ለሚለው የሕግ ባለሙያው፣ ‹‹የትርጉም ስህተት ወይም ሆን ተብሎ ሌሎችን ለማደናገር ሊሆን እንደሚል እገምታለሁ፡፡ እንደሚመስለኝ የድንጋጌው ትርጉም ቀጥታ የተወሰደው በፌዴሬሽኑ በአንቀፅ 31 ንዑስ አንቀፅ 7 የተጠቀሰው የአንድ ፌዴሬሽን አካል ሊግ ወይም ክለብ በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውስጥ ከአንድ በላይ ተወካይ ወይም ተመረጭ ሊኖር አይችልም፤›› ከሚለው የተወሰደ ባይ ናቸው፡፡

የሕግ ትርጉም ‹‹ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እግር ኳሱ አሁን ባለው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እውነታው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መነጋገርንና መወያየትን እንዲሁም ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን የሚፈልግ መሆኑ ነው፡፡ ያለው ነገር ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ውጤቱ ምስክር ነው፤›› የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ ‹‹ፌዴሬሽኑ አለኝ በሚለው መተዳደሪያ ደንብ ለምርጫ የሚቀርቡ ዕጩዎችን ጨምሮ ግልፀኝነትንና ተጠያቂነትን የተላበሰ አይደለም፡፡ በዚህ ዓመት ለሚደረገው ምርጫ ፕሬዚዳንታዊና ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ክልሎች ማቅረብ የሚችሉት ወይም የቻሉት አንድ አንድ ሰው ነው፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በነበረው ምርጫ ወደ ነበረው የዕጩ አቀራረብ ሒደት ስንመለስ ደግሞ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ የቀረቡት ሁለት ናቸው፡፡ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻውና አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለሥራ አስፈጻሚ ከቀረቡት ሁለት ዕጩ ተወዳዳሪዎች አንደኛው ምርጫ በተባለው ‹‹የውሸት ምርጫ›› እንዲወድቅ ሲደረግ፣ አሁን በአመራርነት የሚገኙት አቶ አበበ ገላጋይ ቀርበው ነበር፣ ብለው የነበረውን ምርጫ ሒደት በማሳያነት ይጠቀሳሉ፡፡ እርስ በራሱ የሚጣረሰው የአሠራር ሥርዓት ለምን? ሲሉ የሕግ ባለሙያው ፌዴሬሽኑ በምን ዓይነት በዘልማዳዊ አሠራር ውስጥ እንደሚገኝ ጭምር ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል ጥቅምት 30 ቀን በአዲስ አበባ ሒልተን ሊደረግ የታቀደው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በተያዘለት ቀንና ሰዓት የሚካሄድ ሲሆን፣ የምርጫውን ሒደት በተመለከተ ጉባዔው በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት ይወሰናል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...