Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሰባት ፋብሪካዎችን ዘጋ

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ሰባት ፋብሪካዎችን ዘጋ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ እየተባባሰ ለመጣው የኢንዱስትሪ ብክለት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው የተባሉ ስድስት የቆዳ ፋብሪዎችና አንድ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ እንዲታገዱ በተላለፈባቸው ውሳኔ መሠረት ባለፈው ሳምንት ተዘጉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እነዚህን ፋብሪካዎች ለማገድ የወሰነው ከመጋቢት 2009 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ጉዳዩን በጥሞና ማየት ስለሚያስፈልግ ዕግዱ እንዲቆይ በማዘዛቸው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በቀጥታ ተጠሪነቱ ለከንቲባው እንደመሆኑ፣ ላለፉት ወራት ከታየ በኋላ በመጨረሻ የከተማው ፖሊስና ደንብ ማስከበር የተካተቱበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከሰኞ ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲታሸጉ ተደርጓል፡፡

- Advertisement -

የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዱኛ ወንድሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቆዳ ፋብሪካዎቹ የፍሳሽ ማጣሪያ እንዲገነቡ ከአምስት ዓመት በላይ ጊዜ ቢሰጣቸውም ማጣሪያ ጣቢያውን መገንባት አልቻሉም፡፡

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እንዲታሸጉ የተደረጉት የቆዳ ፋብሪካዎች ድሬ፣ አዋሽ፣ ዋልያ፣ ባቱ፣ ኒውዊንግና አዲስ አበባ ቆዳ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ ከቆዳ ፋብሪካዎቹ ቀደም ብሎ የታሸገው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ደግሞ ይርጋለም አደይ አበባ ነው፡፡

አቶ አዱኛ እንደገለጹት፣ ከፋብሪካዎቹ የሚወጣው ፍሳሽ ለሰው ልጆችና ለእንስሳት ጤና አደገኛ ከመሆኑ በተጨማሪ እስከ አዋሽ ወንዝ ድረስ ያለው ተፋሰስ እየተበከለ ነው፡፡

ፋብሪካዎቹ በቀጥታ ወደ ወንዝ ከሚለቁት ፍሳሽ ውስጥ ከሦስት መቶ በላይ አደገኛ ኬሚካሎች እንደሚገኙ፣ በተለይ ክሮም የተሰኘው ኬሚካል ለካንሰር ሕመም ከመዳረጉም በላይ ለሰው ልጆች የተዛባ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አቶ አዱኛ ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ፀጉር የሌለው ጥጃ መወለዱን በመጥቀስ የኬሚካሎቹን አደገኛነት አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 35/2004 ከተማውን ከፍሳሽና ከደረቅ ቆሻሻ ብክለት የመከላከል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

ፋብሪካዎቹ ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ ለዓመታት ጊዜ የተሰጣቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ጭምር እንደተሰጣቸው የገለጹት አቶ አዱኛ፣ ማስተካከል ባለመቻላቸው ሳቢያ ዕርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

‹‹ፋብሪካዎቹ የፍሳሽ ማጣሪያ ገንብተው በንፁህ የማምረት ዘዴ ከተጠቀሙ በድጋሚ ሊከፈቱ ይችላሉ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በጤናና በአካባቢ ላይ በሚደርሰው ጉዳት መደራደር አይቻልም፤›› ሲሉ አቶ አዱኛ ታሽገው እንደሚቆዩ ተናግረዋል፡፡

የቆዳ ፋብሪካ ከተዘጋባቸው ኩባንያዎች መካከል ድሬ ኢንዱስትሪ አንዱ ነው፡፡ የድሬ ኢንዱስትሪ ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሀጂ በዳዳ ጫሊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የእሳቸው ፋብሪካ ማጣሪያ ጣቢያ አለው፡፡ ‹‹ነገር ግን አስተካክሉ የምንባለውን ለማስተካከል ዝግጁ ነን፤›› ብለዋል፡፡ ይሁንና አቶ አዱኛ ይህንን አይቀበሉትም፡፡ ‹‹ድሬ ቆዳ ፋብሪካ ምንም ዓይነት ማጣሪያ የለውም፡፡ በቀጥታ ወደ ወንዝ የሚለቅ ቢኖር ድሬ ቆዳ ፋብሪካ ነው፤›› ብለዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...