Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአንገት ከመቅላት ወደ ገንዘብ ድርድር የገባው አይኤስ

አንገት ከመቅላት ወደ ገንዘብ ድርድር የገባው አይኤስ

ቀን:

ከአንድ ዓመት በፊት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንንም ያህል ዕውቅና ያልነበረው ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ዛሬ የለዓለም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በተለይ በሶሪያ ላለፉት ሦስት ዓመታት የዘለቀው አለመረጋጋት አድማሱን እንዲያሰፋ አስችሎታል፡፡ በሶሪያ አለመረጋጋት ምክንያት በዓለም ታዋቂ ለመሆን ዕድል ያገኘው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን፣ በሶሪያና በኢራቅ እስላማዊ መንግሥት የመመሥረት ዓላማ እንዳለው ሲናገር፣ አሜሪካና አጋሮቿ ደግሞ በአሸባሪነት ይፈርጁታል፡፡ ገና ከማቆጥቆጡ ተደምስሶ የነበረውና በሶሪያ የተፈጠረው አለመረጋጋት ለማንሰራራት ዕድል የፈጠረለት አይኤስ፣ በሰሜናዊ ሶሪያና በኢራቅ ድንበር ቁልፍ ሥፍራዎችን በመቆጣጠር የኢራቅንም ሆነ የኢራቅን ጦር ኃይል ለማገዝ የመጡ ኃይሎችን እየተፈታተነ ይገኛል፡፡ ለዚህም ደግሞ የጀርባ አጥንት የሆነው በያዛቸው ሥፍራዎች የሚዘርፋቸው ንብረቶች ብቻ አይደሉም፡፡ ቢቢሲ የቀድሞውን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ቹክ ሄግል ጠቅሶ እንደዘገበው፣ አይኤስ በውስብስብና ከአሸባሪ ቡድን በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ ዕርዳታ የሚያገኝ ቡድን ነው፡፡ ጀሃዳዊነትን በማወጅ በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ አክራሪ ቡድኖች መካከል የአፍጋን ታሊባን ከዕፅ ሽያጭ በዓመት 400 ሚሊዮን ዶላር፣ አልሸባብ ከከሰል ንግድና ታክስ በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር፣ ቦኮ ሐራም ከዕገታ ማስለቀቂያ ገንዘብ በመጠየቅ እንዲሁም ገቢ ማሰባሰቢያ በማዘጋጀት አሥር ሚሊዮን ዶላር፣ አልፋስራ ግንባር ዕርዳታ ከማሰባሰብ፣ ከማገትና ማስለቀቂያ ከመጠየቅ ልኩ ያልታወቀ ዶላር በዓመት ሲያገኙ የአይኤስ ግን ከሁሉም በልጦ ይገኛል፡፡ ኢስላሚክ ስቴት ከተቆጣጠራቸው ሰሜናዊ ሶሪያና ኢራቅ አካባቢ ነዋሪዎች ግብር በመሰብሰብ፣ የነዳጅ ዘይት በመሸጥና ከነዋሪዎች ተጨማሪ ክፍያዎችን በመጠየቅ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያገኛል፡፡ ይህም አሜሪካን ጨምሮ የኢራቅን ወታደራዊ ክፍል ለማገዝ የመጡ ጥምር አካላትን ጦር ገትሮ ለመያዝ አቅም ፈጥሮለታል፡፡ አይኤስ እስከዛሬ በነበረው ልምዱ ታክስ ከመሰብሰብ፣ ተጨማሪ ክፍያ ከማስከፈልና ነዳጅ ዘይት ከመሸጥ በተጨማሪ ‹‹ጠላቶቼ›› የሚላቸውን በማገት በገንዘብ መደራደር መጀመሩን ሰሞኑን የወጡ ዘገባዎች አሳይተዋል፡፡ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ አይኤስ ሰሞኑን በለቀቀው የቪዲዮ መልዕክት ያገታቸውን ሁለት ጃፓናውያን እንደከዚህ ቀደሞቹ የእንግሊዝና የአሜሪካ ታጋቾች አንገታቸውን ከመቅላቱ በፊት 200 ሚሊዮን ዶላር መደራደሪያ ጠይቋል፡፡ ማክሰኞ ዕለት በተለቀቀው የአይኤስ አዲስ መልዕክት ድርድሩ ለ72 ሰዓታት ብቻ የሚቆይ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ገንዘቡ በቡድኑ እጅ ካልገባ የታጋጆቹ ዕጣ ፈንታ መቀላት ይሆናል፡፡ አይኤስ ከዚህ ቀደም ያገታቸውን ሦስት አሜሪካውያንና ሁለት እንግሊዛውያን አንገታቸውን በመቅላትና በቪዲዮ በመልቀቅ ከፍተኛ ሽብር የፈጠረ ሲሆን፣ በዚህም በዓለም አቀፍ መድረክ ዕውቅናን አትርፏል፣ የሚዲያው አጀንዳም ለመሆን በቅቷል፡፡ አንገት በመቅላትና ለዓለም በማሳየት ይበልጥ ዕውቅናን ያተረፈው አይኤስ፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው ልማድ በተለየ ሁኔታ ያገታቸውን ጃፓናውያን በገንዘብ ለመለወጥ የድርድር ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ታጋቾቹ ኬንጂ ጐቶ ጆጐ የተባለ ጋዜጠኛና ሃሩዋና ካዋ የተባለ ወታደር ሲሆኑ፣ የመደራደሪያ ሐሳቡን በድምፅና በምሥል አስደግፎ ከለቀቀው ሙሉ ጥቁር ለባሽ ታጣቂ ግራና ቀኝ ተንበርክከው፣ እጃቸውን ወደኋላ ታስረውና ቡርትካናማ የእስረኛ ልብስ ለብሰው ታይተዋል፡፡ ሰይፉን በግራ እጁ አቅንቶ ‹‹መንግሥታችሁ ላይ ጫና ፈጥራችሁ በእጃችን የሚገኙትን ጃፓናውያን ሕይወት ለማትረፍ 72 ሰዓታት አላችሁ፤›› ሲል የተደመጠው የአይኤስ ታጣቂ ከዚህ ቀደም የእንግሊዛዊ የአነጋገር ዘዬ አለው ሲባል ከነበረው አንገት ከሚቀላ ሰው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ለጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በቀጥታ የተለቀቀው የቪዲዮ መልዕክት፣ ‹‹ለጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር እርስዎ አይኤስ ካለበት 8,500 ኪሎ ሜትር ርቀው ቢገኙም፣ እኛን ከሚወጉ ኃይሎች ጋር በበጐ ፈቃደኝነት ተቀላቅለዋል፡፡ የእኛን ሴቶች፣ ሕፃናትና የሙስሊሙን ቤቶች ለማውደም 100 ሚሊዮን ዶላር ለግሰዋል፤›› ብሏል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የጃፓኑን ጠቅላይ ማኒስትር፣ በግብፅ በነበራቸው ቆይታ አይኤስ በኢራቅና በሶሪያ በከፈተው ጥቃት ለተሰደዱና ችግር ውስጥ ለወደቁ ዜጐች ወታደራዊ ያልሆነ 200 ሚሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ በአይኤስ የታገቱትን ጃፓናውያን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ፣ የታገቱት እንዲለቀቁ ጠይቀው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር አብረው እንደሚሠሩ በድጋሚ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ቅድሚያ ለዜጐቻችን እንሰጣለን፤›› ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ፣ ከሽብርተኛ ጋር እንደማይወግኑና ገንዘብ እንደማይሰጡ ጠንከር ብለው አስታውቀዋል፡፡ ከእየሩሳሌም ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹እስልምናና ጽንፈኝነት የተለያዩ ናቸው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሽብርተኝነትንና ፅንፈኝነትን ለመዋጋት አብሮ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ካይሮ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመካከለኛው ምሥራቅ ከጦርነት ጋር በተያያዘ ለተጐዱ ዜጐች ማቋቋሚያ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 200 ሚሊዮን ዶላሩ በኢራቅና በሶሪያ በአይኤስ ምክንያት የተሰደዱ ሰዎችን ለማቋቋም የሚውል ነው፡፡ ጃፓን የገባችው ቃል ከወታደራዊ ድጋፍ ውጪ ቢሆንም፣ ይህ በአይኤስ ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ ይልቁንም 200 ሚሊዮን ዶላሩ ለቡድኑ እንዲሰጥ፣ በምትኩም ያገታቸውን ጃፓናውያን እንደሚለቅ አሳውቋል፡፡ ታጋቾቹም ቁልፍ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ እንደሆኑለት እየተነገረ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...