Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ግልብ ገበያ

በአንድ ሳምንት ውስጥ ሦስት ገጠመኞች አስተናግጃለሁ፡፡ ገጠመኝ አንድ! በአውሮፓውያን አቆጣጠር ተሠልታ፣ የመንግሥት ታክስና ሌሎች ክፍያዎች ተቀናንሰውላት ከምትደርሰኝ ደመወዜ አስቤዛ ለመግዛት ጥቅምት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. (ኦክቶበር 29) በከተማችን ከሚታወቁ ሱፐር ማርኬቶች ወደ አንዱ ጎራ አልኩ፡፡ የምፈልጋቸውን ዕቃ መራርጬ ወደ ገንዘብ ተቀባይዋ አመራሁ፡፡

ከእኔ ቀድመው ገንዘብ ተቀባይዋ ዘንድ የደረሱ ሸማቾች ነበሩና ወረፋ ነበረብኝ፡፡ ከፊት ለፊቴ አንድ ወይዘሮ ክፍያ ለመፈጸም ገንዘብ ተቀባይዋ አጠገብ ካለው ጠረጴዛ ላይ የምትገዛቸውን ዕቃዎች ዘርግታ ሒሳብ እያሠራች ነው፡፡ ወይዘሮዋ ክፍያ ለመፈጸም ከተዘጋጀችባቸው ዕቃዎች መካከል ሦስት በአነስተኛ ፕላስቲክ የታሸጉ ባለጣዕም (ፍሌቨርድ) እርጎዎች ላይ ዓይኔ አረፈ፡፡ ከሦስቱ የታሸጉ እርጎዎች አንዱ ለየት ይላል፡፡ ጠጋ ብዬ ተመለከትኩ፡፡ የተከደነበት ማሸጊያ ተነፋፍቷል፡፡ አብጧል፡፡   የተወጠረውን እርጎ አንስቼ የተመረተበትንና ጊዜ ምርቱን እስከመቼ ድረስ መጠቀም የሚያመልክተው ጽሑፍ ቃኘሁ፡፡ የመጠቀሚያ ጊዜው ኦክቶበር 30 ቀን 2017 ድረስ ይላል፡፡ የተባላሸ ሊባል አንድ ቀን ብቻ ቀርቶታል፡፡ ይምርቱ የተበላሸ ሊሆን ስለሚችል የታሸጉትን እርጎዎች ለመግዛት ክፍያ ለመፈጸም ለምትሰናዳው ወይዘሮ እንዳትገዛ ነገርኳት፡፡ ገንዘብ ተቀባይዋን ‹‹እርጎው ጊዜ ያለፈበት ምልክት ስለሚታይበት ማስወገድ ይገባችኋል፤›› አልኳት፡፡ እንዲህ ያለውን ምርት እንዴት መደርደሪያ ላይ ታስቀምጣላችሁ በማለት ቅሬታዬን ገለጽሁ፡፡ ገንዘብ ተቀባይዋ የተነፋፋውን እርጎ ለብቻው ነጥላ አስቀመጠች፡፡

ከገንዘብ ተቀባይዋ ጋር ስንከራከርበት ስለነበረው ጉዳይ ይከታተል የነበረ ‹‹አለቃ›› ብጤ ሰው ይመጣና እንዲወገድ የተነጠለውን እርጎ አንስቶ አገላብጦ ከተመለከተ በኋላ ‹‹ቀኑ እኮ ገና አላለፈበትም፤›› ብሎ ሊቆጣ ሞከረ፡፡ በፊቱ ላይ የሚነበበው ንዴትና አስተያየቱ ደም የሚያፈላ ቢሆንም፣ ችግሩን በጥሞና ለማስረዳት ሞከርኩ፡፡ ምርቶች የመነፋፋት ባህሪይ ካሳዩ እየተበላሹ መሆኑን የሚጠቁም በመሆኑ፣ ይህንን ማጣራት ነበረባችሁ አልኩት፡፡ መደርደሪያ ላይ መቀመጥ እንዳልነበረበትም የተቻለኝን ተናገርሁ፡፡ የሰውየው ምላሽ ግን ‹‹እኛ አልሠራነው፡፡ የመጠቀሚያ ጊዜውም አላላፈም፤›› የሚል ክርክር ነበር፡፡ ይሄኔ እንዲያስወግድ በኃይለ ቃል ተናገርኩት፡፡ በነገሩ ሌላም ሰው ገባና የኋላ ኋላ ተማምነን ምርቱን እንዲያስወግዱ ማድረግ ተቻለ፡፡  

ገጠመኝ ሁለት የጥቅምት 20 ትዝብት ነው፡፡ አንድ ወዳጄ የክትፎ አምሮቴን ይቀሰቅሰውና ከአንድ ከምናውቀው ክትፎ ቤት እንገባለን፡፡ አዘዝን መጣልን፡፡ ገበታው ግን የማውቀውን ያህል መጠን እንዳልያዘ ስረዳ፣ የክትፎን ጣባ አዟዙሬ ተመለከትኩ፡፡ የጣባው መጠን ስለመቀነሱ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ አስተናጋጁን ጠርቼ ይቺ ጣባ የቀድሞዋ አይደለችም፣ መጠንዋ አነሰብኝ ምንድነው ነገሩ? አልኩት፡፡ ማስተባበል አልቻለም፡፡ ተግባባን፡፡ ሰሞኑን የተቀየረ ጣባ ነው፡፡

ገጠመኝ ሦስት፡፡ ይህ ደግሞ ጥቅምት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የሆነ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ቡና ከምጠጣበት ምግብ ቤት ውስጥ እየተስተናግድኩ ነው፡፡ ለጠጣሁት አንድ ስኒ ቡና አምስት ብር አስቀምጬ፣ በሞባይል ስልኬ እያወራሁ ለመውጣት መንገድ ጀምሬለሁ፡፡ የምግብ ቤቱ አስተናጋጅ ግን ከይቅርታ ጋር ቡና ጨምሯል አለችኝ፡፡ ነገሩ ግር ቢለኝም በስልኬ የጀመርኩትን ንግግር ላለማቋረጥ አንድ ብር አውጥቼ ጨመርኩላት፡፡ አስተናጋጅዋ ግን አሁንም አልተወችኝም፡፡ አንድ ብር አልበቃም፡፡ ይኼኔ ስልኩን አቋርጬ ‹‹ስንት አድርጋችሁት ነው?›› አልኳት፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ የቡና ዋጋ ወደ ሰባት ብር ማደጉ ተነገረኝ፡፡ ጉድፈላ፡፡ ለምን ይህን ያህል ጨመራችሁ? መልሷ ግልጽ ነበር፡፡ ስኳር ስለተወደደ ነው፡፡ ከዚህ በላይ መነጋገር አልቻልኩም፡፡

የመጀመርያውን የሱፐር ማርኬት ገጠመኜ ብዙ ነገር እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ ወይዘሮዋ ያንን እርጎ የምትገዛው ለልጆቿ ይሆናል፡፡ የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበትን እርጎ ሊያረጋግጥ የሚችል የቤተሰብ አባል ባይኖር፣ ተጠቃሚው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መገመት አያቅትም፡፡

የሚከነክነው ጉዳይ ግን ዘመናዊነትን እየተላበሱ በሚገኙ ሱፐር ማርኬቶች ውስጥ እንዲህ ያለ ድርጊት መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን፣ ችግሩን በደንብ እያስረዳሁት እንኳ፣ የሱፐር ማርኬቱ ሠራተኛ ችግሩን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑም ጭምር ነው፡፡ ‹‹ምን አገባህ?›› በሚል ስሜት ከመፋጠጥ ይልቅ ጥፋቱን አርሞ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው ሙግት መግጠሙ ያሳዝናል፡፡

 ሱፐር ማርኬቶች እንዲህ በቀላሉ የሚበላሹ ምርቶችን በየጊዜው እየፈተሹ የማስወገድ ግዴታ ቢኖርባቸውም፣ ይህን የማያደርጉ እንዳሉ አይቻለሁ፡፡ ሸማቾች ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባቸዋል፡፡ በቀላሉ የሚበላሹ የታሸጉ ምግብና መጠጥ ነክ ምርቶችን መረጃ በጥንቃቄ ማየት ግድ ይለናል፡፡ ቅድሚያ ለጤና፣ ጎመን በጤና ማለት እንዲህ ያለው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ 

ስለክትፎዋ ጣባ ማንሳት የፈለግሁት ለምን እንዳነሰች መረዳት በመቻሌ ነው፡፡ መጠንዋ የቀነሰው ሆን ተብሎ፣ ያውም ከሰሞኑ በተደረገ የመጠን ለውጥ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ዋጋ ከመጨመር መጠኑን አሳንሶ ለደንበኛ ማቅረብ ተዘዋዋሪ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደሆነ የሚያሳብቅ አጋጣሚ ነው፡፡ የባሰበት ጣባውንም አሳንሶ ዋጋም ጨምሮ ለደንበኛው ቢያቀርብስ ማን ይከለክለዋል?

የአገልግሎት አሰጣጣችን በየጊዜው እየወረደ ስለመሆኑ እንድታዘብ አድርጎኛል፡፡ ከሰሞኑ የዋጋ ጭማሪ ብቻ ሳይሆን፣ መጠን በማሳነስ እየታየ ያለው ሙከራ ያሳዝናል፡፡ የቡናው ጉዳይ ብዙ ያነጋግራል፡፡ በእኔ እምነት አሳማኝ የሚባል ዋጋ ሊያስጨምር የሚችል አጋጣሚ ሲፈጠር የዋጋ አተማመናችን በዘፈቀደ ለመሆኑ የቡና ደንበኛዬ ድርጊት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡  

እርግጥ ስኳር በአግባቡ ሊቀርብ ባለመቻሉ በጥቁር ገበያ በ40 እና 50 ብር እየገዛን ጥቂት ሳምንታት አሳልፈናል፡፡ ነገር ግን የቱንም ያህል ቢሆን ቢወደድ፣ በጥቁር ገበያም በውድ ዋጋ ቢገዛ አምስት ብር የሚሸጥ አንድ ስኒ ቡና በአንዴ ሰባት ብር የሚገባበት ምክንያት የለውም፡፡ ሸማቾች ፈተናችን በትንሹም በትልቁም ጉዳይ እየተበራከተ፣ የግብይት ባህላችን ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ስለመምጣቱ በየጊዜው የምናስተናግዳቸው ገጠመኞች ይነግሩናል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት