Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ልጅነቴ በሙዚቃ ተጣጥሞ አልፏል›› ፀሐይ ዮሐንስ

‹‹ልጅነቴ በሙዚቃ ተጣጥሞ አልፏል›› ፀሐይ ዮሐንስ

ቀን:

የፀሐይ ዮሐንስ ‹‹ማንበብና መጻፍ›› ዘፈን ‹‹ማንበብና መጻፍ ዋናው ቁም ነገር፤ ከሕይወቴ ጐሎ እሸበር ጀመር›› የሚለው ስንኝ የብዙዎች ትዝታ ነው፡፡ በጊዜው በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረውም ይታመናል፡፡ ‹‹ሳብ ሳም››፣ ‹‹ተባለ እንዴ›› እና ‹‹ያላንቺማ›› የፀሐዬ (ብዙዎች እንደሚጠሩት) ስም ከሚነሳባቸው ዘፈኖች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ ስለ ሀገር ያዜማቸውም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ፀሐዬ ‹‹የኔታ›› የተሰኘ አልበም በቅርቡ ለቋል፡፡ አልበሙንና አጠቃላይ የሙዚቃ ሕይወቱን በሚመለከት ምሕረተሥላሴ መኰንን ከፀሐዬ ዮሐንስ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡  

ሪፖርተር፡- ከመታወቅህ አስቀድሞ የሙዚቃ ሕይወትህ ምን ይመስል ነበር?

ፀሐይ፡- ጃንሜዳ አካባቢ መኖሬ ወደ ሙዚቃ ለመግባቴ ትልቁ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ የልጅነቴን ተሰጥኦ እዛ ነው ያዳበርኩት፡፡ በምንነጋገርበት በዚህ የጥምቀት ሰሞን ብዙ ትዝታ አለኝ፡፡ ጥምቀት ለሙዚቃ ፍቅሬ መንገድ የከፈተ ነው፡፡ ያደግኩበትም ግቢ ጃንሜዳ አጠገብ ባለው ሙዚቀኛ ግቢ ነው፡፡ ጥላሁን፣ መሐሙድና ብዙነሽ የነበሩበት ክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ ጠዋት ደብተር ይዤ ሄጄ እዛ እውላለሁ፡፡ ክብር ዘበኛ ባልሠራም የክብር ዘበኛ ልጅ ስለሆንኩኝ ልጅነቴ በሙዚቃ ተጣጥሞ አልፏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር፡- ድምፃዊነትን ሙያዬ ብለህ ‹‹በርታ ዘመዴ››ን ከተጫወትክ በኋላስ?

ፀሐይ፡- ያኔ ዜማ ማውጣት ጀመርኩ፡፡ ‹‹ማንበብና መጻፍ›› የኔ ዜማ ነው፡፡ አቶ ተስፋዬ ለማ አምባሳደር ቴአትርን ባቋቋሙበት ጊዜ በ1970 ዓ.ም. ከጓደኞቼ ጋር የመጀመሪያ ቅጥሬን አምባሳደር አደረግኩ፡፡ ከዛ በፊት ከክብር ዘበኛ ጋር ለዕድገት በኅብረት ዘመቻ ‹‹በርታ ዘመዴ ዘማቹ ጓዴ››ን ከሒሩት በቀለ ልጅ ጋር ሆነን ሠርተናል፡፡ ከዛ በኋላ አሻራዬ ያረፈባቸው 14 አልበሞች አሉኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመሪያ አልበምህ እንዴት ነበር?

ፀሐይ፡- ሙዚቃ ቤቶች ፕሮዲውስ ያደርጉ ስለነበር ልምድ ያለው ሰው ይፈልጋሉ፡፡ በዛ ወቅት ገና ልጅ ነኝ፡፡ ስሜት እንጂ ልምድ የለኝም፤ ስሜቴን ወደ ተግባር ለመቀየር ገንዘብ ስለሚያስወጣ ፕሮዲውሰሩ ይቸገራል፡፡ እንደ ምንም የመጀመሪያው ካሴት በሱፐር ሶኒክ ሙዚቃ ቤት አሳታሚነት ተሠራ፡፡ ጥሩ እየተሸጠ እያለ በአጋጣሚ እነ መሐሙድ አህመድና ውብሸት ፍስሐ ወደ ኤሜሪካ ከዋልያስ ባንድ ጋር ሄደው በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ታጅበው ‹‹ማለዳ ማለዳ›› ያለበትን ካሴት አወጡ፡፡ ካሴቱ የእኔን ሸፈነውና ብዙ ሳይደመጥ አለፈ፡፡ በዓመቱ በንዴት ‹‹ፍንጭቷ››ን ሠራሁ፡፡ ‹‹ፍንጭቷ››ን ይዤ ስወጣ ፀሐዬ ዮሐንስ የሚለው ስምም ተገኘ፡፡

ሪፖርተር፡- ትንሹና ከፍተኛውስ ክፍያ ስንት ነው?

ፀሐይ፡- ያልተለመደ ዘዬና ድምፅ ይዤ ስለመጣሁ በሽያጭ ‹‹ፍንጭቷ›› በጣም ኃይለኛ ነበር፡፡ ‹‹ሳብ ሳም››፣ ‹‹ተባለ እንዴ›› እና ‹‹ያላንቺማ›› በጣም ጥሩ ሥራዎች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያ ክፍያዬ 3,000 ብር ነበር፡፡ እንደ ጀማሪና በወቅቱ ገንዘቡ ከነበረው ዋጋ አንፃር ትልቅ ነበር፡፡ የ300,000 ሺሕ ብር ያህል አቅም ነበረው፡፡ የመጀመሪያ ካሴት ስም ማግኛ ስለሆነ ከክፍያ ይልቅ ስም ማግኘቱ ላይ አተኩሬ ነበር፡፡

ጥበብን በገንዘብ መለካት አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ በእኛ ሀገር በሥራውና በተሸጠው መጠን አይከፈልም፡፡ መልካም ሥራ በመሥራት መልካም ስም ነው የሚተርፈው፡፡ በ‹‹ተባለ እንዴ›› ጊዜ ክፍያው 100,000 ሺሕ ብርም ደርሶ ነበር፡፡ ከ‹‹ተባለ እንዴ›› በኋላ የካሴት ሥራ የተበላሸበት ዘመን ነው፡፡ ሰው ሸጦ የሚያተርፍበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ኮምፒዩተር መጣና በደቂቃ ሁሉም ሰው የሚቀዳበት ደረጃ ደረሰ፡፡ ሲዲ ከመምጣቱ በፊት ሽያጭ ጥሩ ነበር፤ ከፍተኛ የገቢ ምንጭም ነበር፡፡ ኦሪጅናል ካሴት 13 ብር ይሸጥ ነበር፡፡ ለማባዛት ባዶ ካሴት አምስት ብር ማስቀጃ ሦስት ብር ነበር፡፡ አምስት ብር ጨምሮ ኦሪጅናል መግዛት ስለሚመረጥ ገበያ ነበር፡፡ ዛሬ በአንድ ፍላሽ እስከ 500 ዘፈን ስለሚያዝ ኦሪጅናል የሚገዛ የለም፡፡ አቁሞ የሚያስኬደን ከኮንሰርት የሚገኝ ገንዘብ ነው እንጂ ዛሬ የሚሠራው ለነገ አያበረታታም፡፡ ጥበቡ እየሞተ ይመስለኛል፡፡ ባወጣሁት ልክ ካላገኘሁ የመሥራት አቅሜ ይዳከማል፡፡ ዛሬ እኔ ነገ ደግሞ ሌላው ከዘርፉ ይወጣል፡፡ በ‹‹የኔታ›› አልበም ብዙ ነው ያወጣሁት፡፡ የሚመጣውና የሚገኘው ተመጣጣኝ ካልሆነ ነገ ለጥበብ ብዬ ለፍቼ ልሠራ አልችልም፡፡ አልበሙ በሙሉ ባንድ ነው የተሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዘፈኖችህ ከግል ሕይወትህ ጋር ቁርኝት ያለው ሥራ አለህ?  

ፀሐይ፡- ‹‹ያላንቺማ›› እናቴ ባረፈችበት ሰሞን የተሠራና ስለእናቴ የተጫወትኩት ነው፡፡ ለባለቤቴ የተጫወትኩት ‹‹ምን ይውጠኝ ነበር በሰው ሀገር›› ስደተኛ በነበርኩበት ወቅት የተሠራ ነው፡፡ ከዛ ውጪ አዳዲስ ነገር መጫወት ስላለብኝ በሰው የደረሰና የሰውን ቁስል ነው የምጫወተው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአልበሞችህ የተዋጣለት ሥራዬ የምትለው የቱን ነው?

ፀሐይ፡- ከዛኛው ይኼኛው ይበልጣል ለማለት ይከብዳል፤ ሁሉም አምኜባቸው የሠራኋቸው ናቸው፡፡ ሁልጊዜም ግን የመጨረሻውን ሥራ አስቀድማለሁ፡፡ ምረጥ ብባል ከአልበሞቼ የአሁኑን እወደዋለሁ፡፡ በአዘፋፈን ስልት፣ በግጥም ይዘት፣ በዜማ፣ በሙዚቃ አድጓል፡፡ ከአሁኑ ደግሞ የሚቀጥለውን እወደዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የ‹‹የኔታ›› ዝግጅት ምን ያህል ጊዜ ወሰደ? ሙዚቀኞችና ዘፈን የመረጥከውስ እንዴት ነው?

ፀሐይ፡- ለማጠናቀቅ አራት ዓመት ፈጅቷል፡፡ ‹‹ሳቂልኝ››ን ከሠራሁ በኋላ ሁለት ዓመት ተጉዤ ሥራ ስጀምር በተለየ ሁኔታ ለመሥራት ትልቅ ዝግጅት አድርጌያለሁ፤ ብዙ ሙዚቀኞችም አሳትፌአለሁ፡፡ ወደቀ የሚባለው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ትንሳኤ ለማድረግ ብዙ መስዋዕትነት ከፍያለሁ፡፡ በአበጋዝ ስቱዲዮ አንድ ዓመት ቀጠሮ ይዤ ሠርቻለው፡፡ ቀረጻው ስድስት ወር ፈጅቷል፡፡ ዘፈን መረጣ ላይ ከድሮዎቹ የተለየ ምርጫ አድርጌአለሁ፡፡ ታሪካዊ ዘፈኖች ዘፍኛለሁ፡፡ ከ30 ዓመት በፊት የሠራሁትን ‹‹ማንበብና መጻፍ›› ‹የኔታ› ብዬ አካትቻለሁ፡፡

ድሮ ‹‹ማንበብና መጻፍ››ን መሀይምነትን በተመለከተ ነበር የተጫወትኩት፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ እስክሪብቶና ደብተር ያስጨበጠ ዘፈን ነው፡፡ ያኔ ምንም እንደማያውቅ መሀይም ሆኜ ነበር፡፡ አሁን ስጫወት ሰው ትኩረት አልሰጠውም እንጂ ‹‹ማንበብና መጻፍ ዋናው ቁም ነገር፤ ከሕይወቴ ጎሎ እሸበር ነበር›› ነው የሚለው ያኔ ‹‹ጀመር›› ነበር፡፡ በያኔው ቁጭት ተምሬ እዚህ ስለደረስኩ ያስተማሩኝ የኔታ ክብር ምስጋና ይግባቸው ነው የሚለው፡፡ የጻፈው መኰንን ለማ (ዶክተሬ) ቢሆንም ሐሳቡ የእኔ ነው፡፡ ዘፈኑ ከሕዝብ ጋር ያስተዋወቀኝ በመሆኑ ጐልቶ ወጥቷል፡፡ ‹‹ማንበብና መጻፍ›› ሁለተኛ ዘፈኔ ቢሆንም እንደ መጀመሪያ ሥራ ነው የምቆጥረው፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ማንበብና መጻፍ›› ድጋሚ በመዘፈኑ የተለየ መልዕክት ያለው ይመስላል፡፡ የሙዚቃ ቪዲዮና ግጥሙ ሲታይ ከትምህርት ጋር በተያያዘ ከአሁኑ ትውልድ የታዘብከውን ለመናገርና ለመገሰጽም ይመስላል፡፡

ፀሐይ፡- አዎ እንደዛ ዓይነት ነገር አለው፡፡ በእኔ ዕድሜና ከእኔ በፊት በየኔታ የተማሩ ትላልቅ ምሁራንን ብታይ በሥነ ምግባር፣ ባህልን በመጠበቅና በሌላም ታንጸዋል፡፡ የኔታ ጋር ትምህርት ብቻ አይደለም የምትማሪው፡፡ ዘፈኑ ያንን ዘመን ነው የሚያወድሰው፡፡ የአሁኑን ዘመን ለመውቀስ ብቻ ሳይሆን የኔታን ትውልዱ እንዲያውቅ ነው፡፡ በየኔታ ምን ያህል ሰው እንደተቀረጸ መታወቅ አለበት፡፡ የዘመኑን ልጆች በያኔው ሁኔታ እናስተምር ማለት ከባድ ነው፡፡ ዘመን ተቀይሯል፤ ኢሜይል እየተላከ የሚማሩበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ዘመኑን ለመመለስ ሳይሆን እንዲያም ተምረን እዚህ ደርሰናል ለማለት ነው፡፡ ዘፈኑ ስለማንነትም ነው፡፡ እንግሊዝኛ መናገር አዋቂነትም ማንነትን እስከ ማስቀየር የሚደርስም አይደለም፡፡ ትምህርት ቤት ውስጥ አማርኛ መናገር አይቻልም የተባለበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ህንድ፣ጃፓንና ቻይናን ብንወስድ በራሳቸው ቋንቋና ባህል ነው እዚህ የደረሱት፡፡ ኢትዮጵያዊ በእንግሊዝኛ ስለተናገረ ትልቅና ትንሽ መባል የለበትም፡፡ ባጠቃላይ የማንነት ጥያቄን ለመመለስ እንጂ ትውልዱን ለመውቀስም ብቻ አይደለም፡፡ ክሊፑ መጨረሻ ላይ ሁሉም ወደ ማንነታቸው ተመልሰው ይታያሉ፡፡ ሁሉን መርምሩ የሚጠቅማችሁን ብቻ ውሰዱ ለማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹የኔታ››ን እንዲሁም ‹‹ማንበብና መጻፍ››ን ስትጫወት በስሜት ነው፡፡ ስለ አብነት ተማሪነትና የኔታ ከራስህ ተሞክሮ ንገረን?

ፀሐይ፡- በዘፈኑ ትክክለኛው ነገር ነው የተገለጸው፡፡ የልጅነት ጨዋታ እንዳለ ሆኖ እንደ መቅሰስ ቆሎ በጠርሙስ ተይዞ ይኬድ ነበር፡፡ ጽሑፉ የኔታን ከመግለጹ በላይ ታሪኬም ነው፡፡ ‹‹ማንበብና መጻፍ›› መሠረተ ትምህርት ከመታወጁ አንድ ዓመት በፊት የሠራሁት ነው፡፡ አዋጁን ቀድመነዋል፡፡ አዋጁ ሲታወጅ ከክፍለ ሀገር ተመልሰን ለሬዲዮና ለቴሌቪዥን እንድንሠራ ተደርጓል፡፡ ዘፈኑ ትልቅ ታሪክ ስላለው ነው በስሜት የምጫወተው፡፡

ሪፖርተር፡- ዘፈኑ በመሠረተ ትምህርት ሚና ነበረው ብለህ ታምናለህ? አንተ ዘምተህ ነበር?

ፀሐይ፡- ጥያቄ የለውም፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ እስክሪብቶና ደብተር አስጨብጧል፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ሌላ ዘፈን አልነበረም፡፡ ከዛ በኋላ ነው የነ ፀጋዬና ሌሎች ዘፈኖች የወጡት፡፡ በዘፈኑ በጣም ነው የምኮራው፡፡ በወቅቱ በየቀኑ ጠዋትና ማታ እንደ ሠንደቅ ዓላማ መስቀያ ማውረጃ ዘፈን ነበር የሚዘፈነው፡፡ በያኔው ትውልድ እያንዳንዱ ሰው ጭንቅላት ውስጥ አለ፡፡ ያኔ ለዘመቻ አልደረስኩም ነበር፡፡ ስዘፍን 16 ወይ 17 ዓመት ነበርኩ፡፡ ትምህርት አቋርጬ ነው ወደ ዘፋኝነት የገባሁት፡፡ ትምህርቴን የጨረስኩት ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በማታ ክፍለ ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ አልበምህ ከሕዝብ ጥሩ ምላሽ እያገኘ ነው? የትኛው ዘፈን የበለጠ ተወዷል?

ፀሐይ፡- ምላሹ በጣም ደስ የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሳቂልኝ›› ከወጣ ከወር በኋላ ነው ምላሽ ማግኘት የጀመርኩት፡፡ በዚህኛው ግን ከሦስት ቀን በኋላ ነው፡፡ እንደዚህ እንደሚሆን አውቄ ነበር፡፡ ሁሉ ሰው ህሊና ውስጥ ያለው ‹‹ማንበብና መጻፍ›› መኖሩ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ‹‹ቀበና›› ሞቅ ያለ ዘፈን ነው፡፡ ቀበና የሁሉ ነገር መሠረቴ ነው፡፡ በዚያ ላይ ቀበና ያልተማረ፣ ያልዋኘና ያልተጫወተ የለም፡፡ ብዙ የሚያካትታቸው ሠፈሮች አሉ፡፡ የአገሪቱ ትላልቅ አርቲስቶችና ስፖርተኞች ጥላሁን፣ መሐሙድና አበበ ቢቂላ ጨምሮ የነበሩበት ሠፈር ነው፡፡ ሌላው መሐሙድ የተጨመረበት ዘፈን አለ፡፡ ዘፈኑ እንደ መጽሐፍ ማጣቀሻና የተለየ ነው፡፡ ይኼ ሁሉ ተደማምሮ ሕዝቡ ሲያጣጥመው የበለጠ እንደሚወደድ እርግጠኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ለማስታወስ›› ላይ የመሐሙድ ‹‹ማን ብዬ ልሰይምሽ›› ተካቷል፡፡ አልበሙ መታሰቢያነቱም ለእሱ ነው፡፡ ለየትነበርሽ ንጉሤ የዘፈንከውም አለ፤ ምክንያትህ ምንድነው?  

ፀሐይ፡- የእኛ ሀገር የጥበብ ሰዎች በሕይወት ሳሉ በሠሩት መጠን አይከፈላቸውም፡፡ ለጥበብ መስዋዕት ሆነው እንደ ሻማ ቀልጠው የሚጠፉበት ሀገር ነው፡፡ ሳይመሰገኑ ብዙ አርቲስቶች አልፈዋል፡፡ ጥላሁን በሕይወት ሳለ ‹‹ሳቂልኝ›› አልበምን የእሱ መታሰቢያ አድርጌአለሁ፡፡ ለዘመናት እየዘፈኑ ስላስደሰቱንና አርአያ ሆነው ለዚህ ስላበቁን በሕይወት እያሉ እናወድሳቸው በሚል ስሜት መታሰቢያነቱን ለመሐሙድ አድርጌዋለሁ፡፡ የትነበርሽን ያየኋት አንድ ሰዓት ለማይሞላ ጊዜ በቴሌዥን ነበር፡፡ ስለ ሀገራችን ያላት ራዕይ አስገራሚ ነው፡፡ እንደዚህች ዓይነት ሴት በሕይወቴ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ከውጪ እንደመጣሁ ስለሷ ጠየቅኩ፡፡ ከምትናገረው በላይ በምትሠራው ነገር ድንቅ ሆነችብኝ፡፡ በሕይወት እያለች ሊዘፈንላት የሚገባ ሴት ናት ብዬ የተጻፈ ዘፈን ቀይሬ የእሷ ዘፈን እንዲገባ አደረግኩት፡፡ የተናገረችውን ታሪክ ለደራሲው ነግሬው ዘፈኑ የተጻፈው ከቃለ መጠይቋ ተወስዶ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአልበሙ የግጥም ሐሳብ በመስጠትና በዜማም የተሳተፍክባቸው ዘፈኖች አሉ፡፡  ከቀደምት ሥራዎችህ ጀምሮ በአልበሞችህ በግጥምና ዜማ ትሳተፋለህ?

ፀሐይ፡- እስከ ዘጠነኛ አልበሜ ድረስ ዜማ እሠራ ነበር፡፡ ‹‹ማንበብና መጻፍ›› እና ‹‹ተባለ እንዴ››ን ጨምሮ ወደ 30 የራሴን ዜማዎች ሠርቻለሁ፡፡ ከዛ በኋላ ዜማ ሳወጣ እየተመሳሰሉ መጡ፡፡ ሲመሳሰልብኝ ሰው አልነገረኝም ራሴው ነኝ ማቆም እንዳለብኝ የወሰንኩት፡፡ ጥላሁንና መሐሙድ ይህን ያህል ዓመት የዘፈኑት የሰው ዜማ ስለሚጫወቱ ነው፡፡ የራሳቸውን ዜማ ብዙ የተጫወቱ ሰዎች ከገበያ ወጥተዋል፡፡ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑ የገባኝ ከዛ በኋላ የመጡትን ዘፈኖች አጣጥሜ ስዘፍን ነው፡፡ የሌላ ደራስያን ሥራ እጄ ሲገባ ግሩም አድርጌ ነው የምጫወተው፡፡ የራሴ ዜማ ከሆነ በቀላሉ ስለማውቀው በቀጣዩ ቀን ስቱዲዮ ገብቼ ሊቀረጽ ይችላል፡፡ የሰው ማጥናት ይጠይቃል፤ የተለየ አዘፋፈን ዘዬ ስለሆነ እንደ ባለቤቱ ጥሩ አድርጐ ማዜም ይጠበቃል፡፡ ጥላሁንና መሐሙድ የተለያየ ሰው አዚያዜም ነው የሚጫወቱት፡፡ የተለያየ ስልት ድምፃቸውን ያሳድገዋል፡፡ አስቸጋሪ የሆነ ዜማን ሲወጡት ውበቱና ለዛው እንዳለ ሆኖ ድምፃቸው ሁሉ ይቀየራል፡፡ እኔም ያንን ነው የተጠቀምኩት፡፡ ዜማ ደራሲ በሞላበት ሀገር እኔ ብቻ ላውጣ ብዬም ጥበቡን መጉዳት የለብኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ለሌሎች የሰጠሀቸው ዜማዎች አሉ?  

ፀሐይ፡- ከእስራኤል የመጣ ዮሴፍ የሚባል ጥሩ ዘፋኝ አለ፤ ለሱ ሰጥቻለሁ፡፡ ሌሎችም የሰጠኋቸው አሉ፡፡ ሠርቼ ያስቀመጥኳቸው ዘፈኖች አሉ ለወደፊት የመስጠት ዕቅድ አለኝ፡፡ ከእኔ ዘዬ ውጪ ባለ ዘፋኝ ቢዘፈኑ አሪፍ ይሆናሉ፡፡ እንደዚህ ነው ጥበብ መሆን ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- አልበምህ ላይ ሐዘን፣ ደስታ፣ ናፍቆትና ተስፋ ማድረግን በዘፈኖችህ እንደገለጽክ አስፍረሃል፡፡ በአጠቃላይ በዘፈኖችህ ምን ዓይነት መልዕክት ማስተላለፍ ትፈልጋለህ?

ፀሐይ፡- ዛሬ ስለምወደው ነገር ዘፍኜ በሚቀጥለውም ያንኑ መድገም አልፈልግም፡፡ የዛሬ 20 ዓመት የተጫወትኩትን እንኳ መልሼ መጫወት አልፈልግም፡፡ ግጥም ባልጽፍም እንዴት እንደሚጻፍ አውቃለሁ፡፡ የላይኛው ሐሳብ ከታቹ ከተለያየ ይስተካከል እላለሁ፡፡ ካልተስተካከለ አልጫወተውም፡፡ ብዙ ጊዜ በአዲስ ነገር ዙሪያ መጫወት ደስ ይለኛል፡፡ አንድ ነገር ላይ ማተኮሩ ተመሳሳይ ያደርገዋል፡፡ አንዳንዴ ቀልድና ጨዋታ አካትታለሁ፡፡ እንደ ‹‹ተባለ እንዴ›› እና ‹‹ተነቃ›› ዓይነት ዘፈኖች አጫዋች ናቸው፡፡ እንደማይቆዩ አውቃለሁ ሆኖም ሰው ይወዳቸዋል፡፡ እያንዳንዳችን አፍ ላይ ካለ ነገር ዘፈን ሲወጣ ፈጠራው ደስ ይላል፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ድምፃውያን ስለ ሀገራዊ ጉዳይ መዝፈን በማይደፍሩበት ወቅት አንተ ትዘፍን ነበር፡፡ ዛሬም ቀጥለሃል?

ፀሐይ፡- ስለ ሀገር መዘፈን አለበት፡፡ ለዚህኛው ትውልድ የምናስረክባት ኢትዮጵያ እየወደዳት የሚኖርባት ሀገር እንደሆነች ማሳየት አለብን፡፡ ከየትም አላመጣሁትም፤ የወታደር ቤተሰብ ነኝ፤ ጠዋትና ማታ ስለሀገር የሚዘፈንበትና ሆሆ የሚባልበት ግቢ ውስጥ ስላደግኩ አብሮኝ ያደገ ነገር ነው፡፡ ሠንደቅ ዓላማ ሲሰቀል ጥይት ቢተኮስ እንኳ ማንም የማይንቀሳቀስበትና ስለ ሀገር ፍቅር ስሜት በየቀኑ የሚወራበት ግቢ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ በእያንዳንዱ አልበሜ እነዚህ ነገሮች አሉ፡፡ የምኮራባቸውና የምደሰትባቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ አንዳንዴ ስለኢትዮጵያ ምንድነው አዲስ ነገር የምለው ብዬ ስጨነቅ ጥሩ ዘፈን ይመጣል፡፡ ‹‹ማን እንደ ሀገር›› እንደ ብሔራዊ መዝሙር ተወዳጅ ዘፈን ነበር፡፡ ከዛ በኋላ እንዴት ሌላ የሀገር ዘፈን እንደምጫወት ስጨነቅ ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽህ›› እና ‹‹የሰንደቆች ሁሉ ሰንደቅ››ን አገኘሁ፡፡ ከሀገር በላይ ምን የሚዘፈንለት አለ?

ሪፖርተር፡- ያንተና የቤተሰብህ የውጭ አገር ኑሮ ምን እንደሚመስል ንገረን?

ፀሐይ፡- ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነኝ፡፡ እዚህ አልበም ለመሥራት መጥቼ ብቻዬን ነው ያለሁት፡፡ የትምህርት ጊዜ ስለሆነ ልጆቼ እዛው አሜሪካ ነው ያሉት፡፡ ከኢትዮጵያ ወጥቶ መኖር ይከብዳል፡፡ አሁን ብዙ ኑሮዬን ያደረኩት አዲስ አበባ ነው፡፡ ልጆቹ ኮሌጅ እዛ መማር ስላለባቸው ነው እንጂ የመጀመሪያ ደረጃን እዚህ ነው ያስተማርኳቸው፡፡ ልጆቹ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲያውቁና የማንነት ጥያቄ እንዳያወዛግባቸው የመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ ጨርሰው ሁለተኛ ደረጃ ሲደርሱ ነው ይዣቸው የሄድኩት፡፡ በዚህ በኩል የማስበውን አሳክቻለሁ፡፡ በሙዚቃ ትልቁ ሥራ ያለው እዚህ ነው፡፡ ድሮ አሜሪካ ሀገር የሚሠሩ ሙዚቀኞች ወደዚህ መጥተዋል፡፡ ወደዛ ኮንሰርት ለመሥራት ነው የምሄደው እንጂ ፈጠራው ያለው እዚህ ነው፡፡ ውጭ ሆኖ ስለኢትዮጵያ መዝፈን ከባድ ስለሆነ የግድ ከሕዝቡ ጋር መሆን አለብኝ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርብ ኮንሰርት ይኖርሃል?

ፀሐይ፡- ከሲዲ ሪሊዝ ፓርቲ አንድ ወር በኋላ ኮንሰርት ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- አንተ ከኢትዮጵያ ድምፃውያን ቀዳሚ ቦታ የምትሰጠው ማነው?

ፀሐይ፡- ጥላሁን ገሰሰ ነው፡፡ እሱን እያየሁ ነው ያደግኩት፡፡ ጥላሁን የሚያስደስት ዘፋኝ ነበር፡፡ በሚቀጥለው መቶ ዓመት እንኳን እንደ ጥላሁን ዓይነት ዘፋኝ ይፈጠራል ብዬ አላምንም፡፡ ሁሉንም ነገር ያሟላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች እንዲሁ ለናሙና እንደሚፈጠሩት ጥላሁን እንደዛ ነው ለኢትዮጵያ የተፈጠረው፡፡ ጥላሁን የማይደገም ሰው ነው፡፡ አዚያዜሙ፣ ዘፈኖችን የሚቀይርበት መንገድና አገላለጹን ማመን ያቅታል፡፡ ደራስያን የእኔ ዘፈን አይደለም እስኪሉ ድረስ ነው የሚዘፍነው፡፡

ሪፖርተር፡- መድረክ ላይ ካገኘሀቸው ሽልማቶች ትልቅ ቦታ የምትሰጠውና የማይረሳ አለ?

ፀሐይ፡- ከእስክሪብቶ ጀምሮ ወርቅ፣ መኪናና ሌላም ብዙ አስደሳች ሽልማት ተሸልሜአለሁ፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያስደስተኝ አቅፎኝ የሚያለቅስ ሰው ሳይ ነው፡፡ እንዲህም ዓይነት አፍቃሪ አለኝ ብዬ በሠራሁት ሥራ እንድደሰት ያደርገኛል፡፡ የዛሬ ሳምንት ደብረ ዘይት ላይ ያገኘኋት እናት እኔን ለማግኘት ሰባት ዓመት አስፈልጋኛለች፡፡

ልጇ የሰባት ዓመት ልጅ ሳለች አልበላም ስትል የኔ ሲዲ ይከፈትላታል፡፡ መርፌ ስትወጋም ፀሐዬ ይመጣል በሚል ተባብላ ነው፡፡ ልጅቷ አሁን አሥራ አንድ ዓመቷ ነው፡፡ እናቷን አንድ ሠርግ ላይ አግኝቼያት በጣም ጮኸች፡፡ በብዙ ሙዚቀኞች ብታፈላልገኝም አላገኘችኝም ነበር፡፡ ልጅቷን በሚቀጥለው ቀን አምጥታት እንዴት እንዳቀፈችኝ መናገር አልችልም፡፡ ከሰላሳ ዓመት በላይ ተጫውቼ የ11 ዓመት ልጅ ከወደደኝ ዕድለኛ ነኝ ይኼ ትውልድም ከእኔ ብዙ ይጠብቃል፡፡ ሕፃናት ይቺን ሀገር ይረከባሉና ለእነሱ ፍቅር መስጠት ያስደስተኛል፡፡ እኔ ልጅ ሆኜ ጥላሁን የሰጠኝን ፍቅር ለሌሎች እየሰጠሁ ነው፡፡ ጥላሁን ‹‹እንዴት ነህ›› ብሎኝ ወሩን በሙሉ ተደስቼ ነበር፡፡ የሕፃንነቴን ደስታ ስለማስታውስ ልጅቷን ቀኑን በሙሉ ጠብቃት ብትለኝም እጠብቃት ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት የሌሏትን ሲዲዎች ልኬላታለሁ፡፡ ወርቁ የሕዝብ፣ መኪናው ደግሞ የዶ/ር መሐመድ አላሙዲ ነው፡፡ ሥራዬን ሰው ሲወደውና ሲያከብረው ደስ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሸላሚዎች በመኖራቸው ይመስለኛል ሕይወታችን የቆመው፡፡ ሠርተን የምናገኘው ነገር የለም፡፡ በደርግ ጊዜ ካሴት ሸጬና ሲዲ ሸጬ ያገኘሁት ነገር የለም፡፡ የሚወዱን ሰዎች በመኖራቸውና በየዓለሙ በመበተናቸው እንኖራለን ትልቁ የእኛ ሽልማት ይኼ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሙዚቀኛ ባትሆን ምን ትሆን ነበር?

ፀሐይ፡- ጃንሜዳ አይደል ያደግኩት ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋች ነበርኩ፡፡ ጥሩ ዋናተኛና ቦሊቦል ተጫዋች ነበርኩ፡፡ አሁን ዕድሜ ሆኖ ኳስ ባልጫወትም ቅርጫት ኳስና ቴኒስ እጫወታለሁ፡፡ ስፖርት ላይ ጥሩ ነኝ፤ ዛሬ ካስለመዱኝ ነገ የእኔ ነው፡፡  የማልጫወተው የስፖርት ዓይነት ጐልፍ ብቻ ይመስለኛል፡፡ በየቱ እንደምቀጥል ባላውቅም ስፖርት ስለምወድ ወደዛ የማዘነብል ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ሙዚቃ ላንተ ምንድነው?

ፀሐይ፡- ሙዚቃ የሕይወት ጥም ነው፡፡ ሙዚቃ ባይኖር ዓለም ያስጠላኝ ነበር፡፡ ሙዚቃ ውስጥ መኖርና ለሕዝብ ጥሩ ሙዚቃ ማቅረብ መቻል ያስደስታል፡፡ ሙዚቃ የማያዳምጡ ሰዎች ያሳዝኑኛል፡፡ ሙዚቃ እንኳን ለሰው ለእንስሳትም ጠቃሚ ነው፡፡

አንድ ሀገር በክላሲካል ሙዚቃ ላሞች ሲታለቡ አይቻለሁ፡፡ ክላሲካል ተከፍቶ ነፍሳቸውን ለሙዚቃ ሲሰጡ ብዙ ወተት ይታለባሉ፡፡ ሙዚቃ የዓለም መግባቢያ ቋንቋ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኮፒ ራይት ለዓመታት የኪነ ጥበብ ዘርፉን እየፈተነ ነው፡፡ በቅርብ የሮያሊቲ ክፍያን የሚያስፈጽም አዋጅ ፀድቋል፡፡ በዘርፉ ምን ዓይነት ለውጥ ይመጣል ብለህ ታስባለህ?

ፀሐይ፡- ተግባራዊ ያልሆነ ነገር በአደባባይ መነገሩ ብቻ ፋይዳ አላመጣም፡፡ ተግባራዊ ሲሆን ነው አርቲስቱን ሊያስደስት የሚችለው፡፡ የት ነው እየተደመጠ የሚከፈለው? በወረቀት ወጥቷል የጥበብ ሰዎችን እያስደሰተና ገንዘብ እያስገኘ አይደለም፡፡ እንዲያውም አባብሶታል፡፡ ክሊፕ ለመሥራት ወደ ክፍለ ሀገር ሄጄ የሚያስጠላ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የሚሸጠው ሲዲ ተቀምጦ በፍላሽ ይወሰዳል፡፡ የሠራነው ካልተጠበቀ ጥቅሙ ምንድነው? አሁን ላይ ሆኜ ሳየው ምንም ተስፋ ያለው አይመስለኝም፡፡ 90 ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት ሀገር ላይ አንድ ሚሊዮን ሲዲ ቢሸጥ መንግሥትም የሚያገኘው ጥቅም ቀላል አይደለም፡፡ የኮፒ ራይት ሕግ ጠንካራ ተከታታይ ያስፈልገዋል፡፡ ትላልቅ የጥበብ ሰዎች ሥራዎች ማዳመቂያ እየሆኑ እነሱ መታከሚያና መቀበሪያ እያጡ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሕዝብ ለሕዝብ ቡድኑ ጉዞ ምን ሚና ነበረው? አሁን ካለው የሙዚቃ ድባብ አንፃር እንዴት ታየዋለህ?

ፀሐይ፡- ሕዝብ ለሕዝብ ሊደገም ያልቻለ ታሪክ ነው፡፡ ሀገሪቷ ያሏት ትላልቅ አርቲስቶች ዓለምን የዞሩበት ነው፡፡ በድርቅ ወቅት የረዱንን ሀገሮች በክፉ ዘመን ስለደረሳችሁልን ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች ለማለት የተላከ የኢትዮጵያ የባህል አምባሳደር ነው፡፡ ምላሹም አስደሳች ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ባህል ያላት ነች ተብሎላታል፡፡ የተዘጋጀው ትዕይንት አስደናቂ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ብዙ ቢሞከርም አልተሳካም፡፡ በቡድኑ ተሳታፊ በመሆኔ በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ሕዝብ ለሕዝብ የኢትዮጵያን የረሀብ ገጽታ ቀይሯል፡፡ አለባበሱን፣ የሙዚቃ መሣሪያውን፣ ውዝዋዜውና ባህሉን አሳይቷል፡፡ አልተጠቀምንበትም እንጂ ኢትዮጵያን በዓለም ሙዚቃ ሊያስገባ የሚችል ነበር፡፡ በእነሱ መሣሪያ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም ገበያ ማስገባት አይቻልም፡፡ ማሲንቆ፣ ከበሮ፣ እምቢልታ፣ ክራርና ጭፈራ ስንይዝ ነው ትልቅ ልንሆን የምንችለው፡፡ ሕዝብ ለሕዝብ በዚያው ቢቀጥል ኖሮ ዛሬ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዓለም ትልቅ ደረጃ በደረሰ ነበር፡፡ ይህ አለመሆኑ ቢያስቆጭም ሕዝብ ለሕዝብ ታሪክ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መድገም ባይቻል እንኳን እንደ ሕዝብ ለሕዝብ ተጠቃሽ ቡድን ማዋቀር እንዴት አልተቻለም?

ፀሐይ፡- ቴአትር ቤቶች ተዳከሙ፡፡ ያ ሁሉ ዘፋኝና ተወዛዋዥ ነቅሎ ወጣ፡፡ መንግሥት ለባህሉ ትኩረት ሰጥቶ እንደ ድሮው የውጭ ሀገርና የክፍለ ሀገር ጉዞ የለም፡፡ እኛን ለዚህ ያበቃ ራስ ቴአትር ዛሬ ፈርሷል፡፡ የባህል ዘፈን የሚታየው በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ቴአትር ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የጥበብ ሰዎች ሳናጣ ባህሉ እንደዚህ ቅዝቅዝ ማለቱ ይገርመኛል፡፡ ከራስ ቴአትር እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ የባህል ሙዚቃ ነበር የምሠራው፡፡ እኛ ወጣቶቹ በባህል ሙዚቃ ታጅበን በመዝፈናችን ወጣቱን ክፍል ይዘነው ነበር፡፡ አሁን ውስጡን ባላውቅም እንደ ውጪ ተመልካች ብዙ እንቅስቃሴ ያለ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ከድምፃዊነት በተጨማሪ መጽሐፍ ልትጽፍ እንደሆነና ወደ ኢንቨስትመንቱም እየገባህ እንደሆነ ይነገራል፤ እውነት ነው?

ፀሐይ፡- የሕዝብ ለሕዝብ ታሪክን በመጽሐፍ የማዘጋጀት ዕቅድ አለኝ፡፡ ውሎአችንን እጽፈው ነበር፡፡ ጥራዙ አለ፤ ለማሳተም የሚረዱኝ ደራስያን የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ በኢቨስትመንት አንዳንድ ነገሮች እየሠራሁ ነው፡፡ ቤቴን አፍርሼ ተለቅ ያለ ቤት እየሠራሁ ነው፡፡ ገና በጅምር ያለ ስለሆነ ለንግድ ይዋል አይዋል አልታወቀም፡፡

ሪፖርተር፡- ከደራስያኑ ማንን ታደንቃለህ?

ፀሐይ፡- ብዙ ናቸው፤ እንዳለጌታ ከበደ፣ ይስማእከ ወርቁ፣ ዘነበ ወላ፣ አቤ ጉበኛ፣ በዓሉ ግርማና ሌሎችም አሉ፡፡ ‹‹ልጅነት›› ስለራሴ ሕይወት የተጻፈ ነው የሚመስለኝ፡፡ እነ አቤ ጉበኛ ያለ ዘመናቸው የተፈጠሩ ናቸው፡፡ መሐመድ ሰልማን ፒያሳን የገለጸበት መንገድ እኔ ቀበናን እንደገለጽኳት ነው፡፡ ፒያሳ የሁላችንም ዳውን ታውን ስለሆነ ጥሩ ታሪክ ነው፡፡ ይኼ ትውልድ የተቀዳደደ ጋዜጣም ቢሆን ማንበብ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ፊልምስ ትመለከታለህ?

ፀሐይ፡- ፊልም ደስ ይለኛል፤ ብዙ ነበር መሥራት እችላለሁ ብዬ አምናለሁ እስካሁን ባልጋበዝም ይጠሩኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሜሪካ ስሆን ዘወትር ዓርብ አዳዲስ ፊልም እከታላለሁ፡፡ ከምደሰትባቸው የጊዜ ማሳለፊያዎች አንዱ ነው፡፡ ከአስፈሪ ፊልም ውጪ ከአክሽን፣ የቤተሰብና የፍቅር ፊልም እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ፌስ ቡክ ላይ 5,435 ላይክ ያለው ገጽ አለህ? በማኅበረሰብ ድረ ገጽ ምን ያህል ትሳተፋለህ?

ፀሐይ፡- ብዙም አይደለሁም፡፡ ፌስ ቡኩን በቅርብ ነው የከፈትኩት፡፡ ከዘመኑ ልጆች ጋር መገናኘት አለብኝ በሚል ነው የላይክ ፔጁን የፈጠርኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ሙዚቃ ነው የምታዳምጠው?

ፀሐይ፡- የኢትዮጵያ ሙዚቃ ነፍሴን ነው የሚያጠፋው፡፡ ከዛ ውጪ ባላዳምጥ እመርጣለሁ፡፡ ባህላዊ ሙዚቃ እወዳለሁ፡፡ ባለባህሎቹ ጋር ተኪዶ ቱባ ባህሉ ቢሠራ ጥሩ ነው፡፡ ወላይታ የሠራሁት ምን ያህል እንዳስከበረኝ አውቃለሁ፡፡ ጥናት ተደርጐበት በክብር ቢያዝ በቀጥታ ዓለም አቀፍ ሙዚቃ ውስጥ ሊያስገባን የሚችለው የደቡብ ብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ከነበሩህ ኮንሰርቶች በየትኛው የበለጠ ተደስተሃል?

ፀሐይ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ አውስትራሊያ ፐርዝ ከተማ ላይ የነበረኝ ምሽት አስደሳች ነበር፡፡ ገና ከሲድኒ ስነሳ ነበር አዳራሹ የሞላው፡፡ እስክደርስ ወደ አራት ሰዓት ገደማ የጠበቀው ሰው ፍቅር ደስ ይላል፡፡ ከአንዱ አየር መንገድ ወደ ሌላው ስሄድ ሰው በፌስቡክ እየተነጋገረ በኢትዮጵያ ሠንደቅ አጅቦኝ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ትልቁ ስኬትህ ምንድነው?  

ፀሐይ፡- በዚህ ሙያ ዓመታት ተለፍቶበት የወጣ ሥራ ሰው ጆሮ ከመድረሱ የበለጠ ስኬት የለም፡፡ ብዙ ነገር ተሳክቶልኛል፡፡ ቤትና መኪና ቢኖረኝም አስደሳች አይደለም፡፡ ልጆቼን ለስድስት ወራት ተለይቼ ነው ‹‹የኔታ›› አልበምን የሠራሁት፡፡ ለጥበብ ሰው ሥራውን ሰው ሲወድለት ከማየት በላይ ስኬት የለም፡፡ እግዚአብሔርም ሰውም ልፋትን ይቆጥራል፡፡     

 

      

           

                                             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...