Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርመንግሥት ቃሉን ያክብር! ሊያደርግ የተሳለውን በጊዜው ያድርግ!

መንግሥት ቃሉን ያክብር! ሊያደርግ የተሳለውን በጊዜው ያድርግ!

ቀን:

በከተማው ውስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የተዘረጋው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ሦስት ዓመት አለፈው፡፡ መንግሥት በየመገናኛ ብዙኃኑ ሲነግረን፣ ስንሰማና ስንጓጓ ከርመናል፡፡ ብዙ ጠብቀናል፡፡ አቧራ እየቃምን፣ ጭቃ እየረገጥን፣ ጎርፍ እየወረደብን ሦስት ዓመት ጠበቅን፡፡ የባቡር ፕሮጀክቱ ጥር ወር ላይ ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል ተብሎ ብዙ ሲነገርለት ነበር፡፡ አይደርስ የለ ጥር ደርሶ ተጋመሰ፡፡ የፈረንጆቹ ጥርማ ገሰገሰ፡፡ ባቡሩ ግን ገና እንዳንቀላፋ ነው፡፡ መንግሥትም ዝምታን የመረጠ ይስላል፡፡ ከዓመት፣ ከሁለት ዓመት በፊት ያዘንብ የነበረውን መግለጫ ገታ አድርጎ የተደበቀ መስሏል፡፡ በመሠረቱ ፕሮጀክቱ ለቻይና ኩባንያ የተሰጠው ሙሉ ለሙሉ ሥራውን አጠናቆ እንዲያስረክብ፣ በዚህ ወቅት ብዙ የተባለለት ይህ ባቡር በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሲሽከረከር ሊታይ በተገባው ነበር፡፡ ከጥንስሱ ጀምሮ በርካታ አስተያየቶችን ስያስተናግድ የቆየው ይህ ፕሮጀክት፣ የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ይቀርፍ ዘንድ በመንግሥት ብዙ ሲባልለት የቆየ ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ ብቻ ብዙ ሺሕ የከተማውን መንገደኞች ያጓጉዛል ተብሎለታል፡፡ ባቡሩ ያልፍባቸዋል የተባሉ የአዲስ አበባ ሠፈሮች ቁም ስቅላቸውን አይተዋል፡፡ የንግድ ተቋማት ፈራርሰው፣ የሞቁና የደመቁ የንግድ አካባቢዎች ውኃ ተቸልሶባቸው የተወረረ ከተማ መስለው ነበር፡፡ የባቡሩ መንገድ እንደ ሳሪስ ባሉ አካባቢዎች አምሮበት ሠፈር የማሳመሩን ያህል፣ ከጊዮርጊስ እስከ አውቶቡስ ተራ፣ ከሰባተኛ እስከ ልደታ ባለው መስመር ላይ ከተማውን የተገማመጠ አድርጎት አስቀያሚ ገጽታ ሰጥቶታል፡፡ ይህም ቢሆን ወደፊት ይስተካከል ብለን ብንጠብቅም፣ ለሦስት ዓመታት መታገሳችን ግን በዝምታ መታለፍ የለበትም፡፡ ምሥጋናው ቢቀር በወቅቱ ሊያልቅ ስላልቻለበት ምክንያትና በተባለው ጊዜ ተጠናቅቆ በዚህ ወር ሙከራ ያልጀመረበትን ሰበብ ቢያንስ እኔ የማወቅ መብት እንዳለኝ ይሰማኛል፡፡ ከቻይና መንግሥት በተሰጠ ብድር እየተገባ ያለው የባቡር ፕሮጀክት ከእኔ አልፎ ለመጪው ትውልድ ዕዳ የመሆኑን ሀቅ ሁልጊዜም ስለምናስብ፣ መንግሥት ኃላፊነቱን ይወጣ ብዬ ለመጠየቅ አላቅማማም፡፡ ከባቡሩ መለስ መንግሥት እንዳሻው ቀኑን የሚለዋውጠውን፣ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓትን፣ ሥርዓት ሊያሲይዘው ይገባል፡፡ በዚህ ዓመት ለሕዝቡ በዕጣ ይተላለፋሉ የተባሉት ቤቶች ቁጥር፣ በመስከረም ወር በፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ሳይቀር የተነገረላቸው ናቸው፡፡ አብዛኛው የቤት ተመዝጋቢ፣ ከኪሱም ከኑሮውም ቆጣጥቦ ለመንግሥት ሥራ ማስኬጃ ይሆነው ዘንድ ሲከፍል ቆይቷል፡፡ ከዚህ ሲከፋም ከአሥር ዓመት ያላነሰ ቤት ይደርሰናል ብለው ሲጠብቁ የቆዩ ስንት መቶ ሺሕ ተመዝጋቢዎች እንዳሉ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህ ሁሉ መንግሥት ላይ ጫና በማሳደር የገባውን ቃል አክብሮ ባለው ጊዜና ወቅት፣ ተገቢውን ደረጃ ያሟሉ ቤቶች ማቅረብ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ቤቶቹ መቼ ዕጣ እንደሚወጣባቸው ለማወቅ ምጥ የሆነባቸው ቢወተውቱም፣ ምላሽ የሚሰጣቸው የመንግሥት አካል ያለ አይመስልም፡፡ እንዲሁ በደመነፍስ በዚህ ዓመት የሚል ሾላ በድፍኑ ምላሽና ዲስኩር እንሰማለን፡፡ መንግሥት ቃሉን ያክብር፣ ሲጠየቅም ምላሽ ይስጥ ለማለት እወዳለሁ፡፡ በሌላ በኩል በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚቀርብባቸውን መንግስሥታዊ መሥሪያ ቤቶች የሚያያቸው፣ የሚያስተካክላቸው አካል ያለ አልመስል ብሏል፡፡ በተለይ በተደጋጋሚ ለወቀሳና ለምሬት የዳረጉን መብራት ኃይልና ኢትዮ ቴሌኮም በነዋሪው ላይ ሲያደርሱ የቆዩትን አገልግሎት አሰጣጥ ውጣውረድ በግርዶሽ ከመመልከት በቀር ይህ ነው የሚባል የማስተካከያ ዕርምጃ ወስጃለሁ የሚል የመንግሥት አካል ቀርቦ ብናይ እንዴት በተደሰትን፡፡ የምክንያት ጋጋታ እያቀረቡ በሕዝቡ ላይ ሲደርስ የቆየውን ተፅዕኖ በሚመለከት ፓርላማው ሰምቶ ከማሰማት፣ ፍትሕ ተቋማት አይቶ ካለማየት፣ የሸማቾች መብት ይመለከተናል የሚሉ መሥሪያ ቤቶች ዳር ዳሩን ከመጮህ እንዲህ ባለው የመብት ጥሰትም ላይ ጠባቂነት ቢያሳዩና ለውጥ ቢመጣ በምን ዕድላችን እንላለን፡፡ በሌላው ዓለም ለሕዝብም ለመንግሥትም መሥራት ያለባቸው ከመሥራት ቦዝነው፣ ሕዝብን የሚያማርሩ ባለሥልጣናት ከወንበራቸው በገዛ ፈቃዳቸው ሲሰናበቱ እያየን፣ በእኛም ይሄው መቼ ይመጣ ይሆን ብለን ብንመኝ ከመጎምዠትና ከቅዥት ይቆጠርብን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት ቃል የገባውንም፣ እሠራለሁ ያለውንም ባለው ጊዜና ወቅት አጠናቆ ለሕዝብ አለማቅረብን ባያስከስሰው እንኳ ይቅርታ የማያስጠይቅ መብት አድርጎት ይገኛልና ነው፡፡ (እያደር ያምራል፣ ከጀርመን አደባባይ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...