ከሁለት ሳምንት በፊት በገጠመው የፀጥታ ችግር ማምረት አቁሞ የነበረው ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
ጥቅምት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ተቃውሞ የሚያሰሙ ወጣቶች ሐበሻ ሲሚንቶ ቋሚ ሥራ እንዲሰጣቸው ወይም ደመወዝ እንዲከፈላቸው በመጠየቅ፣ ፋብሪካውን በተለይ የማዕድን ማውጫውን በመቆጣጠራቸው የምርት ሒደቱን ማቋረጡ ይታወሳል፡፡
የሐበሻ ሲሚንቶ ማኔጅመንት አባላት፣ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን የወልመራ ወረዳ አስተዳደርና የወረዳው ፖሊስ ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ መክረማቸውን፣ የሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን አቢ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሆለታ ከተማ ስብሰባ ያካሄዱት የወረዳውና የዞን አስተዳደር ኃላፊዎች፣ የሐበሻ ሲሚንቶ ኃላፊዎችና የወረዳው ፖሊስ አዛዦች ፋብሪካው በገጠመው የፀጥታ ችግር ላይ መክረዋል፡፡
ተቃውሞውን የቀሰቀሱት ሆለታ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው በሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሲሚንቶ ጭነው የሚወጡ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ሸራ የሚያለብሱ ወጣቶች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ከ100 በላይ የሚሆኑት ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው ሸራ በማልበስ ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደቆዩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባ ኩባንያው ለወጣቶቹ ቋሚ ሥራ ለመስጠት እንደማይችል አስታውቋል፡፡ ‹‹ፋብሪካችን ሁልጊዜም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ለእነዚህ ወጣቶች ልንሰጥ የምንችለው ቋሚ የሥራ ቦታ የለንም፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ወጣቶቹ የሚሠሩት ከጭነት ተሽከርካሪዎቹ ጋር በመሆኑ መነጋገር የሚችሉት ከባለተሽከርካሪዎቹ ጋር እንጂ፣ ፋብሪካው ሊከፍላቸው የሚችለው ምንም ዓይነት ክፍያ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
ወጣቶቹ እስካሁን ሲሠሩ እንደቆዩት የጭነት ተሽከርካሪዎቹን ሸራ የማልበስ ሥራ ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ገልጸው፣ ከፋብሪካው ጋር የሥራ ግንኙነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ከወረዳና ከዞን አስተዳዳሪዎች ጋር በጉዳዩ መግባባት ላይ በመደረሱ፣ ፋብሪካው ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምረት መጀመሩን የገለጹት አቶ መስፍን በፋብሪካው አካባቢ የተረጋጋ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
‹‹የወልመራ ወረዳ አስተዳደር ኃላፊዎች የፋብሪካውን አቋም ለወጣቶቹ አስረድተዋል፡፡ የወረዳና የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የወረዳው ፖሊሲና የአካባቢው ማኅበረሰብ ባደረገልን ከፍተኛ ትብብር ማምረት ጀምረናል፤›› ብለዋል፡፡
የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር በ30 መሥራች ባለአክሲዮኖች በ2000 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ የባለአክሲዮኖች ቁጥር ወደ 16,000 አድጓል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ታዋቂ ሲሚንቶ አምራች ኩባንያ ፒፒሲ 51 በመቶ አክሲዮን ባለድርሻ ነው፡፡
በ140 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ በዓመት 1.4 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው፡፡ ፋብሪካው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሚያዝያ 2009 ዓ.ም. ተመርቆ ማምረት መጀመሩ ይታወሳል፡፡