Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያና ጂቡቲ መካከል የየብስ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲጀመር ተፈቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያና በጂቡቲ መካከል በአየር ትራንስፖርት ብቻ ተወስኖ የቆየው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በየብስ የሕዝብ ማመላለሻ የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲጠናከር፣ ሁለቱ መንግሥታት የተስማሙበትን ሰነድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፀደቀው፡፡

ምክር ቤቱ ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባው ሁለቱ መንግሥታት በየብስ የመንገደኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ለመተግበር ያደረጉትን ስምምነት በአዋጅ አፅድቆታል፡፡

በሁለቱ አገሮች ስምምነት መሠረት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቱ የሚጀመረው የሁለቱም አገሮች የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች ስምምነቱን ካፀደቁት በኋላ ነው፡፡ በመሆኑም ስምምነቱ በአሁኑ ወቅት በሁለቱም አገሮች ሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች አዋጅ ሆኖ በመፅደቁ፣ በሁለቱም አገሮች የሚገኙ የሕዝብ ማመላለሻ የንግድ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ከአንዱ ወደ አንዱ አገልግሎት መስጠት ያስችላቸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሁለቱን አገሮች የሚያገናኘው አውራ ጎዳና ግንባታ ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች የትራንስፖርት አገልገሎት መስጠት አያስችላቸውም፡፡ የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅም የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች አገልግሎት ለማስጀመር የሁለቱ አገሮች የትራንስፖርት ጉዳይ ተቋማት ይህንን አዋጅ መሠረት በማድረግ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ስምምነት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የየብስ ሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስጀመር ሙሉ ዝግጅቶችን አጠናቆ የሚገኘው፣ ሁለቱ አገሮች በጋራ የገነቡት የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ የባቡር ትራንስፖርት ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የባቡር መስመር በሁለቱ አገሮች በጋራ የተገነባ ሲሆን፣ የትራንስፖርት አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር በዚህ ስምምነት መመሥረቱን ሪፖርተር ከኢትዮጵያ ምድር የባቡር ኮርፖሬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በዚህ ተቋም ላይ ኢትዮጵያ 75 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ የያዘች ሲሆን፣ ቀሪው 25 በመቶ በጂቡቲ መንግሥት ባለቤትነት ተይዟል፡፡ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ኢትዮጵያን ከጅቡቲ ወደብ በማገናኘት የገቢና የወጪ ንግድ ዕቃዎች በብዛትና በፍጥነት በማጓጓዝ ቀድሞ የነበረውን ከፍተኛ የሎጂስቲክስ ወጪ እንደሚቆጥብ ኮርፖሬሽኑ ያስረዳል፡፡

የጭነት ማመለለሻ ባቡሩ በአንድ ጉዞ ብቻ ዘጠና ከባድ ተሽከርካሪዎች ከጂቡቲ የሚያነሱትን ገቢ ንብረቶች በአሥር ሰዓት ውስጥ ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ ማድረስ ያስችለዋል ተብሏል፡፡ የሕዝብ ማመላለሻ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትም የኢትዮጵያ አስመጪዎችና ትራንዚተሮች ቀደም ሲል ወደ ጂቡቲ ለመግባት ለአየር ትራንስፖርት የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪ ሊቀንስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

የጂቡቲ መንግሥት ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው የወደብ አገልግሎት የሚገኘው ገቢ 70 በመቶ የሚሆነውን የጂቡቲ ዓመታዊ በጀት እንደሚሸፍን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህም በፈረንሣይ መንግሥት የበጀት ድጎማ ላይ ጥገኛ ሆና ለበርካታ ዓመታት የቆየችውን ጂቡቲ ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት ማላቀቅ ችሏል፡፡ የጂቡቲ መንግሥት ከወደብ አገልግሎቱ በተጨማሪ፣ በቀይ ባህር ዳርቻዎች የቱሪዝም መስህቦችንና መዝናኛዎችን በመክፈት ኢትዮጵያውያን በዝቅተኛ ወጪ ወደ ጅቡቲ በመጓዝ በአገራቸው ያጡትን የባህር መዝናኛዎች እንዲያገኙ፣ በዚህም አዲስ የቱሪዝም ኢኮኖሚ ዘርፍ ለኢትዮጵያውያን በማስተዋወቅ የኢኮኖሚ መሠረቱን ለማስፋት ወጥኗል፡፡ ዕቅዱን ዕውን ለማድረግም በኢትዮጵያዊው ባለሀብት አቶ ታዲዮስ በለጠ የተመሠረተው ኩሪፍቱ ሆቴል ኤንድ ስፓ ጂቡቲ የቀይ ባህር ዳርቻዎች አንዱን ቦታ እንዲያገኝ ብድር እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ ባለሀብቱም ግንባታውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም የየብስ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር፣ ጂቡቲ ለኢትዮጵያውያን የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን የተያዘውን ዕቅድ እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡    

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች