Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሀገር ፍቅር ለአንጋፎች ዕውቅና ሰጠ

ሀገር ፍቅር ለአንጋፎች ዕውቅና ሰጠ

ቀን:

በወጣትነታቸው በቴአትር፣ በውዝዋዜ፣ በሙዚቃና ሌላም ያደመቁትን መድረክ ከጡረታ በኋላ ዳግም ማግኘታቸው ያስደሰታቸው ይመስላል፡፡ ዕድሜ በመጠኑ ቢጫጫናቸውም፣ ‹‹አሲና በል አሲና ገናዬ›› እያሉ በሀገር ፍቅር መድረክ ላይ ሲጨፍሩ እንዳፍላነታቸው ነበር፡፡ አርቲስት ዓለማየሁ ፈንታ መዲናና ዘለሰኛ ሲያስደምጡ እንዲሁም ከሌሎች የቴአትር ቤቱ አንጋፋ አርቲስቶች ጋር ተጣምረው ያሬዳዊ ዜማ ሲያቀርቡ ታዳሚው ከመቀመጫው ተነስቶ አክብሮቱን አሳይቷል፡፡ አርቲስት አዳነች ተሰማ ‹‹ሰላም ለምወድህ ለኔ ትዝታ…››ን እያቀነቀኑ ወደ መድረክ ሲወጡም ብዙዎች በስሜት ተሞልተዋል፡፡ አርቲስቶቹ ዳግም በመድረክ የታዩት ጥር 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ቴአትር ቤቱ በጡረታ ለተገለሉ ባለሙያዎች ዕውቅና ለመስጠት ባዘጋጀው መርሐ ግብር ነበር፡፡ የቴአትር ቤቱ 41 አርቲስቶች በቆይታቸው ለሰጡት አገልግሎት ተመስግነዋል፡፡ ከአርቲስቶቹ መካከል በቅርብ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ጥላሁን ወልደማርያም ይጠቀሳሉ፡፡ አዳነች ተሰማ፣ አብራር አብዶ፣ ሀብተሚካኤል ደምሴ፣ ጌታመሳይ አበበ፣ ችሮታው ከልካይ፣ ሳራ ተክሌ፣ ፀዳለ ግርማ፣ ኪሮስ ኃይለሥላሴ፣ ሐዋ ታለ፣ ሞገስ ተካ፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ አበበ ካሳና ዓለማየሁ ፈንታም ይገኙበታል፡፡ የቴአትር ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳዬ ገበየሁ እንደገለጹት፣ ለረዥም ዘመን አገልግሎት የሰጡ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ማስታወስና መዘከር ለወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ዕውቅና የተሰጠው በቅርቡ የሚከበረውን የቴአትር ቤቱን 80ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግም ጭምር ነው፡፡ በጡረታ ለወጡት ዕውቅና መስጠት አሁን በሥራ ላይ ያሉትንም ያተጋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ የቴአትር ቤቱን ዝና ለማደስም አጋዥ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ የዛሬው ሀገር ፍቅር ሐምሌ 11 ቀን 1927 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ፍቅር ማኅበር›› በሚል ነበር የተቋቋመው፡፡ ቡድኑ በ1928 ዓ.ም. በጣልያን በወረራ ሳቢያ ቢበታተንም በ1933 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ፍቅር ቴአትር›› በሚል ዳግም ተቋቁሞ ለዓመታት አገልግሏል፡፡ የቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች በተለያየ ዘመን ለጥበብ የነበራቸውን ሚና ያብራሩት ዕውቅና ከተሰጣቸው አንዱ አርቲስት ኪሮስ ኃይለሥላሴ እንደተናገሩት፣ ቴአትር ቤቱ ከዕድሜው አንፃር አድጓል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለበርካታ ጥቅም የሚውል ተጨማሪ ሕንፃ በመገንባት ማስፋፊያ እንዲደረግለትና ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠውም አርቲስቱ አሳስቧል፡፡ ለአርቲስቶቹ የአበባ ጉንጉን ያጠለቁት የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረፃዲቅ ሐጎስ ሕዝብን ከማዝናናት በተጨማሪ የአገሪቱን ባህልና ታሪክ ከአንድ ዘመን ወደ ቀጣዩ እንዲተላለፍ ያላሰለሰ ጥረት ያረጉ ባለሙያዎችን በመዘከሩ ቴአትር ቤቱን አመስግነዋል፡፡ ‹‹ለረዥም ዓመታት ሕዝብን በማገልገላችሁ ሁሌም እናስታውሳችኋለን፤ ሁሌም እንወዳችኋለን በልባችንም ትኖራላችሁ፤›› ያሉት ኃላፊው፣ አንጋፎችን መዘከር በሌሎች ቴአትር ቤቶች ቢለመድ መልካም ነው ብለዋል፡፡ ዕውቅና በተሰጣቸው አርቲስቶች በእያንዳንዳቸው ስም የ2,000 ብር እንዲሁም በቴአትር ቤቱ ስም የ18,000 ብር ቦንድ ቢጂአይ አበርክቷል፡፡ አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለቴአትር ቤቱ አርቲስት ጥላሁን መታሰቢያ 25 ሺሕ ብር የሚያወጣ ሐውልት በግቢው እንደሚያስገነባም አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...