Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአዲሱ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ግንባታ ወዴት?

አዲሱ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ግንባታ ወዴት?

ቀን:

በአሰበ ተሰማ

የአገራችን ፖለቲካ ሁሉን አቀፍና አሳታፊነቱ ገና መጐልበት ያለበት ነው፡፡ የዴሞክራሲን አዲስ ባህል መገንባት ከተጀመረ ገና ሁለት አሥርት ዓመታት ዕድሜ ብቻ ነው የተቆጠረው፡፡ ከዚያ በፊት በተለይ ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የምሁራንና የወጣት አብዮተኞች እንቅስቃሴ የጐመራበት የፖለቲካ ትኩሳት ዘመን እንደነበር ሲታሰብ፣ ከ50 ዓመት ያላነሰ ዕድሜ አለው ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ረጅሙ የፖለቲካ ትግል ምዕራፍ ከአፍሪካ አገሮች አንፃር ሲታይ ብዙዎቹ ገና ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ በሚዳክሩበት ወቅት፣ እኛ በአገር ውስጥ በአዲስ የፖለቲካ ፍላጐት የተነሳሱ ወጣት የለውጥ ኃይሎችና አብዮተኞች ነበሩ ማለት ነው፡፡ በአንፃራዊነት ‹‹ረጅም›› የሚባለው የፖለቲካ ትግል የታሪክ ምዕራፍ ግን የሚያኮራና ትምህርት የሚወሰድበት አይደለም፡፡ በተለያዩ ትንታኔዎች እንደተዳሰሰው ጽንፈኛ ፍረጃዎች፣ ግጭትና መጠፋፋት ብሎም ትውልድ የሚሻገር ቂምና በቀል የታጨቀበት ነበር፡፡ ዛሬ ባለው የአገራችን ዴሞክራሲ ጅማሮ ላይ ሳይቀር ጠባሳውን እያሳረፈ ወደ ጠርዝ (Climax) የተለጠጠ ንትርክና የፖለቲካ ተገዳዳሪነት እንዲስተዋል እያደረገ ነው፡፡ ደርግ/ኢሠፓ፣ ኢሕአፓ፣ ኢዲዩ፣ መኢሶን፣ ሕወሓት፣ ኦነግ፣ የመሳሰሉ የፖለቲካ ማኅበሮች የቀዳሚው ዘመን ክፋዮች ናቸው፡፡ በኅብረ ብሔርና በብሔር ጐራ ተደራጅተው ብዙም ያልተጓዙ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችም ተፈጥረዋል፡፡ ፈርሰዋልም፡፡ እስካሁንም መቋቋምና መፍረሱ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ለአምስተኛ ብሔራዊ ምርጫ በምትዘጋጀው አገር ውስጥ ከ70 የማያንሱ ብሔር ተኮር ፓርቲዎች ለምርጫ እየተወዳደሩ ያሉት፡፡ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ የፖለቲካ ቡድኖችም ከነመሪዎቻቸው ከአገር ተሰደው በተለያዩ አማራጮች ለመታገል እየሞከሩ ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊና የሥነ ፖለቲካ ባህል ግንባታ ውስጥ እነዚህ ሁሉ ተዋናዮች ምን አስተዋጽኦ አደረጉ ነው ቀዳሚ ጥያቄ መሆን ያለበት፡፡ በዚህ ረገድየዛሬ 22 ዓመት ገደማ የደርግ መንግሥት ተገርስሶ አዲስ ሕገ መንግሥት ለማርቀቅና ለማፅደቅ በተደረገው ጥረት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች መሰባሰብና በአንድ ጠረጴዛ ለመነጋገር የተካሄደው ጥረት በበጐ መጠቀስ ያለበት ነው፡፡ ከእነፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ እስከነ ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮ ኤርትራ ሕዝብ ውሳኔ ይኑር አይኑር ውዝግብ፣ እስከነሌንጮ ለታ የኦሮሞ ሕዝብ ‹‹የነፃነት ጥያቄ›› እና የእነመለስ ዜናዊ ፌዴራላዊ አገር ምሥረታ ሐሳብ የተካሄዱ ዴሞክራሲያዊ ክርክሮች ለአዲስ የአገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጐ እንዳለፈ ታምኖበታል፡፡ የሽግግር መንግሥቱ ምሥረታና የሥልጣን ክፍፍሉም ቢሆን ደርግን ያህል አምባገነናዊ ሥርዓትን በኃይል ያፈራረሰው ኢሕአዴግ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እየወሰደ ያለውን በጐ ዕርምጃ አሳይቶበታል፡፡ ግን ሒደቱ ብዙም ሳይቆይ በኢሕአዴግ አስተሳሰብ ዙሪያ የተሠለፉ ኃይሎችን ብቻ እየሳበ፣ ከዚያ ውጪ ያሉትን እየገፋና ከጨዋታው እያስወጣ ሲሄድ ታይቷል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹አስወጣ›› ሲባል በኢሕአዴግ ገፊነትና አላስጠጋ ባይነት ብቻ ሊመነዘር አይገባም፡፡ ይልቁንም እነኦነግና መሰል የፖለቲካ ኃይሎችም ያላቸውን አቋም በማለዘብ በአዲስ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ላይ ከማተኮር፣ ብቸኛ የሆነውን የዴሞክራሲና የመቻቻል ተገዳዳሪነትን ከመዘርጋት ይልቅ ከመድረኩ መራቅና ሌላ የትግል ሥልትን ነው የመረጡት፡፡ ይኼ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ሒደት መደነቃቀፍ አሉታዊ ሚና ነበረው፡፡ ከዚያም ወዲህ ኦነግ በምዕራብና በምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ እንደ አርበኞች ግንባር ያሉቱ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ ኦብነግና ኢሊታሂድም በምሥራቅ ኢትዮጵያ በተለያየ ደረጃ ከኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ጋር ተዋግተዋል፡፡ በጋምቤላ፣ በአፋርና በቤንሻንጉል ሕዝቦች ስም መጠሪያቸውንና ዓላማቸውን የሰደሩ ሸማቂዎችም ሲፍጨረጨሩ እንደነበር ማስተባበል አይቻልም፡፡ በእርግጥ ሁሉም ተዋጊዎች ኢሕአዴግ በመጣበት መንገድ ድል እየቀናቸው ደጋፊና የፖለቲካ አቅም እያዳበሩ መምጣት አልቻሉም፡፡ ድልም ሲቀናቸው አልታዩም፡፡ ለዚህ እውነት የተለያዩ ጉዳዮችን በምክንያትነት መጥቀስ ይቻል ይሆናል፡፡ አንደኛው ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ ያለው ፖለቲካዊ ተቀባይነት ከተገዳዳሪዎቹ የበለጠ በመሆኑ፣ የመንግሥቱ ወታደራዊ አቅምና የሽምቅ ውጊያ የመከላከል ልምድ መዳበር በማየሉ፣ ሕዝብ ካሳለፋቸው አሰቃቂና ረጅም የጦርነት ጊዜያት አንፃር ደግሞ ውጊያ ውስጥ ለመግባት አለመፈለጉ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ዛሬ ባለችው ዓለም በየትኛውም አገር የሚካሄድ የትጥቅ ትግል እንደ ቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ድጋፍ የማግኘት ዕድል የለውም፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣናው ካላት ተሰሚነት አንፃርም ከኤርትራው ሻዕቢያ በስተቀር የትኛውም የጐረቤት አገር ለሸማቂዎች የጦር መሸጋገሪያ (ቤዝ) መሆን አይፈልግም፡፡ እነዚህና ሌሎች የተለያዩ የፖለቲካ መላምቶችን መዝዞ ለማጤን ቢሞከር፣ የፖለቲካ ተፎካካሪነት ባህላችን አሁንም የአሸናፊና የተሸናፊነት አባዜ አላጣውም፡፡ ፍጥጫ፣ ቂም በቀልና መጠቃቃትም አልተለየውም፡፡ በአሁኑ ሁኔታ በውጭ የሚገኙና መኖራቸው በመሪዎቹ ህልውና ላይ ብቻ የወደቀ የሚመስሉት ኢሕአፓ፣ መኢሶንና መሰሎቻቸውን ጨምሮ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጃቸው ግንቦት ሰባትና ኦነግም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንና አሁን ያለውን መንግሥት በኃይል ብቻ ለማፈራረስ አልመው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በእነዚህ ዳርና ዳር በተወጠሩ የፖለቲካ ፍጥጫዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ አንፃራዊ ልማትና ዕድገት በአገሪቱ ቢዘመገብም፣ የዴሞክራሲ ባህሉ ስለማደጉ እምብዛም ደፍሮ መናገር አይቻልም፡፡ ከአምስትና ከአሥርት ዓመታት ላለነሰ ጊዜ ጉልህ የሆነ መቀራረብና የፖለቲካ መሳሳብ ያልታየበት የፖለቲካ ምኅዳር የአንድ ተጨማሪ ትውልድን ማለፍ የሚጠብቅ ይመስላል፡፡ ዛሬም ድረስ በሁለቱም ጫፍ ያሉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሪዎች ‹‹የኢሕአፓ ትውልድ›› የሚባሉቱ ፖለቲካውን የሚበዙበትና በከረረ ፍላጐት የሚያጦዙት መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ በዚህም ከግራና ከቀኝ ዘመም መፈላለግ የወጣ መናቆር ገጽታውን እየቀያየረ ከመታየቱ ውጪ፣ አዲስ የብሔራዊ መግባባትና የዴሞክራሲያዊ አንድነት መንፈስ የተላበሰ አገራዊ አስተሳሰብ አልተወለደም የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ ለአገራችን የዴሞክራሲ ባህል በሚፈለገው ደረጃ አለመፋፋት የፖለቲካ ተገዳዳሪነት ባህሉ ጫፍና ጫፍ የረገጠ፣ መቀራረብ ያልጐለበተበትና ሚዛናዊ የሆነ አስተሳሰብ ያልዳበረበት ነው ሲባል የተለያዩ መገለጫዎች አሉት፡፡ አንደኛው ለዴሞክራሲ ባህል መሠረታዊ ጉዳይ የሚባለው የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሒደቱ በሚዛናዊነትና በገለልተኝነት፣ በብሔራዊ ጥቅምና የአገር ደኅንነት ላይ የታነፀ መሆን አልቻለም፡፡ በተለይ ከሚዲያና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በተያያዘ ወይ ማንቆለባበስ አልያም ማጥላላት ላይ የተንጠለጠለ መራራቅ በዝቶ እየታየ ነው፡፡ ሚዛናዊ ሆኖ በገለልተኝነት የቆመና በሙያው ሥነ ምግባር እየተመራ ያለ የዘርፉ ተዋናይ በዝቶና ጐልቶ አልወጣም፡፡ ቢኖርም በግራና በቀኝ ኃይሎች ተርታ እንዲሠለፍ ይፈለጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹም በሁለት መንገድ የሚገለጹ ናቸው፡፡ በአንደኛው ዘርፍ ያሉት በተጨባጭ የፖሊሲና የደጋፊ ብዛትም ሆነ ጥራት የሌላቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶች ‹‹አሻንጉሊት›› ሲሏቸው ሌሎቹ ለስም ብቻ ‹‹ተፎካካሪ ፓርቲ›› የተባሉ አገራዊና ሕዝባዊ መሠረት የሌላቸው መሆናቸው በደንብ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል የሚጠቀሱት የፖለቲካ ተዋናዮች ደግሞ እምብዛም አሁን ላለው ዕድገት፣ ለውጥና የዴሞክራሲ ጅምር ዕውቅና የማይሰጡ ናቸው፡፡ መንግሥትም ጽንፈኛ ተቃዋሚ፣ ሕጋዊና ሕገወጥነትን የሚያቀላቅሉ፣ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ዕውቅና የማይሰጡ እያለ የሚገልጻቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የለውጥ ፍላጐታቸው ወደቆየው የዜሮ ድምር ፖለቲካ (Zero Sum Game) እየማተረ መሄዱና በእርግጥም ከጥላቻ ፖለቲካ ላለመላቀቃችን እውነትም የዚሁ አስተሳሰብ ነፀብራቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን የጠራ አቋም ይዘው የሚራመዱ ደግሞ የሉም ማለት አይቻልም፡፡ አገራችን እየገነባች ነው በሚባለው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከሚነገረው በላይ ‹‹የልማታዊ መንግሥት ግንባታ›› የሚለው አስተሳሰብ መስፋትና መዘውተርም ሌላ ጥያቄ ያጭራል፡፡ መንግሥት የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ልዕልናን ለማረጋገጥ ከአገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይህ አንድና ወጥ አመለካከት የመቅረፅ ፍላጐት ደግሞ ሌሎች አማራጮችን ወደ ጠላትነት የሚገፋና ግራ ዘመም ባህሪ እንዳለው፣ የሌሎች አገሮችንም ተሞክሮ በመጥቀስ የሚከራከሩ ብዙ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ሁሉም ‹‹ልማታዊ›› መንግሥታት እስከ ግማሽ ምዕተ ዓመት በሥልጣን ላይ በቆዩ ገዥ ፓርቲዎች የተመሩ ናቸው፡፡ በዴሞክራሲ ባህል ግንባታው ባይሳካላቸውም በልማት የሚታሙ አለመሆናቸውም ይታወቃል፡፡ ቻይና፣ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ታይዋንና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአፍሪካ ተጠቃሽ የሆነው የአገራችን ልማታዊ መንግሥትም ረጅም ጊዜ በሥልጣን የመቆየት ፍላጐት ያለው ብቻ ሳይሆን፣ ለልማት ትልቁን አትኩሮት የሰጠ መሆኑን መጠራጠር ያዳግታል፡፡ ያም ሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት፣ የግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ከምንም በላይ የሕዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት ከዘነጋ የሚከፈለው ዋጋ እጥፍ ድርብ መሆኑ አይቀርም፡፡ ዜጐች በዝምታ፣ በአድርባይነትም ሆነ በቸልተኝነት አልተናገሩም፣ ለለውጥ አልተንቀሳቀሱም በሚል ከመርህና ከሥርዓት ውጪ ሊሆን የሚችል አስተዳደር ሊፈጠር አይገባም፡፡ አዲሱ ትውልድ በዘመናዊ የፖለቲካ አስተሳሰብና በዴሞክራሲ ግንባታ ፋና ወጊ ሒደት ውስጥ ጐልቶ እንዲወጣ የሚመኙ ሰዎች አክራሪና የቀደመው ሥርዓት ትርፍራፊ የነካካቸውን የፖለቲካ ኃይሎችን የሚተቹትን ያህል፣ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግንም ‹‹በህቡዕ›› መውቀስ ጀምረዋል፡፡ ለዚህም አንደኛው አሁን ያለው መንግሥት ለመተቸትና ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ የነበሩትን በሮች ዘግቷል፡፡ ‹‹ተገዳዳሪ ያላቸውን ሁሉንም ኃይሎች በሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪ ዓይን ከማየት ይልቅ ጠላትና ‹‹አገር አጥፊ›› አድርጐ ማየቱ ትዝብት ላይ እየጣለው ነው፡፡ ከምንም በላይ አድርባዮችና ‹‹አጨብጫቢዎች›› እየበዙ ነው፡፡ ዜጐች የመሰላቸውንና ያመኑበትን ከመናገር ይልቅ አንድ ነገር ብቻ (ቢያምኑም ባያምኑም) እንዲያቀነቅኑ ሆነዋል፡፡ ሥርዓቱ ወዳለፈው የታሪክ ምዕራፍ እየተመለሰ ከነባሩ ሁኔታ ጋር የአሁኑን ሲያዛምድ፣ የሚገለሉና የሚወቀሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስላለመኖራቸው አለመረጋገጡና አገዛዝን ከሕዝብ የማይለዩ ጭፍን ፖለቲከኞች እየበዙበት መምጣታቸው ቀላል ቁጥር የሌላቸው ዜጐችን እያሳዘነ ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶች በታጨቁበት ሁኔታ የአዲሱ ትውልድ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ወዴት እየሄደ ነው? ብሎ መጠየቅ ነውር የለውም፡፡ ዘንድሮ አምስተኛው ጠቅላላ አገር አቀፍ ምርጫ ሲካሄድ ፍርኃት፣ ሥጋት፣ ሐሳብን ከመግለጽ ይልቅ በህቡዕ ማንጐራጐር ሊነግሥ አይገባም፡፡ ጥላቻ፣ ጽንፈኝነት፣ ዘረኝነትና ትምክህት አብረውን ሊያዘግሙ አይገባም፡፡ ምርጫ በሕዝብ ድምፅ አገርን የሚመራ ኃይልን ወደ ሥልጣን ለማምጣት እንጂ ለሁከትና ብጥብጥ፣ ወይም ለተስፋ መቁረጥና የተለየ አመለካከት ለያዙ ዜጐች ወደ ዳር መገፋት፣ ወይም ለብዙኃኑ ድምፅ ተቀባይነት መንስዔ ማጣት መንስዔ ሊሆን አይገባም፡፡ ከሁሉም በላይ በአዲሱ ትውልድ አዕምሮና ሥነ ልቦና ውስጥ እኩልነት፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሁሉም ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህን የዘነጋ በዕለት የፖለቲካ ትርፍ ላይ ያተኮረ ሥሌት አገር ተረካቢ አዲስ ትውልድ የማይረከባት ሌላ ኢትዮጵያን እስከ መፍጠር ያደርሳል፡፡ ሕዝብ ይደመጥ፡፡ ፖለቲከኞች ከጽንፈኛና ከአስመሳይ ጉዞ ይውጡ፡፡ ልማት ብቻ አገርን በሰላምና በዘላቂ ደኅንነት ሊያቆይ እንደማይችል ግንዛቤ ይያዝ፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...