Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ይድረስ ለሪፖርተርየአገራችን የወቅቱ ችግሮችና መፍትሔዎች

  የአገራችን የወቅቱ ችግሮችና መፍትሔዎች

  ቀን:

  የአገራችን ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡና እየሰፉ ቢመጡም፣ በመንግሥት በኩል ግን ለችግሮቹ ትኩረት ባለመስጠት ነገሮች ወደ አሳሳቢ ደረጃ እየደረሱ፣ ሕዝብም  ሥጋት ላይ በመውደቅ ለህልውናው ዋስትና እያጣ ነው፡፡

  ችግሮቹን አስመልክቶ ለመንግሥት ጠቃሚ አስተያየቶችና ምክሮች በባለሙያዎችና ምሁራን እየተጠኑ በተለያዩ ጊዜያት ቢቀርቡም፣ የሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ የተለያዩ የግል ሚዲያዎች በተለይ በርዕሰ አንቀጾቻቸው ሐሳብ ሲሰጡ ቢቆዩም፣ በመንግሥት በኩል ጥናት በግብታዊትና ሕዝብ ሳይመክርባቸው በሚወሰዱ ዕርምጃዎች ችግሮች እየተባባሱ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ የማስፋፊያ ማስተር ፕላን እንዲሁም በቅርቡ የብር ምንዛሪ ማሻሻያ ከብዙዎቹ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ ግን አሳማኝ ያልሆኑ ምክንያቶችን ከመደርደር ባሻገር የኃይል ዕርምጃዎችን ጭምር ሲወስድ እየታየ ነው፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል በተከሰተው ግጭት የበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ መጎዳትና መፈናቀል በክልሎቹም ሆነ በፌዴራል ደረጃ መንግሥት የለም ወይ የሚያሰኝ የሕዝብ እሮሮ እየተደመጠ ነው፡፡

  በአገራችን የሚታዩ ችግሮች ምንድን ናቸው?

  አንደኛ የመጻፍ፣ የመናገር፣ የመሰብሰብና በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ዕጦት መባባስ አንዱ ነው፡፡ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት ለመግለጽ በመሞከራቸው ምክንያት መንግሥት የፀረ ሽብር አዋጅ በማወጅ ሽብርተኛ እያለ የሚከሳቸውና የሚያስራቸው ብሎም በእስር ወቅት ልዩ ልዩ ጥቃት እየተፈጸመባቸው መሆኑ እየታየ ነው፡፡

  ሌላኛው ችግር የሥራ አጡ ቁጥር በየጊዜው መጨመር ነው፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶች ቤት መዋላቸው እየተበራከቱ ለመጡት ችግሮች አንዱ መገለጫ ነው፡፡

  በዋጋ ግሽበት ምክንያት የምግብና የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ፣ የኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሲሆን፣ በነጋዴው ኅብረተሰብ ላይ የግብር ጫና ማድረጉና በዚህም ምክንያት የሕዝቡ እሮሮ እየባሰ መምጣት መንግሥት ሊመለከታቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው፡፡

  ሌላው ችግር ቀደም ሲል በነበሩት መንግሥታት እንኳ እንብዛም ያልተከሰተና ያልተለመደ ነገር ግን በየአካባቢው እያቆጠቆጠ ያለው ብሔር ተኮር ግጭት ነው፡፡ የዜጎች በገዛ አገራቸው መገደልና መፈናቀላቸው እየታየ ነው፡፡ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል የሚኖሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ እንደ ጉራፈርዳ፣ ይርጋ ጨፌ፣ ኮንሶ ካሉት አካባቢዎች የተፈናቀሉት በርካታ ዜጎችም ይታወሳሉ፡፡

  ከአገር የሚሰደዱ የዜጎች ቁጥር በየጊዜው መጨመርና የአገሪቱ ገጽታ እየጎደፈ መምጣት ብሎም መንግሥት ያሉበትን መሠረታዊ ችግሮች ተረድቶ ሊቀርፋቸው ባለመቻሉ ስደቱ ሊቆም አልቻለም፡፡

  በመንግሥት አመራር ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች በከፍተኛ ሁኔታ በሙስና መዘፈቅና የተጠያቂነት አሠራር አለመኖር እየታየ ነው፡፡ ለማስረጃ ያህል የስኳር ፕሮጀክቶች በብድር በተገኘ ገንዘብ እንዲገነቡ ሲጠበቅ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሆን ተብሎ መባከኑና መመዝበሩ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

  የጠባብ ብሔርተኝነትና የክልላዊነት አመለካከት ጎልቶ መታየትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲደበዝዝ የሚደረገው አጉራዘለልነት ሊታይ ይገባዋል፡፡

  የትምህርት ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በሚገኝበት ወቅት በመንግሥት በኩል አሁን ድረስ ብዛት ላይ ትኩረት ያደረገ አካሄድ መከተል እየታየ ነው፡፡

  በአንዳንድ ክልሎች ተደጋጋሚ ድርቅ በመከሰቱ የዜጎች በምግብ እጥረት መጠቃት፣ የእርሻ ሥራው ውጤት በዝናብ ላይ መመሥረቱና በሕዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት የአንድ ቤተሰብ የእርሻ መሬት መጠን እየቀነሰ መምጣቱ ሊገታ አልቻለም፡፡

  በመንግሥት አመራርነት ቦታ ላይ የሚመደቡ ሰዎች በልምድ፣ በችሎታና ዕውቀት ሳይሆን በፖለቲካ ታማኝነት የሚመደቡ በመሆናቸው የመልካም አስተዳደር ዕጦት መስፋፋቱ የመንግሥት ጉልህ ችግር ነው፡፡

  ከዚህ በላይ የተጠቃቀሱት ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለማቃለል በመንግሥት በኩል መወሰድ ስለሚገባቸው ዕርምጃዎች የሚከተሉት የመፍትሔ ሐሳቦች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

  አንደኛ የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማለትም የመጻፍ፣ የመናገር፣ ሐሳብ በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብቶችን ማክበር፣ ማስከበር ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ፣ በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ፣ ቃታ ያልሳቡ ነገር ግን ሽብርተኛ እየተባሉ የታሠሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በአጠቃላይ የፖለቲካ እስረኞችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት ይገባል፡፡

  ሰላማዊም ሆነ የትጥቅ ትግል ከሚያካሂዱ ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ምንም ቅድመ ሁኔታ ግንኙነት በመፍጠርና በሠለጠነ መንገድ የጠረጴዛ ዙሪያ ሰላምን በሚፈጥር ሁኔታ ድርድር ማካሄድ፣ ኢሕአዴግም ለዚህ እንቅስቃሴው የግትርነት አቋሙን በማሻሻል በሰጥቶ የመቀበልን መርኅ መከተል ይጠበቅበታል፡፡

  በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታየውን ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ ኢንዱስትሪዎችንና የሰብል ምርት የሚያመርቱ ሰፋፊ የግል እርሻዎችን ማስፋፋት፣ ለዚህም እንዲረዳ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ማበረታታት፣ የፓርቲና የመንግሥት የንግድ ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወር ይጠበቅበታል፡፡ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ብዛት ከአገሪቱ ዕድገት ጋር በማጣጣም የሚሰጠውም ትምህርት ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡

  በየጊዜው እየጨመረ ያለውን ኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ለሠራተኞችና ለጡረተኞች ደመወዝና አበል የመጨመር ጥረት ሲደረግ ይታያል፡፡ የዚህ ዓይነቱ አሠራር ግን በሰዎች እጅ የሚዘዋወረው ገንዘብ በጨመረ ቁጥር በርካታ ገንዘብ ጥቂት ሸቀጦችን በማሳደድ የዋጋ ግሽበቱን እንደሚያባብስ በተጨማሪም በቅርቡ የብር ምንዛሪ መጠን በ15 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው የኑሮ ውድነቱ በመባባስ ላይ ነው፡፡

  ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆነው መንግሥት ከውጭ የሚያስገባው በነዳጅ፣ በስንዴ፣ በስኳር እንዲሁም በምግብ ዘይት ላይ በቂ ድጎማ በማድረግ በኑሮ ውድነት መንግሥትን እያማረረ የሚገኘውን ሕዝብ ሊታደገው ይገባል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል ያላግባብ ወደ ውጭ በባለሥልጣኖችና በግለሰቦች የሚሸሸውን የውጭ የምንዛሪ በቁርጠኝነት መቆጣጠር እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ ወይም በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ የሚላኩና የሚገቡ ሸቀጦችን መከላከል፤ በዚህ ሥራ በሕግ በ15 በመቶ እንዲቀንስ የተረገውን የብር ምንዛሪ ተመን፣ በአሥር በመቶ እንዲጨምር በማድረግ የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኙ ምርቶች ላይ እሴት እየጨመሩ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ገቢን በማሳደግ ላይ መንግሥትና ሕዝቡ እንዲረባረቡ ማድረግ ይገባል፡፡

  በየአካባቢው እየተባባሰ የሚታየውና ብሔር ላይ ያተኮረውን ግጭት ለማወስገድ ከመነሻው በጠባብ አመለካከት የሚንቀሳቀሱ፣ በየክልሉ የሚገኙ አመራሮችም ሆነ ግለሰቦች በቅርብ በመቆጣጠር ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ተቀራርቦ በአንድነቱ በሰላም ተዋዶ እንዲኖር መሥራት ይገባል፡፡ የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ስለኢትዮጵያዊነትና ስለአንድነት አስፈላጊውን ቅስቀሳ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በየትኛውም ክልል ለሚነሱ ግጭቶችም ሆነ የሰዎች መፈናቀል የክልል አመራሮች ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል የመኖርና ሀብት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብቱ በተግባር የተረጋገጠ እንዲሆን የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት እንዳለበትና ተጠያቂ እንዲሆኑም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚውን በአንክሮ መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡

  እየተስፋፋ የመጣውን ሙስና በጥልቀትና በቆራጥነት ለማስወገድ በተለይ በሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ ትልልቅ ሕንፃ ገንብተው የሚያከራዩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር ሆነው ምርመራ ተካሂደባቸው ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንደምናየው ማስረጃ የለም እየተባለ በማድበስበስ ትላልቆቹን ዓሳዎች ላለመንካት በትናንሾቹ ላይ መረባረብ ‹‹አህያውን ፈርቶ ዳውላውን›› የሚያሰኝ ነው፡፡ መንግሥት የፀረ ሙስና ትግሉን በጥልቀት እያካሄዱኩ ነው የሚልበት አግባብ ከፕሮፓጋንዳ ሊያልፍ ባለመቻሉ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ስለዚህ ትግሉ ከዓሳው ጭንቅላት መጀመር አለበት፡፡

  መንግሥት ኃላፊነት ቦታ ላይ የሚመደቡ ሰዎች በክልል ወይም በፖለቲካ ታማኝነት መሆኑ ቀርቶ፣ በችሎታ፣ በዕውቀትና በልምድ እየተመዘኑ ቢሆን፣ በአገሪቱ በስፋት እየታየ ያለውን የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሊቀርፍ ይችላል፡፡ ከዚህ በላይ ያቀረብኳቸው የአገራችን ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦች አዲስ አይደሉም፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት በግትርነት አቋሙ ከሕዝብ ለሚቀርቡ ገንቢና ጠቃሚ አስተያየቶች ትኩረት ባለመስጠቱ ግን የአገሪቱ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በመምጣት ላይ በመሆናቸው እኔም የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት ባለችኝ አነስተኛ ዕውቀት ይኼንን አስተያየት ሰንዝሬያለሁ፡፡ የመንግሥት ለውጥ እንደ ቦትስዋናና እንደ ጋና ፍትሐዊና ተዓማኒ በሆነ የሕዝብ ምርጫ የሚሆንበትን ጊዜ በሕይወቴ ለማየት እናፍቃለሁ፡፡ ኢሕዴግም በምርጫ ተሸንፎ ሥልጣኑን እንደሌሎች አፍሪካውያን መንግሥታት በሰላማዊ መንገድ ቢያስረክብ እንደ ዴሞክራሲ ጀግና እቆጥረዋለሁ፡፡

  (ማቴዎስ ሸመሎ፣ ከሐዋሳ)

  ***

  በመንግሥት ዕርምጃ የተወሰደባቸው ፀረ ኮንትሮባንዲስቶች እንጂ ዋናዎቹ ተዋናዮች አይደሉም

  ሥልጣናት ስለሚመሩት መሥሪያ ቤት የሥራ አፈጻጸም አስመልክተው ብዙውን ጊዜ ሲናገሩ፣ በገሃድ ካለው እውነታ ጋር እጅጉን የተራራቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተጨባጭ የተሠራውና በሪፖርታቸው የሚቀርበው ሲታይ በቁጥር አለያም በዓይነት የሚለያይ በመሆኑ፣ በውስጥ ሠራተኞቻቸውና በተገልጋይ ላይ ግርታ ሲፈጠር ይታያል፡፡

  ለሪፖርታቸው መጣመም ምክንያት ከፈለግን በየደረጃው አልፎ ቢሯቸው በሚደርሰው የሐሰት ሪፖርት እየተመሩና ይኼንንም በሚያደርጉ አሳሳች የበታች ሹማምንቶቻቸው ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ቆራጥ ባለመሆናቸው የተነሳ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

  ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ በቅርቡ የኮንትሮባንድ ንግድ በአገሪቱ መስፋፋቱን አስመልክቶ ኃላፊነቱ የተሰጣቸው መሥሪያ ቤቶች በአዳማ ከተማ ተሰብስበው እንደነበር በሪፖርተር ጋዜጣ ያነበብኩት ዜና ነው፡፡

  ስለ ኮንትሮባንድ ንግድ ያለከልካይ መስፋፋት፣ አሁን በተጨባጭ ምን መልክ እንዳለው፣ በአገር ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት፣ ስለዋናዎቹ ተዋናዮቹ (አስተላላፊዎችና ተባባሪዎቻቸው) ሚና ምን እንደሚመስል በስፋት በሌላ ጽሑፍ እመለስበታለሁ፡፡

  ለዛሬ ግን በዚሁ የአዳማ ከተማ ስብሰባ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ክቡር አሰፋ ዓብዩ መሥሪያ ቤታቸው ለሕገወጥ ንግዱ ተባባሪ ናቸው ባለቸው 80 አባላት ላይ ዕርምጃ መውሰዱን መናገራቸውን ሳነብ፣ እኚህ ባለሥልጣን በእርግጥም ፍጹም በተሳሳተ ሪፖርት ላይ ተመርኩዘው እንደተናገሩ ተረድቻለሁ፡፡

   ከቡድን እስከ ዳይሬክቶሬት በተዘረጋ መረብ እየታገዘ በየዕለቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የኮንትሮባንድ ዕቃ ይገባል፣ ይወጣል፡፡ እኔ በተጨባጭ እንደማውቀው በጥቅም ተሳስሮ ለኮንትሮባንድ ተባባሪ ሆኖ የግል ሀብቱን የሚያፈራው ሳይሆን፣ ሥራዬና ተልዕኮዬ ነው ብሎ ኮንትሮባንድን በመከላከል ለመሥሪያ ቤቱ ውጤት የሚያስገኘው እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ዕርምጃ እየተወሰደበት ነው፡፡ ለዚህም ማስረጃ የሚፈልግ ካለ ለማቅረብ ዝግጁ ነኝ፡፡ በመሆኑም ክቡር ኮሚሽነር አሰፋ ዓብዩ ሊያውቁት የሚገባው ሀቅ፣ ዕርምጃ ተወሰደባቸው ተብሎ ሪፖርት የቀረበላቸው 80 አባላት አብዛኛዎቹ ሥራቸውን በተገቢው መንገድና በዓላማ ጽናት በመፈጸማቸው ብቻ ለጥቅመኛው ቡድን እንደ ሥጋት ተቆጥረው በግምገማ የሐሳብ ውንጀላ የቀረበባቸው ናቸው፡፡ ይኼንን ለማረጋገጥ አሁን በሥራ ላይ (በተለይ ጅጅጋና ሐረር) ያሉትን ሀብትና ንብረት ማየት ብቻ ይበቃል፡፡ ያን ጊዜ 80 ንጹሐን ተባረው 800 ሌቦች በመቅረታቸው የኮንትሮባንድ ንግድ አሁን እንደአሸን መፍላቱን ይረዱታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ለችግሮች እውነተኛ መፍትሔ ለማግኘት እንዲቻል በሐሰት ሪፖርት መመርኮዝ ይብቃ እላለሁ፡፡

  (ሳጅን ደነቀው ሞላ፣ ከምሥራቅ ኢትዮጵያ)

  spot_img
  Previous articleየሳምንቱ ገጠመኝ
  Next articleበለስ
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...