ትምህርት ሚኒስቴር በ2010 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አምጥተው ከኦሮሚያ ክልል ወደ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲና ከሶማሌ ክልል ወደ ኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ለነበሩ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች አዲስ ምደባ ማውጣቱ ታወቀ፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደጠቆሙት የኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ ጊዜ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በ2010 ዓ.ም. ከክልሉ ወደ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው የነበሩ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች፣ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ሌሎች ዩነቨርሲቲዎች ተመድበዋል፡፡ ከሶማሌ ክልል በኦሮሚያ ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የነበሩ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች በአገሪቱ ባሉ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መመደባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ እንደተገለጸው በጅግጅጋና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የነበሩ የ2010 ዓ.ም. ተማሪዎች አዲስ ምደባ ተሠርቶላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲሱን ምደባ ይፋ አድርጓል፡፡
ጉዳዩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንደያዙትና በቅርቡ በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንደሚሰጡ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፣ በ2010 ዓ.ም. በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው የነበሩ የክልሉ ተማሪዎች በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች መመደባቸውን አረጋግጠዋል፡፡
‹‹የክልሉ መንግሥት ለትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ጥያቄ ያቀረበበት ዋነኛ ምክንያት ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ የክልሉ ተማሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰባቸው ስለሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ይሻሻላል የሚል ተስፋ ነበረን፡፡ ነገር ግን እስካሁን ሊሻሻል ስላልቻለ ይህን ጥያቄ ለማቅረብ ተወስኗል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
‹‹እኛ እንዲመለሱ አዘን ሳይሆን ልጆቹ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት እየደረሰባቸው በመሆኑ ጥለው መጥተዋል፡፡ ስለዚህ የፀጥታው ችግሩ እስኪፈታ ድረስ አመራሮች የችግሩን ጥልቀትና መጠን ገምግመው የያዙት አቋም ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከሦስት ሳምንት በፊት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው መሄድ እንደሌለባቸው ተቃውሟቸውን ለሁለት ቀናት ያህል ሲገልጹ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁለተኛ ዓመትና ከዛ በላይ ስላሉ ተማሪዎችም የኦሮሚያ ክልል ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ጋር እየተወያየ መሆኑን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም እስካሁን በጉዳዩ ላይ የተደረሰ ስምምነት አለመኖሩን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ኦሕዴድ በሰባተኛው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ስምምነት ላይ ከደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል፣ ከሶማሌ ክልል ጋር ያለውን አስተዳደራዊ ወሰን በሕዝብ ውሳኔ መፍታት አንዱ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ግን አሁንም በሁለቱ ክልሎች መካከል እየተደረገ ያለውን ውይይት ችግር ውስጥ እንዳይከተው የሚሠጉ አሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የሶማሌ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡