Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሕልምና ሪፖርትን ምን አገናኛቸው?

ሰላም! ሰላም! ዕድሜ እንደ ዘበት እንዲህ ሲነጉድ ዝም ትላላችሁ ግን? ያኔ እንደነገሩ ተሳታፊ ሆነን ከምድብ የተባረርንበት የአፍሪካ ዋንጫ ሁለት ዓመት ደፍኖ ነው ሌላ ሽሚያ የምናየው? ‘ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ፣ መጠጥ ሲጥል እያሟሟቀ’ አዘውትረው የሚሉት ባሻዬ ወደው አይደለም ለካ? አደራ ደግሞ በለመደ አፋችሁ ጊዜው ተጭበርብሯል እንዳትሉና በሳቅ እንዳልሞት። በህቅ እንቅ ድምፅ ድጋሚ በሚቆጠርበትና በሚጣራበት ሦስተኛው ዓለም ውለን ማደራችን ሳያንስ ደግሞ፣ ከፈጣሪ ጋር እንሟገት እንዴ? ሰው ሆድ ሲብሰው ምን የማይለው አለ ብዬ እኮ ነው እንዲህ የምሆነው። ልክ አይደለሁ? “ታዲያ እኔን ያብሰከሰከኝ መሸ ነጋ ከማለት ውጪ ልብ ብዬ ያለፈውን ዕድሜዬን የምታዘብበት ሰዓት ማጣቴ ነው። ወይኔ የሰውዬው ልጅ!” ስል ማንጠግቦሽ ሰምታኝ ኖሮ፣ “ከአፍሪካም በምሥራቅ አፍሪካ ምድር ላይ እየኖርክ ይኼን ያህል ስለጊዜ ምን ያብሰከስክሃል?” ብላ በነገር ልትይዘኝ አማራት። እሷን ልሸሽ ከቤት ስወጣ የባሻዬ ልጅ ጠለፈኝና “የሚጠበቅ የምድብ ጨዋታ አለ፤” ብሎ ይዞኝ ሄደ። “የኑሯችን የምድብ ጨዋታ መቼ ለየለትና ነው የሌላ የምናየው?” ብለው ሊሰማኝ አልቻለም። ‘በለው ጠልዘው! ውገረው!’ ሲል ተመልካቹ እኔ ‘እውን የአፍሪካ ዋንጫ ነው? እኮ እኛ እንደዚያ ከተንጫጫን፣ የእርግብ አሞራ እያልን በየመንገዱ የሰው መኪና ከሰባበርን ሁለት ዓመት ሆነን?’ እያልኩ ኳሱን መከታተል አልቻልኩም። እሱም፣ “አንበርብር ምን ነክቶሃል? ሰላሳ አንድ ዓመት እኮ ያለእኛ ተሳትፎ ተካሂዷል። እውን ጊዜው ነው ወይስ በዚህ ዋንጫ አለመሳተፋችን ቆጭቶህ ነው?” ብሎ ውስጤን ይመረምር ያዘ። “ተመርምሬ ከማጣትህ ውጪ ደህና ነህ ተባልኩኝ፤” ያለኝ ሰው ወዲያው ትዝ አለኝ። አንዳንዱ ሰው ደግሞ ትዝ የማይል ሥፍራ ጥልቅ እያለ ትውስ ይላል። ምናልባት ለዚህ ይሆን የሚያባክነን ኑሮ ላይ ሰንካላ ትዝታ እየተጨመረብን በወጉ ሳንኖር ዕድሜ የምንቆጥረው? ልጠይቃችሁ እስኪ? በየቤታችን ያስቀመጥነው ቋጠሮ እኮ በዛ። ታዲያ እርስ በርስ ያልገባንን ሳንጠያየቅ ከላይ ያሉት ተጠያቂነትና ግልጽነትን ከየት ያመጡታል? እውነቴን እኮ ነው! “ዴሞክራሲና ገንዘብ ቅጠል አይደለም አይሸመጠጥም፤” (የገንዘቡን እንኳ እርሱት ድብን ተደርጎ እየተሸመጠጠ ነው) የሚለኝ ማን ነበር? እንዲህ ከውስጤ ጋር ስጠዛጠዝ ደግሞ ከደጅ የሚጠዘጥዘኝ አላጣሁም። መቼ ዕለት አንድ ‘ሪሞርኬ’ ላሻሽጥ ደፋ ቀና ስል አንድ ወዳጄ መንገድ አግኝቶኝ የምርጫ ካርድ መውሰዴን ጠየቀኝ። በጥድፊያዬ ብዛት ገና እንዳልወሰድኩ በቸልታ ልነግረው አልኩና ቆም አልኩ። “ቅርስ ብቻ ሳይሆን የአንዳንድ ሰው ነገር አፈላለግ ‘ታክቲክ’ ራሱ በዩኔስኮ መዝገብ መመዝገብ አለበት፤” የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ወዲያው ታወሰኝ። አንዳንዴ ብቻዬን ስሆንና ከሰዎች ጋር ያለኝን ግንኙት እዚህ ግንብ ላይ ተደግፌ ሳጤን፣ የባሻዬ ልጅ አባባል ከሰማይ የወረደ ሊመስለኝ ይዳዳኛል። ምነው? መና ብቻማ ከሰማይ ከጠበቅን ወዮልን። እናም ይኼ ወዳጄ ትዳሬን፣ ሥራዬን፣ ብስጭትና ደስታዬን ጠይቆኝ የማያውቅ፣ “የምርጫ ካርድ ወስደሃል?’ ብሎ የሚጠይቀኝ ተልኮ ቢኖረው ነው አልኩላችሁና “ቆየሁ!” አልኩት ተጀንኜ። ‘ደግ አድርገሃል!’ ዓይነት አንገቱን ወዝውዞ ሲያበቃ፣ “እና ማንን ልትመርጥ አስብክ?’ አይለኝም? ገና ቅስቀሳው እንኳ ሳይጀመር። ከዚህ በላይ ነገር ፍለጋ፣ ከዚህ በላይ ያጋች ታጋች ድራማ አለ? የእኛ የእኛ ሲሆን በዜና አይነገርም እንጂ፣ እንዲህ ነው በአጥብቆ ጠያቂ በየሄድንበት የእናት ሞት ስናረዳ የምንውለው። ይገርማል እኮ! ታዲያ እኔስ ማን ነኝ? የዛሬን አያድርገውና አዲስ አበባ እንዲህ በልማት ሳትጨስ የጨስኩ አራዳ አልነበርኩ? “ከአባትህና ከእናትህ ማንን ነው በጣም የምትወደው?” ሲባል “አያቴን!” እንዳለው ጮሌ (መቼም የዛሬ ልጅ በመሰበርም በማሳበርም የሚደርስበት የለም) “ዕጩ ነህ እንዴ?” ብዬ አፈጠጥኩበት። እሱም አንዴ በጥያቄ ተለክፏል ያልሰማኝ መስሎ፣ “ግን ዝም ብለህ ስታስበው ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ የሚሆን ይመስልሃል?” ብሎ ሌላ ጥያቄ አመጣ። ይኼው እስከዛሬ ዝም እንዳልኩ እያሰብኩ ነው። ዝም ብሎ ማሰብ ካልተከለከልን ምን እንፈልጋለን? ወዲያው ‘ሪሞርኬውን’ እገዛለሁ የሚል ደንበኛ አገኘሁ። ወደቆመበት ሥፍራ በገዛ መኪናው እየመራሁ ስወስደው፣ “ሙዚቃ ልጋብዝህ እስከዚያ፤” ብሎ ደንበኛዬ ‘ሲዲ’ ከተተ። (‘የሰው መውደድ ይስጥህ’ ሲሉን ያሳደጉን ፍቅራችን ከዘፈን ግብዣ የማያልፍበት ዘመን እንደሚመጣ ይታያቸው ነበር? አጣሩልኝ እስኪ!) ‘ለቁም ነገር መተጋገዝና መተባበር ይቅርና ማኪያቶ መጋበዝ የዳገት ሩጫ ያህል በከበደበት ዘመን ወገኔ ወዶ አይደለም በየኤፍኤም ጣቢያው ሙዚቃ ሲገባበዝ የሚውለው’ እያልኩ አዳምጣለሁ። በከፊል የማገኘውን ኮሚሽን እያሰብኩ ወጪዬንና ትርፌን አወራርዳለሁ። የተጋበዝኩትን ‘እናቴ ስትወልደኝ መቼ አማከረችኝ እደግ ማሞ ብላ’ን እያዳመጥኩ፣ ተሸራርፋ ኪሴ የምትቀረዋን ሳስብ ልቤን ሸፍት ሸፍት አለው። ድንግጥ አልኩ። ሁኔታዬን ታዝቦ ደንበኛዬ “ምነው?” ሲለኝ “የሕይወት ነገር እየገረመኝ፤” ብዬ ‘ፍሬቻ’ ሳላሳይ ታጠፍኩ። ምን ነክቷችኋል ምንም ቢሆን የአራዳ ልጆች ነና! (አጉል ቀርቃሪና ገንዘብ አምላኪዎች እየሆንን ብናስቸግርም) እሱም “ስማ ሰው ማለት ከልጅነት ቀናነቱ ጋር በየዕለቱ እየተጣላ የሚኖር ፍጡር ማለት ነው። ሳትማከር ትመጣለህ። በየቀኑ እየኖርክ በምታየው ነገር እንግድነት እንደተወናበድክ ወድቀህ ተነስተህ ጠብ ሳይል ታልፋለህ። ይዘህ አትረካ (ብር እንደሚቆጥር ሌባ ጣቱንና አውራውን እያፋተገ) አጥተህ ከሰው አትቆጠር። ወዲያ ወዲህ እንዳልክ ብቻ ማለፍ፤” እያለ ወሰወሰኝ። ግን ከንፈር ከመምጠጥ ለጥቂት ዳንኩ። የተናገረው ሀቅ ቢሆንም ይኼን የሚያወራኝ ደንበኛዬ በዕድሜው የተጠቀመ፣ የሠራ፣ ጠንካራና ምሥጉን ከበርቴ መሆኑ ከጨዋታው ጋር አልሄድ አለኝ። ኩመካ የያዘም መሰለኝ። መጠርጠር ነዋ? አስመዝግቡት የማይባል ሀብት እኮ ብዙ ያናግራል፡፡ ባለጠጋው ደንበኛዬ ስለሕይወት የደሃ ሰው ፍልስፍና ሲፈላሰፍ የሚዳቋና የአያ አንበሳ ተረት ውል እያለ አስቸገረኝ። ኧረ የአንበሳንና የሚዳቋን ‘ቻት’ አልነገርኳችሁም እንዴ? አልሰማችሁም የአያ አንበሳን ጉድ? ምናለበት ጠዋት ተነስታችሁ ዝሆኖች ተጣልተው ስለሰበሩት ድልድይ ዜና ከምትሰሙ፣ የንቦችንና የዝንቦችን ገድል ለማነፃፀር ከምትለፉ፣ እንዲህ የእነ አያ አንበሳን ስላቅ ብታነፈንፉ? ምን ይላችኋል? ዓለም እንደሆነች መቼም አትሞላም፡፡ ሁሌም ዘጠኝ ቁጥርን እንደለበሰች ናት፡፡ የት ትሄድባችኋለች? እውነቴን ነው! ስለዓለም እርማችሁን አውጥታችሁ ያልጨረሳችሁ ምርጫ ከመድረሱ በፊት ጨርሱ! ተናግሬያለሁ! አሁን ስብራት የማይጠግን ቅል የማይሰብር አጉል ቅኔ መቀኘቱን ትቼ ተረቱን ልንገራችሁ። ተረት ተረት!(አደራ የላም በረት እንዳትሉ እንኳን የላም የሰው በረት ጠፍቷል) የዱሩ አለቃ ባለግርማ ሞገሡ አንበሳ አንድ ቀን ከተወለደ ጀምሮ የማያውቀው የረሃብ ስሜት ተሰማው። የሚበላ ነገር ፈልጎ ባለማግኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ ጫካው ውስጥ ከዕለት ዕለት እየናረ የመጣው የኑሮ ውድነት ያሳስበው ጀመር። በዚህ በችግሩ ጊዜም አንድም ወዳጅ ‘የት ነው ያለኸው? ምን እያደረግክ ነው? ምን ተሰማህ? ከፋህ? ተደሰትክ?’ ሳይለው በመቅረቱ የሥጋ ለባሽ አፈጣጠር ክፉኛ አሳዘነው። (ማጠጋጋት ለምዶባችሁ የእኔን ታሪክ ኮርጆ ፊልም ሊያደርገው ነው ብላችሁ ብትከሱኝ የለሁበትም! መቼም ዘንድሮ ነገረ ፈጅ የሆነ ነው ይኼ ‘ቻፓ’ የማያሳርፈው) እናም አያ አንበሴ ከፍቶት እያንጎራጎረ ሲጓዝ ከሚዳቆ ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠሙ። “አያ አንበሳ! እንዲያው የዛሬን ማሩኝ! መብራት ጥሻለሁ! እባክዎ?! ሌላ ቀን እንደፈለገዎ!” አለች። የአራዊት አለቃም፣ “ግድ የለም አልነካሽም! እኔ እንዲያውም ‘ቬጂቴሪያን’ ልሆን ሳስብ ነው የመጣሽው። አረፍ ብለን ስለተፈጥሮና ስለኑሮ ስንክሳር አዋይተሽኝ ትሄጃለሽ፤” ሲላት፣ “አይ አንበሳ! ሥጋም ሥጋ ነው፣ ቅጠልም ቅጠል ነው፣ ሆድን ሲርበው ማንከት ነው እንጂ ምክር ምንድነው?” ብላ ቆይቶ እንደማይምራት ስለገባት እግሬ አውጪኝ አለች። ‘የዘንድሮ ሰው አፉና ግብሩ ለየቅል ሆኗል’ ሊለኝ የባሻዬ ልጅ ይህቺን ምፀት አዘል ተረት ‘ሼር’ ሲያደርገኝ፣ መቼም በረባ ባረባው መቅናት እንወዳለንና በሚዳቆ እንግሊዝኛ የመስማት ችሎታ ቀናሁ። እኛ በአንድ ቋንቋ መግባባት አቅቶናል አንተ ሌላ ትላለህ ስትሉኝ ሰማኋችሁ፡፡ በሉ እንሰነባበት። ለሁሉም ጊዜ አለው እንዲል ጠቢቡ ንጉሥ ለመገናኘት፣ ለመለያየት፣ ለመምረጥ፣ ለመመረጥ፣ ልማታዊ ባለሀብት ለመሆን ብቻ ምን አለፋችሁ ለሁሉም ጊዜ አለው። የሁሉን ነገር ጊዜ ማወቅና መወሰን ጠቢብነት ይመስለኛል። እኔ ደላላው አንበርብር ለዚህ የጠቢብ ሰው ዘመነኛ ምክር ‘ስፖንሰር’ የሚያደርገኝ ባላገኝም፣ ያለኝን ለማካፈል አልሳሳም። ‘ራሴን በራሴ ካላለማሁት ማን ያለማልኛል?’ ብዬ በሬን አልዘጋም። ስለዚህ ያ የነገርኳችሁን ሥራ ጠቅ ጠቅ አድርጌ በጎኑ አንድ ቪላ ቤት አሻሽጬ የባሻዬን ልጅ ውረድ እንውረድ አልኩት። ኳስ እያየን አንዳንድ ለመጎንጨት ወደ ግሮሰሪያችን ዘለቅን። እሱ እንደምታውቁት ሞቅ ሲለው የማይነግረኝ ነገር የለም። “በሕልሜ” አለና ጀመረ። “ድልድይ ላይ ተንጠላጥዬ፣ ከሥር ኃይለኛ ጎርፍ እየጎረፈ፣ ስሰቃይ አንድ ሰው መጣና ጎትቶ ሲያድነኝ አየሁ። ጎርፉ የሚወስዳቸውና የሚያሰጥማቸው ግን ብዙ ነበሩ፤” አለኝ። “እና ባሻዬ እያሉ እንደ ጥሩ ሕልም ፈቺ ለምን ለእኔ ትነግረኛለህ?” ስለው “አይ የእሱ አፈታት ትንሽ ልማታዊና ምናባዊ ሆብኛል፤” ብሎኝ በሐሳብ ጭልጥ አለ። “ምን ብለው ፈቱልህ?” ስለው፣ “ጎርፉ ድህነት ነው። ድልድዩ ልማት ነው። እጅህን ይዞ ያተረፈህ የልማት፣ የዕድገትና የብልፅግና አምባሳደር የሆነው መንግሥታችን ነው’ አይለኝ መሰለህ? ኧረ ተወኝ!” ብሎኝ ሳቀ። ባሻዬ አንዳንዴ ‘ሲፎግሩ’ እስከ ጥግ መሆኑን ስለማውቅ እኔም ከት ብዬ ሳቅኩ። “እና ምን አልካቸው?” ስለው “ንገረኝ ያልኩህ የሕልሜን ፍቺ እንጂ የዓለም ባንክን ሪፖርት አይደለም አልኩታ! ይቀልዳል እንዴ ሰውዬው!” እያለኝ ስናፌዝ አመሸን። በፌዝ መቆየቱ ሲሰለቸን የገሐዱ ኑሯችን ፍቺ ወደሆነው የባሻዬ ልጅ ሕልም ተመልሰን “ጥቂቶች እየተነሱ ብዙኃን የሚወድቁት ግን እስከ መቼ ነው?” እንባባላለን። ‘ተሻጋሪው ጥቂት የሚሰጥመው ብዙ!’ እኮ ወዴት ወዴት? እያሰብንበት ብንሰነብት ምን ይመስላችኋል? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት