Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኬንያ ድንበር ደርሶ በተመለሰው ስኳርና በአጠቃላይ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ አመራሮች ተወቀሱ

ኬንያ ድንበር ደርሶ በተመለሰው ስኳርና በአጠቃላይ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ አመራሮች ተወቀሱ

ቀን:

‹‹ባህር ውስጥ ከገባን በኋላ ነው ችግሩን የተረዳነው››

‹‹ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቶችን ከሜቴክ መንጠቅ አይችልም››

የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አህመድ አብተው

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ስኳር ወደ ኬንያ ኤክስፖርት ለማድረግ የሽያጭ ውል ከተፈጸመ በኋላ ኢትዮጵያ ሞያሌ ድንበር ከደረሰ በኋላ ውሉ ተቋርጦ እንዲመለስ በመደረጉና በስኳር ፕሮጀክቶች አሳዛኝ አፈጻጸም ሳቢያ፣ በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚዎችና በቦርድ አመራሮች ላይ የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ የሰላ ትችትና ወቀሳ አቀረበ፡፡

ወቀሳውን ያቀረቡት የፓርላማው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮርፖሬሽኑን የሥራ አፈጻጸም ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በገመገመበት መድረክ የተገኙ የምክር ቤት አባላትና የሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች አመራሮች ናቸው፡፡

በዕለቱ የ2010 ዓ.ም. ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ኮርፖሬሽኑ ያቀረበ ቢሆንም፣ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ተጠናቀው የአገሪቱን የስኳር ፍጆታ ከበቂ በላይ አጥብበውና ለውጭ ገበያ ኤክስፖርት አድርገው በየዓመቱ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛሉ የተባሉት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች መካከል፣ የተወሰኑት በ2010 ዓ.ም. እንኳን ተጠናቀው ወደ ምርት እንደሚገቡ የኮርፖሬሽኑ አመራሮች ማረጋገጫ መስጠት ተስኗቸዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያ የአፈጻጸም ሪፖርቱን ካዳመጡ በኋላ፣ ‹‹አመራሩ ግን ጤነኛ ነው?›› ሲሉ የተሰማቸውን ሐዘን በጥያቄ መልክ ለአመራሮቹ አቅርበዋል፡፡

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በቋሚ ኮሚቴው ሲሠሩ በቆዩባቸው ሦስት ዓመታት በተለይ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ፣ በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካዎች በየዓመቱ ዘንድሮ ይጠናቀቃሉ እየተባለ ሪፖርት ሲቀርብ እንደነበር ገልጸው፣ በ2010 ዓ.ም. በተመሳሳይ ዘንድሮ ይጠናቀቃሉ መባሉ እንዳሳዘናቸው በስሜት ተናግረዋል፡፡

‹‹ከውድቀት ውድቀት የሚሸጋገር ተቋም ይዘን ወዴት ነው የምንሄደው? እንዴት ነው ራሳችን ከዚህ ውድቀት ማዳን ያልቻልነው?›› ሲሉ ትችት አዘል ጥያቄያቸውን ለአመራሮቹ ወርውረዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳወቅ አብቴ ቀደም ብሎ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተከሰተ ድርቅ፣ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የሸንኮራ አገዳዎች በመበላሸታቸው እንዲወገዱ መደረጉን በወቅቱ ገልጸው ነበር፡፡

በለስ ሁለት ስኳር ፋብሪካን በተመለከተ ከኮንትራክተሩ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ተነጥቆ ለሌላ ኮንትራክተር በመተላለፉ፣ በዚህ ዓመት ግንባታውን ወደ 75 በመቶ ለማድረስ ዕቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡

ወልቃይት የስኳር ፋብሪካም ከሜቴክ ከተወሰደ በኋላ ፕሮጀክቱን የያዘው ኩባንያ ጥሩ አፈጻጸም ቢኖረውም፣ የመስኖ ፕሮጀክቱና ግድቡ እኩል ባለመሄዳቸው በሙሉ አቅሙ ማምረት እንደማይጀምር ግልጽ አድርገዋል፡፡

የበለስ ሁለት ስኳር ፋብሪካ የግንባታ አፈጻጸም 25 በመቶ ቢሆንም፣ ከ75 በመቶ በላይ ግን ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ የግንባታ አፈጻጸሙ 25 በመቶ ሆኖ ይህንን ያህል ክፍያ መለቀቁ፣ እንዲሁም የዚህን ፕሮጀክት ውል በማቋረጥ ከሜቴክ እንዲነጠቅ መወሰኑ ግራ ያጋባቸው የቋሚ ኮሚቴው አባላት ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

ስኳር ኮርፖሬሽን ግዙፍ የአገር ሀብት እያንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ኦዲት ተደርጎ አለማወቁም ሌላው የፓርላማ አባላቱ ያነሱት ጥያቄ ነበር፡፡

በ2009 ዓ.ም. ከፍተኛ የክረምት ዝናብ በኦሞ የስኳር ፕሮጀክቶች የሸንኮራ ተክል ላይ ያረሰው ጉዳትን በተመለከተ፣ የዝናቡ መጠን እንዲህ ይሆናል ተብሎ በጥናት ወቅትም አለመታየቱን የኮርፖሬሽኑ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ደምሴ ገልጸዋል፡፡ በለስ ሁለት ስኳር ፋብሪካ ከሜቴክ ቢነጠቅም ወደ ሌላ ኮንትራክተር ለማስተላለፍ ሜቴክ ያከናወናቸውና ያመረታቸው የፋብሪካው ማሽነሪዎችን ሒሳብ የመገመት ሥራ እንደተጠናቀቀ፣ ለሌላ ኩባንያ ፕሮጀክቱ ይተላለፋል ብለዋል፡፡ ከ2003 ዓ.ም. አንስቶ ስኳር ኮርፖሬሽኑን የፋይናንስ ኦዲት ተደርጎ ባያውቅም፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ኋላ ተሂዶ መሠራት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

አመራሮቹ በሰጧቸው መልሶች ያልተደሰቱት የቋሚ ኮሚቴው ሊቀመንበር አቶ ገብረ እግዚአብሔር፣ ‹‹ውጤት ማምጣት ላለመቻሉ ውጫዊ ምክንያት አትደርድሩ፤›› ሲሉ ግሳጼ ያዘለ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‹‹በዝናብ ምክንያት ነው፣ በአየር ንብረት ለውጥ ነው እያላቸሁ ችግሮቻችሁን ወደ ውጪ አትግፉ፣ ዝናብ ነገም ይመጣል፡፡ ወደፊትም ይዘንባል፤›› ብለዋቸዋል፡፡ በቀረበው የሩብ ዓመት አፈጻጸም ላይ ኪራይ ሰብሳቢነትን እንደሚታገሉና መልካም አስተዳደርን እንደሚያሰፍኑ አመራሮቹ መግለጻቸውም የይስሙላ ሆኖባቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲፋቅልን ዓይነት ንግግርማ ሞልቷል፡፡ አንድ ጠብ ያለ ውጤታማ ሥራ የለም እንጂ፤›› ሲሉ ተችተዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም ሌሎች የቋሚ ኮሚቴው አባላት እውነቱን ተነጋግሮ መተራረም እንደሚሻል በመጠየቅ፣ የቦርድ አመራሮች ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ ‹‹ችግሩ የአመራሮች ነው፣ የእኛ ችግር ነው፤›› በማለት፣ ኃላፊነቱን በራሳቸውና በሌሎች የኮርፖሬሽኑ አመራሮች ላይ ጥለዋል፡፡ ‹‹ቀድሞ የነበረው አመራር የፈጠረው ችግር ቢሆንም ከኃላፊነት መሸሽ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በሲስተም (ሥርዓት) ነው መንግሥት ኃላፊነቱን የሚወጣው፤›› ብለዋል፡፡

በመቀጠልም የችግሮቹ ሁሉ ቁልፍ ነው ያሉትን አሥር የስኳር ፕሮጀክቶችን በሜቴክ አማካይነት ለመገንባት መሞከሩ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የስኳር ፕሮጀክቶቹ የመስኖ፣ የእርሻ፣ የሲቪልና የኢንጂነሪንግ ሥራዎችን በአንድ የያዘ ሆኖ ሁሉንም በአንድ የአገር ውስጥ ኩባንያ መሪ ተዋናይነት፣ ለዚያውም ልምድ ሳይኖረው እንዲያካሂድ መወሰኑ ዋናው ቁልፍ ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ችግር ባህር ውስጥ ከገባን በኋላ ነው ችግሩን ያወቅነው፤›› ብለው፣ በአሁኑ ወቅት ኩራዝ አንድና በለስ አንድ ፕሮጀክቶች ብቻ በሜቴክ ሥር እንደሚገኙ አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ዘንድሮ ይጠናቀቃሉ ቢባልም፣ ‹‹ማስተማመኛ ግን መስጠት አልችልም፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሜቴክን ውል በራሱ ማቋረጥ እንደማይቻል፣ ይህንን ማድረግ የሚችለው ተቆጣጣሪ በሆነው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር አማካይነት ለመንግሥት ቀርቦ በመንግሥት ውሳኔ ውሉ ሊቋረጥ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ከኬንያ ድንበር የተመለሰውን 4,400 ቶን ስኳር በተመለከተም ችግሩ የኮርፖሬሽኑ ሳይሆን፣ ስኳሩን ወደ ኬንያ ለማድረስ የተዋዋሉት ትራንስፖርተሮች ግዥውን ከፈጸመው ኩባንያ ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ውሉ እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡

በስኳር ኤክስፖርት የወደፊት ንግድ ላይ አሉታዊ ገጽታ በኮርፖሬሽኑ ላይ በመፍጠራቸው፣ እንዲሁም ኤክስፖርቱን በማስተጓጎላቸው ሊጠየቁ ይገባል በማለት ቦርዱ ስለወሰነ ውሳኔውም ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲመራ ይደረጋል ብለዋል፡፡

የፓርላማ አባላቱ ግን አሁንም በሚሰጠው ምላሽ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ የየወሩን የድርጊት መርሐ ግብር ለቋሚ ኮሚቴው እንዲልክ፣ እንዲሁም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የመቆጣጠር ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ መፈታት ያልቻለ ችግርን ከማዘል ለመንግሥት አቅርቦ ማስወሰን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...