በውብሸት ሙላት
ሰሞኑን የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ራሱ የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም የሚመለከት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት በፌስቡክ ገጻቸው የሚያሰራጯቸው መልዕክቶችና የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሥርጭት ዋነኛ አጀንዳዎች ሆነዋል፡፡ የቴሌቭዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎቹ የመንግሥትንም የግልንም የሚመለከቱ ናቸው፡፡
የማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚጠቀምና ሌሎች ተጠቃሚዎች የሚጽፏቸውን ወይም የሚጭኗቸውን ጽሑፎች፣ ምስሎችና ድምጾች ለሚከታተል ሰው፣ አልፎ አልፎ ጥላቻን ያዘሉ ንግግሮች ማስተዋል የሚቻል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር፣ በርካታ በጎ ዕሴቶችን በፍጥነት ሊያወድም እንደሚችል እሙን ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር፣ አድልኦና መገለልን ብሎም እጅግ አደገኛና ዘግናኝ ወንጀሎችን ሊያስከትል እንደሚችል ታሪክ ምስክር ነው፡፡
ከሰለባዎቹ አንፃር ሲታይ የጥላቻ ንግግሩ የሚፈጸመው፣ ብሔርን መሠረት አድረጎ፣ የሃይማኖት ተከታዮችን፣ ስደተኞችንና ሌሎች ቡድኖች ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ በጥላቻ ንግግር ምክንያት በተለያዩ አገሮች የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ተከስተዋል፡፡
የጥላቻ ንግግርም ቡድናዊ ቅርፅ ለመያዝ በእጅጉ የተጋለጠ ነው፡፡ ታሪክም ያሳየን ይኼንኑ ነው፡፡ በርካታ አገሮች ከራሳቸውም ገጠመኝም ይሁን ከሌሎች የታሪክ ጠባሳ በመማር የጥላቻ ንግግሮችን የሚከለክሉ ሕግጋት አውጥተዋል፣ ተግባራዊ ለማድረግም ተቋማትን አደራጅተዋል፡፡
በኢትዮጵያም በተለይ ብሮድካስተሮች የሚሰራጩ ፕሮግራሞችን በተመለከተ በቅድሚያ የመከታተልም እንደ ሕጉ መንቀሳቀሳቸውን የመከታተል ሥልጣንና ተግባር የተጣለበት ለብሮድካስት ባለሥልጣን ነው፡፡ ከሰሞኑም፣ በግልም በመንግሥትም በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተላለፉ ፕሮግራሞችን መነሻ በማድረግ የተለያዩ ሐሳቦች በመገናኛ ብዙኃን ተላልፈዋል፡፡
የብሮድካስት ባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተርም መገናኛ ብዙኃን ላይ የተለያዩ የማሻሻያ ፕሮግራሞች ማድረግ የሚያስችላቸውን ሥልጠና እንደሚሰጥ አሳውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይኼንኑ አረጋግጠዋል፡፡ እንግዲህ ለዚህ መነሻ ከሚሆኑት ምክንያቶች የሚያስተላልፉት ፕሮግራሞች ይዘት ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም ይሁን ሌሎች ተቋማት የጥላቻ ንግግር ምንነቱን፣ ይዘቱን፣ መንስዔውን፣ መዘዙንና ሌሎችም ጭብጦች ላይ በመመርኮዝ ጥናት ያጠናሉ፣የፍትሕ ተቋማትን እንደሌሎች አገሮች የማሠልጠን፣ ሕዝብን የማንቃት ሥራ ቢፈጽሙ፣ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ሕዝቡም በሰላምና በመቻቻል የመኖር ዕሴቱን ይበልጥ ያጎለብተዋል፡፡
ሚዲያዎችና ሐሳብን የመግለጽ መብት
አንዳንድ ጊዜ ውዥንብር የሚመጣው ሐሳብን በነፃነት ከመግልጽና ገደቦቹን በቅጡ ካለመለየትም ስለሚሆን ከሕገ መንግሥቱ በመጀመር ተያያዥ መብቶችን ከገደቦቹ ለመለየት ይቻል ዘንድ የተወሰኑ ነጥቦችን እናንሳ፡፡
በዋናነት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መነሻው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ አንቀጽ 29 ሙሉ በሙሉ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ ጋር የሚያያዙ መብቶችንና ግዴታዎችን የሚገልጽ ነው፡፡ በመጀመሪያው ንዑስ አንቀጹ ላይም ማንም ሰው የመሰለውን አመለካከት የመያዝ መብት ያለው መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ለማስጠበቅ በመንደርደሪያነት የሚያገለግል ነው፡፡
ከዚያ ውጭ ማንም ሰው የመሰለውን ሐሳብና አመለካከት የመያዝ ወይም የመጣል መብትን በተመለከተ ጥበቃ ቢደረግለትም ባይደረግለትም ብዙም ለውጥ አያመጣም፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው የመሰለውን፣ ያመነበትን፣ የፈለገውን ወዘተ አመለካከት ቢይዝና ሌላውን ቢተው ሌላ አካል በግዳጅ በተቃራኒው የሆነን ሐሳብና አመለካከት እንዲይዝ ወይም እንዲጥል ማድረግ የሚቻል ባለመሆኑ ነው፡፡ በዋናነትም ውስጣዊ ነው፡፡ መቼም ቢሆን መገደብ የሌለበት መብት ነው፡፡
ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ተግባራዊ ለማድረግ ከሚያገለግሉ ከመገናኛ ብዙኃን ውስጥ በተለይ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ሥርጭቶች በተደራሽነታቸውም ይሁን በሚፈጥሩት ተፅዕኖ ከሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች የላቀ ነው፡፡ ተፅዕኖው አዎንታዊም አሉታዊም ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንኑ በመረዳት መንግሥትም ይሁን ሌሎች አካላት የመሰላቸውን አመለካከት ለማስተላለፍ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ከሚፈጥሩት ተፅዕኖ አንፃር አገሮች ከሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በተለየ ሁኔታ ጥብቅ ሕግ አበጅተው፣ ደንብ ቀርፀው፣ አሠራር ዘርግተው እንደሚያስተዳድሩት የታወቀ ነው፡፡
የዩኔስኮ (UNESCO) የብሮድካስቲንግ የአሠራር መመርያም የተፅዕኖውን ደረጃ ካስረገጠ በኋላ ደንብ የማስፈለጉን ጉዳይ በተመለከተ ሁለት ዓቢይ መነሻዎች እንዳሉት ያስረዳል፡፡
የመጀመሪያው የሚገናኘው ከዴሞክራሲ ጋር ነው፡፡ አገሮች የሚፈልጉትን ማኅበረሰብ ለመቅረፅ፣ የዴሞክራሲ ባህል ለመገንባት ይቻል ዘንድ ጥበቃም ደንብም ያስፈልገዋል፣ የሚል ይዘት አለው፡፡ ሁለተኛው አመክንዮ ኢኮኖሚያዊ ነው፡፡ ንግድም፣ኢንቨስትመንትም ሌሎችም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማሳለጥና ለማበረታታት ከሚኖረው አስተዋጽኦ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ምክንያቶች ይህንን ዘርፍ በአግባቡ መተዳደር ያለበት መሆኑን ለማስረዳት የቀረቡ ናቸው፡፡ አሉታዊውን በመቀነስ አዎንታዊውን ለማጎልት የሚረዱ የሕግና የሥነ ምግባር ደንቦችን መተግበርም ማስተዋወቅም የተጀመረው እነዚህ ሚዲያዎች ሲፈጠሩ ጀምሮ ነው፡፡
ከላይ የተገለጹት ዴሞክራሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች እንደተጠበቁ፣ መብቶች ስለሚገደቡባቸው ቅድመ ሁኔታዎች የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦችን በአስረጅነት የሚያቀርቡ አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱና በሰፊው የሚታወቀው ‘የጉዳት መርሕ’ ነው፡፡ በዚህ መርሕ መሠረት መብት ሊገደብ የሚገባው የሌላን ሰው መብት የሚጎዳ ከሆነ ነው፡፡ የገደቡ ምክንያት ሌሎችን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲባል ነው፡፡ የራስን ሐሳብ በሚያስኬደው መጠንና ጥግ ድረስ ለመግለጽ እንጂ ሌላ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚሰጥ ጥበቃ መሆን እንደሌለበት ይገልጻል፡፡
ሌላው፣ የጥፋት መርሕ የሚባለው ነው፡፡ ለማኅበረሰቡ ጥፋት ወይንም የወንጀል ባሕርይ ካለው ማለትም ንግግሩ የሚመለከተው ሰው መጠን፣ የተነገረበት ወቅት እንዲሁም፣ የተናጋሪውን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ማኅበረሰቡን ማስቀየሙን ወይም ጥፋት መሆኑን ብሎም ከመገደብ በመለስ በሌላ መንገድ ማስቀረት የማይቻል ከሆነ ሊገደብ እንደሚገባው የሚያስረዳ መርሕ ነው፡፡ በመሆኑም እንዲህ ዓይነቱን ወንጀል ማድረግ ሌሎችን ይታደጋል፡፡
የብሮድካስት አገልግሎት በሕገ መንግሥቱ ላይ አንቀጽ 29 ላይ የተገለጸውን የዜጎችን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና መረጃ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ ሁነኛ ዘዴ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ማንኛውም ሚዲያ ደግሞ ሊተላለፋቸው የማይችላቸው ገደቦች አሉበት፡፡ እነዚህ ገደቦችም በዋናነት በሕገ መንግሥቱ በዚሁ አንቀጽ ላይ ተዘርዝረዋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6) ላይ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንደተገለጸው ሐሳብን በፕሬስና በማናቸውም መገናኛ ብዙኃን ማንኛውም ሰው ሲገልጽ የሐሳቡ ይዘት ምንም ይሁን ምን፣ ሐሳቡ በመገለጹ የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ መከልከል አይቻልም፡፡
የብሮድካስት አገልግሎት ሰጭዎችን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕግ የሚገደብባቸው ‘የወጣቶችን ደኅንነት የሚያናጉ፣ የግለሰብን መብት የሚጥሱና ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫ ማድረግ፣ የጦርነት ቅስቀሳ ማድረግ’ ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከአራቱ ውጪ በሌሎች ምክንያት ፈጽሞ ሐሳብን በነፃነት በማናቸውም የፕሬስ ውጤቶችም ይሁን በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዳይገለጹ መከልከል ወይም ወንጀል ማድረግ ፈጽሞ ከሕገ መንግሥቱ ውጭ ነው፡፡
ከላይ ከተገለጹት አራት መሠረታዊ ገደቦች በስተቀር በአገሪቱ በየትኛውም ደረጃ ላይ የሚገኝ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው አካል ይዘቱን መሠረት ያደረገ ሐሳብን በነፃነት መግለጽን የሚገድብ ሕግ ማውጣት አይችልም፡፡ አራቱ በተራቸው ወደ በርካታ ዝርዝር ክልከላ ሊመነዘሩ ይችላሉ፡፡ ሲመነዘሩ ቢኖሩም ግን የግለሰብን መብትና ሰብዓዊ ክብር፣ እንደቡድን የወጣቶች አስተዳደግን የሚመለከት፣ እንደተቋም ደግሞ ከጦርነት ቅስቀሳን የሚመለከቱ ብቻ መሆን አለባቸው፡፡
ሕገ መንግሥቱ፣ የሚተላለፈው ሐሳብ የሚያስከትለውን ውጤት በማሰብ የሐሳብን ነፃነት በሕግ መገደብ እንደማይቻል ይገልጻል፡፡ በመሆኑም በሕትመትም ይሁን በሌላ መንገድ የሚገለጽ ሐሳብ መንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖር ወዘተ በማለት ወንጀል ማድረግን ሕገ መንግሥቱ ፈጽሞ አይፈቅድም፡፡
ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ሲከተለው ከነበረው ፖሊሲ አኳያ መገናኛ ብዙኃን የሚጠበቅባቸውን ያህል ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም የሚገባውን አስተዋጽኦ ሊያደርግ አልቻለም፡፡ ይህ ከእንደገና ተመልሶ የፈጠረው ችግር መኖሩን መረዳት ቀላል ነው፡፡ በተለይ ሚዲያዎች መቻቻልን ከማጎልበት ዴሞክራሲን ባህል ከማድረግ አንፃር የሚዲያዎቹ መኮስመን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚተላለፉትን የተወሰኑ መልዕክቶችን በቀላሉ መግራት ሳይቻል እንዲቀር አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡
የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎችና ሕጉ
የሬዲዮ ሥርጭት 75፣ የቴሌቪዥን ደግሞ 50 ዓመታት አልፏቸዋል ከኢትዮጵያ ጋር ከተዋወቁ፡፡ በማናቸውም መለኪያ ቢመዘኑ የዕድሜያቸውን ያህል ዕድገት አላሳዩም፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመንግሥት እንጂ የግል ሬዲዮም ቴሌቪዥንም የለም ነበር፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከነበረው ሃይማኖታዊው የሉትራን ሬዲዮ (ብሥራተ ወንጌል) በስተቀር፡፡ አሁን ላይ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ፈቃድ አግኝተው ሥራ ላይ የሚገኙ 20 የብሮድካስት ሚዲያዎች አሉ፡፡ ይህ ቁጥር፣ ከውጭ የሚተላለፉትን የሃይማኖትና ሌሎች የመዝናኛ የብሮድካስት ሚዲያዎችን አይጨምርም፡፡ እንዲሁም፣ በኤሌክትሮኒክ ብቻ የሚሰራጩ የብሮድካስት አገልግሎቶችን አይዝም፡፡
ከሚፈጥረው ተፅዕኖ አንፃር የብርድካስተሮች ለረጅም ዘመናት ሳይስፋፉ መቅረታቸው ጉዳታቸው ያው ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ መገንባት ላይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለዚያም ነው የብሮድካስት አገልግሎት አዋጁ ቁጥር 533/1999 ዓ.ም. ከዴሞክራሲ ጋር የተያያዙ መርሆችን የዘረዘረው፡፡
አዋጁ በመርህነት ካስቀመጣቸው ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያንጸባርቅና ሚዛናዊ መሆን አንደኛው ነው፡፡ ለሥርጭት የሚቀርብ ማንኛውም ፕሮግራም ከይዘት አኳያም ይሁን ከምንጭ ትክክል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የሚሰራጨው ፕሮግራም ዜና ከሆነም በቅድሚያ ዜናው እውነትም ትክክልም መሆን አለበት፡፡ ትክክልና እውነት መሆን ብቻ አይበቃም፤ ሚዛናዊና ከአድልኦ የፀዳ መሆን አለበት፡፡ ብሮድካስተሮች እነዚህን መርሆችን የመከተልና የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡ መፈጸም ያለባቸው ተግባራት ናቸው፡፡
በብሮድካስት አዋጁ ላይ የተጣሉበትን ግዴታዎች ያልተወጣ ወይም የጣሰ ብርድካስተር ሥርጭት ከመስጠት በጊዜያዊነት ሊታገድ ይችላል፡፡ ከመታገድ አልፎም ሙሉ በሙሉ ፈቃዱ ሊሰረዝም ይችላል፡፡ ፍቃድ የሚያሰርዙ በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ከአዋጁ መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ተገቢነት ያላቸውን ምክንያች ብቻ ከአዋጁ አንቀጽ 30(4) ላይ እንጥቀስ፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው ብሮድካስተሮች የሚያሰራጩት ፕሮግራሞች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ግዴታዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ብሮድካስተር እንዳይፈጽሙ የተከለከሏቸው ተግባራት አሉ፡፡ የሚያስተላልፏቸው ፕሮግራሞች ፍጹም መሆን የሌሉባቸውን ጉዳዮች ተዘርዝሯል፡፡
ማንኛውም ብሮድካስተር መፈጸም ከሌለባቸው ጉዳዮች አንዱ የሰው ልጅን ሰብዕና፣ ነፃነት፣ ሥነ ምግባርና እምነት የሚያንኳስስና የሚጻረር ፕሮግራም ማስተላለፍ የለበትም፡፡ የግለሰብን ሰብዕና ነፃነትና የቡድንንም ይሁን የግለሰብን እምነትና ያጎለበታቸውን በጎ ሥነ ምግባሮች የማጣጣል ይዘት ያለውን ፕሮግራም ማሰራጨት ክልክል ነው፡፡
የሚተላለፈው ፕሮግራም በራሱ የመንግሥት ተቋማት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ከሆነም ፍጹም ክልክል ነው፡፡ ለአብነት የመንግሥት የፀጥታና የደኅንነት ተቋም ወይም መከላከያ ሠራዊቱን የሚመለከቱ መረጃዎች ሆነው መሰራጨታቸው አገሪቱን ስለሚጎዳ ከተከለከሉ እነዚህን ማስተላለፍ እንደማይቻል ከሕጉ መረዳት ይቻላል፡፡
ሌላው ማንኛውም ብሮድካስተር ማስተላለፍ የማይችለው ግለሰብን፣ ቡድንን (ብሔርን፣ ሃይማኖትን ወዘተ) እና ድርጅትን ስም የሚያጠፋ፣ በውሸት የሚወነጅል መሆን የለበትም፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ስም ማጥፋት ሲባል የመረጃውን እውነትነት ብቻ የሚመለከት አለመሆኑን ነው፡፡ ቁምነገሩ መረጃው እውነት ቢሆንም እንኳን የቀረበበት ዓላማ፣ የአሰራጩ ፍላጎት ሆን ብሎ ስም ለማጥፋት ከሆነም የማይፈቀድ መሆኑ ነው፡፡ እውነት ብቻውን ከተጠያቂነት ላያድን ይችላል፡፡
በአዋጁ ላይ ሌላው በገደብነት የተቀመጠው ሕዝብን ከሕዝብ ወይም አንድ ብሔርን ከሌላ የሚያጋጭ እንዲሁም ጦርነትን የሚቀሰቅስ ይዘት ያለውን ፕሮግራም ማስተላለፍ አለመቻሉ ነው፡፡ እዚህም ልብ ልንለው የሚገባው ጉዳይ የሚተላለፈው ወይም የሚሰራጨው ፕሮግራም ይዘቱም ይሁን ምንጩ ትክክልና እውነት መሆን ወይም አለመሆን መለኪያ አይደለም፡፡ የተከለከለው፣ የሚተላለፈው ፕሮግራም አንድን ብሔር ከሌላ ሊያጋጭ የመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ እውነት ሆኖም የሚያጋጭ ከሆነ፣ ትክክለኛ መረጃም ሆኖ የእርስ በርስም ይሁን ከሌላ አገር ጋር ጦርነትን የሚቀሰቅስ ከሆነ ብሮድካስተሮች ማሰራጨት አይችሉም፡፡ እነዚህ ክልከላዎች የተቀመጡት አዋጁ አንቀጽ 30(4) ላይ ነው፡፡
ክልከላዎች ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተጠቀሱት አራት ገደቦች በጣም የሰፉ መሆናቸው ዕሙን ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ አኳያ የሚገለጸውን ነገር ይዘቱ መሠረት በማድረግ ወይም በመገለጹ ምን እንደሚያመጣ ከግምት በማስገባት የሚከለክል ሕግ እንደማይወጣ ሕገ መንግሥቱ ላይ ተቀምጧል፡፡ እርግጥ ነው ብሔራዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮችንም ለገድብ በምክንያትነት አልተቀመጡም፡፡ በርካታ አገሮችና በእኛም አገር በተለያዩ ሕች ላይ ግን በገደብነት ተቀምጠዋል፡፡
ክልከላዎቹ ሕገ መንግሥታዊ ይሁንም አይሁኑም፣ በመገደብና መረጃዎቹን ለሕዝብ ይፋ ከማድረግ አንፃር አገራዊ ጥቅምና ጉዳታቸው የትኛው እንደሚያመዝን ጥናትና ምርምር ቢያስፈልገውም አሁን ባሉት ሕጎች ግን ክልከላዎቹ የጸኑ ናቸው፡፡
የጦርነት ፕሮፓጋንዳ እንደ ገደብ
ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከሚገደብባቸው ሁኔታዎች ውስጥ የትኛውም ዓለም አቀፍ ሰነድም ይሁን ብሔራዊ ሕግጋት ከሚጋሯቸው አንዱ የጦርነት ፕሮፓጋንዳ መንዛት ነው፡፡ የጦርነቱ ፕሮፓጋንዳው የእርስ በርስም ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ ነገር ግን በተለያዩ ብሔሮች፣ ጎሳዎች፣ ሃይማኖተኞች ወዘተ መካከል ግጭት እንዲፈጠር ያለማቋረጥ ማነሳሳትም እንዲሁ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የጦርነት ፕሮፓጋንዳን አያካትትም ማለት ነው፡፡
ለፕሮፓጋንዳ የሚውሉ ቃላትና ዓረፍተ ነገሮች በራሳቸው እንደ ጥቃት ከመሆን አልፈው አካላዊ ጥቃትን ጠሪ ናቸው፡፡ በድንገት በሁለት ሰዎች መካከል የሚፈጠረው ግጭት ቡድናዊ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ አስቀድሞ የተነዛው ፕሮፓጋንዳ ሰፊ ከሆነም በድንገት የሚፈጠር ግጭትን በግለሰብ ደረጃ ብቻ መግታት አዳጋች ይሆናል፡፡
ከፊት ለፊቱ ሲታይ ፕሮፓጋንዳውን፣ ማነሳሳቱን የሚፈጽሙት ሚዲያዎች ቢሆኑም፣ ሚዲያዎቹ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ውስጥ እንዲገቡ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዩጎዝላቪያና በሩዋንዳ የሆነውም እንዲሁ ነው፡፡
በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የፕሮፓጋንዳ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ውጤት አልባ ማድረግ የሚቻለው ተዓማኒ፣ ግልጽ፣ የሐሳብ ብዙኃነት ማስተናገድን ባሕርይው ያደረገ፣ ዘመኑን የዋጀ ሚዲያ በማስፈን ነው፡፡ መዝጋትና መከልከል መፍትሔ አለመሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ማኅበረሰቡም የሚያገኛቸውን መረጃዎችን እውነትነታቸውን የሚያጣራበትን አማራጭ ማስፋት ነው፡፡
የብሮድካስት ሕጉና አተገባበር ለፌ ወለፌነት
ከላይ የተጠቀሱትን ክልከላዎች መተላለፍ ፍቃድን ያስነጥቃል፡፡ በወንጀልም ያስጠይቃል፡፡ ለደረስውም ጉዳት በፍትሐ ብሔር ካሳ መክፈልን ያስከትላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያጋጭ ሐሳብ ወይም መልዕክት ከተላለፈ በኋላ አንድም ጥላቻን በሕግ ብዙም መፋቅ ስለማይቻል፣ እልቂት ከደረሰም በምንም መልኩ የሚካስ ስላልሆነ ከሕግ ባለፈም ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ኃላፊነት መላበስን ይጠይቃል፡፡ እነዚህን ሥራ ላይ ለማዋል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ያለበት ኃላፊነት ከፍተኛ ስለሆነ የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡
ከኢትዮጵያ የሚሰራጩትን የብሮድካስት አገልግሎቶች ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን በሕግ የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለሥልጣኑ የመቆጣጠር ሕጋዊ አድማሱ የሚቆመው ከኢትዮጵያ የሚሰራጩት ላይ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም፣ በማኅበራዊ ሚዲያ መልክ የሚተላለፉትን የብሮድካስት አገልግሎቶች አይጨምርም፡፡ ከኢትዮጵያ ቀርፀውና አዘጋጅተው ከውጭ አገር የማሰራጪያ ጣቢያ የሚለቀቁትንም አይቆጣጠርም፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ የብሮድካስት አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ ሊያገኙ አይችሉም፣ በሕግ ስለተከለከለ፡፡
እንግዲህ በሕግ የሃይማኖት ተቋማት የብሮድካስት ፈቃድ ሊሰጣቸውም፣አገልግሎት ሊሰጡም አይችሉም፡፡ በሕግ ክልክል ነው፡፡ በተግባር ግን በርካታ የሃይማኖት ተቋማት የቴሌቪዥንና የሬዲዮ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ለሥርጭቱ የሚሆኑት ቀረጻዎችም በአገር ውስጥ የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ ተዘጋጅተው ከሌላ አገር ተሰራጭተው ተመልሰው ለኢትዮጵያውያን ይቀርባሉ፡፡ ሕጉ በአገር ውስጥ ፈቃድ በማውጣት የብሮድካስት አገልግሎት መስጠትን ቢከለክልም፣ ዞሮ ዞሮ ሥርጭቱ ግን አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ሕጉ ማሳካት የፈለገውን ግብ አላሳካም፡፡ በቁጥር ሲሰላም ሃይማኖታዊ ካልሆኑት ይበልጣሉ፡፡ ሕጉና እየሆነ ያለው እዚህና እዚያ (ለፌ ወለፌ) ነው፡፡
ሌላው ጉዳይ ደግሞ የብሮድካስት ሚዲያ የሚመራባቸው መርሆች አሉ፡፡ ሊከተላቸው የሚገባም የሥነ ምግባርና የሕግ ኃላፊነቶችም አሉበት፡፡ መተላለፍ የማይችላቸው ገደቦችም እንዲሁ፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንም ይኼንኑ የማስከበርና የመቆጣጠር በሕግ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡
ይሁን እንጂ፣ በ1999 ዓ.ም. የወጣው የባለሥልጣኑ ማቋቋሚያ አዋጅ በተለያዩ ሞገዶች አማካይነት በተለመደው መንገድ የሚያሰራጩትን እንጂ በኢንተርኔት (በመካነ ድር/ዌብ ሳይት) አማካይነት የሚሰራጩትን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን ስለመኖሩ የተቋቋመበት አዋጅ አያመለክትም፡፡ በመሆኑም፣ በሕጉ ላይ ከታሰበው በተጨማሪ የሚሰራጩ የብሮድካስት አገልግሎቶችን መከታተልና መቆጣጠር አይችልም፡፡ በተግባር ግን በርካታ ሰው ባለበት ቦታ ሆኖ በእጅ ስልኩ ይከታተላል፡፡ ባለቤታቸው ከግለሰቦች ጀምሮ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ሕጉ፣ ብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎች ሊያከብራቸው የሚገቡትን ሁኔታዎች ቢዘረዝርም ሕጉ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችለው 20 የብሮድካስት አገልግሎት ሰጭዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪዎቹ የትየለሌ፣ አዋጁ የሚመለከታቸው እንዲሁም ባለሥልጣኑ የሚከታተላቸው ሁለት ደርዘን የማይሞሉ፡፡ ሕጉና በተግባር እየሆነ ያለው እዚህና እዚያ (ለፌ ወለፌ)፡፡
ለኢትዮጵያዊያን እንዲሆኑ ታስበው የሚሰራጩት የብሮድካስት አገልግሎቶች በርካታ ቢሆኑም፣ የብሮድካስት ባለሥልጣኑ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን አማካይነት ሊከታተላቸውና ሊቆጣጠራቸው የሚችለው ግን 20 ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ 20 ተቋማት የሚሰጣቿው አገልግሎቶች እንደ ሕጎቹ መሆናቸውን መከታተል ይችላል፡፡ ሕግ ከጣሱም አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰድ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በተመሳሳይ መስክ የተሰማሩ ነገር ግን ከሌላ አገር የሚሰራጩ እንዲሁም በኢንተርኔት የሚተላለፉት ላይ ግን ሥልጣን የለውም፡፡
የብሮድካስት አዋጁ ሲወጣ በአገሪቱ ውስጥ እንዲሰፍን በማሰብ በዓላማነት ይዟቸው የተነሳውን ግቦች ብሎም እንዲፈጠር የታሰበውን ማኅበረሰብ፣ እንዲከበሩ የተፈለጉትን ግዴታዎች በፍጹም ለማሳከት አይችልም፡፡ ከእሱ ቁጥጥር ውጭ በርካታ የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎች ስላሉ፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ የተቀመጡ ገደቦች የማይመለከታቸው አሉ ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ከሕግ አንፃር ብቻ ሲታይ ነው፡፡
ከላይ የቀረበው የሕግና የተግባር ለፌ ወለፌነት እንዳለ ሆኖ በባለሥልጣኑ ሥር የሚገኙ የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎች የሚያስተላልፏቸው ፕሮግራሞች አልፎ አልፎ ችግር እየተስተዋለባቸው ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ቢኖር፣ ባለሥልጣኑ ስለችግሮቹ አስተያየት የሚሰጠው ከሕዝብ ብዙ ጩኸት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ዋና ተቆጣጣሪ እየሆነ የመጣውም ሕዝቡ ይመስላል፡፡ በእርግጥ ባለሥልጣኑ እስካሁን ዕርምጃ አልወሰደም፡፡ ያልወሰደበት ምክንያቶችን በሁለት ጎራ የተከፈሉ ናቸው፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩትና በተለያዩ የሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ‹‹የመጀመሪያው ጉዳይ የችግሩ ምንጭ ሚዲያው ሳይሆን ሌላ የተደበቀ ጉዳይ በመሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ ሁሉም ሚዲያ በአመለካከት ረገድ ችግር ያላባቸው ስለሆነ…›› እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የዋና ዳይሬክተሩ የመጀመሪያው ምክንያት በሕግም ይሁን በሌላ መለኪያ ዕርምጃ ለመውሰድ በምክንያትነት የሚያገለግል እንጂ ላለመውሰድ ሊሆን አይችልም፡፡ የትኛውም የሚዲያ ተቋም (የብሮድካስትም ጭምር) ፈቃድ ላገኘበት እንጂ ከዚያ ውጭ የሆነ ተግባር ውስጥ መሰማራት አይችልም፡፡ ‹‹ሌላ የተደበቁ ጉዳይ›› ከፈጸመም የተቋቋመበትን ዓላማና ሕጉንም ስለሚጥስ እንዲያስተካከል ማድረግ የባለሥልጣኑ ግዴታ ነው፡፡ ሌላ የተደበቀ ጉዳይ መኖሩን ባለሥልጣኑ አውቆ ዕርምጃ አለመውሰድ ባለሥልጣኑ በሕግ የተጣለበትን ግዴታ አለመወጣት ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም፣ ‹‹ሌላ የተደበቀ ጉዳይ›› ካለ የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪው አስተዳደራዊም ይሁን ሌላ ዕርምጃ አይወሰድበትም የሚል በአዋጁ ላይ የተገለጸ ነገር የለምና!
የዋና ዳይሬክተሩ ሁለተኛው ምክንያት ሁሉም ሚዲያዎች በአመለካከት ረገድ ችግር ስላለባቸው ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ያስተዋላቸውን ችግሮች ቶሎ እንዲቀርፉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን፣ ባለሥልጣኑ አትኩሮት ማድረግ ያለበት ከሕግ አንፃርም ሊለካ የሚችለው የሚዲያዎቹ የአመለካከት ችግር መኖር ወይም አለመኖር ሳይሆን ያስተላለፉት/ያሰራጩት ፕሮግራም ይዘት ላይ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ መላቅጡ ባልለየ አሉባልታና የሴራ ፖለቲካ ትንታኔ በተለያዩ ሚዲያዎች እየታመስን ባለንበት ወቅት እንዲሁም በቀላሉ የብሔር መልክ የሚይዙ ግጭት በአገራችን በተለያዩ ክፍሎች እየተፈጠሩ ባለበት ወቅት የባለሥልጣኑ ዋና ትኩረት ሕግ በማስከበር ወይም እንዲያከብሩ በማድረግ ሌሎች የሚዲያ ተቋማትም ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ማድረግ እንጂ ወደ ፊት ሥልጠና መስጠት ሊሆን አይችልም፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡