በፌዴራል መንግሥት ተረቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውና በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንዲደረግ ሆኖ የተዘጋጀው የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ አዋጅ እንዳይፀድቅ፣ የኦሮሚያ ክልል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ጠቅላይ ሚንስትሩንና ፓርላማውን በደብዳቤ ጠየቀ።
የክልሉ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ጥያቄውን ለከፍተኛው የፌዴራል መንግሥት ያቀረበው፣ ቀደም ሲል አዋጁን ላመነጨው ለፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ላቀረበው ተመሳሳይ ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱና የሕግ ሰነዱንም ፓርላማው ለማፅደቅ በዝግጅት ላይ መሆኑን በመረዳቱ ነው።
ረቂቅ አዋጁ በሕገ መንግሥቱ ለክልሎች የተሰጠውን ሥልጣን ከግምት ያላስገባና ለመተግበር አስቸጋሪ ሆኖ በመዘጋጀቱ፣ ሊፀድቅ እንደማይገባው ሰሞኑን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተላከው ደብዳቤ ይገልጻል።
ክልሎች ደግሞ በሕገ መንግሥት የተቋቋሙ ራሳቸውን የቻሉ መንግሥት ሆነው ሳለ፣ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 2(18) የፈቃድ ሰጪ አካላት ትርጓሜ በትራንስፖርት ባለሥልጣን የዕውቅና ሠርተፊኬት የተሰጠው የመንግሥት አካል ማለቱ፣ የክልልን ሥልጣን ከግንዛቤ ያላስገባና ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረን መሆኑን በደብዳቤው ገልጿል። በአዋጁ አንቀጽ 6(1)(2) ደግሞ ባለሥልጣኑ የፈቃድ ሰጪ አካላት ማሟላት የሚገባቸውን መሥፈርት ያወጣል፣ በመሥፈርቱ መሠረት ፍቃድ ሰጪው መሥፈርቱን ስለመሟላቱ ተመልክቶ የዕውቅና ሠርተፊኬት ይሰጠዋል፣ ሠርተፊኬቱን ይሰርዛል፣ ያግዳል በማለት የተቀመጠው ድንጋጌም በሕገ መንግሥት የተቋቋመን ክልል ሥልጣን በአዋጅ የተቋቋመው ባለሥልጣን የሚጋፋ ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል።
በሌላ በኩል የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ለፌደራል መንግሥቱ ለብቻ የተሰጠ ባለመሆኑ፣ ክልሎች አስፈጻሚ አካላትን በሚያቋቁምበት አዋጅ እንደ ተግባር ይዘው ሥራዎችን እየሠሩ እያሉ ይህ አዋጅ እንዲህ መውጣቱ የክልልን ሥልጣን እንደ መቀማት ስለሚቆጠር ከዚህ አንፃርም እንዲታይ ጠይቋል።
በአዋጁ አንቀጽ 8(6) የታክሲ አገልግሎት የአሽከርካሪዎች ሥልጠናን በተመለከተ ባለሥልጣኑ የሚያዘጋጀውን ልዩ ሥልጠና በመውሰድ የምስክር ወረቀት መያዝ ያስፈልጋል ማለቱ፣ ከኦሮሚያ ክልል ስፋት አንፃር ይህ አገልግሎት በባለሥልጣኑ ብቻ እንዲሰጥ ወይም በባለሥልጣኑ በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረት አገልግሎት እንዲሆን ከማድረጉ ባለፈ፣ አገሪቱ ከምትከተለው የፖለቲካ ርዕዮት አንፃር ሥልጣን አንድ ቦታ እንዲሰበሰብ የሚያደርግ አዝሚያሚያ የሚታይበት በመሆኑ፣ እርምት ሊደረግበት እንደሚገባ የክልሉ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ገልጿል።
ጉዳዩን በተመለከተ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያምን ለማነጋገር የተያደረገው ጥረት አልተሳካም። ረቂቁን ከትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመተባበር በዝርዝር እንዲመለከትና የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ የተመራለት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ተሰማ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በረቂቁ ላይ የሕዝብ ውይይት መድረክ ሰኞ ጥቅምት 27 2010 ዓ.ም. ቀን ይካሄዳል ብለዋል፡፡ የሕግ ሰነዱ ከክልሎች ሥልጣን ጋር የሚጋጭ ይዘት ካለው በዚሁ መድረክ መነሳቱ እንደማይቀርም ገልጸዋል።
ቋሚ ኮሚቴዎቹ ማናቸውንም ሥጋቶችና የተዛነፉ የሕግ አንቀጾች አንድ በአንድ ሳይመለከቱ ረቂቁ እንዲፀድቅ ውሳኔ እንደማያቀርቡ፣ እንደተባለው ከክልሎች ሥልጣን ጋር የሚጋጭ ከሆነም ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ተመርቶ የክልሎች ይሁንታ የሚጠየቅበት አሠራር መኖሩን አቶ ጴጥሮስ አስረድተዋል።