Saturday, June 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ዓለምን እያመሰ ያለው ሽብርተኝነትና ኢትዮጵያ

በአማን ኤልያስ

ሽብርተኝነት የዓለምን ሰላም፣ የሕዝቦችን ደኅንነትና ነፃ እንቅስቃሴ እያወከ ነውጥና ሥጋትን ማንገሥ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከሰሞኑ በሰላምና በደኅንነቷ በምትታወቀው አውሮፓዊት አገር ፈረንሣይ የንፁኃን ደም ፈሷል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት፣ ሴቶችና ያልታወቁ የዓለም ሕዝቦች በሽብርተኝነት መዘዝ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በቅርቡ በናይጄሪያ አንድ አካባቢ ከሁለት ሺሕ በላይ ንፁኃን ሰዎች በአሸባሪው ቦኮ ሐራም ዘግናኝ እልቂት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ አሥራ ሁለት ንፁኃን ዜጎች ብዙዎቹ ጋዜጠኞችና ፖሊሶች የሆኑበት የፓሪሱ እልቂት የተፈጸመው በሁለት አክራሪና ጽንፈኛ ሃይማኖተኛ ነን በሚሉ ወንድማማቾች ነው፡፡ እነዚህ አሸባሪዎች ከቀናት በኋላ ቢገደሉም በሌላ ቦታ 15 ንፁኃንን አግተው በማቁሰላቸውና ለሕልፈት ሕይወት በመዳረጋቸው ፈረንሣይን በሐዘንና በሥጋት ሲንጧት ሰንብተዋል፡፡ ዓለምም ይበልጥ በመቀራረብ ከፈረንሣይ ጎን በመቆም ሽብርተኝትን ለመፋለም የየአገሮች መሪዎች ቃል ተገባብተዋል፡፡ አሸባሪነት ያደገ ያላደገ፣ የሠለጠነ ያልሠለጠነ፣ አገርና ሕዝብ ሳይለይ የንፁኃንን ዕድሜ ማሳጠርና አገርን ሥጋት ላይ መጣልን አስፍቶ ቀጥሎበታል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፖኪስታን ታሊባን በጣት የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ፖኪስታን ውስጥ አንድ መንደር የሚገኝ የሕፃናት ትምህርት ቤት ገብተው ከ100 በላይ የሚሆኑ ሕፃናትን በመትረየስ ፈጅተዋል፡፡ ምክንያታቸው ከአክራሪና ፅንፈኛ እስላማዊ አስተምህሮ ‹‹የሚቃረን›› ያሉት ዘመናዊ (የምዕራባዊያን) ትምህርት ማጥፋት የሚል ነው፡፡ በቅርቡ በጎረቤት አገር ኬንያ አልሸባብ የተሰኘው አሸባሪ ቡድን በተደጋጋሚ ንፁኃንን መፍጀቱን ታዝበናል፡፡ በናይሮቢ የዌስት ጌት ታላቁ የገበያ ማዕከል እስከ ሰሜን ምዕራብ ኬንያ የገጠር ነዋሪዎች ድረስ በጅምላ ጨፍጭፏል፡፡ አልሸባብ የሞተ መስሎ እያደባ በሞቃዲሾና በሌሎች የሶማሊያ አካባቢዎች የአጥፍቶ ጠፊ በትሩን በንፁኃን ላይ መሰንዘሩም አልቀረም፡፡ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ገደማ ሌላው ዓለምን ከጫፍ ጫፍ ያንቀጠቀጠው የሽብር ቡድን አልቃይዳ ነው፡፡ በተለየ ዋነኛ መሪው ኦሳማ ቢን ላደን ከመገደሉ በፊት በአሜሪካ የኒውዮርክ መንታ ሕንፃዎችንና ፔንታጎንን፣ በታንዛኒያ፣ በኬንያና በኡጋንዳ እንዲሁም መካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ ድረስ ከፍተኛ ሥጋትነቱን በግብረ ሽብሩ አረጋግጧል፡፡ መካከለኛው ምሥራቅን ‹‹የእርግማን ምድር›› አድርጎ ሰላምና መረጋጋት የነጠፈበት ቀጣና ወደ መሆን ያደረሰው የአልቃይዳን አቅጣጫ እየተከተለ የመጣው፣ ሃይማኖታዊ አክራሪነትና ፅንፈኝነት የወለደው ሽብርተኝነት መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት ያደግታል፡፡ የቀጣናው አገሮች በተለይ አምባገነናዊ መንግሥታቸውን በኃይልም ሆነ በሌላ መንገድ ሲያወርዱ ዴሞክራሲያዊነትን መጎናፀፍ አልቻሉም፡፡ እንዲያውም በሽብርና በሁከት ንፁኃን የሚረግፉባቸውና ያልተረጋጉ የመሆን ዕጣ ፈንታ ሲጋረጥባቸው ታይቷል፡፡ ኢራቅ ሳዳም ሁሴንን በሌሎች እገዛ ብታሽቀነጥርም በየቀኑ በርካታ ንፁኃን ዜጎች በሽብርተኞች ቦምብ የሚነዱባት የቁጣ ምድር ሆናለች፡፡ ያላት የተፈጥሮ ማዕድን ሀብት ዜጎችን ከመጥቀም ይልቅ ለባዕዳን ሲሳይና ለቀውስ መንስዔ ከመሆን አልዳነም፡፡ በየመን፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በግብፅ (አልፎ አልፎ ቢሆንም) እየታየ ያለው የሽብር ሥጋት ሽፋኑን ሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት ያስመስል እንጂ፣ የለየለት ውንብድናና በሰብዓዊነት ላይ የተጋረረጠ ሽብር ነው፡፡ የሥልጣኔ፣ የዕድገትና የብልፅግና እንቅፋትነቱም የለየለት ነው፡፡ በአጠቃላይ አረመኔያዊነት የሚታይበት ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መነሻውን በኢራቅና በሶሪያ አድርጎ እስከ ሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም አውሮፓና አሜሪካ ለመድረስ የተቋመመው አይኤስ የተሰኘውን ቡድን እንቅስቃሴንም መታዘብ ይቻላል፡፡ ዛሬ በየአቅጣጫው በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞችን፣ ክርስቲያኖችንና አይሁዶችን አንገት በሰይፍ እየቀላና በጅምላ እየረሸነ በአንድ ጉድጓድ የሚቀብር ኃይል ሆኗል፡፡ ለዘብተኛና ሚዛናዊ የሚባሉ የእስልምና ዕምነት ተከታዮችንና መንግሥታዊ ሥረዓቶችንም የሚያፈራርስ ፀረ ሰላምና ፀረ ሕዝብ ኃይል በመሆኑ፣ ዓለም (በተለይ የምዕራቡ ካምፕ) በአንድነት ሆኖ እየታገለው ነው፡፡ ዓለምን እየናጣት ያለው ግብረ ሽብር የምግባርና የዓለም ተመሳስሎ ያለው፣ የሰላም ሃይማኖት በሆነው እስልምና ውስጥ ተደብቆ ፋጥቱን ያረዘመ አሳሳቢ ሥጋት መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ትናንት በመንግሥታት ደረጃ ያጠብቃሉና ያከራሉ የሚባሉት እነ ኢራን፣ ሶሪያ፣ ዮርዳኖስና ሳዑዲ ዓረቢያ ራሳቸው የሚፈሩት ኃይል እያቆጠቆጠ ነው፡፡ በአገራችንም ያለው የፀረ ሽብርተኝንት ትግልና የአደጋው ሥጋት ‹‹ከማስመሰሉ የፖለቲካ ጨዋታ›› ወጣ ብሎ ለተመለከተው ከሌላው ዓለም የተለየ አይደለም፡፡ ‹‹Terrorism In Ethiopia and the Horn of Africa – Threat, Impact and Response›› በሚል ርዕስ ሰፊ የምርምር ሥራቸውን ያቀረቡትን የወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል (2011 እ.ኤ.አ.) መድሐፍን በስፋት መመርመር ይቻላል፡፡ ይኼ ከፍያለ የምርምር መጽሐፍ በጉዳዩ ላይ በጥልቀትና ከማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከፖለቲካዊ አንድምታው አንፃር ፈትሿል፡፡ ዜጎች በየተኛውም ሁኔታ ወደ ተስፋ መቁረጥ፣ ድህነት፣ መገለልና መገፍተር ሲደርስባቸው ለሽብርም ሆነ ለአመፃ እንዴት ሰለባ እንደሚሆኑ፣ የዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ካምፕ መናኸሪያ የሆነችው ሶማሊያና የእነ አልሸባብ ምኞትና ፍላጎት ምንነት፣ አሊትሃድ፣ ኦብነግና ኦነግን በመሰሉ የአገር ውስጥ የዓመፅ ተጋሪዎች የተቃጡ የሽብር ድርጊቶችንና የተመከቱበትን መንገድም በስፋት ተተንትኗል፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ አርበኞች ግንባር፣ የቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃ አውጪ ግንባርና የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዋ ኅብረት ግንባር ያሉ የታጠቁ ኃይሎች በኤርትራ መንግሥት (ሻዓቢያ) ጭምር ያደረሷቸው የሽብርና የንፁኃን ዜጎች ጉዳቶችም ተብራርተዋል፡፡ (በእርግጥ መጽሐፉ ለንባብ ከበቃ በኋላ ግንቦት 7 የተባለው ሥርዓቱን በአመፅ ለማፈራረስ እየተንቀሳቀሰ ያለ ኃይልንም መንግሥት በሽብርተኝነት ፈርጆታል)፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ሽብርተኝነትን በተመለከተ እየተንፀባረቀ ያለው ሐሳብ ግን መንታ ገጽታ እንዳለው አደባብሶ ማለፍ ያስቸግራል፡፡ አንደኛው መንግሥት ሃይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነትን በሁሉም ሃይማኖቶች እንደሚንፀባረቅ አድርጎ በማቅረብ፣ ዓለምን አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እያሰፈረ ያለውን ራቢጣ አል-ዓለም-አል ኢስላሚያ ጋር የተያያዘውን የአክራሪነት አስተሳሰብ በፅናት እየመከተ ያለመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ‹‹ሽብርተኛ›› የሚለውን ፍረጃና ስያሜ በፖለቲካ ተቀናቃኝነት ስም መንግሥቱንም ሆነ ሥርዓቱን በትጥቅ እየተፋለሙት ላሉ የፖለቲካ ኃይሎች ጭምር በመስጠቱ በተጨባጭ አደጋውን ነጥሎ ለመከላከል አላስቻለም የሚለው ነው፡፡ እንዲያውም ሽብርተኛ በሚል ሰለባ የሚሆኑ የፖለቲካ ተገዳዳሪዎች መኖራቸው ዜጎችን ከመንግሥት ትግል በተቃራኒው እንዲሠለፉ ሊያደርግ መቻሉ እያሰጋ ይገኛል፡፡ ዓለምንም ሆነ አገራችንን ኢትዮጵያ ክፉኛ የሚያሳስባቸው የሽብርተኝነት አደጋ ግን ተመሳሳይ መገለጫዎች እንዳሉት መመርመር ተገቢ ይሆናል፡፡ አንደኛው ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው እ.ኤ.አ. በ1962 ከተመሠረተው ራቢጣ አል-ዓለም-አል ኢስላሚያ (Muslim World League) አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው፡፡ የሃይማኖት አክራሪነትም ሆነ ጽንፈኝነት በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ መንፀባረቁ ማስተባበል ባይቻልም፣ እስልምናን ተገን ያደረገው የከረረ አስተሳሰብ የሽብርተኝነት መገለጫ እየሆነ መምጣቱን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ እዚህ ላይ ሰሞኑን በፈረንሣይ በንፁኃን ላይ የተፈጸመው ግብረ ሽብር በኋላ ‹‹All Muslims are not Terrorists. But all Terrorist are Muslims.›› የሚለው ገለጻ የማኅበራዊ ድረ ገጾችና መገናኛ ብዙኃን መወያያ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይኼን ሐሳብ ሳንሸፋፍን በግልጽ ተወያይተንበት ከጽንፈኛና ከጅምላ ፍረጃ በተላቀቀ መንገድ ሚዛናዊ ሆኖ መፈተሽ ይገባል፡፡ ለዚህም የራቢጣ አል-ዓለም-አል-ኢስላሚያ ምንነትንና መነሻን ተመልክቶ፣ እንዴት በዓለም ላይ ተጠናክሮ እየተስፋፋ የመጣ አክራሪ አስተሳሰብ እንደሆነ ማወቅ ይስፈልጋልና እንመልከተው፡፡ ‹‹ሰላም፣ ኢስላምና ሽብርተኝነት›› (Peace, Islam and Terrorism) በሚል ለንባብ የቀረበ መጽሐፍ እንደተነተነው ራቢጣ አል-ዓለም-አል-ኢስላሚያ መቀመጫውን ሳዑዲ ዓረቢያ ያደረገ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ ዓላማውም የእስልምና ሃይማኖትን በማስፋፋትና በማስረፅ ሙስሊም በሆኑና ባልሆኑ ሕዝቦች ላይ (በኃይል ጭምር) ጫና መፍጠር ነው፡፡ የእምነቱን አተገባበሮች በዋሃቢያ አስተምሮት መሠረት ላይ የሚያርፍ በመሆኑ በአስተምህሮው ላይ የሚነሱ ተቃዋሚ ሐሳቦችንና የስም ማጥፋት መረጃዎችን ማኮላሽትና ፍሬ እንዳያፈሩ ማድረግንም ያካትታል፡፡ ‹‹ሕዝቦች በሙሉ በአሏህ (በፈጣሪ) ሕግ መሠረት በሸሪዓ እንዲተዳደሩ ማድረግ›› የሚለው መርሁም የአገራችንና የመንግሥታችን ዓላማዊ (ሴኪዩላር) ወይም ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው የሚለውን ባህሪ የሚፈታተን መሆኑ እየታወቀ እንዲስፋፋ ይሠራበታል፡፡ መጽሐፉ የአስተምህሮውን መሠረታዊ ጭብጥ በአንድ መስመር ሲገልጸው ‹‹There Shall be no Peace Without the Application of the Principles of Islam›› (የእስልምና መርሆዎች በየትም ካልተተገበሩ ሰላም አይኖርም) የሚል ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ራቢጣ አል ኢስላሚያ ዋንኛው የዋሃቢያ የሎጂስቲክስ፣ የፋይናንስና የፕሮፓጋንዳ ቋት ነው፡፡ የእኛን አገር ጨምሮ በከፍተኛ ድጎማ ለሚገነቡ መስጊዶች፣ መድረሳዎችና ጁመአዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የኅትመት ውጤቶች፣ ሲዲዎችና ቪዲዮዎች ወጪ ይሸፍናል፡፡ ይኼ ድርጅት በመካና በመዲና የሚገኙትን ሁለት ቅዱሳን ሥፍራዎች በሳዑዲ መንግሥት ስም የተቆጣጠረ በመሆኑ፣ የወሃቢ ደጋፊ ካልተሆነ ቪዛ የሚከለክል እንደሆነም የሚያስረዱ አሉ፡፡ በእስልምና ውስጥ አክራሪ የሚባሉ ፍልስፍናዎችን በማራመድ የሌሎችን ሃይማኖቶች እስከ መግፋትና የአገሪቱን የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት ሕገ መንግሥታዊ ባህሪ በመገዳደርም ይታወቃል፡፡ ከሦስትና ከአራት ዓመታት ወዲህ በአገራችን በአወልያ ‹‹የሙስሊም ተወካዮች›› እና በመንግሥት መካከል ከተነሳው ውዝግብ በኋላ እየገነነ የመጣው አስተሳሰብና ለዘመናት ከኖረው ኢትዮጵያዊ እስልምና ተቃራኒ የሆኑ አመለካከቶች፣ የእዚሁ ኃይል ድጋፍ እንደነበራቸው በተለያየ መንገድ ተገልጿል፡፡ ይህንን ማን ይክዳል? ጊለስ ኬፐል የተባሉ ጸሐፊ በ1970ዎቹ መጨረሻና በ1980ዎቹ መጀመርያ የወሃቢያ አስተምህሮን ለማስፋፋት ዓለም አቀፍ ዘመቻ መደረጉን ያወሳሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማት፣ በኢንዱስትሪዎችና በግዙፍ ፋብሪካዎች በነባር የእስልምና አማኞችና ሙስሊም ባልሆኑ ሕዝቦች ላይ በከፍተኛ የሀብት ደጋፍ የተካሄደው የወሃቢያ አስተምህሮ መስፋፋት ከምዕራባዊያንና የሥልጣኔ አስተሳሰብ በተቃራኒ መቆምን አበረታትቷል፡፡ ሃይማኖታዊ በሆነው የሰማያዊ መዳኛ ሕግ ምድር ሁሉ እንዲተዳደርና በየአገሩ እስላማዊ መንግሥት እንዲስፋፋ ተሞክሯል፡፡ ለዚህም የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮችን በማማለልና በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በጫናና በወረራ ለማሳመን ካልሆነም ለመፍጀት የተደረጉ የሽብር ድርጊቶች በየአገሩ ተከስተዋል፡፡ በእኛም አገር መንግሥት ለዓመታት አስታሞት እንጂ በጅማ፣ በስልጤና በምሥራቅ ሐረርጌ ዞኖች ምን ዓይነት አስከፊ ድርጊቶች እንደተፈጸሙ ታሪክ መዘገቡ አይቀርም፡፡ በእስልምና ውስጥ ስመ ገናና የነበሩ አባቶችና የሃይማኖት መሪዎችን ማሳደድና እንደ ኋላቀር መቁጠርም የአስተምህሮቱ መገለጫ ነው፡፡ የእምነት ነባር ቅርሶችና መስጊዶችን ማፍረስ፣ እንደ ሙዚቃ፣ ፊልም፣ ዘመናዊ ትምህርት፣ ልቦለድ መጻሕፍትና የፎቶግራፍና የቀረፃ ሥራዎችንና ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን ባለመፍቀድ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ዕርምጃዎችን እስከ መውሰድ ይገፋል፡፡ እነዚህና ሌሎች በጋዜጣ ጽሑፍ ተገልጸውና ተተንትነው የማያልቁ የአስተምህሮቱ ሕግጋቶችና መርሆዎች ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ ዓለማዊነትንና ከሌሎች እምነቶች ጋር ያለ አብሮነትን ይጎዳል፡፡ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ እሴቶችንም ይንዳል፡፡ በዚህ ዘመን ቦኮ ሐራም፣ አልሸባብ፣ አልቃይዳ፣ አይኤስአይኤል፣ ታሊባንም ሆኑ ሌሎች የሽብር ድርጅቶችና የሐሳባቸው ተጋሪ ወጣት ጂሃዲስቶችና አጥፍቶ ጠፊዎች የአክራሪነት ደረጃና አቅም ይለያይ እንጂ መነሻቸው ጽንፍ የወጣ የእምነት አስተምህሮ ነው፡፡ አስተምህሮውን አስፋፍተውና አጠናክረው የሌሎችን መብት በመጨፍለቅ ለመሄድ ሳይችሉ በመቅረታቸው ወደ በቀልና የዕልቂት አጥፍቶ መጥፋት ጠርዝ ላይ መድረሱን መጠራጠር አይገባም፡፡ በእርግጥ እዚህ ላይ ‹‹አሜሪካ፣ እስራኤልና ሌሎች ኃያላን አገሮችስ አሸባሪ አይደሉም ወይ?›› የሚሉ ተከራካሪዎች ሊመጡ ይችላሉ፡፡ አምባገነንና ሕዝብን ሊያዳምጡ የማይችሉ መንግሥታዊ አሽባሪዎች እንዳሉም የሚናገሩት እውነት የለውም ማለት አይቻልም፡፡ በየትኛውም ደረጃኛ ሁኔታ የሰዎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብትን መጣስና በተለየ ሁኔታ ግልጽ መድልኦና በደል መፈጸም ከሽብርተኝነት ተነጥሎ ሊታይ የማይችል ፋጥት ነው፡፡ በእዚህ ጽሑፍ እየተመለከትነው ያለው ሽብርተኝነት ግን መብትን ለማስከበርም ሆነ ለፅድቅ በሚል ያልተዘጋጀውንና ንፁኃንን እየፈጀ ያለውን ግብረ ሽብር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አገራችንን ጨምሮ መላው የዓለም ሰላም ወዳድ ሕዝቦችና መንግሥታት በጋራ ሊረባረቡ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ያለችበትን ቀጣናና በውስጥ እያደገ የመጣው የአክራሪነትና የጽንፈኝነት ፍላጎት ዘላቂ መፍትሄና ተከታታይ ዕርምጃን ይሻል፡፡ መንግሥት የተሻለ አቅም በፈጠረበት ደኅንነት፣ ፖሊስና የመከላከያ ኃይል የጎረቤት አገሩን የሽብር ቡድን አልሸባብ ሊመክተው ቢችልም፣ በአገር ውስጥ አሁንም ሰፋፊ ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ ‹‹ድምፃችን ይሰማ!›› እያለ በየአካባቢው የሚያንገራግረው ሰፊ ቁጥር ያለው ወጣት ኃይል ሽብርተኝነትንና የመብት ጥያቄን ነጣጥሎ እንዲመለከት መደረግ አለበት፡፡ ብሶት ያለበት በደመነፍስ ተነስቶ ያልተገባ ድርጊት ውስጥ ሲገባ ውጤቱ አስከፊ ስለሚሆን፣ መንግሥት በብርቱ ሊያስብበት ይገባል፡፡ በየአካባቢው አብሮ ለመኖር የማያስችሉ ነውጠኛ ፍላጎቶች ይንፀባረቃሉ፡፡ ዘረኝነትንና ጠባብነትን በማራመድ እግረ መንገድ የሃይማኖት አክራሪነትን አየጆበኑ ንፁኃንን ለመግደል የማይመለሱ አሉ፡፡ በቅርቡ በጋምቤላ 80 የሚደርሱ፣ በአሶሳ 42 ያህል ዜጎች እንዴትና በምን ሞቱ ብሎ መፈተሽ ይገባል፡፡ በሌሎች አካባቢዎች የተረገዙ ቀውሶችስ አሉ? ወይም የሉም? የሚለውን ጥናታዊ መልስ መስጠት ግድና ግድ ነው፡፡ መንግሥት ሁሉንም ዓይነት እንቅስቃሴ በአንድ የሽብርተኝነት ቅርጫት ውስጥ አጉሮ መጓዙም ለውጥ ለማምጣት አያስችልም፡፡ እውነተኛውና አስፈሪው ዓለም አቀፍ አሸባሪነት ከላይ ለመነካካት እንደተሞከረው የራቢጣ አል-ዓለም-አል-ኢስላሚያ ፍልስፍና የከረረ ርዕዮት አራማጅነት የወለደው ነው፡፡ ሽብርተኝነትን ለመመከት ፈጣሪ ይርዳን፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles