Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የምርት ገበያው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ሥራ የገባው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን ለመጀመር መንቀሳቀስ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ምርት ገበያው በአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ውስጥ እንደፈር ቀዳጅ የሚቆጠረውን የኤሌክትሮኒክስ ግብይት አገልግሎት እጀምራለሁ ካለበት ጊዜ አንፃር ሲታይ የዘገየ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችለው ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አዲሱ የግብይት ቴክኖሎጂ ምርት ገበያው ሥራ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ተገበያዮች በግንባር በመቅረብ በመድረክ ከሚደረገው ግብይት ጎን ለጎን ተገበያዮች ባሉበት ቦታ ሆነው በግብይቶች ላይ ለመሳተፍ ያስችላቸዋል፡፡ ከምርት ገበያው ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱን ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ተጠናቋል፡፡ በምርት ገበያው ባለሙያዎች የተሠራው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ቴክኖሎጂ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታውና የፕሮግራም መንደፍ ሒደቶቹን በማጠናቀቁ፣ በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለሚሆኑ የምርት ገበያው ተገበያዮች እንዲሞከር ተደርጓል፡፡ አዲሱ አገልግሎት በአካል ከሚደረገው ግብይት ጎን ለጎን እንዲካሄድ የሚደረግ ሲሆን፣ ምርት ገበያው በሚያገበያያቸው ምርቶችና በሁሉም አካባቢዎች ያሉ አባላት በኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ሥርዓት ውስጥ ያልፋሉ ማለት እንዳልሆነም ታውቋል፡፡ አዲሱ የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ እንደገለጹት፣ የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ በቅርቡ ሥራ ሲጀምር ተግባራዊ የሚደረገው በተወሰኑ ምርቶችና በተመረጡ ቦታዎች ላይ ነው፡፡ እስካሁን ባለው የምርት ገበያው አሠራር መሠረት፣ በመገበያያ መድረኩ ላይ በአካል ተገኝተው ገዥና ሻጭ ከፍ ባለ ድምፅ መሸጫና መግዣ ዋጋዎቻቸውን እያስታወቁ ግብይት የሚያካሂዱበት ሲሆን፣ የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ግን በአካል መገኘት ሳያስፈልግ በድረ ገጽ በኩል በቀላሉ ግብይቱን ለመፈጸም ያስችላል፡፡ ይህ ማለት ግን የመድረክ ግብይቱ ይቆማል ማለት እንዳልሆነ አቶ ኤርሚያስ ጠቅሰዋል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ሲጀመር በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ የሚያነጣጥር ሲሆን፣ አገልግሎቱ በቀላሉ ሊቀላጠፍባቸው ይችላሉ የተባሉ ከተሞችን በመምረጥም የሚተገበር ይሆናል፡፡ ምርት ገበያው በተወሰኑ ምርቶችና በተመረጡ ከተሞች ላይ አገልግሎቱን ለመጀመር ያሰበው፣ የኢንተርነቴት መሠረተ ልማትን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ በቅድሚያ ይጀመርባቸዋል ተብለው የሚመረጡት አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት የሚደርስባቸው ከተሞች ሲሆኑ፣ እነዚህ የምርት ገበያው አገልግሎት ቀድመው የሚያገኙ እንደሚሆኑም ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ በቀጥታ ከኢንተርኔት ጋር የተያያዘ በመሆኑም አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችሉ ተጨማሪ አማራጮችን የመጠቀም አማራጭ ሊታሰብ እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ከዚህ አገልግሎት መጀመር ጋር ተያይዞ፣ የኢንተርኔት ግብይቱን የሚመራ ሕግ እንደተሰናዳ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምርት ገበያው የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱን ለማካሄድ በየትኛውም አካባቢ ያሉ የግብይቱ ተዋንያን የግብይቱን ሒደት ቴክኖሎጂ በመጠቀም የግድ ማረጋገጫ መያዝ ስላለባቸው፣ ማረጋገጫውን ለማግኘት የሚያስችሉና ሌሎች ከአገልግሎቱ አሰጣጥ ጋር የተቆራኙ ጉዳዮችን የያዘ የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ በዚህ ሕግ ውስጥ በዋናነት ከተቀመጡ ነጥቦች መካከል፣ በኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ውስጥ የሚሳተፉ ተገበያዮች በኤሌክትሮኒክስ ግብይቱ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ማግኘት እንዳለባቸው የሚደነግገው አንዱ ነው፡፡ ይህም ሠርተፊኬት የሚጠው የኤሌክትሮኒክስ ግብይቱን በተመለከተ የሚሰጠውን ሥልጠና መውሰዳቸውና ሥልጠናውንም በብቃት ማጠናቀቃቸው ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ምርት ገበያው ወደዚህ የግብይት ሥርዓት መግባቱ የተለያዩ ጥቅሞች እንደሚያስገኝሉት ይገልጻል፡፡ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን ከማስረጽ ባለፈ የተቀላጠፈ የግብይት ሥርዓት እንዲኖርና የግብይት መጠኑንም በማሳደጉ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጠ ይዘረዝራል፡፡ ምርት ገበያው ከአገሪቱ ዋነኛ የወጪ ንግድ ምርቶች ውስጥ እንደ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ማሽላና ቦሎቄ ያሉ ምርቶችን በማገበያየት የሚታወቅ ነው፡፡ የምርት ገበያው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በ2006 በጀት ዓመት ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውንና ከ586 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ መጠን ያላቸው ምርቶችን ማገበያየት ችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ 236 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የሚሸፍነው ቡና ነው፡፡ ሆኖም በ2006 በጀት ዓመት ከቡና የበለጠ ምርት ገበያው ያገበያየው የሰሊጥ ምርት ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ከ278 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ሰሊጥ በምርት ገበያው በኩል ተገበያይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ሰሌዳ ከቡና በ42 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ብልጫ በማስመዝገብ ከፍተኛ ግብይት የተደረገበት ሊሆን ችሏል፡፡ ምርት ገበያው ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ቡና ከሌሎች የገበያው ምርቶች ውስጥ አብላጫውን የግብይት መጠን ይዞ የቆየ ቢሆንም፣ በ2006 በጀት ዓመት ግን በሰሊጥ ሊበልጥ ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች