Thursday, December 7, 2023

የታላቁ ህዳሴ ግድብ አካባቢያዊ ፋይዳ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታን የመሠረት ድንጋይ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ከጣለች በኋላ ይበልጥ ተወሳስቦ ነበር፡፡ ግድቡ በሁለቱ አገሮች ላይ መሠረታዊ ጉዳት ያስከትላል? አያስከትልም? የሚለው ጉዳይ አዲስ የውዝግብ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ መጀመርያ ላይ ሁለቱም ግድቡን ተቃውመው እንዲቆም ጠይቀው ነበር፡፡ በተለይ ግብፅ የግድቡ ግንባታ በፍጥነት ካልተገታ የኃይል ዕርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ አስጠንቅቃ ነበር፡፡ በኋላ ግን ሱዳን የግድቡን ዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ጥቅሞች በመገንዘብ፣ ከኢትዮጵያ ጋር መሥራት መጀመሯ ለግብፅ ዕረፍት የማይሰጥ ሥጋት ሆኖባታል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ ኮሚቴ 16ኛውን ስብሰባውን ከማካሄዱ በፊት፣ የአገሮቹ የውኃ ሚኒስትሮች የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጎብኝተው ነበር፡፡ በወቅቱ የግብፅ የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አቲ (ዶ/ር) የግድቡ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት በመዘግየቱ ሥጋት እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡

እንደተገመተውም እ.ኤ.አ. ከኦክቶበር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ለአምስተኛ ጊዜ በሩዋንዳ ኪጋሊ ኮንቬንሽን ሴንተር በተካሄደው የናይል ቤዚን ዴቨሎፕመንት ፎረም ላይ፣ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ የግድቡ ግንባታ ከ60 በመቶ በላይ እንደ ደረሰ መንግሥት በቅርቡ መግለጹ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን ብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጌዲዮን አስፋው (ኢንጂነር) ግድቡ በዓመት 12,128 ጊጋ ዋት አወር እንደሚያመነጭ፣ በዚህም በዓመት ከ750 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ገቢ ያስገኛል ተብሎ እንደሚገመት ገልጸዋል፡፡ አጠቃላይ ኃይል የማመንጨት አቅሙም መጀመርያ ላይ 5,250 ሜጋ ዋት፣ በኋላ ላይ ደግሞ 6,000 ሜጋ ዋት የነበረ ቢሆንም አሁን 6,490 ሜጋ ዋት ደርሷል፡፡

ኢንጂነር ጌዲዮን የዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን መሪ አባልም ነበሩ፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተካሄዱ የሦስትዮሽ ድርድሮችም በቀጥታ ተሳታፊ ስለነበሩ በጉዳዩ ላይ ከማንም የተሻለ መረጃ አላቸው፡፡ ‹‹በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ላይ የሚገነባ ግዙፍ ፕሮጀክት የሦስቱን አገሮች ተቀራርቦ አብሮ መሥራት ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ መሠረታዊ ጉዳት እንዳያስከትል ተደርጎ እየተገነባ መሆኑን በመግለጽ፣ የተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ከግብፅና ከሱዳን ጋር ለማካሄድ ፈቃደኝነቷን ማሳየቷንና ይህንንም ለማከናወን ዓለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ፓናል 2004 .. እንዲቋቋም ማድረጓንም አስታውሰዋል፡፡ የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች በጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም. ቡድኑ የሚሠራበትን ዝርዝር መመርያ እንዳፀደቁም ጠቅሰዋል፡፡ ቡድኑ የግድቡን የዲዛይን ሰነዶች በመገምገም ግድቡ ለሦስቱ አገሮች የሚሰጠውን ጥቅምና በታችኛው ተፋሰስ አገሮቹ ላይ ተፅዕኖ የሚኖረው ከሆነ፣ እሱን በመመርመር ግልጽ መረጃ በማውጣት በአገሮቹ መካከል የተሻለ ግንዛቤና መተማመን እንዲፈጠር የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር፡፡

ግንቦት 24 ቀን 2005 .. የጥናቱ ሪፖርት ለሦስቱ አገሮች ይፋ ሲሆን ተጨማሪ ጥናቶች እንዲደረጉ ነው ምክረ ሐሳብ የቀረበው፡፡ ‹‹ሪፖርቱን ሦስቱ አገሮች፣ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ፣ አካባቢያዊ ድርጅቶችና ሲቪል ማኅበራት በተለያዩ መንገዶች ነው የተቀበሉት፡፡ ይህም የመነጨው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቡድኑ ውጤት ላይ የጠበቁት ነገር የተለያየ በመሆኑና አንዳንዶቹም አስቀድመው የሚያምኑባቸው ሐሳቦች ስለነበሯቸው ነው፤›› ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

የሪፖርቱን የተወሰኑ ክፍሎች ቆርጠው ለሚፈልጉት የፖለቲካ ዓላማ የተጠቀሙ አካላት እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡ በዚህም ፅንፍ የያዙ ሐሳቦች ተነስተው የግድቡ ግንባታ እንዲቆም የሚጠይቁ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ውጤቶች መታየታቸውንና የበፊቱ የግብፅ መንግሥት አባላት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት እንዲከፈት እስከ መጠየቅ ደርሰው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከሪፖርቱ ይፋ መሆን በኋላ ባሉት ዓመታት አገሮቹ እየመከሩ ያሉት ቡድኑ በሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ላይ ነው፡፡ ከሦስቱም አገሮች አራት አራት ኤክስፐርቶች ተውጣጥተው የመሠረቱት የሦስዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴም እነዚህ ምክረ ሐሳቦች የሚተገበሩበትን መንገድ እንደሚከታተል ኢንጂነር ጌዲዮን አመልክተዋል፡፡

በዚህ መሀል በ2007 ዓ.ም. ሦስቱ አገሮች በህዳሴ ግድቡ ላይ የመርህ መግለጫ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱ ከዓለም አቀፍ የውኃ ሕግና ከሲኤፍኤው የተወሰኑ ድንጋጌዎችንና መርሆዎችን ይዟል፡፡ ኢንጂነር ጌዲዮን ይህ ስምምነት የሦስቱ አገሮች የድርድር ፍሬ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹በዚህ ስምምነት ኢትዮጵያ ከናይል ቤዚን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (ሲኤፍኤ) እንዳፈነገጠች ተደርጎ በስህተት ሲተረጎም ነበር፡፡ በመሠረቱ ይህ በስምምነቱ አንቀጽ 34 ላይ የተወሰኑ የተፋሰሱ አገሮች በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ስምምነት እንዲያደርጉ የተደነገገውን ሐሳብ መዘንጋት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና በሦስትዮሽ ድርድሩ ሒደት በተለይ በተፅዕኖ ግምገማው ላይ ስምምነት ለማድረግ እንዳይችሉ ያደረጉ ጉዳዮች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡ አሁን በጥቅም ላይ የዋለው የውኃ መጠንና እሱ የሚሰላበት መነሻ፣ እንዲሁም ወደፊት የሚያስፈልግ የውኃ መጠን አገሮቹን እንዳላስማሙ ጠቅሰዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በፎረሙ የቀረቡ አንዳንድ ጥናቶች አገራቸው ከሌሎች የውኃ እጥረት ካለባቸው የተፋሰሱ አገሮች በተቃራኒ ውኃ በገፍ እንዳላት ተደርጎ መቅረቡን ተቃውመው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ውኃው በአካል መኖሩ እንደ ትልቅ ጉዳይ መታየት የለበትም፡፡ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በውኃ እጥረት የሚሰቃዩት የውኃ ሀብታቸውን የማልማት የኢኮኖሚ አቅም ስለሌላቸው ነው፡፡ ውኃውን ለመጠጥና ለካፒታል ኢንቨስትመንት የመጠቀምና ይህን ለማድረግ ተቋማዊ አቅም ስለመገንባቱም ውይይቱ ግንዛቤ ውስጥ ሊያስገባ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ግድቡን በተመለከተ ሦስቱ አገሮች ያላቸው ልዩነት በተለይ በግድቡ አሞላልና አለቃቀቅ፣ እንዲሁም ኃይል ማመንጨት ሲጀምር የሚኖረው ጥቅምና ጉዳት ምን ይመስላል? በሚሉት ሁለት ጉዳዮች በዋነኛነት የሚገለጽ ነው፡፡ ኢንጂነር ጌዲዮን ሦስቱ አገሮች በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚኖራቸው ትብብር በሳይንሳዊ ዕውቀት ላይና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ መመሥረት እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

ከዚሁ አንፃር የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ (ኤንቢአይ) ሴክሬታሪያት ዋና ዳይሬክተር ኢኖሰንት ንታባና (ኢንጂነር) ሲናገሩ፣ ‹‹ኤንቢአይ ሳይንሳዊ ዕውቀቶችን ያመነጫል፣ ያከማቻል፡፡ ይሁንና በሌሎች ምንጮች ላይም እንመሠረታለን፡፡ ፎረሙ በናይል ላይ የሚሠሩ ሌሎች መጥተው ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉና እንዴት በትብብር ተፋሰሱን እንደምናለማ ለምንወስደው ውሳኔ የሚያግዝ ሐሳብ እንዲያካፍሉን ዕድል ይሰጣል፤›› ብለዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ለተፋሰሱ አገሮች ጭምር የሚጠቅም በመሆኑ የትብብር መስህብ አለው፡፡ እርግጥ ነው ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ጥናቶች ግድቡ ግብፅንና  ሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ተጠቃሚ የሚያደርግባቸው ሳይንሳዊ እውነታዎች እንዳሉ ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ለአፈር ዝቅጠት፣ የውኃውን ፍሰት ለመቆጣጠር፣ እንዲሁም ከድርቅና ከጎርፍ የታችኛውን የተፋሰስ አገሮች በመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ያስገነዝባሉ፡፡ ኢንጂነር ጌዲዮን ግድቡ የተጠራቀመ ውኃን በድርቅ ጊዜ በመልቀቅ፣ እንዲሁም ርካሽ ታዳሽ ኃይል በማቅረብ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ትልቅ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

ዶ/ር ስለሺ በህዳሴ ግድቡ ላይ በርካታ ውይይቶች ቢደረጉም በአብዛኛው አሉታዊ ጎኑ እንደሚንፀባረቅ ተችተዋል፡፡ ‹‹የግብፁ አስዋን ወይም የሱዳኑ መሮዌ ግድቦች ባይኖሩ የኃይል ማመንጫ ግድብ የት ሊገነባ ይችላል? በእኔ አመለካከት ሊገነባ የሚችለው አሁን ህዳሴ ግድቡ የሚገኝበት ቦታ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ውኃ ያከማቻል፣ የታችኛውን የተፋሰስ አገሮች ከጎርፍ ይጠብቃል፣ ኃይል ያመነጫል፡፡ እርግጥ አንዳንዶች በሙሌቱ ወቅት ውኃ ስለሚቀንስ የአስዋን ግድብ ኃይል የማመንጨት አቅም እንደሚቀንስ ይከራከራሉ፤›› ብለዋል፡፡

በተለይ ከድንበር ዘለል ትብብር አንፃር የግድብ ኃይል የማመንጨት አቅም ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ዶ/ር ስለሺ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለግብፅና ለሱዳን ጭምር ከፍተኛ ኃይል የመሸጥ ዕድል እንደሚፈጥርላት አስታውሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ራሷ የኃይል አቅርቦት ችግር ስላለባት ይህን ለመለወጥ ካለው ጠቀሜታ ባሻገር ለጂቡቲና ለሱዳን ከወዲሁ የኃይል ሽያጭ እያከናወነ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ለኬንያ፣ ለታንዛኒያና ለደቡብ ሱዳን ደግሞ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገችና መስመር እየዘረጋች እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ነገር ግን በግብፅ ካይሮ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስና ፖለቲካል ሳይንስ ፋኩልቲ መምህርና በአሁኑ ወቅት ግን በጀርመን የልማት ኢንስቲትዩት እየተመራመሩ የሚገኙት ግብፃዊዋ ራዊያ ተውፊቅ (ዶ/ር)፣ ግድቡ ለሁሉም ጥቅም ይሰጣል በሚለው ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ግድቡ የሚሰጠውን ጥቅምና ጉዳት ለማስላት ግልጽ መሥፈርቶች እንደሌሉም ይከራከራሉ፡፡ በተለይ ‹መሠረታዊ ጉዳትን› መተርጎም፣ አሁን በጥቅም ላይ የዋለውንና ወደ ፊት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለውን የውኃ መጠን መለካትና በሚደርስ ጉዳት ላይ ስለሚከፈል የካሳ ክፍያ ስምምነት አለመኖሩ ትልቅ ተግዳሮት መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡ ጥቅም ለሁሉም አገሮች ይሰጣል እንኳን ቢባል ጥቅሞቹ ተመጣጣኝ እንዳልሆኑ አመልክተዋል፡፡

ኤንቢአይ ለተፋሰስ አገሮች ጥሩ የውይይት መድረክ ሆኖ እያገለገለ ቢሆንም፣ ሲኤፍኤው ቢያንስ በፈረሙት ስድስት አገሮች ፀድቆ ወደ ሥራ ያልገባበት ምክንያት ግን አጠያያቂነቱ ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ የናይል ቤዚን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን (ሲኤፍኤ) ያፀደቁ ብቸኛ አገሮች ናቸው፡፡ ዶ/ር ስለሺ ስምምነቱ የተወሰነ መደነቃቀፍ አጋጥሞት ወደ ሥራ ባይገባም፣ የተፋሰሱን ችግሮች መፍቻ መንገዶች ጭምር መያዙን አስታውሰዋል፡፡

ውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሾመ አጥናፌ፣ ኢትዮጵያ የውኃ ሀብቷን ለማልማት ተፋሰስ አቀፍ ስምምነት እስኪፈጸም እንደማትጠብቅ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በትብብር መሥራት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ይሁንና ተፋሰስ አቀፍ ስምምነቱን ለመፈጸም ረዥም ጊዜ እየወሰደ ነው፡፡ ይህ እስኪሳካ በግል፣ በሁለትዮሽና ከተወሰኑ አገሮች ጋር በጋራ በተለያዩ ተቋማቶቻችንና ዘርፎቻችን አማካይነት መሥራታችንን እንቀጥላለን፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ተሾመ ለአብነትም ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከኬንያ ጋር እየሠራች እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በተመሳሳይ የሱዳኑ የውኃ ሀብትና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ሙታዝ ሙሳ አብደላ (ዶ/ር) በትብብር አስፈላጊነት ላይ ጥርጣሬ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በትብብር ጉዳይ ላይ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ አመለካከት እንደሌለው አመልክተዋል፡፡ በተለይ በውኃ እጥረት ላይ የተፈጠረው ዕይታ ለትብብር እንቅፋት እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹ብዙዎቹ ጥናቶች የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ እንደሆነና የውኃ ሀብታችን ግን ተመሳሳይ እንደሆነ በመጥቀስ ያስጠነቅቃሉ፡፡ ይኼ አስፈሪ ቋንቋ ትብብር ይከለክላል፡፡ ሁሉም ሰው አሁን የውኃ እጥረት እያጋጠመ እንደሆነ ያምናል፡፡ እኔ የውኃ እጥረት አለ ብዬ አላምንም፡፡ ከሆኑ አሥርት ዓመታት በፊት የዓለም ሕዝብ ቁጥር 1.6 ቢሊዮን ብቻ ነበር፡፡ የውኃ ሀብታችን ግን ያኔም ተመሳሳይ ነበር፡፡ አሁን የሕዝብ ቁጥር በሰባት እጥፍ ጨምሯል፡፡ ሰው ግን እየኖረ ነው፡፡ ስለዚህ የውኃ እጥረት ወደፊት እንዴት እንደሚመጣና እስካሁን ለምን እንዳልመጣ አሳማኝ ሳይንሳዊ ጥናት ሊነግረን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ፎረሙ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከመከረ በኋላ ተፋሰሱን ከችግር ለማዳን የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦች በመስጠት ተጠናቋል፡፡ ለአብነት ያህልም አገሮቹ በተናጠል ወደ ልማት ከገቡ በጣም ከፍተኛ የሆነ የውኃ እጥረት እንደሚኖር፣ በትብብር ከሠሩ ግን እጥረቱን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንደሚችሉ ምክር ተሰጥቷል፡፡ 

የናይል ቤዚን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ስለሺ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀጣዩን ፎረም ከሁለት ዓመት በኋላ እንደሚያዘጋጅ አብስረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -