Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊጠቢቡ ሰሎሞን ዴሬሳ  (1930 - 2010)

ጠቢቡ ሰሎሞን ዴሬሳ  (1930 – 2010)

ቀን:

‹‹በአንድ በኩል ስታስበው ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ እኔ የትግራይ ሰው ነኝ፣ እኔ አማራ ነኝ ብሎ አፍ ሞልቶ መናገሩም አለማወቅ ይመስለኛል፡፡ በሴት አያቶቻችን በራፍ ላይ ማን እንዳለፈ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው? የእኔን ጥሩ ኦሮሞነት እግዚአብሔርና የሴት አያቶቼ ናቸው የሚያውቁት፡፡ የሁሉንም እንዲሁ፡፡ ጦር ባለፈ ቁጥር በመዋለድ፣ በንግድ በመገናኘት፣ ተቸግሮ ከአገር ወጥቶ ሌላ ቦታ በመኖር ይቀላቀላል፡፡››

ዕውቁ ገጣሚና ጸሐፊ፣ ጋዜጠኛና የፍልስፍና መምህር ሰለሞን ዴሬሳ በ1991 ዓ.ም. ከሪፖርተር መጽሔት ጋር በነበረው ቆይታ የኢትዮጵያውያን ኅብረ ብሔራዊነት፣ የኢትዮጵያን ሞዛይክነት ያመሰጠረበት አገላለጹ ነበር፡፡ በሥነ ጽሑፍና በሥነ ግጥም፣ በሥነ ጥበብና ቴክኖሎጂ ክህነቱ ተጠባቢነቱ ሁነኛ ሥፍራ ነበረው፡፡ ሰሎሞን ደሬሳ፡፡ ለአምስት አሠርታት በነበረው ሥነ ጥበባዊ፣ ሥነ ጽሑፋዊና ሥነ ጋዜጣዊ አበርክቶው ትይዩ በተካነበት  የምሥራቅ (ኦሬንታል) ፍልስፍና እና በጠሊቅ ንባብ ከቀሰመው የምዕራባውያን ፍልስፍና ጋር አስተሳስሮ አሜሪካ ሚኔሶታ ዩኒቨርሲቲ በአይሁድ፣ በክርስትና፣ በእስልምና፣ በቡድሂዝምና በሌሎች ታላላቅ ሃይማኖቶች ላይ የሃይማኖት ንፅፅር (ኮምፓራቲቭ ሪሊጂን) ትምህርት ፕሮፌሰር ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ ሆኖ ሳለ ነበር፣ በቀደመው ራዲዮ አዲስ አበባ (ራዲዮ ኢትዮጵያ) የእንግሊዝኛ ዜና አንባቢ ሆኖ የተቀጠረው፡፡

- Advertisement -

ጋዜጠኝነቱን ያጠናከረው በራዲዮ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮና የቴሌቪዥን ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅነት ድረስም ደርሷል፡፡ በ1950ዎቹ አጋማሽ ይታተም በነበረው ‹‹አዲስ ሪፖርተር›› የእንግሊዝኛ መጽሔትም አዘጋጅ ሆኖም ሠርቷል፡፡

ቅድመ አብዮት በባህር ማዶ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ጥልቅ አሳቢነት›› (ክሪቲካል ቲንኪንግ) እና የፈጠራ ጽሑፍ (ክሬቲቭ ራይቲንግ) ያስተምር የነበረው ሰሎሞን፣ በ1962 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የመጀመርያውን የግጥም መድበል ‹‹ልጅነት›› አሳትሟል፡፡ የአገጣጠም ሥልቱ ለየት ያለ በመሆኑ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ ከልጅነት ሌላ ሦስት ጅምር ተውኔቶች፣ የአጫጭር ልቦለድ ስብስቦችን ግጥሞቹም ነበሩት፡፡ ‹‹ዘበት እልፊቱ ወለሎታት›› የተሰኘው ሁለተኛው የግጥም መድበሉንም በ1992 ዓ.ም. አሳትሟል፡፡ ሰሎሞን በእንግሊዝኛና በፈረንሣይኛ የደረሳቸው ግጥሞቹ በስመ ጥሩ ‹‹አፍሪካን አርት›› መጽሔት ጨምሮ በተለያዩ ኅትመቶች ታትመውለታል፡፡

አቶ ሰሎሞን ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረበት ዘመን በ1930 ዓ.ም. በቀድሞ አጠራር በወለጋ ጠቅላይ ግዛት ከጊምቢ ከተማ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጩታ መንደር የተወለደው ከእናቱ ወ/ሮ የሺመቤት ዴሬሳ አመንቴና ከአባቱ አቶ ዳንኪ ላንኪ ነበር፡፡ በአራት ዓመቱ የትውልድ ቀዬውን ለቆ ዕድገቱን በአዲስ አበባ ሲያደርግ፣ በተፈሪ መኰንንና በጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤቶች ትምህርቱን አጠናቋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የጀመረውን ከፍተኛ ትምህርት ቢያቋርጥም፣ አሜሪካ ሄዶ የባችለር ዲግሪውን በኦሬንታል ፊሎሶፊና በአሜሪካ ሥነ ጽሑፍ አግኝቷል፡፡

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ አማርኛ ያስተምር የነበረው ሰሎሞን፣ ዎልፍ ሌሰላው ‹‹ኢትዮጵያን ዲክሽነሪ›› ብሎ ያሳተመውን መዝገበ ቃላት ካዘጋጁት 11 ኢትዮጵያውያን አንዱ ነበር፡፡ ገጸ ታሪኩ እንደሚያሳየው፣ በአሜሪካ የነበረውን ጥናት በ1958 ዓ.ም. ፈጽሞ ሲመለስ በራዲዮ ኢትዮጵያ ከ1961 እስከ 1963 ዓ.ም. የፕሮግራም ዳይሬክተር፣ ራዲዮና ቴሌቪዥን በጋራ ይመራ የነበረውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስን (ኢቢሲ) ከ1963 እስከ 1964 ዓ.ም. በምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅነት መርቷል፡፡

በእነዚያ የጋዜጠኝነት ሕይወቱ በጸሐፊነት፣ በአዘጋጅነትን በተራኪነት በመምራት በኢትዮጵያ ታሪክ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ጥበብ ዙሪያ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካን የነፃነት ተጋድሎ የሚመለከት ርዕሰ ጉዳዮችን ይዳስስ ነበር፡፡

የ1966 ዓ.ም. አብዮት በኋላ በአሜሪካ በስደት ኑሮውን የጀመረው ከዩኒቨርሲቲ መምህርነት እስከ ፊልምና ቴሌቪዥን ጽሑፍ አዘጋጅነትና በሌሎችም ሥራዎች የዘለቀ ነበር፡፡ የመንግሥት ለውጥ በ1983 ዓ.ም. ከተደረገ በኋላ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አዲስ አበባ በተደጋጋሚ የዘለቀው አቶ ሰሎሞን ዕውቀትና ልምዱን በተለያዩ መድረኮች ያስተላልፍ ነበር፡፡

ከሰባት ወራት በፊት ባደረበት ጽኑ ሕመም ሳቢያ ሕክምናውን ሲከታተል ቆይቶ ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኔሶታ ከተማ መኖሪያ ቤቱ በ80 ዓመቱ ማረፉን ታናሽ ወንድሙ አምባሳደር ብርሃኔ ዴሬሳ ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡ የሰሎሞን ዴሬሳ አስከሬን በራሱ ኑዛዜ መሠረት በሚኔፖሊስ ማቃጠያ ኅብረት ሥፍራ ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን እንዲቃጠል ተደርጓል፡፡

ከአሜሪካዊቷ ባለቤቱ ጋር ጎጆ መሥርቶ የአንዲት ልጅ አባት ሲሆን፣ የልጅ ልጆችም አይቷል፡፡

ነፍስ ኄር ሰሎሞን ዴሬሳ ከ19 ዓመት በፊት ስለ ‹‹መንፈሳዊነት›› ለሪፖርተር መጽሔት እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

‹‹መንፈሳዊነት አሁን ያለውን የአገራችንን ማኅበራዊ ችግር ለመፍታት ሊጠቅመን ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ግን እንደሚታየኝ ለኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስና እስልምና እንደ ሃይማኖት ሆነው አይታዩኝም፡፡ ለእኔ ማንነት (Identity) ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የማንነት መለያ የሆነ ሃይማኖት አለን፣ አይጎድለንም፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊነት ይጎድለናል፡፡

‹‹መንፈሳዊነት ለእኔ የእምነት ጉዳይ አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር የማመንና ያለማመን አይደለም፡፡ መንፈሳዊነት መጨረሻው ራስን ማወቅና አንድ መሆን ነው፡፡ የሰው ልጅ አንድ ሆኖ አይፈጠርም፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ትወለዳለህ፣ በአንድ በኩል የአባትህን በአንድ በኩል የእናትህን ይዘህ ትወለዳለህ፡፡ በሌላ በኩል አሳዳጊዎችህን፣ ወንድሞችህን፣ ጓደኞችህን ሁሉ ትመስላለህ፡፡ መምህራንህን ትመስላለህ፡፡ ስለዚህ እኔ ከእነዚህ ሁሉ እንደ ቡትቱ ጨርቅ ተሰብስቤ ተጣፍኩኝ፡፡ እና ለእኔ መንፈሳዊነት የእምነት ነገር ሳይሆን ሳልሞት ምናልባት አንድ ሰሎሞን ሊፈጠር ይችላል ወይ? ይህ ሁል ጊዜ የራስህ ፈንታ፣ የራስህ ተግባር፣ የራስህ ግዴታ ነው፡፡ መንፈሳዊንት በመጨረሻው ከብትንትኑ የተጣጣፈ ሰው አንድ ሆኖ ተሰብስቦ ይሞታል ወይ? ይህ ደግሞ በእምነት ሳይሆን በጥረት ነው የሚገኘው፡፡››

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...