Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለአሜሪካ የኮንግረስ አባላት የቀረበውን የሰብዓዊ መብት የውሳኔ ሐሳብ መንግሥት አጣጣለው

ለአሜሪካ የኮንግረስ አባላት የቀረበውን የሰብዓዊ መብት የውሳኔ ሐሳብ መንግሥት አጣጣለው

ቀን:

የአሜሪካ ኮንግረንስ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝን አስመልክቶ በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ ድምፅ እንዲሰጥበት፣ በአሜሪካ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ያቀረቡትን ጥያቄ መንግሥት አጣጣለው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ረቡዕ ጥቅምት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ ኤችአር 128 በመባል የሚታወቀው የውሳኔ ሐሳብ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ የለውም፡፡

የአሜሪካ ኮንግረንስ የሚያሳልፋቸው አራት ያህል የውሳኔ ሐሳቦች ቢኖሩም፣ ሁለቱ በተለይም ‹‹ቢል›› እና ‹‹ሪዞሊዩሽን›› የሚባሉትን የውሳኔ ሐሳቦች የትኛውም የኮንግረንስ አባልና የትኛውም የውትወታ ቡድን ሊያቀርባቸው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡

በዚህ የውሳኔ ሐሳብ መሠረት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ማዕቀብ ሊጣል እንደሚችል የሚያነሱ አካላት እንዳሉ አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሜሪካና ኢትዮጵያ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ያላቸው አገሮች በመሆናቸው የሚመጣ ለውጥ እንደማይኖር ገልጸዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች በፀረ ሽብር፣ በሰላም ማስከበር፣ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ላይ በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በቅርብ ጊዜ ወደ አሜሪካ አቅንተው በነበረበት ጊዜ፣ እሳቸውም አብረው በመሄድ የኮንግረንስ አባላትን አግኝተው ይህንን እንዳረጋገጡላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹አዲሱ የውሳኔ ሐሳብ በሒደት ላይ ነበር፡፡ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ እንደነበሩ የውሳኔ ሐሳቦች ብዙም የሚያመጣው ተፅዕኖ የለም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የውሳኔ ሐሳቡ ወጣ አልወጣ ትርጉም እንደሌለው ጠቁመው ምክንያታቸውን ሲያብራሩም፣ የውሳኔ ሐሳቡ መሬት ላይ ያሉ ጉዳዮችን የሚያሳይ ባለመሆኑና ኢትዮጵያና አሜሪካ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ በጋራ ለመሥራት ከዚህ ቀደም ስምምነት አላቸው ብለዋል፡፡

ደብዳቤ የጻፉ የመብት ተሟጋቾች በአሜሪካ የአማራ ማኅበር፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሴንተር ፎር ጀስቲስ ኤንድ አካውንቲቢሊቲ፣ ኢትዮጵያ ሒውማን ራይትስ ፕሮጀክት፣ ፎረም ሐውስ፣ ሒውማን ራይትስ ዎች፣ ኦሮሞ አድቮኬሲ አሊያንስ፣ ሶሊዳተሪ ሙቭመንት ፎር ኤ ኒው ኢትዮጵያና ቶርቸር ኤንድ አቦሊሽን ሰርቫይቨርስ ስፖርት ኮኦሊሽን የሚባሉ ተቋማት መሆናቸውን፣ ኮንግረንሱም ለውይይት ኦክቶበር 2 ቀን 2017 የያዘውን ቀነ ቀጠሮ ምክንያቱ ባልታወቀ ጉዳይ መሰረዙን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ቃል አቀባዩ ኮንግረሱ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ውይይት ለማድረግ የያዘውን ቀነ ቀጠሮ የሰረዘበት ምክንያት በኢትዮጵያ መንግሥት ግፊት ነው መባሉን በተመለከተ ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቦላቸው፣ ‹‹ፈጽሞ ውሸት ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ኤችአር 128 በአንድ የኮንግረስ አባል የቀረበ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የ71 የኮንግረንሱን አባላት ድጋፍ ማግኘት እንደቻለ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በሌላ ዜና የኖርዌይ አልጋ ወራሽ ልዑል ሃብን ማግነስና ባለቤታቸው ልዕልት መቲ ማሪት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡ አቶ መለስ እንዳሉት የኖርዌይ ልዑልና ባለቤታቸው ከሰኞ ጥቅምት 27 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ የሥራ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡

የንጉሣዊያኑ ቤተሰቦች ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡

እንግዶቹ ከአዲስ አበባ ውጪ የመስክ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የጠቆሙት አቶ መለስ፣ ‹‹ሁለቱ አገሮች በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በጋራ ይሠራሉ፤›› ብለዋል፡፡

ልዑሉና ልዕልቲቱ በዓመት አንዴ ብቻ በሌላ ዓለም ጉብኝት እንደሚያደርጉ የተጠቆመ ሲሆን፣ ይህ ጉብኝት በአፍሪካ ሁለተኛው እንደሆነ ታውቋል፡፡ የኖርዌይና የኢትዮጵያ መንግሥታት የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመረው ከዛሬ 75 ዓመታት በፊት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...