Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አዲስ አመራር በመጣ ቁጥር የቀድሞውን እያፈረሱ ከመሄድ ይልቅ የተጀመረውን ማስቀጠል ይመረጣል››

አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር)፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዲሱ ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከ70 ዓመታት በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ አንጋፋ ከሆኑ መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ተርታ የሚሠለፈው ይህ ንግድ ምክር ቤት፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ አመራር ለመምጣት በሚሹ ወገኖች ይደረጋል በተባለ ሽኩቻ ስሙ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ በተለይ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫዎች በሚካሄዱበት ወቅት ተደጋጋሚ ውዝግቦችና ቅሬታዎች ሲስተዋሉ እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ በተደረገው ምርጫ ከበፊቶቹ በተሻለ ያለ ውዝግብ ተፈጽሟል፡፡ በዚህ ምርጫ ንግድ ምክር ቤቱን ለመምራት በፕሬዚዳንትነት የተመረጡት የ39 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ አቶ መላኩ የአማራና የጎንደር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ በዚህ ምርጫ የተሳተፉት ከአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተወክለው ነው፡፡ በጎንደር ከተማ የተወለዱት አቶ መላኩ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጎንደር ከተማ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ካጠናቀቁ በኋላ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋክልቲ በኤሌክትሪካል ምህንድስና የመጀመርያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከወጡ በኋላ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩት አቶ መላኩ፣ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በፕሮጀክት ማኔጅመንት ስፔሻላይዜሸን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ህንድ ከሚገኘው ኪሲኪም ማኒፓል ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ለሦስት ዓመታትም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአይሲቲ ሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት ባለሙያ ሆነው ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጎንደር ሪል ስቴት፣ የአሽከርካሪዎች ማሠልጠኛና የትራንስፖርት ድርጅቶችን ሥራ አስኪያጅና ባለቤት በመሆን ይመራሉ፡፡ አቶ መላኩ ከንግድ ሥራዎቻቸው በተጨማሪ በጎንደር ከተማ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በመስጠት በሃይማኖታዊ ሥራዎቻቸው ይታወቃሉ፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ መላኩ፣ አዲሱ ኃላፊነታቸውን በተመለከተ፣ እንዲሁም በንግድ ምክር ቤቱ መሪነታቸው ወቅት ማከናወን ስላሰቡዋቸው ሥራዎችና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር አቀፍ ደረጃ የንግድ ማኅበረሰቡን የሚወክለውን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡ የምርጫውን ሒደት እንዴት አገኙት?

ኢንጂነር መላኩ፡- እኔ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ ላይ ስሳተፍ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት በተካሄደው ምርጫ የጎንደር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በመወከል የጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊ በመሆን እንደ መራጭ ተሳትፌአለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ተወዳዳሪ በመሆን ነበር የቀረብኩት፡፡ በቀደሙት ምርጫዎች ላይ ይኼ ነው ብዬ የምገልጸው ነገር ባይኖርም፣ የዘንድሮው ምርጫ ጥሩ ፉክክር የታየበትና ዴሞክራሲያዊ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- መራጭ ሆነው ድምፅ በሰጡበትና አሁን ደግሞ ተወዳዳሪ ሆነው በቀረቡበት ምርጫ መካከል ነበር የሚሉት ልዩነት አለ? የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫዎች ውዝግብ አያጣቸውም ይባላልና በዚህ ጉዳይ የእርስዎ ሐሳብ ምንድነው?

ኢንጂነር መላኩ፡- ስለቀድሞው ብዙም ግንዛቤ የለኝም፡፡ ነበር የሚባለውን ችግር ከውጭ ከመስማት ሌላ በጥልቀት የማውቀው ነገር የለም፡፡ አሁን ግን የነበረውን ሒደት ከወሬ በዘለለ በደንብ ተከታትየዋለሁና የምርጫ ሒደቱ ጥሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በፊት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የምርጫ መመርያ ፀድቋል፡፡ ይህም በመሆኑ በዚህ መመርያ ብቻ ምርጫው እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ ሁለተኛው በተለይ ከነበሩት ውዝግቦች አንፃር አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ፣ ምርጫው ፍትሐዊና ሰላማዊ እንዲሆን ለማስቻል ያቀረባቸው ሐሳቦች ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ በርካታ ወንበሮች ያሉዋቸው ክልሎችና የዘርፍ ማኅበራት በዛ ያሉ ዕጩዎች ይዘው ይመጡና ከአንድ አካባቢ የሆኑት ይመረጣሉ፡፡ አሁን ግን ከሁሉም አባል ምክር ቤቶች በእኩል ውክልና እንዲመጡ በማድረግ የተመራጮች ስብጥር በተሻለ ሁኔታ እንዲታይ አድርጓል፡፡ በአጭር አነጋገር ለመናገር ውኃ ቅርፅ የለውም፡፡ ግን የምታፈስበትን ቦይ ካዘጋጀህለት ወደ ምትፈልገው ቦታ በአግባቡ ይፈሳል፡፡ በአግባቡ ከፈሰሰልህ ደግሞ ወደ ምትፈልገው ዓላማ ያደርስሃል፡፡ ስለዚህ እስከ ዛሬ ድረስ ለችግሮች ዋናው ምክንያት ሲስተም አለመኖሩ ነው፡፡ ወይም ጥርት ያለ የምርጫ አካሄድ ካለመኖሩ የመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡ የዘንድሮውን ምርጫ በተመለከተ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተሰጡት አስተያየቶች የአሁኑ ምርጫ ሁሉንም ወገን ያስደሰተ መሆኑ ነው፡፡ በወቅቱ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራት መሪዎችና የቀድሞ አመራሮች ጭምር ስለነበሩ ከሰጡት አስተያየቶች የተረዳሁትም ይህንኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን አሁን እየታየ ያለና በግልጽም አስተያየት እየተሰጠበት ያለ ጉዳይ ቢኖር፣ የአገሪቱ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ደካማ መሆናቸው ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች ሊያከናውኑዋቸው ከሚገቡ ሥራዎች አንፃር ምንም እየሠሩ አይደለም እየተባሉም ነው፡፡ እንዲህ ያለውን አስተያየት እንዴት ያዩታል?

ኢንጂነር መላኩ፡- አሁን ለምሳሌ አንድ ግለሰብ በቀጥታ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል አይደለም፡፡ አባላቱ በየክልሉ ያሉ በተለያዩ ደረጃ የተዋቀሩ ዘርፍና ማኅበራት ናቸው፡፡ የክልል ዘርፍ ምክር ቤቶችም ቢሆኑ በቀጥታ ግለሰብ አባል ነጋዴ አባል የላቸውም፡፡ አባሎቻቸው የከተማ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ የግለሰብ ነጋዴ አባል ያላቸው የከተማ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ናቸው ማለት ነው፡፡ ለእኔ ከላይ ያለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠንካራ አወቃቀር አለው፡፡ ጠንካራ የሰው ኃይል አለው፡፡ በጥሩ አደረጃጀት የሚገኝም  ነው፡፡ ነገር ግን የመጨረሻው ተጠቃሚ አባል ነጋዴ አባል የሆነባቸውን የከተማና የወረዳ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ላይ ሠርተን ጠንካራ እንዲሆኑ ማስቻል ይገባናል፡፡ ከላይ ተንጠልጥለን ስለሠራን ብቻ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዲስ አበባ ላይ ሆኖ እንኳን ከ15 ሺሕ በላይ አባል የለውም፡፡ ስለዚህ አብዛኛው አባል ያለው በየከተማና በየወረዳ ላይ ነው፡፡ እነዚህ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ከሌሉ በስተቀር ላይኛው ላይ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ትልልቅ የሚባሉ ሥራዎችን እንኳን ብንሠራ፣ ከሥር ያለው አባላችን ላይገነዘበን ይችላል፡፡ እስካሁንም እኮ ሥራ ይሠራል፣ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለአባሉ ላይታይ ይችላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአዋጅ ቁጥር 341/95 መሠረት አባልነት በግዴታ ሳይሆን በውዴታ መሆኑንም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ አብዛኛው የንግድ ኅብረተሰቡ አባላት ችግር ካልተፈጠረባቸው በቀር ለአባልነት ብዙም የሚያጓጓቸው ነገር የለም፡፡ በፊት በነበረው አዋጅ አባልነት በግዴታ ነበር፡፡ ስለዚህ ከንግድ ምክር ቤቱ ምክር አገኛለሁ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት መረጃ አገኛለሁ፣ በዚህ መንገድ እጠቀምበታለሁ ብሎ ያንን አደረጃጀት ለመጠቀም በማለት አይደለም አባል የሚሆነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ብዙ ጊዜ ችግር የሚፈጠረው፡፡ ነገር ግን ንግድ ምክር ቤቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች አባል ለሆነውም ላልሆነውም የሚጠቅምበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ በከተሞች ግብር ይግባኝ ኮሚቴ ላይ የንግድ ምክር ቤቶች አባል ለሆነውም ላልሆነውም አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ድክመቱ ከአደረጃጀቱ ጋር የተያያዘ ነው ማለት ነው?

ኢንጂነር መላኩ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ከላይ ጥሩ አወቃቀር ያለው ስለሆነ ጠንካራ ሥራ ይሠራል፡፡ ነገር ግን ሥር ያሉትን አባል ንግድ ምክር ቤቶች ለማጠናከር እስከ ከተማና ወረዳ ወርዶና የመጨረሻዎቹን አባላት ደርሶ አጠናክሮ እስካልሠራ ድረስ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ለምን?

ኢንጂነር መላኩ፡- ለምሳሌ ከተማና ወረዳ ላይ ያሉ ንግድ ምክር ቤቶች ራሳቸውን ችለው ነው ዕውቅና ያገኙት፡፡ ክልል ላይ ያሉት ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችም ራሳቸውን ችለው ነው ዕውቅና ተሰጥቷቸው እየሠሩ ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ራሱን ችሎ ነው ያለው፡፡ በመካከላቸው የዕቅድና የሪፖርት ግንኙነት ሰንሰለት የላቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የሆነበት ምክንያት ለምንድነው? በየራሳቸው አወቃቀር ተደራጅተው እንዲሠሩ አዋጁ ስለሚፈቅድ ነው?

ኢንጂነር መላኩ፡- አዎ አወቃቀራቸው ለየብቻ ነው፡፡ ለየብቻቸው ነው አወቃቀር የተሰጣቸው፡፡ በዚህ ዓይነት አሠራር የተደራጁ በመሆኑ ሥራቸውም በዚሁ መንገድ ነው የሚሄደው፡፡ ጠንካራ የሆኑ ንግድ ምክር ቤቶች እንዳሉ ሁሉ ጠንካራ ያልሆኑም አሉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ትልቁ ሥራ የሚሆነው አባል ንግድ ምክር ቤቶቹን አጠናክሮና አቅማቸውን አጎልብቶ አባላትን መሠረት ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተደጋጋሚ ጠንካራ ንግድ ምክር ቤት ሊኖር ያልቻለው ጠንካራ አመራሮች ስላልነበሩት ነው የሚል ነገር ይነሳል፡፡ ወደ ንግድ ምክር ቤቶቹ አመራርነት ለመምጣት የሚታየውም ሽኩቻ ጠንካራ ንግድ ምክር ቤት እንዳይኖር ማድረጉን የሚጠቅሱም አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?

ኢንጂነር መላኩ፡- እኔ በግሌ ማለት የምችለው፣ ከዚህ ቀደም ንግድ ምክር ቤቱን ሲመሩ የነበሩ አመራሮችን በሙሉ የማያቸው በጠንካራ ጎናቸው ነው፡፡ ጠንካራ ስለሆኑ ሕንፃ ገንብተው ራሱን እንዲችል ያደረጉት እኮ ነባሮቹ አመራሮች ናቸው፡፡ ዛሬም የተዘረጋውን ሲስተም ያኖሩት እኮ እነዚህ ጠንካራ አመራሮች ናቸው፡፡ እኛ እንደ አዲስ ተመርጠን ስንገባ የተዘጋጀ ሲስተም ነው የምናገኘው፡፡ ከዚህ በፊት ላለፉት ብዙ አሠርት ዓመታት የነበሩት ጠንካራዎቹ የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች፣ ለእኛ መልካም የሆነ መሠረት ጥለውልን ሄደዋል፡፡ እኛ ደግሞ የእነሱን ተቀበልን፡፡ የራሳቸችንን አሻራ ጥለን ለተተኪው እንተዋለን እንጂ፣ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አንድ የተመረጠ ሰው ሁሉን ሥራ አጠናቆ ሊሠራ አይችልም፡፡ ለተመረጠበት ጊዜ የሚቻለውን ሠርቶ ለቀጣዩ ያስረክባል፡፡ ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን ብሎም ገንዘባቸውን መስዋዕት አድርገው ሥራ ሠርተው ለንግድ ምክር ቤቱ አሻራቸውን ያስቀመጡና ጠንካራ ሥራ ሠርተው ያለፉ የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች ነበሩ ብዬ ነው የማምነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ጠንካራ አይደለም የሚባለው የአገሪቱን ንግድ ምክር ቤቶች ከሌሎች አገሮች አቻዎች ጋር በማነፃፀር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የንግድ ማኅበረሰቡ በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ ችግሩ ከራሱ ከንግድ ማኅበረሰቡ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌሎች ተፅዕኖዎችም ያሉበትን ችግሮቹን ለመፍታት አልቻለም ሊባል ይችላል፡፡ ለማንኛውም የንግዱ ማኅበረሰብ አሁን አሉበት የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት እርስዎ ምን ለማድረግ አስበዋል? የተለየ ነገር ይዘው ይመጣሉ?

ኢንጂነር መላኩ፡- ከዚህ በፊት የነጋዴው ችግሮች እየተጠኑ በዘላቂነት ለመፍታት ከመንግሥት ጋር የምንገናኝባቸው የምክክር መድረኮች አሉ፡፡ ችግሮቹ ግን በጣም ሰፊ ስለሆኑ በአገር አቀፉ ንግድ ምክር ቤት ብቻ እያጠናህ የምትፈታው አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ክልል ያለው የችግር ዓይነት ይለያያል፡፡ የእያንዳንዳቸው ማኅበራት ጉዳይ ይለያያል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ትልቁ ሥራው እያንዳንዱ ንግድ ምክር ቤት በራሱ ዛቢያ ላይ እየተሽከረከረ በአካባቢው ያለውን ችግር በራሱ መፍታት እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ የኦሮሚያ ንግድ ምክር ቤት፣ የአማራ ንግድ ምክር ቤት፣ የደቡብ ንግድ ምክር ቤት፣ የትግራይ ምክር ቤት እያለ ሁሉም ማኅበራት ራሳቸውን ችለው ያሉባቸውን ችግር እያስጠኑ ሊፈታ የሚችልበትን መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ ያለበለዚያ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ብቻ በወረዳ፣ በከተማ ንግድ ምክር ቤትና በዘርፍ ምክር ቤቶች አሉ የሚባሉትን ችግሮች እያሰባሰበ አጥንቶ መዝለቅ አይችልም፡፡ አደረጃጀት የሚያስፈልግበት ትልቁ ነገር በእያንዳንዱ ደረጃ እየተጠና አገራዊ የሆነውን በአዋጅና በፌዴራል ደረጃ፣ ሊመለሱ የሚገባቸውን ነገሮች ወደ ላይ እያመጣ እንዲሠራ ይጠበቅበታል፡፡ በከተማና በወረዳ በዘርፍ ሊመለስ የሚገባውን ደግሞ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር እየተፈታ መሄድ አለበት ብዬ ነው የማስበው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ወደዚህ የኃላፊነት ቦታ ለመምጣት ሲያስቡ ብመረጥ ይዤ እመጣለሁ ብለው ያሰቡዋቸው አዳዲስ ነገሮች ይኖራሉ?

ኢንጂነር መላኩ፡- የንግድ ምክር ቤት አመራር እንደ እግር ኳስ ተጨዋቾች በጋራ ውጤት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በእግር ኳስ የአሥራ አንድ ተጨዋቾች ውህደት ነው ጎል እንዲቆጠርና አሸናፊ እንድትሆን የሚያደርግህ፡፡ እጅግ ጎበዝ አጥቂ ቢኖርም እንኳን፣ ለዚህ አጥቂ የሚያቀብለው ከተከላካይ እስከ አማካይ ከሌለ ውጤት ማስመዝገብ አይቻልም፡፡ አሥራ አንዱም መዋሀድ አለባቸው፡፡ አሁን ትልቁ ነገር የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠንካራ የሆነ አደረጃጀት ስላለው ይህንን መጠቀም መቻል ይኖርብናል፡፡ ይህንን ለመጠቀም ደግሞ የቦርዱ አንድነትና መዋሀድ የመጀመርያው ትልቅ ነገር ይሆናል፡፡ ከጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጋር መናበብ መቻል ሌላው አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በጽሕፈት ቤት ያሉ ብዙ ልምድ ያላቸው ሠራተኞች አሉ፡፡ የእነሱንም አቅም በመጠቀም የንግዱ ኅብረተሰብ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ አሠራሮችን መዘርጋት፣ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ከአባል ምክር ቤቶች ጋር ጥሩ የሥራ ከባቢ መፍጠር የአንዱ የፕሬዚዳንት ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ የቦርድ አባላት በአንድ ላይ ተባብረን አዳዲስ አሠራሮችን ለማምጣት ተናበን እንሠራለን፡፡ መሠረታዊው ነገር ግን አባላትን መሠረት ያደረገ አቅምን በመገንባት፣ ጥሩ አሠራር እንዘረጋለን የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ በነበሩ የተለያዩ ውዝግቦች ምክንያት ጠንካራ የሚባሉ የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት ከንግድ ምክር ቤቱ ሸሽተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር አለ የሚባለውን ችግር ለመፍታትስ ምን አስበዋል?

ኢንጂነር መላኩ፡- እሱን ወደ ሥራው ገብተን አሉ የሚባሉትን ነገሮች ሁሉ ዓይተን መረጃዎችን ሰብስበን ልንወስንበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ችግሮችን በስትራቴጂ የመፍታት አሠራር ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- ንግድ ምክር ቤቶች ለንግዱ ማኅበረሰብ የቆሙ ናቸው፡፡ ለንግድ ማኅበረሰቡ የሚሠሩ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የሚፈጥራቸውንም ችግሮች መመልከት ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን የብር የምንዛሪ ለውጥ ሲደረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል ተብሏል፡፡ ይህ የሆነው በንግዱ ማኅበረሰብ ነው፡፡ ስለዚህ የንግድ ማኅበረሰቡ ሥነ ምግባር የተላበሰ የንግድ ባህል እንዲያዳብር ምን እሠራለሁ ይላሉ?

ኢንጂነር መላኩ፡- ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ከመንግሥት ጋር ሆኖ ያፀደቃቸው መመርያዎች አሉ፡፡ ትልቁ ነገር የንግድ ፈቃድ አውጥተው መነገድ ብቻ አይደለም፡፡ ከሸማቾችም አዋጅ አንፃር ንግድ ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 341/95 መሠረት በንግዱ ማኅበረሰብና በመንግሥት መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ማገልገል ማለት ነው፡፡ ነጋዴዎች መብታቸው እንዲከበር፣ ሕግና ደንብን ደግሞ አክብረው እንዲሠሩ ማድረግ፣ አዋጅና መመርያዎችን አውቀው በአገራቸው የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማስተማር ትልቁ ሥራችን ነው፡፡ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑና ግብረ ገብነት የጎደላቸው ሥራዎች እንዲያስተካክሉ በየደረጃው ባሉ ንግድ ምክር ቤቶች እንዲረዱ ማድረግ ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩህ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ግለሰብ አባል የለውም፡፡ ስለዚህ ይህንን ማድረግ የምንችለው በከተማና በወረዳ ንግድና ምክር ቤቶች ነው፡፡ ስለዚህ ከታች ያለው አደረጃጀት ጠንካራ ካልሆነ እኛ ከላይ የተንጠለጠልን ነው የምንሆነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ጥንካሬ የሚገለጸው ከሥር ያሉትን አባል ምክር ቤቶችን ማጠናከርና ሥልጠና መስጠት ስንችል ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሆነዋልና በመጀመርያዎቹ አንድ መቶ የሥራ ቀናት ዋና ዋና ክንውንዎ ምን ይሆናሉ ብለው ያስባሉ?

ኢንጂነር መላኩ፡- እኛ አዲስ ገቢዎች ብንሆንም ከእኛ በፊት የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ከቀድሞ ቦርድ አባላት ኃላፊነትን ስንረከብ የምንወስዳቸው ሥራዎች አሉ፡፡ የቀድሞ ቦርድ የወሰናቸው ውሳኔዎች፣ ያፀደቃቸውና የጀመራቸው ሥራዎች በሙሉ ተረድተን የራሳችን አድርገን እነዚህን ማስፈጸም የመጀመርያ ሥራችን እናደርጋለን፡፡ የቀድሞ ቦርድ ያፀደቀው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አለ፡፡ ይህንን ዕቅድ ተረድተን ለማስፈጸም መትጋት፣ ምናልባት ደግሞ የጎደሉ ነገሮች አሉ ከተባሉ እነሱን አሟልተን እንዲፈጸሙ ማድረግ፡፡ ሌላው የፀደቀና ሥራ ላይ የዋለ የ2010 ዓ.ም. ዕቅድ አለ፡፡ እኛም የቀድሞም ቦርድ አንድ ስለሆንን ይህንን ማስፈጸም ነው፡፡ ዋናው ነገር የተጀመረውን ማስቀጠል ነው፡፡ ሁልጊዜ አዲስ አመራር በመጣ ቁጥር የቀድሞውን እያፈረሱ ከመሄድ ይልቅ የተጀመረውን ማስቀጠል ይመረጣል፡፡

በተለይ ዘንድሮ ከአዋጅ ቁጥር 341/95 ማሻሻል ጋር ተያይዞ የቀድሞ ቦርድ የጀመራቸውን ሥራዎች እኛ ማስቀጠል አለብንና ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እንሠራለን፡፡ ሌላው በ2021 የዓለም ቻምበር ጉባዔ ለማዘጋጀት ዕጩ ሆነው ከቀረቡ ስድስት አገሮች መካከል አንዷ አገራችን ኢትዮጵያ በመሆኗ፣ ይህንን በተመለከተ የቀድሞው ቦርድ የጀመረውን ሥራ እኛም እንገፋበታለን፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮችን እንፈጽማለን፡፡ የአዲሱ ቦርድ አባላት መክረን የምንተገብረውም ነገር ይኖራል፡፡ ትልቁ ነገር የአመራር ስትራቴጂ ማስቀመጥና በተለይ በተለይ በጽሕፈት ቤት ያለውን የሰው ኃይል በመጠቀም መሥራት ነው፡፡ ተስማምተህ ተደማምጠህ ከሠራህ የምትፈልገውን ግብ ትመታለህ፡፡  

ሪፖርተር፡- እስካሁን ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ካገለገሉ አመራሮች በዕድሜ አነስ ይላሉ፣ 39 ዓመትዎ ነው፡፡ ምናልባት ይህ ጅምር በንግድ ምክር ቤቶች አካባቢ ለወጣት የንግድ ሰዎች በር ይከፍታል?

ኢንጂነር መላኩ፡- ወጣትም ሆነ ሽማግሌ ለእኔ ጉልበት ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ቀላል ምሳሌ ልስጥህ፡፡ በገጠር አንድ ገበሬ ሲያርስ በሬና ወይፈን ያቀናጃል፡፡ በሬው እንዴት እንደሚያርስ ያውቃል፡፡ ጉልበቱ ግን ትንሽ ደከም ያለ ይሆናል፡፡ ወይፈኑ ደግሞ ጉልበት አለው፡፡ ስለዚህ ያኛው ልምድ ይኼኛው ጉልበት ስላለው የበለጠ ይቀናጃሉ፡፡ አሁን ትልቁ ነገር እኔ ብቻ ፍፁም ነኝ፣ የሚለው ነገር ከመጣ በማኅበር አመራርና አደረጃጀት ላይ ትልቅ ችግር ያመጣል፡፡ ከዚህ ቀደም ንግድ ምክር ቤቱን የመሩ ትልልቅ ሰዎች ያላቸውን ልምድ መጠቀም ካልቻልን ታዲያ ምኑን አመራር እንባላለን? ስለዚህ የእነሱንም ልምድ ተጠቅመን የእኛንም ጨምረን ጥሩ ሥራ ይሠራል ብለን እናስባለን እንጂ፣ ወጣት ሽማግሌ በማለት የምለየው ነገር አይኖርም፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...

‹‹የኢትዮጵያን የውስጥ ችግሮች ሁሌም የሚያባብሰው ከውጭ የሚመጣ አስተሳሰብ ነው›› ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር) የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር የውጭ ግንኙነት ኃላፊም ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት አሥርት ዓመታት ታሪክ አስተምረዋል፡፡...