Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጋምቤላ የሚነሳውን ግጭት ለማስቆም የመሬት ባለቤትነት ምዝገባ እንዲደረግ ተወሰነ

በጋምቤላ የሚነሳውን ግጭት ለማስቆም የመሬት ባለቤትነት ምዝገባ እንዲደረግ ተወሰነ

ቀን:

በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን በየጊዜው የሚነሳውን ግጭት ለማስቆም የመሬት ባለቤትነት ምዝገባ እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡ ዞኑ የመሬት ባለቤትነት ምዝገባ ማካሄድ የሚስችለው ኮሚቴ አቋቋሟል፡፡ በሚካሄደው የመሬት ባለቤትነት ምዝገባ ከአራት ሔክታር መሬት በላይ የያዘ አካል፣ በኢንቨስተርነት እንደሚመዘገብ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቶማስ የማሎ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ አስተዳደር ምክር ቤት የሚመራው ኮሚቴ ምዝገባው እንዴት መካሄድ አለበት የሚለውን ጉዳይ ካጠና በኋላ፣ ለምዝገባው የሚያስፈልገው በጀት ይመደባል ተብሏል፡፡ በቅርብ ተነስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት የቀድሞ የማጃንግ ዞን አስተዳደር ኃላፊዎች ከሥልጠናቸው መነሳታቸው ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዞኑን በጊዜያዊነት የተሾሙ ባለሥልጣናት እየመሩት ይገኛሉ፡፡ አዲስ የተሾሙት የማጃንግ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቶማስ የማሎ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዞኑ ሥር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግር ተንሰራፍቶ የቆየ በመሆኑ መሬት በሕገወጥ መንገድ ሲተላለፍ ቆይቷል፡፡ በአካባቢው ለሚነሳው ግጭት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ የመሬት ይዞታ ጉዳይ ጎልተው ከሚነሱት አንዱ ነው፡፡ የማጃንግ ብሔረሰብ አባላት መሬት ለሦስተኛ ወገን በሽያጭ እንደሚያስተላልፉ ይነገራል፡፡ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ የመሬት ወረራ እንዳይከሰት የመሬት ምዝገባው ወሳኝ እንደሆነ አቶ ቶማስ ገልጸዋል፡፡ በማጃንግ ዞን ከነባሩ የማጃንግ ሕዝብ በተጨማሪ በርካታ የተለያዩ ዜጎች በጋራ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች በቡና፣ በማር፣ በቅመማ ቅመምና በሌሎች የግብርና ምርቶች ይተዳደራሉ፡፡ በአካባቢው በሚገኘው የግብርና መሬት ግብይት የመንግሥት ድርሻ አነስተኛ ስለነበር ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል ተብሏል፡፡ አቶ ቶማስ እንዳሉት በአካባቢው ከመቶ ሔክታር በላይ የያዘ ሰው አለ፡፡ ነገር ግን ይህ ባለይዞታ እንደ ኢንቨስተር መቆጠር ሲገባው እንደተራ ገበሬ እየተቆጠረ መንግሥት ማግኘት ያለበትን ጥቅም ከማሳጣቱም በላይ፣ ሕገወጥነት እንዲሰፍን አድርጓል ይላሉ አቶ ቶማስ፡፡ በመሬት ባለቤትነት ምዝገባ ወቅት የሚቀነስም ሆነ የሚጨመር መሬት የለም የሚሉት አቶ ቶማስ፣ የመሬት ባለቤትነት ምዝገባው አስፈላጊነት የዞኑ መሬት ያለበትን ሁኔታና ኢንቨስተሩን ከሌላው ገበሬ ለይቶ ለማወቅ ነው ብለዋል፡፡ በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የማጃንግ ዞን በአብዛኛው በደን የተሸፈነ ነው፡፡ ከተፈጥሮ ሀብት ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚነሳው ግጭት ለማስቀረት መንግሥት የተለያዩ ሥራዎችን በማካሄድ ላይ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከሚካሄዱ በርካታ ሥራዎች ውስጥ የመሬት ባለቤትነት ምዝገባና የማንጃግ ብሔረሰብን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግ ተጠቃሾች ናቸው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...