Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባለኢንዱስትሪዎችን በአባልነት በመያዝ ሲሠራ የቆየው ማኅበር ቢሮ ታሸገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎችን በአባልነት በመያዝ፣ በተለያዩ መጠሪያ ስሞች ከ22 ዓመታት በላይ ሲንቀሳቀስ የቆየው ‘ናሽናል አሶሴሽን ኦፍ ኢትዮጵያን ኢንዱስትሪስ’ የተባለው ማኅበር ጽሕፈት ቤት ታሸገ፡፡ በጆሞ ኬንያታ መንገድ ሜጋ ሕንፃ አካባቢ ከሚገኙ የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ከሚያስተዳድራቸው ሕንፃዎች መካከል በአንዱ ውስጥ የሚገኘው የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት የታሸገው፣ ጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው፡፡ ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያላክተው፣ ጽሕፈት ቤቱን ያሸገው የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የቀጣና ሦስት ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ኤጀንሲው ጽሕፈት ቤቱን ሊያሽግ የቻለውም ማኅበሩ ከኤጀንሲው የተከራየውን የቢሮ ውል እንዲያድስ ተጠይቆ በወቅቱ ባለማደሱ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ኤጀንሲው ጽሕፈት ቤቱን ከማሸጉ ቀደም ብሎም ለማኅበሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ በተገባው ውል መሠረት የኪራይ ውሉን ሊያድስ ባለመቻሉ ከኅዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የኪራይ ውሉን ማቋረጡንና ታህሳስ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ቢሮውን እንዲያስረክብ አሳስቦ ነበር፡፡ በዚሁ የኤጀንሲው ደብዳቤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ማኅበሩ ቢሮውን የማያስረክብ ከሆነ ግን፣ በሁለቱ ተዋዋዮች የውል ስምምነት መሠረት ሕጋዊ ዕርምጃ የሚወስድ መሆኑም አስጠንቅቆ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የናሽናል አሶሴሽን ኦፍ ኢትዮጵያን ኢንዱስትሪስ የሥራ ኃላፊዎች ግን የኤጀንሲው ዕርምጃ ተገቢ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ማኅበሩ የሚገለገልበትን ቢሮ ኪራይ ውል ለማደስ ያልቻለበት አሳማኝ ምክንያት እንደነበረውና ይህንንም ለኤጀንሲው በተደጋጋሚ ያስረዳ ቢሆንም፣ ሊቀበል ባለመቻሉ ቢሮውን አሽጎብናል በማለት ይናገራሉ፡፡ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ጋር በገባው ውል መሠረት የኪራይ ውሉን ለማሳደስ ያልቻለበት ዋና ምክንያት ደግሞ፣ ማኅበሩ ሕጋዊ ሰውነቱን የሚያረጋግጥለት ፈቃድ ለማሳደስ በተደጋጋሚ ለማኅበራትና ለበጎ አድራጎት ማኅበራት ኤጀንሲ ያቀረበው ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ ምላሽ ካለማግኘቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ባልታደሰ ፈቃድ የቢሮ ኪራይ ውሉን ለማሳደስ ባለመቻሉ የተፈጠረ ክፍተት መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ጋር በተገባው የቢሮ ኪራይ ውል ውስጥ የኪራይ ውሉን አድሶ ለመቀጠል ማኅበሩ የታደሰ ፈቃድ ማቅረብ እንዳለበት የሚያመላክት መሥፈርት በመኖሩ፣ የኪራይ ውሉ ሊታደስ አልቻለም፡፡ ማኅበሩና ኤጀንሲው በኪራይ ውል ጉዳይ መነጋገር ከጀመሩ ከዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ኤጀንሲው ማኅበሩ የኪራይ ውሉን እንዲያድስ ደብዳቤ የጻፈው በኅዳር 2007 ዓ.ም. ብቻ ሳይሆን፣ በሚያዝያ 2006 ዓ.ም. ተመሳሳይ ደብዳቤ ጽፎ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቢሮ አልባ በመሆን በንብረቱ ላይ ጽሕፈት ቤቱ የታሸገበት ማኅበር ከዚህ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለበት እንኳን ለማወቅ ተቸግሯል፡፡ ማኅበሩ የማኅበራትና በጎ አድራጎት ኤጀንሲ ፈቃዱን ባለማደሱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰደው ቢሆንም፣ ውጤቱ ሳይታወቅ ጽሕፈት ቤቱ መታሸጉ የማኅበሩ ህልውና አደጋ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ማኅበሩ ባለፉት 22 ዓመታት በተለያዩ ስያሜዎች ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ከ22 ዓመታት በፊት ሲቋቋም የኢትዮጵያ የግል ኢንዱስትሪዎች ማኅበር የሚል መጠሪያ ነበረው፡፡ ቀጥሎም የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች ማኅበር የሚል ስያሜ ይዞ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ደግሞ ማኅበራት እንደ አዲስ እንዲደራጁና እንዲመዘገቡ ሲደረግ፣ እንደገና አዲስ ስያሜ ይዞ እንዲሠራ ሊገደድ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡ በዚህም ምክንያት የማኅበሩ ስያሜ ናሽናል አሶሴሽን ኦፍ ኢትዮጵያን ኢንዱስትሪስ በሚል እንዲጠራ ቢወሰንም፣ በአዲሱ አሠራር መመዝገብና ፈቃዱን ለማደስ አልቻለም፡፡ የማኅበሩ አመራሮች ማኅበሩ ያሳለፋቸው በርካታ ውጣ ውረዶች እየጠናከሩ መጥተው፣ በአሁኑ ጊዜ የህልውናው ማክተሚያ ላይ የተደረሰ ይመስላል ይላሉ፡፡ ማኀበሩ ከዚህ ቀደም ከ200 በላይ አባላት ይዞ የሚንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች አባላቱ ከግማሽ በላይ ቀንሰውበታል፡፡ ለአባላቱ መቀነስ እንደ አንድ ምክንያት የሚወሰደው ይኸው ፈቃድ የማደስ ጉዳይ ሲሆን፣ አንዳንድ አባላቱም ወደ ሌላ ተመሳሳይ ማኅበራት እንዲካተቱ የሚደነግጉ ሕጎች በመውጣታቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች