Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መድን ድርጅት ከ20 ዓመት በኋላ ካፒታሉን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ አሳደገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛውን የገበያ ድርሻ የያዘው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ ካፒታሉን ወደ 592 ሚሊዮን ብር እንዲያሳድግ ተፈቀደለት፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እስካሁን ይዞት የቆየው የካፒታል መጠን 61 ሚሊዮን ብር ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ይህ የካፒታል መጠን ከአብዛኛዎቹ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያነሰ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም የኩባንያውን ካፒታል መጠን ለማሳደግ በቀረበ ጥያቄ መሠረት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ የኩባንያው ካፒታል በ870 ከመቶ አድጎ 592 ሚሊዮን ብር እንዲሆን መወሰኑን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አስታውቋል፡፡ እንደ ኩባንያው መረጃ ከሆነ፣ የኩባንያውን የተፈቀደ ካፒታል ለማሳደግ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ኩባንያው እየሰጠ ያለው አጠቃላይ የአደጋ ሥጋት ሽፋን መጠን በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ ነው፡፡ ለዚህም በአስረጅነት በ1987 ዓ.ም. እና በ2006 ዓ.ም. የመድን ሽፋን መጠኑን በማነፃፀር አቅርቧል፡፡ በ1987 ዓ.ም. ኩባንያው የሰጠው አጠቃላይ የአደጋ ሥጋት ሽፋን መጠን ከ32 ሚሊዮን ብር የማይበልጥ እንደነበር አስታውሶ፣ በ2006 ዓ.ም. ግን የሥጋት መጠኑ አንድ ትሪሊዮን ብር መድረሱን አመልክቷል፡፡ ይህን ግዙፍ የአደጋ ሥጋት ለመሸከም ካፒታሉን ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ ሳቢያ ካፒታሉን እንዲያሳድግ መፈቀዱን ይጠቅሳል፡፡ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከተፈቀደው የካፒታል መጠን ውስጥ 322 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ገንዘብ ኩባንያው ካጠራቀመው ትርፍ ላይ ተቀንሶ ለካፒታል ማሳደጊያ እንዲውል ይደረጋል፡፡ ቀሪው 209 ሚሊዮን ብር ደግሞ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ድርጅቱ ለመንግሥት ፈሰስ ከሚያደርገው የትርፍ ድርሻ ላይ በመቀነሰ የሚሸፈን ነው ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ካፒታል ማደግ የድርጅቱን የአደጋ ሥጋት የመሸከም አቅም ስለሚያጎለብተው ሽፋን ከሰጠው የአደጋ ሥጋት አብላጫውን በራሱ የመያዝ አቅሙን እንደሚያሳድግለት ኩባንያው አስታውቋል፡፡ ኩባንያው የሥጋት ሽፋን አሰጣጥን በራሱ አቅም እንዲሸፍን ማድረጉም ለጠለፋ መድን ሰጭ ኩባንያዎች አሳልፎ የሚሰጠውን ሥጋት በእጅጉ እንደሚቀንስለትም የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡ በውጭ አገር ለሚገኙ የጠለፋ መድን ሰጪ ድርጅቶች በአረቦን የሚከፈለው የውጭ ምንዛሪ ሚዛን ላይ የሚፈጠረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከመቀነሱም ባሻገር፣ ለድርጅቱ ትርፋማነት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ከዚህ ቀደሙ የላቀ ያደርገዋል በማለትም የካፒታል ዕድገቱ የሚሰጠውን ጠቀሜታ ያብራራል፡፡ የአገሪቱን የመድን ኢንዱስትሪ የገበያ ድርሻ በመሪነት የያዘው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ የገበያ ድርሻውን አሁን ካለበት ደረጃ በመጨመር ትርፋማነቱን ማሻሻል እንደሚያስችለውም ተጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በአሁኑ ወቅት የገበያ ድርሻው ወደ 41 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የገበያ ድርሻው በግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እየተወሰደበት ቢመጣም፣ አሁንም ከፍተኛው የገበያ ድርሻ እንደያዘ ይገኛል፡፡ መድን ድርጅት በ2006 ዓ.ም. ከታክስ በፊት 446 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ በበጀት ዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ብር አረቦን የሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም ከዕቅዱ አንፃር 612 ሚሊዮን ብር ቅናሽ የታየበት እንደነበር መግለጹ ይታወሳል፡፡ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ 17ቱ የመድን ድርጅቶች በ2006 በጀት ዓመት አምስት ቢሊዮን ብር የሚደርስ አረቦን ያሰባሰቡ ሲሆን፣ አጠቃላይ የኢንዱስትሪው ዕድገትም 3.4 ከመቶ ብቻ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪው ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት ኩባንያዎች አነስተኛ ካፒታላቸው በአማካይ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ከጥቂት ወራት በፊት ባካሄዷቸው ጠቅላላ ጉባዔያቸው ላይ ካፒታላቸውን እስከ 300 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ወስነዋል፡፡ ካፒታላቸውን 300 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ ከወሰኑት የግል ኩባንያዎች ውስጥ ኅብረትና ኒያላ ኢንሹራንስ ይጠቀሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች