Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የፓርኪንግ እጦት የፈተናቸው ኢንቨስተር

ዮቤክ ቢዝነስ ኩባንያ የተለያዩ የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ይሠራል፡፡ የኤሌክትሪክ ዕቃዎችን ያቀርባል፣ ግዙፍ ግንባታዎችንም በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመግባት ማሸጊያዎችንና የኤሌክትሪክ ኮንዲውቶችን በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባ ሰንጋ ተራ አካባቢ ሁለት ሕንፃዎችን እየገነባ ሲሆን፣ ሕንፃዎቹ በአሁኑ ሰዓት ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቀዋል፡፡ ከእነዚህ ሕንፃዎች በተጨማሪ ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ በቅርቡ ሥራ ከጀመረው ስፖርት አካዳሚ አጠገብ የሆቴል ግንባታ እያካሄደ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ያሉት ግንባታዎች የተገባደዱ ቢሆንም ኩባንያውን የሚያስጨንቀው ነገር አለ፡፡ አቶ ብርሃነ ግደይ የኩባንያው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ቢያፈሱም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጎናቸው ሆኖ ሊደግፋቸው አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት ሦስቱም ሕንፃዎች የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) ችግር ያሰጋቸዋል፡፡ በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ውድነህ ዘነበ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ ቦታዎች ግንባታዎችን እያካሄዳችሁ ነው፡፡ ‹‹እኛ ግንባታ ብናካሂድም የአዲስ አበባ አስተዳደር እየደገፈን አይደለም›› የሚል ቅሬታ አላችሁ፡፡ መነሻችሁ ምንድነው?

አቶ ብርሃነ፡- እኔ ከትንሽ ነው የተነሳሁት፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎችን እያካሄድኩ ነው፡፡ የተለያዩ ግዙፍና ውበት ያላቸው ሕንፃዎች እየገነባሁ ነው፡፡ ነገር ግን ሥራዎቹን ስንሠራ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር እየደገፈን አይደለም፡፡ መደገፍ እንኳ ቀርቶ ምን እየሠራን እንደሆነ የሚመለከት አካል አጥተናል፡፡ ሕንፃው ምን ችግር አለበት ብሎ የሚጠይቅ የለም፡፡ እኛ በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም መልስ የሚሰጥ አካል የለም፡፡ ሕንፃዎቹ ከፍተኛ ገንዘብ የወጣባቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን መውጪያ መግቢያ ይጎላቸዋል፡፡ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) የላቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ሰንጋ ተራ ያሉት ሁለቱ ሕንፃዎች በስንት ካሬ መሬት ላይ ነው ያረፉት? የወጣባቸው ካፒታልና ያለባቸው ችግር ምንድነው?

አቶ ብርሃነ፡- የቦታው ጠቅላላ ስፋት 2,400 ካሬ ሜትር ነው፡፡ ሁለቱን ሕንፃዎች በሁለት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፉ ናቸው፡፡ አንዱ ሕንፃ አሥራ አምስት ፎቅ ሲሆን፣ አንደኛው ደግሞ አሥር ፎቅ ነው፡፡ ቤዝመንት አለው፡፡ ቤዝመንቱ ለፓርኪንግ አገልግሎት ይውላል፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ በሕንፃዎቹ የሚገለገለው ሰው ብዛት ያለው በመሆኑ ሌሎች አገሮች እንዳለው የፓርኪንግ ሕንፃ ሊኖር ይገባል፡፡

በተለይ አንደኛው ሕንፃ መግቢያ መውጪያ የለውም፡፡ ለእኔ የግንባታ ፈቃድ ሲሰጠኝ የፓርኪንግ ችግር እንደሚፈታ ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ አሁን ከፊት ለፊቱ ነባር ግንባታዎች ቢፈርሱም ቦታውን ግን ማግኘት አልቻልንም፡፡ አንዱ ሕንፃ መንገድ ዳር በመሆኑ ችግር የለውም፡፡ አንዱ ሕንፃ ግን በጣም ችግር ውስጥ ነው ያለው፡፡ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን አጢኖ ከፊት ለፊት ያለውን መሬት የዚሁ ፕሮጀክት አካል ቢያደርገው የሚል ጥያቄ አለን፡፡ ቦታው ያለበት ችግር በድጋሚ ሊታይ ይገባል፡፡ እኛ ተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ሰሚ አላገኘንም፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ካሬ ሜትር ቦታ ነው የፈለጋችሁት? ይህንን ችግር ለመፍታት የምታካሂዱት ግንባታስ ምንድነው?

አቶ ብርሃነ፡- የምንፈልገው ከ500 እስከ 600 ካሬ ሜትር ቦታ ነው፡፡ ይህ ቦታም ከሕንፃው ፊት ለፊት የሚገኝ ነው፡፡ መንግሥት በመልሶ ማልማት የያዘው ቦታ ነበር፡፡ በግራ በኩል ደግሞ እንዲሁ ከአንድ ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ አለ፡፡ በእኛ አመለካከት ይህ ቦታ ፓርኪንግ ሕንፃ ሊገነባበት ይገባል፡፡ ሰንጋ ተራ የተጨናነቀ አካባቢ ነው፡፡ ብዙ ሕንፃዎች እየተገነቡ ነው፡፡ ነገር ግን የፓርኪንግ ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ራሱን ችሎ ፓርኪንግ ሕንፃ ቢገነባ መፍትሔ አይሆንም?

አቶ ብርሃነ፡- ከሠራ ጥሩ ነገር ነው፡፡ እሱም መፍትሔ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት ከሚሠራ ይልቅ ባለሀብት ቢሠራ ይሻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለእኔ ቢሰጠኝ ከሕንፃዎቼ ጋር የተጣጣመ እስከ አሥር ፎቅ ከፍታ ያለው የፓርኪንግ ሕንፃ እገነባለሁ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለአገርም ጥሩ አይደለም፡፡ የእኔም ሞራል ይነካል፡፡ እኔ የሠራሁት ሕንፃ ውበት ብቻ ሳይሆን መውጪያ መግቢያ ኖሮት አስፈላጊውን ግልጋሎት ሊሰጥ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ለእነዚህ ሕንፃዎች ምን ያህል ወጪ ተደርጓል?

አቶ ብርሃነ፡- ለሁለቱ ሕንፃዎች እስካሁን 475 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገናል፡፡ በአሁኑ ወቅት 95 በመቶ ተጠናቋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕንፃዎቹ በተወሰኑ የንግድ ዓይነቶች ላይ እንዲያተኩሩ ትፈልጋላችሁ?

አቶ ብርሃነ፡- የፋይናንስ ተቋማት አሉ፡፡ የተለያዩ ሬስቶራንቶች፣ ቢሮዎች ይኖራሉ፡፡ ከዚህ ውጭ በአብዛኛው የኮንስትራክሽንና የኤሌክትሪክ ዕቃዎች መሸጫ ሱቆች ይኖራሉ፡፡ ሕንፃዎቹ ሁለት ጀነሬተሮች፣ ከ16 ሰው በላይ የሚይዙ አራት አሳንሰሮች አሉት፡፡ ውስጡ በጣም የተመቻቸ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቤዝመንቶቹ ምን ያህል ተሽከርካሪ መያዝ ይችላሉ?

አቶ ብርሃነ፡- ሁለቱም ቤዝመንቶች መቶ ተሽከርካሪዎችን መያዝ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ በሕንፃው ላሉት ሦስትና አራት ባንኮች ደንበኞች እንኳ በቂ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ቦትውን ቢፈቅድላችሁ ምን ያህል ተሽከርካሪ የመያዝ አቅም ያለው ሕንፃ የመገንባት ሀሳብ አላችሁ?

አቶ ብርሃነ፡- ቦታውን ቢሰጡኝ፣ ራሱን የቻለ ሦስተኛ ሕንፃ እገነባለሁ፡፡ ሕንፃው አሥር ፎቅ እንዲኖረው አድርጌ ተሽከርካሪዎች እንዲስተናገዱበት አደርጋለሁ፡፡ በእያንዳንዱ ፎቅ 50 ተሽከርካሪ የመያዝ አቅም ይኖራል፡፡   

ሪፖርተር፡- ኢምፔሪያል አካባቢ ለሆቴል የሚሆን ሕንፃ በመገንባት ላይ ናችሁ፡፡ ሆቴሉን እንዲያስተዳድርላችሁ የጠየቃችሁት ዓለም አቀፍ ኩባንያ ፍላጐቱን ቢገልጽም፣ ሆቴሉ የፓርኪንግ ችግር ያለበት በመሆኑ ድርድሩ አልተቋጨም የዚህ ፕሮጀክት ችግር ምንድነው?

አቶ ብርሃነ፡- እንደሚታወቀው መንግሥት በአገሪቱ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል እጥረት በመኖሩ ባለሀብቶች ወደዘርፉ እንዲገቡ ገፋፍቷል፡፡ በዚህ መሠረት ቦታ ወስደን ደረጃውን የጠበቀ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ሕንፃ ገንብተናል፡፡ በውጭ አገር ያሉና የሚታወቁ ብራንዶች ሆቴሉን ለማስተዳደር ፍላጎት አሳይተው፣ ድርድርም ተካሂዷል፡፡ ነገር ግን አሁንም ትልቅ እንከን የሆነው የፓርኪንግ ቦታ አለመኖር ነው፡፡ ይህንንም ለአስተዳደሩ አቅርበናል፡፡ ነገር ግን ያን ያህል ትኩረት አልተሰጠም፡፡ ይህ ችግር እኛ ላይ ብቻ የደረሰ ሳይሆን ብዙ ባለሀብቶችም ተመሳሳይ ችግር እየደረሰባቸው ነው፡፡ ሆቴል ሲባል መኝታ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ባሻገር ሊታሰብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የእኔ ሆቴል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ሦስት ኪሎ ሜትር ብቻ የሚርቅ በመሆኑና የግንባታ ደረጃውም የተሻለ በመሆኑ የውጭ ኩባንያዎች ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ነገር ግን የተሽከርካሪ ማቆሚያ ባመኖሩ ጉዳዩ በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፡፡ እኔም ሞራሌ እየተነካ በመሆኑ፣ ግንባታውን ማፋጠን አልቻልኩም፡፡

ሆቴሉ 275 አልጋ አለው፡፡ የፓርኪንግ ችግሩ ቢፈታ በዚህ ሰዓት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ አስተዳደሩ በሚገባ ሊያስተናግደኝ ይገባ ነበር፣ ነገር ግን የሆቴሉ ግንባታው እስከ 600 ሚሊዮን ብር ወጥቶበት ቆሞ ቀርቷል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

                                                                                                  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች