Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር መተዳደር ያለባት በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ ነው!

በማንኛውም አገር የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት የሕግ የበላይነትን ማስከበር ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን የያዙ መንግሥታት ከምንም ነገር በፊት የሚያስቀድሙት የሕግ የበላይነትን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት የሚጠቅመው ጠንካራ፣ አስተማማኝና ዘለቄታዊነት ያለው ሥርዓት ለመገንባት ነው፡፡ አምባገነኖች ደግሞ ሕግን በሚመቻቸው መንገድ ቀርፀው ሕገወጥነት የሥልጣናቸው መጠበቂያ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ ባለሥልጣናቱ እንደፈለጉ እየፈነጩ የአገር ሀብት ሲዘርፉና ሕዝብ ሲያሰቃዩ ጠያቂ ስለሌለባቸው፣ ሥርዓተ አልበኝነት ይሰፍንና ትርምስ ይፈጠራል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት የሥልጣን መባለጊያ እየሆኑ ሲሽመደመዱ፣ የሠራተኞች ሞራል እየተነካ አገልግሎቶች ሲስተጓጎሉና በፖለቲካና በጥቅም የተሳሰሩ ቡድኖች ከሕግ በላይ ሲፎልሉ የሚታዩት በአምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት ያስኮረፋቸው ወገኖች ደግሞ አሻፈረኝ ብለው ሲነሱ ሁከት ይቀሰቀሳል፡፡ የንፁኃን ሕይወት ይረግፋል፡፡ የአገር አንጡራ ሀብት ይወድማል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር አለመተዳደር ጦሱ የከፋ ከመሆኑም በላይ፣ የአገር ህልውናን አጣብቂኝ ውስጥ ይከታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ክስተት በተለያዩ አገሮች ውስጥ በተደጋጋሚ በመታየቱ፣ ብዙዎች ትምህርት ወስደውበት ትክክለኛውን ጎዳና መርጠዋል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ጎዳና፡፡

      ወደ አገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ስንመለስ ለዓመታት በተበላሹ ግንኙነቶች ምክንያት በየጊዜው በሚቀሰቀሱ ግጭቶችና ሁከቶች በርካቶች ውድ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በብዙ ሥፍራዎች መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች ተዳክመዋል፡፡ ለዓመታት የተጠራቀሙ ብሶቶች መተንፈሻ በማጣታቸው ሳቢያ ለሞትና ለውድመት የሚያጋልጡ ብጥብጦች እያስተናገደች ያለች አገር ውስጥ፣ ቆም ብሎ ማሰብና አዲስ ፍኖተ ካርታ (Road Map) ለማውጣት መነጋገር የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ በማጥቃትና በመከላከል አስተሳሰብ ውስጥ ብቻ በመታጠር፣ ከአገርና ከሕዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም ውጪ መነታረክ አሁን ጊዜው አይደለም፡፡ ነገር ግን ካሁን በኋላ በሕግ የበላይነት ሥር እንዴት መተዳደር እንደሚቻል መነጋገር፣ ለበርካታ አገራዊ ችግሮች መፍትሔ መነሻ ይሆናል፡፡ ለሰላምና ለዴሞክራሲ መሠረቱ የሕግ የበላይነት ነው፡፡ ልማትና ብልፅግና የሚገኘው በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ ነው፡፡ የጥላቻና የቂም ጎዳናን በመተው መወያየትና መደራደር የሚቻለው ሕጋዊ ማዕቀፎች ሲኖሩ ነው፡፡ ለሕግ የበላይነት ትኩረት የማይሰጥ ማንኛውም እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ የቡድን ጥቅምን ማስጠበቅ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተቃራኒውን ወገን ለሌላ አመፅ ያስነሳል፡፡ የሕግ የበላይነት ልዕልና ይኖረው ዘንድ ግፊት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

      የሕግ የበላይነትን የማክበርና የማስከበር ትልቁ ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት በመጀመርያ ተቋማቱ ከፖለቲካ መሣሪያነት ነፃ እንዲወጡ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ የመንግሥት አሠራር ግልጽና ለሕዝብ ተጠያቂነት እንዳለበት በግልጽ ተደንግጓል፡፡ መንግሥታዊ ተቋማት አሠራራቸው ብልሹ የሚሆነውና በሥልጣን መባለግ ልማድ የሚሆነው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጠፋ ብቻ ነው፡፡ ተቋማት የሚሽመደመዱትና የሙሰኞች መጫወቻ የሚሆኑት ሕግ ባለመከበሩ ነው፡፡ አንድ ተቋም ሲመሠረት በሕግ የተሰጠው ኃላፊነትና ተጠያቂነት ሲኖርበት፣ ተሿሚውም እንዲሁ ኃላፊነቱና ተጠያቂነቱ ሰፍሯል፡፡ ነገር ግን በሚሊዮኖችና በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ላይ ጉዳት ሲደርስ ጠያቂ የለም፡፡ ድንገት በሚደረጉ የፀረ ሙስና ዘመቻዎች ተቋማት ምን ያህል የግለሰቦች መጫወቻ እንደነበሩ ሲሰማ፣ የሕግ የበላይነት ምን ያህል እንደተናቀ ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በመንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት በስፋት የሚታየው የአገልጋይነት ስሜት መጥፋት፣ ዓይን ያወጣ ጉቦ፣ ከግዥ ሕጉ በተቃራኒ የሚፈጸመው መረን የወጣ ሌብነት፣ በተዝረከረከ የፋይናንስ ሥርዓት ሳቢያ የሚወድመው የአገር ሀብት፣ ወዘተ. የተቋማቱን መሽመድመድና የሕግ ጥሰቶች ቁልጭ አድርጎ ያመላክታል፡፡ የዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዓመታዊ ሪፖርቶችን ማገላበጥ ለዚህ አባባል በቂ ምስክር ነው፡፡ የደካማ ተቋማትንና ተጠያቂነት ያልለመደባቸውን ሹማምንት ገመና በሚገባ ያጋልጣል፡፡

ዜጎች በሙሉ በሕግ ፊት እኩል መሆን እንዳለባቸው በንድፈ ሐሳብ (Theory) ደረጃ ይታወቃል፡፡ ከአንድ ዜጋ ጀምሮ አገሪቱን የሚመሯት ጠቅላይ ሚኒስትር ድረስ በሕግ ፊት እኩል ሲሆኑና ተጠያቂነታቸውም በዚያው ልክ ሲሆን፣ የሕግ የበላይነት ለመረጋገጡ ትክክለኛ ማሳያ ነው፡፡ አንዱ የሚጠየቅበትን ጥፋት ሌላው ዝም ሲባልበት፣ አንደኛው ንፅህናው እየታወቀ ያለ ጥፋቱ መከራ በሚያይበት ወንጀል፣ ሌላው እስከ አንገቱ ተነክሮበት ጠያቂ ሲጠፋ ስለሕግ የበላይነት የመነጋገር የሞራል ብቃት አይኖርም፡፡ በጠራራ ፀሐይ ሕገወጥነታቸው ያገጠጠ ወረበሎች እንዳሻቸው እየደነፉ ጠያቂ ሳይኖርባቸው፣ ንፁኃን ፍትሕ አጥተው ሲያለቅሱ ወይም ተገደው ፍትሕን በገንዘብ እንዲገዙ እየተደረገ ስለሕግ የበላይነት መነጋገር ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ሥርዓት አልበኝነት የሚፈጠረው ሕግ የሚያከብረው ሲያጣ ነው፡፡ እሴት ሳይጨምሩ በአንድ ሌሊት ሚሊየነሮች የሚፈለፈሉት ገደብ የሌለው ሥልጣን ሕጉን ሲደረምሰው ነው፡፡ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ፖለቲካዊ ነውጥ ሊያስከትል የቻለው ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ አይነኬዎች ስለበዙ ነው፡፡ ጤናማ ዜጎችን አንገት የሚያስደፉ እንዲህ ዓይነት አስከፊ ድርጊቶች ተወግደው ለአገር የሚበጅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማስፈን የሚቻለው፣ በተቻለ መጠን መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ለሕግ የበላይነት የመታገል ወኔ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ዲስኩር ፋይዳ የለውም፡፡

ሌላው ቀርቶ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ እንዲከበሩ ማድረግ ሲቻል፣ ለሥርዓተ አልበኝነት የሚያጋልጡ ብልሹ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ ዜጎች በነፃነት ብልሹ አሠራሮችን ሲያጋልጡ፣ የሌብነት ቀዳዳዎች እንዲደፈኑ ሲያመላክቱ፣ አምባገነንነትን የሚያራቡ ድርጊቶች በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦች የሚከሽፉባቸው ነፃ የውይይትና የክርክር መድረኮች ሲፈጠሩ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ ያለምንም መሸማቀቅ ሐሳባቸውን ሲያንሸራሽሩና ሌሎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሕጋዊ ከለላ ሲያገኙ ሕገወጥነት በሩ ይዘጋበታል፡፡ በነፃነት መነጋገር፣ መደራደርና የሚያግባባ ውሳኔ ላይ መድረስ የሚቻልበት የዴሞክራሲ ጅማሮ ይገኛል፡፡ ግለሰብም ይሁን ፓርቲ፣ የትምህርት ተቋም ይሁን የሲቪክ ማኅበር፣ ፖለቲከኛ ሆነ ማንም በሕግ የበላይነት ሥር ተግባራቸውን ሲያከናውኑ የሚተማመኑት በሕግ ብቻ ይሆናል፡፡ መገለማመጥና ካሁን አሁን ምን ያገኘኝ ይሆን የሚለው ሥጋት ሥፍራ ያጣል፡፡ ለአገር ብዙ ነገሮችን ማበርከት የሚችሉ ምሁራንም ሆኑ በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሠለፉ ወገኖች በነፃነት አደባባይ ይወጣሉ፡፡ በኃላፊነት ስሜት የሚፈለግባቸውን ያበረክታሉ፡፡ ይህ መልካም ምኞት ይሰምር ዘንድ የሕግ የበላይነት ከሙሉ ክብሩ ጋር ይረጋገጥ፡፡

ሁሌም እንደምንለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚሰፍነው በዴሞክራሲያዊ ዓምዶች ላይ ነው እንጂ፣ በአመፅና በግርግር ወይም በአንዱ አሸናፊነትና በሌሎች እጅ መስጠት አይደለም፡፡ የአገሪቱ ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት መሆን ያለበት መላው ሕዝብ በነፃነት በሚሰጠው ውሳኔ ብቻ ነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው፡፡ ይህ በገቢር ይታይ ዘንድ ደግሞ ከጠባብ ፖለቲካዊና ቡድናዊ ትስስር በላይ ሕዝብና አገርን ማስቀደም የግድ ነው፡፡ በዚህ ትስስር ውስጥ ብቻ ማድፈጥ አምባገነንነትን ከማራባትና የአገር ህልውናን አደጋ ውስጥ ከመክተት ውጪ ምንም አይገኝም፡፡ ይልቁንም በሰጥቶ መቀበል መርህ ልዩነትን እያቻቻሉ ለሐሳብ የበላይነት ልዕልና በመገዛት የሕዝብን ልብ ማማለል ይሻላል፡፡ ተቋማት የፖለቲካ መሣሪያ እንዳይሆኑ፣ የፀጥታ ኃይሎች የፖለቲካ ገመድ ጉተታ ውስጥ እንዳይገቡ፣ ያረጁና ያፈጁ ጨለምተኛ አስተሳሰቦች ገለል ተደርገው ወጣቱ ትውልድ በነፃነት እንዲቀራረብና እንዲወያይ ዕድሉ እንዲመቻች፣ ጠመንጃ ነካሽ አስተሳሰቦች ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሐሳብ ፍልሚያ ቦታቸውን እንዲለቁ፣ በዜጎች ሕይወት እየቆመሩ ሒሳብ የማወራረድ ኋላቀር ድርጊቶች አደብ እንዲገዙ፣ ወዘተ. ማድረግ የሚቻለው የሕግ የበላይነት ሲከበር ብቻ ነው፡፡ ይህ የሚያስማማን ከሆነ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ለኢትዮጵያችንና ለሕዝባችን ስንል አገር መተዳደር ያለባት በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ ነው ማለት አለብን!

 

 

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...