በአዳማ ከተማ ገልማ አባ ገዳ አዳራሽ ሲካሄድ የነበረው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ኮንፈረንስ፣ የአሥር ዓመት ድርጅታዊ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ተጠናቀቀ፡፡
የኦሮሚያ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለሪፖርተር እንደተናገሩት የክልሉን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ የአሥር ዓመት የድርጅቱ ስትራቴጂ ይፋ ሆኗል፡፡
ስትራቴጂው ከዚህ በፊት በክልሉ ይስተዋሉ ለነበሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ከመጠቆም ባሻገር፣ አመራሩ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ቁመና እንዲኖረው ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ኮንፈረንስ ባለአሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ ወጥቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል በክልሉ ሕዝብ መካከል ያለውን የአንድነት መንፈስ ማጠናከር፣ በኅብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የሕዝቡን ተሳትፎ በማረጋገጥ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ መብቶችና ግዴታዎች ሳይሸራረፉ እንዲተገበሩ እንደሚያደርግ፣ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተለዩ ችግሮችን እንደሚፈታ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት የተጀመረውን ትግል አጠናክሮ በመቀጠል የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚን በልማታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ እንደሚቀይር፣ በትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን እንዳይማሩ የሚያዘናጉትን አጥብቆ እንደሚያወግዝና ከወሰን ጋር በተያያዙ የሚከሰቱ ሕገወጥ ተግባራትን በማረም የሕግ የበላይነት እንደሚያሰፍን መግለጹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ኦሕዴድ ሰሞኑን ያካሄደው ኮንፈረንስ ከዚህ በፊት ከነበሩት በይዘትና በቅርፅ ልዩ እንደነበር ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡ የቀረቡ የመወያያ አጀንዳዎች ወቅታዊ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩና ከዚህ በፊት ከነበሩት ከፍ ባለ ደረጃ እንደቀረቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለውይይት መነሻነት በቀረቡ ጽሑፎችና ሪፖርቶች ላይ ተሳታፊዎች ያለምንም ፍርኃትና መሸማቀቅ ሐሳባቸውን በነፃነት ሲያንፀባርቅ እንደነበር ከምዕራብ ሸዋ ዞን የመጡት የኑኑ ወረዳ ኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረፌራ ቱሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት አቋም ሲያዝ ይኼማ ጠባብነት አለው ተብሎ ይፈረጃል፡፡ ይኼ በአሁኑ ወቅት መቅረት እንዳለበት አቅጣጫ ስለተሰጠ አባላት ነፃ ሆነው ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፤›› ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) አባል ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ኦሕዴድ በአገሪቱ ካሉ ክልሎች መካከል ሰፊውን የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ቁጥር የሚሸፍነውን የኦሮሚያ ክልል ያስተዳድራል፡፡ በዚህ ሰፊ ክልል ውስጥ ያለውን ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች መፍታት ማለት በአገሪቱ የተጋረጡትን ችግሮች ከሞላ ጎደል መፍታት ተደርጎ እንደሚቆጠር ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሁለት ወራት የተቃውሞ ሠልፎች የተካሄዱ ሲሆን፣ ደም አፋሳሽ ግጭቶችም ተከስተው ነበር፡፡ ከሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች የሚገኙ መሆናቸውም ይታወቃል፡፡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ደግሞ በዚህ ግጭት ከሁለቱም ክልሎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከገርባ ጉራች እስከ አምቦ፣ ከሻሸመኔ እስከ ቡኖ በደሌና ሌሎች አካባቢዎች በነበሩት ግጭቶችም ቀላል የማይባል ንብረት ወድሟል፡፡ ከሰላሳ በላይ ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡
በአዳማ ከተማ በገልማ አባ ገዳ አዳራሽ ከመስከረም 19 እስከ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የተካሄደው የኦሕዴድ ሰባተኛ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ደግሞ፣ የተከሰቱ ችግሮች ይፈታል የሚል ዕምነት በብዙዎች ዘንድ ሰፍኖ ነበር፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኦሕዴድ አባላትና ደጋፊዎች ተገኝተው ነበር፡፡ ለአምስት ቀናት የቆየው የኦሕዴድ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ከዚህ በፊት ከነበሩ ኮንፈረንሶች ልዩ እንደነበር ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከባሌ ዞን ጎባ ከተማ አስተዳደር የመጡት አቶ በቀለ አሰፋ በዚህ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ ‹‹ሰባተኛው ኮንፈረንስ እስካሁን ከተካሄዱ ኮንፈረንሶች በይዘትም ሆነ በቅርፅ የተለየ ነበር፡፡ የቀረቡ አጀንዳዎች ከፍ ባለና ክልሉ አሁን ያለበትን ሁኔታ ባገናዘበ ደረጃ ተገምግመዋል፡፡ በውስጠ ድርጅት ግንባታዎች ላይ የነበሩ የኪራይ ሰብሳቢ አመለካከቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲሰበሩ አዲስ አቅጣጫ ተቀምጧል፤›› ብለዋል፡፡
በክልሉ ውስጥ በሚከሰቱ ግጭቶች መንስዔና ከሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው ግጭት መነሻ ላይ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦች መተማመን ላይ እንዳይደርሱና አገሪቱ ወደ ብተና እንድትሄድ የሚያደርጉ ሙከራዎች እንደነበሩና ይኼ፣ ችግር ሳይውል ሳያድር እንዲፈታና የአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል ኦሕዴድ ትኩረት ሰጥቶ መምከሩንም ገልጸዋል፡፡
ኮንፈረንሱ ከተቀመጠለት ጊዜ በላይ መርዘሙ ዋነኛው ምክንያት ከእህት ድርጅቶች ጋር ያለውን ግንኙነት ግልጽ ለማድረግና የነበሩ ብዥታዎችን ለማስተካከል እንደነበርም ገልጸዋል፡፡
በምሥራቅ ወለጋ የጌዶ ወረዳ የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታመነ ደመላሽ በበኩላቸው፣ በአገሪቱ ውስጥ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶችን መነሻ አድርጎ አንዱ አንዱን ጥሎ ለመሄድ ሩጫ እንዳለ፣ ኦሕዴድ ይኼንን ችግር ለመፍታት ወደ አንድነት በመምጣት ሰፊ ሥራ መከናወን እንዳለበት ውይይት መድረጉን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አንድነታችን እስካልተጠናከረ ድረስ በፌዴራሊዝም ሥርዓት ላይ ብዥታዎች እየተፈጠረና እየሰፋ ከሄደ አገሪቱ መበታተን ላይ ትደርሳለች፡፡ በመበታተን ደግሞ ሁሉም ተጎጂ ነው የሚሆነው በማለት ፌዴራሊዝም መሬት መንካት እንዳለበት ውይይት ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት በርካቶች ሕይወታቸው እንዳለፈና በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩት ደግሞ ከቀዬአቸው በተፈናቀሉ ሰዎች ሳቢያ፣ የመበቃቀል ድርጊት እንዳይፈጸም ጠንክሮ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡
ከምዕራብ ጎጂ ዞን ካብያ ወረዳ የመጡት አቶ ታሪኩ ጉዞ በበኩላቸው፣ ኦሕዴድ ባለፉት አምስት ዓመታት ያሳለፋቸውን ጉዞዎች እንደገመገመ ተናግረዋል፡፡ ከፌዴራሊዝም ሥርዓት ይበልጥ ተጠቃሚው የኦሮሞ ሕዝብ መሆኑንና ሥርዓቱን ለማስቀጠልም ትልቅ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
የኦሕዴድ ሰባተኛው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ በአዳማ ሲካሄድ በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔነት ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት የኦሕዴድ መሥራች አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድር፣ በቅርቡ በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንትና የኦሕዴድ ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮችና ሌሎች የድርጅት ኃላፊዎች ተገኝተው ነበር፡፡
በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቀው የገልማ አባ ገዳ አዳራሽ በማጠናቀቂያው ዕለት በኦሕዴድ አባላት ተጨናንቆ ነበር፡፡ በአቶ ለማ መገርሳ፣ በኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የተመራው የማጠቃለያ ዝግጅት ለየት ያለ እንደነበር ታይቷል፡፡
አቶ አዲሱ አረጋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኮንፈረንሱ ላይ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ለሕዝብ የተገባውን ቃል ከመተግበር አኳያ ተስፋ የሚሰጥ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ተስተውሏል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ በመሠረታዊነት የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ጥያቄዎችን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ቅደም ተከተሉን አስጠብቆና ሕዝቡን የመፍትሔ አካል አድርጎ መፍታት ይቻላል በሚል ስምምነት ላይ መደረሱን አቶ አዲሱ ጠቁመዋል፡፡
በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የመነቃቃት ስሜት እየተፈጠረ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አዲሱ፣ ስሜቱን ማጠናከርና በአዲሱ አመራር ላይ እየጣለ የመጣውን ተስፋ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ ላይ ርብርብ ለማድረግ መግባባት እንደተፈጠረ ገልጸዋል፡፡ ይኼንን የመነሳሳት ስሜት ለአገሪቱ ሰላምና ብልፅግና በሚውልበት መንገድ ላይ አቅጣጫ መቀመጡንም አክለዋል፡፡
ሌላው የውይይቱ ጭብጥ ሆኖ የተወሳው የኅብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ግንባታው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለኦሮሞ ሕዝብም ሆነ አገር ወሳኝ መሆኑን፣ ከዚህ ሥርዓት ውጪ ሌላ አማራጭ ሊኖር እንደማይችል ውይይት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ሆኖም በፌዴራሊዝም ሥርዓቱ በርካታ ችግሮች እያጋጠሙን ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች የሥርዓቱ ችግሮች አድርገን መውሰድ የለብንም፡፡ በግልጽነት፣ በኃላፊነትና በመደማመጥ ስሜት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚያጋጥሙንን ችግሮች እየፈታን ወደፊት መራመድ አለብን የሚል ድምዳሜ ነው የተያዘው፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ሕገ መንግሥቱ ለዜጎች የሚያጎናጽፋቸው መብቶች ሳይሸራረፍና በተሟላ መንገድ ተግባራዊ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ፣ በየደረጃው ያለው አመራር ጠንካራ ትግል ማድረግ እንዳለበት ማሳሰቢያ መስጠታቸውም ታውቋል፡፡
የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በበኩላቸው፣ በጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ወቅት የተለዩ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለመሸከም በተለመደው ድርጅታዊ ቁመና ስለማይቻል፣ የአሥር ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መነደፉን ለኮንፈረንሱ አባላት ገልጸዋል፡፡ የድርጅቱ አባላትና አመራሮች ይኼንን ዕቅድ መሠረት አድርገው በክልሉ የሚነሱ ሁለንተናዊ ችግሮችን ጊዜ ሳይሰጡ መፍታት ተገቢ እንደሆነ አስምረውበት እንዳለፉ ተጠቁሟል፡፡ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ችግር መሸከም የሚያስችል ቁመናና ተተኪ አመራር ለመፍጠር ሲባል ዕቅድ መዘጋጀቱንም አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በአሁኑ ወቅት ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አዲሱ አመራር ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለና አሁንም ቀሪ አራት ሚሊዮን ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ እንደያዘ ተገልጿል፡፡
በክልሉ የተወሰኑ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችና የተቃውሞ ሠልፎች አንደኛው ምክንያታቸው ከፍትሕ መጓደል ጋር የተያያዘ እንደሆኑ ሲነገር ይደመጣል፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በኮንፈረንሱ ውሳኔ እንደተላለፈም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኦሕዴድ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ‹‹በኮንትሮባንድ ይሁን፣ በሕገወጥ ዘረፋ፣ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር የሕዝቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያጎድሉ ነገሮችን እንታገላለን የሚል አቋም ተወስዷል፤›› ብለዋል፡፡
የኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎችና ኮንትሮባንዲስቶች ክልሉን የሁከትና የግርግር ማዕከል ለማድረግ የተለያዩ ሴራዎችን ሸርበው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ አዲሱ፣ በዚህ በፈጠሩት ሴራም ሠልፎችና ግርግሮች ተፈጥረው የዜጎች ሕይወት እያለፈ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ አልፎም በወንድምና በእህት ሕዝቦች መካከል ግጭት የማስነሳት ምልክቶች እየታዩ ስለሆነ፣ ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ ለማድረግ ሕዝባችንን አስተባብረን ይኼን ሴራ በማጋለጥ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ስለዚህ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች በሙሉ ያለምንም ሥጋት ሠርተው መኖር እንዲችሉ ለማድረግ ነው የታቀደው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹የተከለከሉ ሠልፎችን በማስተባበር፣ ገንዘብ በመመደብና የተከለከሉ ሰንደቅ ዓላማዎችን በመጠቀም ሕዝቡን ለመቀስቀስ፣ በአንዳንድ ቦታዎች እንዲያውም በገንዘብም ጭምር በመግዛት ሠልፎች እንዲካሄዱ አድርገዋል፡፡ ሁከትና ግርግር እንዲፈጠርና ከዚያ በኋላ ደግሞ የወንድሞቻችንን ሕይወትና አካል በማጉደል ለዘመናት አብረው በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር ሠርተዋል፡፡ ይኼን ከመሠረቱ የሚንድና በልማታዊ አስተሳሰብ የሚተካ አሠራር ኦሕዴድ ዘርግቶ እየሠራ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የእነዚህን አካላት ማንነት በኮንፈረንሱ ወቅትም በግልጽ አልተነገረም፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የኦሕዴድ ሰባተኛው ኮንፈረንስ በተጠናቀቀ ማግሥት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች (የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ) አባ ገዳዎች፣ ሽማግሌዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ ቡድን ወደ አማራ ክልል መዲና ባህር ዳር አቅንቷል፡፡ ይኼ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል የሚካሄደው የሕዝብ ለሕዝብ የትስስር መድረክ፣ የመጀመርያው እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡
ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በባህር ዳር ለማካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት የሁለቱ ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ ላይ የሁለቱ ሕዝቦች አንድነትና ለኢትዮጵያ ስለከፈሉት መስዋዕትነት፣ ለሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ተግዳሮቶች ላይና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡ ኮንፈረንሱን አቶ ለማና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደሚመሩት ታውቋል፡፡
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው፣ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የሚደረገውን የትስስር መድረክ ለመካፈል ወደ ባህር ዳር የመጣውን ልዑካን ቡድን የክልሉ ሕዝብ በየቦታው አቀባበል እንዳደረገለት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
በዚህ ኮንፈረንስ ላይ አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ምርቃትና የተለያዩ ድምፃውያን አዝናኝ ፕሮግራሞቻቸውን እንደሚያቀርቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል የተወጣጡ አባገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አርቲስቶችና ወጣቶች ወደ ባህር ዳር ያቀኑት ‹‹አንድ ነን አንለያይም›› በሚል መፈክር ነው፡፡ በቅርቡ ደግሞ የአማራ ክልል የሕዝብ ተወካዮችና ከፍተኛ አመራሮች በኦሮሚያ ክልል ተመሳሳይ ኮንፈረንስ እንደሚያካሄዱ ታውቋል፡፡