Tuesday, September 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ቦሌ የሚያመራው ታክሲ ውስጥ ከጥቂት ተሳፋሪዎች ጋር ተቀምጠናል፡፡ ወያላው ‹‹ቦሌ! ቦሌ!›› እያለ ተጨማሪ ተሳፋሪዎች ሲጣራ፣ በዚህ መሀል ቁመተ ረዥምና ትከሻ ሰፊ ጎረምሳ ከአንዲት ቆንጆ ወጣት ጋር ገብተው ቦታቸውን ያዙ፡፡ ወጣቷ እሱ ላይ ጥብቅ ስላለች እሱ ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡ ገብተው እንደተቀመጡ ጎረምሳው አንዳች የሚያህል የሞባይል ስልኩን ያወጣና መነጋገር ይጀምራል፡፡ እኔ በ40 ዓመት ዕድሜዬ እንዲህ ዓይነት ሥርዓት አልበኛና ጋጠወጥ ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ንግግሩ በሙሉ በአስፀያፊ የብልግና ቃላትና በስድብ የተሞላ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ እየጮኸ ስለሚነጋገር የታክሲውን ተሳፋሪዎች በሙሉ ማለት ይቻላል አሸማቆናል፡፡ ከንግግሩ መሀል፣ ‹‹መጣውልህ አንተ ቆሻሻ›› እና ‹‹እደፋሀለሁ›› የሚሉት ደግሞ በተደጋጋሚ ይሰማሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ቆንጅዬዋ ወጣት ምንም እንዳልተፈጠረ እየተፍነከነከች ትስቃለች፡፡ ታክሲያችን ከሥምሪቱ ቦታ ተንቀሳቅሶ መስቀል አደባባይን ስናቋርጥ የሾፌሩ ረዳት፣ ‹‹ወንድም ድምፅህን ቀንስ ወይም በጨዋነት ተነጋገር›› የሚል ማሳሰቢያ ጣል አደረገለት፡፡ በዚህ ጊዜ ያ ወጠምሻ ጎረምሳ ንግግሩን ገታ አድርጎ፣ ‹‹አንተ ምን አልክ?›› ብሎ ለዱላ ከመቀመጫው ሲነሳ ረዳቱ ከወንበር ሥር የብረት ዘነዘና የመሰለ ነገር አወጣ፡፡ ረዳቱ በዓይን ሲገመገም ይህንን አንዳች የሚያህል ወጠምሻ ለመመካት አቅም ባይኖረውም፣ ለክፉ ጊዜ ያዘጋጀው የብረት ዘነዘና ወጠምሻውን ወደነበረበት እንዲመለስ አስችሎታል፡፡ ታክሲው ፍላሚንጎን አልፎ ወደ ኦሊምፒያ ሲቃረብ በብልግና ቃላት እየተጠቀመ ሲያደነቁረን የነበረው ጎረምሳ ስልኩን ኪሱ ከተተ፡፡ ከዚያም ረዳቱን በነገር መውጋት ጀመረ፡፡ ረዳቱም፣ ‹‹ሰማህ? ብትከበር ይሻልሃል፡፡ ያለበለዚያ አናትህን ብዬ እገላግልሃለሁ፤›› ሲለው ሌሎች ተሳፋሪዎች ‹ተው! ተው!›› እያሉ አበረዱት፡፡ በዚህ መሀል ከወጠምሻው ጋር ያለችው ቆንጆ፣ ‹‹አንተ አታፍርም? ቢይዝህ እኮ አንድ ጉርሻ ነው የሚያደርግህ…›› እያለች ነገሯን ስታደራ አንዲት እናት፣ ‹‹ምነው ልጄ? ነገር ማብረድ ሲገባሽ ታባብሻለሽ? በይ ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት ንግግር ከአንቺ አፍ አይውጣ፤›› አሏት፡፡ ከመልክ በስተቀር ምግባር የጎደላት ይህቺው ወጣት፣ ‹‹እማማ በማይመለከትዎት ነገር ጣልቃ አይገቡ፤›› ስትላቸው፣ ‹‹ልጄ እኔ ጤነኛ መስለሺኝ እንጂ የአማኑኤል ምልስ መሆንሽን መቼ አውቄ?›› ብለው ሲገረምሟት ረዳቱና የተወሰኑ ተሳፋሪዎች ሳቁ፡፡ ያ ደረቱ እንደ ጃንሜዳ የሰፋው ብልሹ ጎረምሳ፤ ‹‹ተያቸው ይሳቁ፡፡ ቦሌ ስንደርስ ምን እንዳሳቃቸው ቃላቸውን እንቀበላለን፡፡ ከዚያም አይቀጡ ቅጣት እንቀጣቸዋለን…›› እያለ ሲመፃደቅ በሞባይል ስልኩ ጽሑፍ ሲያነብ የነበረ አንድ ጎልማሳ፣ ‹‹አንተ ስድ አደግ አይበቃህም? ማንን ነው የምትመረምረው? አንተ ማን ሆነህ ነው የምትቀጣው? ሕግ አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ከሕግ በላይ የሆንከው ማን ስለሆንክ ነው? ይህንን በአስቸኳይ ካልነገርከኝ እኔ ራሴ እዚሁ ምርመራ እጀምርብሃለሁ፤›› ሲለው ወጠምሻው በድንጋጤ ይሁን በመገረም ዓይኑ ፈጠጠ፡፡ ያቺ ቅልብልብ የምትለው ጠፍቷት አንዴ ውጭ ውጩን ሌላ ጊዜ ደግሞ የታክሲውን ጣሪያ በዓይኖቿ መዳሰስ ጀመረች፡፡ በዚህ ውጥረት ውስጥ ተሳፋሪዎች ‹‹ወቸው ጉድ›› እያሉ እርስ በርስ ማውራት ሲጀምሩ አንዲት ረጋ ያለች ሴት፣ ‹‹ፈረንጆች ጨዋነት ሲያከትም ብልግና ይነግሳል እንደሚሉት፣ ይሉኝታና ኃፍረት ጠፍቶ በባለጌ እንወረር?›› በማለት አጠገቧ ካለው ወጣት ጋር ወሬ ጀመሩ፡፡ የሁለቱ ርዕስ ከሌሎች ሹክሹክታዎች በላይ ስለገነነ እኛም ተደባለቅናቸው፡፡ ይህቺ ሴት የዘመኑን ብልግናና ይሉኝታ ቢስነት እያነሳች ወጉን ስታሰፋው ‹‹ነገርን ነገር ያነሳዋል›› በሚል በወሬ ተጠመድን፡፡ በዚህ መሀል ያ ወጠምሻ ጎረምሳና ልጅቷ ድምፃቸውን እንዳጠፉ ፍሬንድሺፕ አካባቢ ሹልክ ብለው ሲወርዱ ግርማ ሞገሳቸው ጠፍቶ ነበር፡፡ ማንም ከመጤፍ ሳይቆጥራቸው ሹክክ እንዳሉ ተለዩን፡፡ ከሴትየዋ አጠገብ የተቀመጠ ወጣት እንዲህ አለን፡፡ ‹‹በአሁኑ ጊዜ ራስ ወዳድነት በመንሰራፋቱ ይሉኝታና ህሊና የሚባሉ ጠቃሚ ነገሮች እየጠፉ ናቸው፡፡ ህሊና ሳይኖር ሲቀር ብልግና ይበረታል፡፡ ራስ ወዳድነት ጣሪያ ሲነካ ብልግናና ሌብነት ኩራት ይሆናሉ፡፡ ድሮ በአገራችን ጨዋነት፣ ሥነ ምግባርና ኩራት የደህና ሰው መገለጫ ነበሩ፡፡ ሌላው ቀርቶ ‹ኩራት እራት ነው፣ ከፍትፍቱ ፊቱ…› እየተባለ ብዙ አልባሌ ነገሮች ይናቃሉ፡፡ አሁን ግን ሰው መሳደብ፣ ማመናጨቅ፣ ጥላቻ መዝራት፣ ዝርፊያ፣ ሐሜትና ስግብግብነት በርክተዋል፡፡ የዘመኑ ሰው ‹‹ከፍትፍቱ ፊቱ› የሚባለውን ዕድሜ ጠገብ ብሂል ገልብጦት ‹ፍትፍቱን በልተህ ጥፋ ከፊቱ› እያለ ይሳለቃል፡፡ ይኼ ደግሞ የሞራል ውድቀትን ያሳያል…›› እያለ ሲነግረን አስደመመን፡፡ ወጣቱ የበሰለ መሆኑ ያስታውቃል፡፡ እኔ በበኩሌ ‹‹ድሮ ቀረ›› በሚባለው አባባል የማምን ባልሆንም፣ በዚህ ዘመን የማያቸው አሳዛኝ ድርጊቶች ግን ያበሳጩኛል፡፡ ብልግናና ራስ ወዳድነት ከመጠን በላይ ሆኖ በየመንገዱ ‹እናትህን….› ሲባል፣ በየቦታው ጉበኞች ተገልጋዮችን አላስቀምጥ ሲሉ፣ ሥልጣን ሕዝብን ማገልገያ መሣሪያ መሆኑ ቀርቶ የቡድን መጠቃቀሚያ ሲሆን በጣም ያበግነኛል፡፡ ይህንን እያሰላሰልኩ ሳለሁ ቦሌ ጫፍ ደርሰን ከታክሲ ወረድን፡፡ አንዳንዴ አጋጣሚ አይጠፋም አይደል? ቦሌ ጫፍ ላይ ያለው ኖክ ማደያ አጠገብ በከፍተኛ ድምፅ የሚናገር ሰው ቀልቤን ያዘው፡፡ ይህ ንክ የሚመስል ነገር ግን ልባም ሰው፣ ‹‹አቤቱ ፈጣሪ ሆይ! አገሪቱን ከምግባረ ብልሹዎች፣ ከህሊና ቢሶችና ከራስ ወዳዶች ጠብቃት!›› እያለ በተደጋጋሚ ሲማፀን መልዕክቱ ለሁላችንም መሰለኝ፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ (ወንድወሰን ተስፋ፣ ከልደታ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...