እነሆ ጉዞ ከስታዲየም ወደ ጎተራ ልንጓዝ ነው። ጨለማው በርትቷል። ከመሸ ልንጓዝ፣ በቀም ያልከሰከስነውን ነገራችንን ማልደን ልንሸክፍ በይደር ይዘን ወደየማደሪያችን እንሯሯጣለን። ኑሮ ብለውት እንደ መቃብር የሞቃቸው ጎዳና አዳሪዎች የለበሷት ብጣቂ ጨርቅ አጠረችን ሳይሉ፣ ሳይገላበጡ ህልምና ቅዠት ሲፈራረቅባቸው አልፎ አልፎ እናያለን። “አይገርምም የሰው ልጅ! ለመኖር እኮ መሬቱ ይበቃ ነበር፣ ሸንሻኙ በጥብጦ እንጂ፤” ይላል አንድ ቀውላላ ተሳፋሪ መጨረሻ ወንበር ላይ። “ምን ሸንሻኙ ብቻ? እኛስ ራሳችን ስኬት፣ በገንዘብ የሰበሰብናቸው ነገሮች ድምር ውጤት እየመሰለን ካለን በላይ ስንመኝ፣ ከተሰጠን በላይ ስንጠይቅ መቼ የእነሱን ያህል እንቅልፍ ይወስደናል?” ትለዋለች በግራ በኩል ጥጓን ይዛ የተቀመጠች ወይዘሮ። ወያላው በመሀል የተሳፋሪውን ጨዋታ ያቋርጣል፡፡ “አሥር አሥር ብር ነው። እንቢ ካላችሁ ይጨምራል! ልብ አድርጉ፤” እያለ ያስፈራራል። “ምን ታስፈራራናልህ? እንዳንተ ዓይነቱ በዝቶ መደንገጥ ካቆምን ቆየን እሺ!” ወዲያው ከጋቢና አንዱ ይጮሃል። ይኼን ጊዜ አንድ ወጣት ከሴት ጓደኛው ጋር ተያይዞ ወደ ወያላው ይጠጋል። “የት ናቸሁ?” እንዲገቡለት ይለማመጣል። የሚሄዱበትን ሲነግሩት፣ “ደስ ስላላችሁኝ በቃ አምስት ብር እቀንሳለሁ። ግቡ በ15 ብር አላቸው፤” ሴቲቱ፣ “በቃ እንግባ ታክሲ አናገኝም፤” ትለዋለች። “ለምን ተብሎ በአምስት ብር አትወስደንም?” ወጣቱ መከራከር ጀመረ። “እየሞላ ነው ብትገቡ አይሻልም? መጨረሻ ነው ዋጋው፤” ወያላው እንደ ጂንስ ነጋዴ ያግባባቸዋል። “አንተ ወጣት ሆነህ የወጣት ነገር አይገባህም እንዴ?” ይላል ወጣቱ የሴት ጓደኛውን እየተሻሸ። ንፋስ በለበሰችው አጭር ቀሚስ ሥር እያፈተለከ ያቁነጠነጣት ጓደኛው ዓይን ዓይኑን ታየዋለች። ከተሳፈሪዎች መሀል ሦስተኛው ረድፍ ላይ ከጎኔ የተቀመጠ ወጣት፣ “ቱ! ከዚህ በላይ ሞት የለም። ያውም ሴት ፊት ኪሴን ‘ላስፎግር?’” ይላል በተብታባ አንደበቱ። ሁለታችን ላይ ተደርቦ የተቀመጠ ጎልማሳ ደግሞ፣ “የሦስት ሺሕ ዓመታት ታሪክ ይዘን ለምን ሴቶቹ ፊት ማጣታችን እንደሚያዋርደን አይገርምም?” ይላል። ዝም ብሎ ማዳመጥ መቻል አንዳንዴ እንዴት ያለመታደል መሰላችሁ? በስንት ጭቅጭቅ አንድ አንድ ብር ተቀንሶላቸው ጥንዶቹ ገብተዋል። ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀምራለች። ወያላው በጨለማ ሒሳብ ሲቀበል እንዳይሳሳት በቀን ያበጃትን አምፖል አብርቶ፣ “ቤታችሁ ገብታችሁ ሒሳብ የምታወራርዱ ሰዎች ካላችሁ መብራት ሊጠፋባችሁ ስለሚችል እዚህ መሥራት ስለምትችሉ። ይመቻችሁ፤” እያለ ማስታወቂያ ይለፍፋል። “አሁን ለእኛ አዝኖ አይመስልም? ስንት ያስገባሉ ስንት ያስወጣሉ ብሎ ሊሰልል እኮ ነው። ነቄ ለነቄ፤” ትላለች መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች ጠይም ዓይን አፋር አላስችላት ብሏት። “ኤድያ የእኛ ደግሞ የትኛው ገቢያችንና ወጪያችን ነው የሚሰለለው? በባዶ ኪስ ኩራቴ እራቴ የሚለው ሁሉ ያለው መሰለሽ? አይምሰለሽ!” ይላታል ጎኔ የተቀመጠው ጎልማሳ ከፊል ወደ እሷ ዞሮ። “እኔ መቼ መሰለኝ አልኩህ! ሂድና ገዢዎቻችን አይምሰላችሁ በላቸው። በሰርክ ሩጫችን ኩራታችን አላንበረክከን ብሎን እንጂ ደልቶን እንዳልሆነ አስረዳቸው፤” ስትል እንደመቆጣት ብላ መለሰችለት። ሁለቱ ሲዘጋጉ ከፊታችን መሀል መቀመጫ ላይ የተቀመጡ በዕድሜ ጠና ጠና ያሉ ተሳፋሪዎች ጨዋታ ጀምረዋል። “ሰው ቀዳዳ ሲያገኝ እንደደ ጃዝማች (ስም ጠርተው) ነው የሚናገረው እባክህ፤” ይላሉ አንደኛው። “ምን ብለዋል ደግሞ እሳቸው? አንተ ሰውዬ እየቆየህ ስትሄድ ትውስታህ ይጨምራል፤” ይላሉ ወዳጃቸው። “ደጃዝማች ከሆነ ሰው ጋር ይጋጩልሃል። ንጉሡ ለሆነ በዓል ደግሰው ድንኳን ውስጥ ሲያበሉ ደጃዝማች ጫፍ መግቢያው ላይ ተቀምጠውልሃል። ንጉሡ ያላዩ መስለው ዓይተዋል። ኩርፊያቸውም ገብቷቸዋል። እናም ዝናብ መጣል ጀመረ። ይኼኔ ንጉሡ ‘ደጃዝማች ወዲህ ገባ በል እንጂ! ዝናቡ ይመታሃል እኮ!’ ቢሏቸው፣ ‘ኧረ ዝናቡስ ደህና ነው እኛን ያስቸገረን ፀሐዩ ነው’ አሏቸው። ይኼውልህ እዚህ ታክሲ ውስጥም ደጃዝማቾች አሉ ልልህ ነው፤” ብለው ሲያበቁ ሁለቱም ተያይዘው መሳቅ ጀመሩ። እኛም እንዲሁ፡፡ ወያላችን ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። “ለወያላም ቲፕ ይተዋል’ የሚል አዲስ መመርያ ወጥቷል እየተባለ ነው። እኔ እንኳን ዛሬ መስማቴ ነው፤” እያለ ከፊት ያለው የሚሰጠውን መልሱን እንዲተውለት ይጥራል። አንዳንዱ ላይ ይሳካለታል። ግን በወያላው ነገረ ሥራ አንጀቷ የተቃጠለ ወይዘሮ ድንገት ቀና ስትል፣ “ጌታዬ ሆይ! እባክህ 11 ሚሊዮን ዶላርና ጤናዬን ስጠኝ!” የሚል ጥቅስ ዓይኗ ገባ። ፈገግ ብላ “11 ሚሊዮን ዶላር የመሰብሰብ ዓላማ ይዘህ ነዋ በዚህ ጨለማ እንዲህ የምትበዘብዘው!” አለችው። ወያላው መልስ ሳይመልስ በፈገግታ ዞሮ አያት። “ደግሞ ሚሊዮኑን ጠይቀህ ጤናም እንዳይቀርብህ ማሰብህ ብሩህ ብትሆን ነው!” ብትለው ደግማ፣ “ያለጤናማ ገንዘብ ብቻውን ‘የማይድን በሽታ ነው’ በይው፤” አላት። ድንግት ጥቅሱ ዘና አድርጓት መለሳለስ የጀመረችው ወይዘሮ ትስቃለች። “እውነቱን ነው! ዘንድሮ ሳይኖረው ከሚራበው ይዞ የማይበላው ብሷል። ይመስለናል እንጂ አጥቶ ከመታረዝ ይዞ መማቀቁ ይብሳል፤” ሲሉ አንደኛው አዛውንት የጨዋታ ምህዳሩን ለጠጡት። ይኼኔ አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት፣ “ምነው ‘ፋዘር’ እርስዎ ትልቅ ሰው አይደሉ? ብዙ ነገር አላዩም በመኖር? ከሌለ ማን ዞር ብሎ ያይና ነው? እኔ ልንገርዎ ሳይኖረኝ ከምኖር ኖሮኝ ባዛጋ እመርጣለሁ፤” አላቸው። በልጁ ንግግር ደንግጠው አዛውንቱ ወደኋላ ለመዞር ሲንጠራሩ ወንበሩ ሰባራ ነበርና ተኝቶ አስተኛቸው። ወያላው ቶሎ ብሎ ፌዝ በለመደ አንደበቱ፣ “ለደንበኞቻችን ምቾት አስበን ከአውሮፓ ያስመጣነው ነው። አይዞዎት አባት፤” እያለ ይወሸክታል። አዛውንቱ ግን ወያላውን ችላ ብለው፣ “የዛሬ ልጆች የሚቀድመውን ትታችሁ የሚከተለውን ስታስቀድሙ ሳያችሁ ታሳዝኑኛለችሁ። ሌላውን ተውትና ዛሬ ከፍቅር በፊት ገንዘብ ካልያዛችሁ ትዳር ይዞ ዘር መተካት ትፈራላችሁ። ልጅ በልጅነት፣ ትውልድ በፍቅር እንደሚታነፅ መገንዘብ አልችል ብላችሁ ገንዘብን የሁሉ ነገር መፍትሔ ስታደርጉ ዕድሜያችሁ በዋዛ አልፎ ቁጭ። ስማ! ገንዘብ በየትኛውም ዕድሜ ላይ ሊገኝ ይችላል ዕድሜ ግን አንዴ ከጠፋ ጠፋ ነው፤” አሉትና ወንበራቸውን ለማቃናት ይታገሉ ጀመር። ውሉ የተወለጋገደ ከመሰለው ጨዋታ እኛም የተቀበልነውን ተቀብለን የተውነውን ትተን ጉዞአችን ቀጠለ። እንዲህ እንዲህ ደግሞ የዲሞክራሲውን ምኅዳር ሌሎቻችን ካላሰፋነው ከአንድ ወገን ብቻ እንዴት ይሰፋል?! እየተጓዝን ነው። ታሪፍ ተከራክረው የገቡት ጥንዶች አንዳንድ ሲባባሉ ቆይተው ዓይናችን እያየ አፍ ለአፍ ተያይዘዋል። “ሥልጣንን ተገን አድርገው በጠራራ ፀሐይ የሚዘርፉን ሳይበቃን፣ ጨለማን ተገን እያደረጉ መንገድ ለመንገድ የሚናከሱ ደግሞ መጡ?” ትላለች ከኋላችን ጥጓን ይዛ የተቀመጠች ሴት። “አሁን ‘ኪሲንግ’ መሀል መናከስን ምን አመጣው? ፍቅር ጠፋ፣ ፍቅር አነሰ፣ ፍቅር ተረሳ እያላችሁ ስንፋቀር ደግሞ መተቸት ምንድነው?” ይላል አጠገቧ የተሰየመው ቀውላላ። “ዘወር በል! ፍቅርን እንዲህ ካለው የሥነ ምግባር ዝቅጠት ጋር አታገናኘው፤” ስትለው መንገድ እንዳገኛት ረስቶና እንደ እኩያው ቆጥሮ፣ “እንዲያው እኛ ምን ይሻለናል? ስንት የሚወገዝ ነውር ሳለ፣ ዓይኑን ያወጣ ሂያጂነት፣ ስግብግብነት፣ ምቀኝነትና አጭበርባሪነት ነግሶብን በሰው ቆዳ የምንቀበር ይመስል በሰው ፍቅር ደርሰን ድንጉር የምንለው ነገር አይገባኝም?” አለ ለሁላችን እንደሚያወራ ሆኖ። በቀኘ ያለው ጎልማሳ ደግሞ ተቀብሎ፣ “እንደሱ አትልም? እነአምታታው በከተማን የጀግንነትና የአርበኝነት ማዕረግ እየሰጠን ሌባውን ‘እሱ ይችልበታል! ቆራጥ ነው! ቆራጥ ናት!’ ስንል በምንውልበት አፋችን ደግሞ መልሰን የሞራልና የሥነ ምግባር ጠበቆች ነን ብለን እንመፃደቃለን። ይብላኝልን!” ብሎ በሐሳብ ተሻረከው። እንደ እኔ ደግሞ በሁለቱ መሀል አስተያየት ለመስጠት አቅቶት ሳንዱች የሆነው አንዴ ጥንዶቹን እያየ፣ አንዴ ምራቁን እየዋጠ፣ አንዴ ዓይኑን እየጨፈነና ጆሮውን እየደፈነ ይጓዛል። በዚህ አያያዛችን ለመራጩ ከሚታደለው ይልቅ ለመሀል ሰፋሪዎች የሚሰጠው ካርድ ሳይልቅ አይቀርም አትሉም? ጉዟችን ወደ መገባደዱ ነው። ጥንዶቹ ከሁላችን በፊት መውረጃቸው ደርሶ ሲወርዱ ሁለቱ አዛውንቶች ከሾፌሩ ጀርባ ከተቀመጠችው ወይዘሮ ጋር እያወሩ ነበር። “እኔ መቼ ለየሁሽ ብለሽ ነው? አውቃሃታል? እኛ ጋ ነው እኮ ዕቁብ የምትጥለው፡፡ ባለፈው ዕጣ የወጣላት?” ይላሉ አንደኛው አዛውንት። በጉዟችን መገባደጃ እንዲህ የሞቀ ሰላምታ ሲለዋወጡ ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠ ተሳፋሪ ደግሞ በስልክ፣ “እኔ ከዚህ በላይ አልታገስም ብዬሃለሁ። ነገ ጠዋት ሚስቱ ፊት ነው ቤቱ ድረስ ሄጄ የማዋርደው። ገንዘቤን ይስጠኝ በቃ!” ብሎ እንደ ኃይድሮጂን ቦንብ ፈነዳ። ፍንዳታው የረበሻቸው ጋቢና የተቀመጡ ተሳፋሪዎች ዘወር ብለው፣ “አቦ ቀስ ብለህ አውራ በለው። ‘ቼክ’ እንዳንጽፍለት እዚሁ፤” ይባባላሉ። የማጣቱን ቁጭትና ብሶት በእነሱ የኑሮ መደላደል፣ ሙላትና መትረፍረፍ በሰከንድ እንደሚያረግቡት አምነው ይስቃሉ። በዚህ ሁሉ ጫጫታ መሀል መጨረሻ ወንበር ጥጓን ይዛ የተቀመጠች አጭር የጠይም ቆንጆ፣ “አወይ ልጅነቴ! እኔስ ደርሶ ልጅነቴ እየናፈቀ አስቸገረኝ፤” ብላ ሲያመልጣት በአካባቢዋ ያሉ ሁሉ ሰሟት። “እንዴት?” ሲላት ከጎኗ ተጣቦ የተቀመጠው ቀውላላ፣ “አታየውም ኑሯችንን? ደስታችን፣ ሰላማችን፣ ሳቃችን፣ ሐዘናችን፣ ጭንቀታችን ምኑ ቅጡ፣ ሁሉ ነገር ከገንዘብ ጋር ተቆራኝቶ ስታይ የምንም ነገር ባሪያ ያልሆንክበት፣ ስለምንም ነገር የማትጨነቅበት ዛሬህን ብቻ የምትኖርበት የልጅነት ዘመን አይናፍቅህም? ማደግ እኮ እንዴት ያለ ክፉ ነገር መሰለህ?” አለችው። “እዚህ ጋ ወራጅ አለ! አደራ የመጨረሻውን ዓረፍተ ነገር ስትደጋግሚው ሰው እየመረጥሽ!” ብሎ ወያላው በሩን ከፈተው። እኛም መጨረሻችን መሆኑን አውቀን ቀስ በቀስ ተግተልትለን ወርደን ተበታተንን። ሕልማችን ወደፊት ልባችን ወደኋላ እየቀረ፣ ‘አይ ገንዘብና ሰው!’ እያልን ነጎድን። መልካም ጉዞ!